ለቸኮለ! ዓርብ ነሐሴ 21/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረ ጺዮን ገ/ሚካዔል ለትግራዩ ጦርነት በድርድር ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ድርጅታቸው ፍላጎቱ መሆኑን ለተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ማሳወቃቸውን ዓለማቀፍ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ድርጅታቸው ገለልተኛ አሸማጋይ እንደሚፈልግ የገለጹት ደብረ ጺዮን፣ አፍሪካ ኅብረት ግን ለጦርነቱ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም ማለታቸው ተገልጧል።
2፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የቀድሞውን የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሌሴጎን ኦባሳንጆን ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የኅብረቱ ከፍተኛ ወኪል አድርጎ እንደሾማቸው አስታውቋል። የኦባሳንጆ ሹመት ኅብረቱ በቀጠናው ሰላም፣ ጸጥታ እና መረጋጋት ለማስፈን እና ችግሮች በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈቱ ለማስቻል እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑን የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። ኦባሳንጆ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ቀጠናው እንደሚጓዙ የኅብረቱ መግለጫ አመልክቷል።
3፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ትናንት በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለስምንተኛ ጊዜ ባደረገው ውይይት ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አሳስቧል። ቻይና እና ሩሲያ ኢትዮጵያ ችግሩን በዋነኛነት ራሷ ለመፍታት አቅም እንዳላት በመጥቀስ በሀገሪቱ ላይ የሚደረግን ማናቸውም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። ሕንድ እና ኬንያም የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የያዘውን አቋም እንደሚደግፉ አሳውቀዋል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፣ ጦርነቱ የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታና የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ ላይ ጥሎታል በማለት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል። በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አጽቀ ሥላሴም የሀገራቸውን አቋም አስረድተዋል።
4፤ የትግራዩ ጦርነት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካልተሻሻለ ኢትዮጵያ ከአሜሪካው የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት (አጎዋ) ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አሜሪካ ማስጠንቀቋን ሮይተርስ ዘግቧል። የአሜሪካ ከፍተኛ የንግድ ሹም ካትሪን ታይ ይህንኑ ማስጠንቀቂያ የሰጡት፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ማሞ ምህረቱ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ትናንት ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው፣ ጉዳዩ ኢትዮጵያን ለማስፈራራት እየዋለ ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሕወሃት የቀጠረው ቫን ባተን ሞንታንግ የአሜሪካ ፖሊሲ አግባቢ ኩባንያ በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ ከአጎዋ እንድትሰረዝ የአሜሪካ ንግድ ፖሊሲ አውጭዎችን እየወተወተ መሆኑን በተደጋገሚ ገልጧል።
5፤ አፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ የሰሜን ኢትዮጵያውን ግጭት እንዲሸመግሉ 55 ያህል አፍሪካዊያን ልሂቃን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ተማጽነዋል። ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ አፍሪካዊያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ መብቶች ተሟጋቾች፣ ደራሲያን እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በጻፉት ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በፍጥነት ማሽቆልቆሉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ጦርነቱ በፖለቲካዊ ውይይት እንጅ በጦር ሜዳ ሊፈታ እንደማይችል በመጥቀስም፣ ተፋላሚ ወገኖች በኢጋድ ማዕቀፍ ስር ንግግር እንዲጀምሩ ወይም የውጭ ሽምግልናን እንዲቀበሉ የኢትዮጵያ ጉረቤቶች ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ልሂቃኑ ጠይቀዋል።
6፤ በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 455 ፍልሰተኛ ኢትዮጵያዊያንን ዛሬ ወደ ሀገራቸው እንደመለሰ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ከተመላሾቹ መካከል፣ 129 ሕጻናት እና 326 ሴቶች ይገኙበታል። በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በበኩሉ፣ በሀገሪቱ እስር ቤቶች ታስረው የቆዩ 100 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ወደ ሀገራቸው መመለሱን በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል።
7፤ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆላ ወረዳ በጥቅምት 2011 ዓ.ም ሁለት የጤና ተመራማሪዎችን በደቦ ፍርድ በገደሉ 32 ተከሳሾች ላይ የባሕርዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ከ1 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት እንደወሰነባቸው ዶቸቬለ ከሥፍራው ዘግቧል። ከሳሾቹ የጤና ተመራማሪዎቹን በወረዳው አዲስ ዓለም ከተማ በደቦ ፍርድ ደብድበው የገደሏቸው፣ ተመራማሪዎቹ የአካባቢውን ሕጻናት ምንነቱ ያልታወቀ እና ለጤና አደገኛ የሆነ መርፌ ወግተዋል በሚል ያልተረጋገጠ ወሬ ተነሳስተው ነበር። ተከሳሾቹ ከሁለቱ ሟቾች ሌላ 3 የጤና ባለሙያዎችን ደብድበው ማቁሰላቸው ይታወሳል።
8፤ ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ነሐሴ 20 ላስተላለፈው “የሱማሌ ክልልን መንግሥት እና ሕዝብ ያስከፋ ስም ማጥፋት” ዘገባ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሱማሌ ክልል በኮምንኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የክልሉ መንግሥት ከፋና ይቅርታ የጠየቀው፣ የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ “የምሥራቁ ጁንታ በአፋር ሕዝብ ላይ ጦርነት ከፍቷል” በማለት በሱማሌ ሕዝብ ላይ ያወጣውን ስም የሚያጠፋ መግለጫ ፋና በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በመዘገቡ እንደሆነ ገልጧል። ፋና የሠራው ዘገባ የአፋር እና ሱማሌ ሕዝቦችን ሊያጋጭ የሚችል ነው ሲል ወቅሷል ክልሉ። ጣቢያው ጥፋቱን ማመኑን ለክልሉ መግለጹን የጠቆመው መግለጫው፣ ሆኖም በይፋ ይቅርታ ካልጠየቀ ክልሉ ከጣቢያው ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያቋርጥና ጣቢያውን በሕግ እንደሚጠይቅ አስጠንቅቋል። [ዋዜማ ራዲዮ]
ተጨማሪ ያንብቡ:  በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ወቅት ታግተው የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉ ተገለጸ

1 Comment

  1. የምን ድርድር? ሊጥ ከሚሰርቅ ሌባ ጋር ምን አይነት ሰላም ይፈጠራል? እንዴት ነው ሰው እየዘረፈና ሃገር እያፈረሰ ልደራደር የሚለው። የተመድን ስብሰባ ደስኳሪዎች ትኩር ብሎ ላየ የአንዳንዶች ውሸትና ከወያኔ ጋር መሰለፍ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ለዚህም ቀዳሚዋ ሃገር አሜሪካ ናት። ይህ ስብሰባ እንዲሆን ጥሪ ካደረጉት ሃገሮች መካክል ደግሞ አየርላንድ ጭራሽ አይኗን በጨው የታጠበች ሃሳቧ የሚያምታታና አፍቃሪ ወያኔ እንደሆነች በግልጽ ይታወቃል። ድሮ ገና ወያኔ በረሃ እያለ በሱዳን በኩል በእርዳታ ስም በመግባት ወያኔ እንዲጎለብት ካደረጉት ሃገሮች አንዷ አየርላንድ ናት። ባጭሩ አሜሪካ የፈለገችውን በተመድ በኩል ማድረግ እንደማትችል በግልጽ የታየበት ስብሰባ ነው። በዝጉ ስብሰባ ቡጢ ገጥመው እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም።
    ወያኔ ሃርነት ትግራይ ( ወያኔ ባርነት ትግራይ) – አሁን ምጥ ውስጥ ሲገባና የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር ሆ ብሎ እንደተነሳበት ሲረዳ እርቅ ይላል። ጌታቸው ረዳ በቅርቡ እርቅ ጭራሽ አንፈልግም አላለም ነበር? አዲስ አበባ ለመግባት የሚከለክለን ምድራዊ ሃይል አይኖርም አላለም። እባካችሁ ሂድና ግቡ። እንያችሁ። እንዴት የሃገሪቱ ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አክ እንትፍ እንዳላችሁ መረዳት ተሳናችሁ? ሌላው ቢቀር አሁን በአፋርና በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸማችሁት በደል ያቀባብራል? እንዴት እንስሳትን በጥይት ደብድቦ ከሚገል የሰው በድን ጋር ሰው ለእርቅ ቁጭ ይላል። ወያኔ አንገቱ ገመድ ውስጥ እንደገባ ያውቃል። ለዚህ ነው ኡኡታው አሁን ከፍ ያለው። ለትግራይ እናቶችና አባቶች ልጆቻችን የት አሉ ሲባል ምን ሊመልስ ነው? ሁሌ በትግራይ ቲቪ የሚነገረው ድል አደረግን፤ አዲስ አበባ ጥግ ደርሰናል ነው። ጉዳዪ ግን የኋልዪሽ ሩጫ ነው። የአሜሪካ እርቅ አርጉ ማለት ከሞትና ከመታሰር የተረፉ የወያኔ ተላላኪዎቿን ከማይቀርላቸው የሞትና የእስራት ጽዋ ለማትረፍ ነው። ያው በአፍጋኒስታን እንደሚያረጉት ለቅመው ያውጡና ይውሰዷቸው። ሰው እፎይ ይበል ከእነዚህ እባቦች።
    ለዘመናት ሲያስር፤ ሲገል ሲያፍን ሲሰውር የነበረው የአማራ ህዝብ ባርነት በቃኝ ብሎ ስለተነሳበት ወያኔ ግራ ተጋብቷል። ወያኔ ያልተረዳው የአማራ ህዝብ በፊትም ዝም ማለቱ የመታገሱ መግለጫ እንጂ እንደ ተበደለ ጠፍቶት አይደለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጋሃነም ድረስ እሄዳለሁ፤ ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን ያለው ወያኔ እንዴት ነው ለሽምግልና የሚበቃው? ያው እንደ ተለመደው የፈጠራ ወሬውን እየነዛ፤ እየዘረፈና እየሰረቀ በዚያው ወርቃማ ህዝብ እያለ አፍር ባስመሰለው በትግራይ ህዝብ ያሞኝ እንጂ እንደገና ከወያኔ ጋር የሰላም እርቅ እናርግ ማለት ተመልሰህ ተጠናክረህ ውጋኝ ማለት ነው። ወያኔን ለማጥፋት ጊዜው አሁን ነው። ይህን አመቺ ጊዜ ያልተጠቀመ መንግስት ደንቆሮ ነው። ወያኔ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ራሱ በጫረው እሳት እየተለበለበ ነው። መጥፋት ያለበትን ድርጅት ለማጎልበትና በሰላም ስም ጊዜ ለመግዛት የሚደረገው የውስልትና ፓለቲካ ለማንም አይጠቅምም። ማንም ሰው አሜሪካኖች የሚሉትን መስማት የለበትም። የሚናገሩት ሌላ የሚሰሩት ሌላ። ጊዜው ተቀይሯል። ጋሃነም አውራጅን ወያኔን ሲኦል ለመክተትና በሩን ለመከርቸውም ጊዜው አሁን ነው። የትግራይ ህዝብም እፎይ ይበል። ህዝባንች የወያኔ ሞቶ መቀበር አማራጭ የማይገኝለት ምርጫ አድርጎ መንቀሳቀስ አለበት። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share