በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል

 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሕንነት ጉዳዮች አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

የአካባቢው ማህበረሰብም መንግስት በወንጀለኞች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥና ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ትብብራቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ለዞኑ የጸጥታ ችግር ዘላቂ እልባት ማበጀት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችን ያሳተፈ የሰላም ጉባኤ በግልገል በለስ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በመተከል ዞን በየጊዜው በሚፈጠር የውክልና ጦርነት በርካታ ንጹሃንን ለሞትና መፈናቀል መዳረጉን ገልጸዋል።

በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚሹ አካላት በሚያቀናብሩት ሴራ የአካባቢው ማህበረሰብ በፀረ ሰላም ሃይሎች በርካታ ችግሮች እየደረሱበት መሆኑንም አንስተዋል።

መንግስት ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ቢያቀርብም እስካሁንም በጥፋት መንገዳቸው የቀጠሉ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ጸረ-ሰላም ሃይሎችን መታገል አለበት ብለዋል።

በዞኑ ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድም አረጋግጠዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በዞኑ የውክልና ጦርነት አጀንዳ አንግበው በተላላኪዎቻቸው በኩል በህዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥሩ የጥፋት ፈፃሚዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

የዞኑ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የመከላከያ ሠራዊትና የክልል ልዩ የጸጥታ ሃይል በዞኑ ማሰማራቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎች እጃቸውን ለመንግስት እንዲሰጡ ጠይቀው፤ እጅ የማይሰጡ ካሉ ግን የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዐማራው ከወልቃይት፣ጠገዴ እና ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ ጎን ሊቆም ይገባዋል! - ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት     

የጸጥታ ሃይሉ በወንጀለኞች ላይ ለሚወስደው እርምጃ የአካባቢው ማህበረሰብ ተባባሪ እንዲሆንም ሌተናል ጄነራል ሐሰን ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)

1 Comment

  1. መከረኛው የአገሬ ህዝብ አሁን ወደ የሚገኝበት እጅግ አስከፊ ሁለንተናዊ ቀውስ እንደሚገባ ግልፅና ግልፅ የሆነው ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት የጎሳ አጥንት ስሌት ሥርት አሽከርነት ሥር የኖሩት እና ከሦስት ዓመታት በፊት ደግሞ ፈጣሪያቸውን ፣ አሳዳጊያቸውንና የበላይ አዛዣቸውን (ህወሃትን) ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ ገፍትረው አስተሳሰቡን ፣ ህገ መንሥቱንና መንግሥታዊ መዋቅሩን ግን እጅግ በከፋ የተረኝነት ፖለቲካ ሲያስኬዱት ከምር “ምነው አደብ ግዙና ወደ ተሻለ ሥርዓተ ፖለቲካ እንሄድ እንጅ” ከማለት ይልቅ በአድርባይነት በተለከፉ ምሁራን ተብየ ወገኖቹ ተታሎ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ አሜካላዎችን ( ደመኞችን) የለውጥ ሐዋርያት በሚል እራሱን ማቄል ብቻ ሳይሆን ለታላቅ ዓላማ ሲል ከረቂቅ የማሰቢያ ኢንጅን (አእምሮ) ጋር የፈጠረው ፈጣሪ ያቀረበለትን ወርቃማ እድል ያበላሸ እለት ነው።

    እናም ቀድሞ ህወሃት ሲያስፈልገው መሣሪያ አስነግቦ በነፍሰ ገዳይነት ፣ ሲያሻው ደግሞ እንደ ደመነ ነፍስ አጋሰስ (የጭነት እንስሳ) ግትልትል ጓዙን እያሸከመ ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ዋነኛ ብአዴናዊያን መካከል የሆነውና ከካድሬነት ወደ የአማራ ገዥነት ፣ ከዚያም ተረኝነቱን በተቆጣጠረው ኦህዴድ ፈቃድ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነት እና እንደገና አሁን ደግሞ በቅጡ እንኳን ሳይነገረው አሁን ወደ አለበት የሥራ ምድብ የተጠራው ገዱ አንዳርጋቸው ነው።
    መቼም በእንዲህ አይነት የፖለቲካ ሰብእና ውድቀት እና የሞራል ዝቅጠት ከተለከፉ ፖለቲከኞች ፍትሃዊና ዘላቂ መፍትሄ ይወለዳል ብሎ ከማመንና ከመጠበቅ የባሰ የፖለቲካ ድንቁር እና የሞራል ጎስቋላነት የለም።
    በእነ ሽመልስ አብዲሳ እና በእነ ታየ ደንዳ የፖለቲካ የሴራ እና በኦነግ የመስክ ዘመቻ በንፁሃን የአማራና ሌሎች ኗሪዎች ላይ ጀኖሳይድ ሲፈፀም እና በመቶዎች የሚቆጠሩ በጅምላ ተገድለው በግሬደር አንድ ጉድጓድ ውስጥ እንደ ቆሻሻ ነገር አፈር ሲመልለስባቸው ተባባሪ የነበረው እና ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በሚል ስም ወንጀለኞችን ደህንነት ተብየውን ጨምሮ በየመንግሥት መ/ቤቱ እንዲሰገሰጉ ያደረውስ የክልሉ ገዥ አይደለም እንዴ?

    የተፈፀመውን እጅግ ዘግናኛ ወንጀል አስቁሞ ለምርመራ ለማቅረብ የሚረዳ ሥራ መሥራት ቀርቶ ለወንጀሉ ተባባሪ በሚመስል አኳኋን ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታው አካል የሆነው የኮማንድ ፖስት ተብየው አስተባባሪ አይደለም እንዴ?

    ሽምግልና መልካም ነበር ፤ በትክክክል ለሚጠቀምበት አሁንምና ወደ ፊትም መልካምና ጠቃሚ ነው። ጥያቄው እንዲህ አይነት ሽማግሌነትና ሽምግልና የአሁኒቷ ኢትዮጵያ እውነታ አካል ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከመቻል ወይም ካለመቻል ላይ ነው ።
    እውን እጅግ መሰሪና አደገኛ የሆነው ሥርዓተ ኢህአዴግ (ሥርዓተ ጎሰኝነት/መንደርተኝነት) በቀጠለበት መሪር እውነታ ይህን ጥያቄ በሚዛናዊነትና በትክክል መመለስ ይቻላል? በእኔ እምነት ሳይሆን በመሬት ላይ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ አንፃር ፈፅሞ የሚቻል አይደለም።
    የሽምግልና እሴት በተጎሳቆለበት እና የጎሳ መሪ ተብየዎችም በየራሳቸው የጎሳ ዓለማት ውስጥ በሚሽከረከሩበት እውነታ ውስጥ እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት የሚረጋግጥባትን የጋራ ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ማድረግ ይቻላል በሚል ጉባኤ፣ ምክክር ፣ ሸንጎ ወዘተ እያሉ የዲስኩር ድሪቶ መደረት በመከረኛው ህዝብ መከራና ውርደት መሳለቅ ነው የሚሆነው ።
    እናም ትክክለኛው እና ዘላቂው መፍትሄ ለዘመናት እጅግ አስከፊ በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ከሥሩ መንቀል ብቻ ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share