የትግራይ ቀዉስ፤ በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል ወይስ በትግራይና በአማራ ህዝብ መካከል?

the wider image: grim aftermath of ethiopian battle offers rare clues of brutal war
the wider image: grim aftermath of ethiopian battle offers rare clues of brutal war

በመፍትሔዉ ፍለጋ ሁሉም ዜጋ ያስብበት (በዶ/ር በቀለ ገሠሠ)

1ኛ/ መንደርደሪያ፤

ከነዚያ ክልሎች አካባቢ የሚሰሙት ዜናዎች እጅግ በጣም የሚያሰቅቁና የሚያሳሳስቡ ናቸዉ። ግድያዉ፤ መፈናቀሉና ሰቆቃዉ እየበረከተና እየተባባሰ መሄዱን ማመን ያስቸግራል። ለምን? ለምን? ለምን? እነዚህ ጥያቄዎች ቶሎ እልባት ካላገኙ የበለጡ እጅግ አሳሳቢ ጉዳቶች ሊደርሱ ስለሚችሉ ችግሮቹ በሚከተሉት መንገዶች በአጣዳፊ መንገድ እንዲፈቱ ላሳስብ እወዳለሁ።

2ኛ/ የፌደራልና የህወሃት ጉዳይ

ህወሃትና ካድሬዎቹ ለ27 ዓመታት ብዙ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል። ፖሊቲካዉን እንደፈለጉት አሽከረከሩት። የዉሸት ትርክቶችን ነዙ። እስከዛሬ ድረስ በሥራ ላይ ያለዉን መርዘኛና ከፋፋይ ሕገ መንግሥት ዘረጉ። በከፋፍለዉ መግዛት ፖሊሲያቸዉ ህዝብን ከህዝብ አጋጩ። የብድር ገንዘብና የሀገር ንብረት መዝብረዉ በዉጪ ባንኮቻቸዉ አስቀመጡ።

ከ27 ዓመታት በኋላ ግን በተቀጣጠለዉ የህዝብ ትግል ከማዕከላዊ መንግሥት ተገፍተዉ ወደመቀሌ አፈገፈጉ። በመጨረሻም  ሁለት ተጨማሪ ከባድ ወንጀሎች ፈጸሙ፤ 1ኛ/ በሰሜን ክንፍ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ላይ ጉዳት አደረሱ፤ 2ኛ/ በማይካድራ በሚኖሩት ወገኖች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሱ ተሰማ። በዚህ ምክንያት ፌደራል መንግሥት ሕግና ሥርዓትን አስጠብቃለሁ ብሎ በህወሃት ላይ ጦርነት ከፈተ። ዳሩ ግን ዓላማዉን በደንብ ሳይመታና ህዝቡን ሳያረጋጋ ትግራይን ጥሎ ወጣ። ህወሃት ግን ያንን ክፍተት በመጠቀም ወዲያዉኑ ወደሥልጣኑ ተመልሶ ከባድ ጉዳቶች ለመሰንዘር ፉከራዉን ጀመረ።

ዛሬ ከትግራይ ክልል በመዉጣት በወልቃይት፤ በራያ፤ በአላማጣ፤ በአፋር፤ ወዘተ ላይ ጉዳቶች ለማድረስ እየሞከረ መሆኑ ይሰማል። ይሄ ጎዳይ የክልሎቹ ብቻ ሳይሆን የፌደራል መንግሥት ዋና ኃላፊነት መሆን አለበት። ችግሩ የአማራና የትግራይ፤ ወይም የትግራይና የአፋር መስሎ መታየት የለበትም፤ ሀገራዊ ጉዳይ ነዉና። ማንኛዉም ክልል ድንበሩን አቋርጦ ወጥቶ በህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በዋናነት ክልሎች ደጀን ይሆናሉ እንጂ ብቻቸዉን የሀገር ፀጥታ አስከባሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። ጥቃቶች በሚደርሱባቸዉ ቦታዎች በሙሉ በፌደራል መንግሥትና በመከላከያ ኃይል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይጠበቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጀግናው ወጣት ፖለቲክኛ አንዱአለም አራጌ የክብር አቀባበል ጥሪ ፍራንክፈርት

 

3ኛ/ በክልሎች መካከል የድንበር ግጭቶችን በተመለከተ

ተደጋግሞ እንደተገለፀዉ፤ ህወሃት ወደሥልጣን ሲመጣ የአማራ/ጎንደር አካላት የሆኑትን ምድሮች በጉልበት ቆርጦ ወደትግራይ ከለለ። እነዚህም ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትን፤ ወዘተ ሲያጠቃልሉ ከወሎ ደግሞ እነራያን ይመለከታል። ይሄ ችግር የአማራንና የትግራይን ህዝብ እርስ በርስ በማያናክስ መንገድ ሊፈታ ይችላል። 1ኛ/ ድንበሮችን በተመለከተ በቂ ታሪካዊ መዝገቦችና መረጃዎች አሉ። ዳሩ ግን ምድሮቹ ወደቀድሞዎቹ ክልሎች/ክፍሎች ይመለሱ ማለት የትግራይ ህዝብ አይኑርበት ማለት አይደለም። ህዝባችን ከጥንቱ ጀምሮ ወደፈለገበት ቦታ እየተዘዋወረ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ መብት ነበረዉ። የህወሃት ከፋፋይ ሕገ መንግሥትና አምባገነንነት ያመጣብን አባዜ እንጂ በጭቁን ህዝብ መካከል ጠላትነት የለም።ህዝባችንም ይሄን ሃቅ በደንብ ማስታወስ ይኖርበታል።

ከዚያም ከዚህ ብዙ እልቂቶች ይሰማሉ። ስለዚህ ምን እንደምንጠብቅ ሊገባኝ አልቻለም። የትግራይ ህዝብ ለሺዎች ዓመታት በአብሮነትና በመልካል ጉርብትና ከአማራዉ፤ ከአፋሩ፤ ወዘተ ጋር በሰላም ኖሯል። ዛሬም በሰላም እንዳይኖር መከልከል የለበትም። ልጆቹን ለጦርነት መማገድ የለበትም። ልጆችን ወደትምህርት ቤቶች እንጂ ወደጦር ሜዳዎች መላክ እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃጢያት ነዉ። ገበሬዉ በሰላም ካላረሰ፤ ነጋዴዉ በሰላም ካልተንቀሳቀሰ ምን ሊበላ ነዉ?

ይህ ጉዳይ በፓርላማና በድንበር ኮሚሺን አማካኝነት እልባት ሊያገኝ ይገባል። ሰላምና ዕድገት ይሰፍኑ ዘንድ ከፋፋዩም ሕገ መንግሥት ቶሎ መለወጥ ይኖርበታል።

ከነሩዋንዳ እንኳን መማር የማይችሉ ጽንፈኞች መበርከት እጅግ በጣም ያሳዝነኛል። እነዚህ ሰዎች ከስህተቶቻቸዉ እስኪማሩ ድረስ የሚሊዮኖች ሕይወት መጥፋት የለበትም።

ካለዚያ ጉዳቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ፤ ወደሌሎችም ክልሎች ይቀጣጠላሉ። የተለመደዉ ርሃብ፤ ጥማት፤ እርዛት፤ ስደት፤ ልመናና እንግልት እየባሰበት ይሄዳል። ሰላም ሳይኖር ዕድገት ሊመጣ አይችልም። ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል።እግዚአብሔር ሁሉን አሟልቶ የፈጠራትና ለሁሉም የዳቦ ቅርጫት መሆን የሚትችል የተቀደሰች ሀገር እንደዚህ ስትወርድ በማየቴ ዘዝናለሁ፤ አለቅሳለሁ። የተማርነዉም፤ የታገልነዉም ለዲሞክራሲና ለዕድገት እንጂ እንደዚህ ዓይነት ዉርደትና ጥፋት ለማየት አልነበረም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፋኖ ጉዳይ እና መፍትሔዎች

 

4ኛ/ የሀገራዊ እርቀ ሰላም አስፈላጊነት

አንዲት ጣት በሰበሰች ተብላ ተቆርጣ አትጣልም ይላሉ አበዉ ሲተርቱ። በርግጥ ህወሃት በትግራይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላት። መፍትሔዉ ግን አማራጭ የተሻለ ሥርዓት ግንባት በማመቻቸት ህዝብን መሳብ እንጂ ማራቅ አያዋጣም።

የትግራይም ህዝብ የዓማራ ጭቁን ወገኑን እንደጠላት ማየት ትልቅ ኃጢያት ነዉ። ጠላቶች የተፈራረቁ በዝባዥ አምባገነን ሥርዓቶች ናቸዉ እንጂ ጭቁን ህዝብ አይደለም። እንንቃ ጎበዝ፤ ቅን ልቦና ይስጠን። አሁን ያለነዉ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ መሆኑን አንርሳ።

አሁን የሚታየዉ እኮ ከፍተኛ እልቂት ነዉ። ይሄ እስከመቼ ድረስ ሊቀጥል ይችላል? በከፍተኛዉ እየተሰቃዩ ያሉት እኮ ሕፃናት፤ ሴቶችና አረጋዉያን ናቸዉ። ባለሥልጣናት እኮ ልጆቻቸዉና የዘረፉት ሀብትም ዉጭ ሀገራት ናቸዉ። እንደሀገር የምንቀጥል ከሆነ እርማት ማድረግ ይኖርብናል።

ይሄን ጥያቄ በተመለከተ የሚከተሉት አካላት ከእንቅልፋቸዉ ነቅተዉ የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነቶችና ግዳጆች እንዲወጡ በትህትና ላሳስብ እወዳለሁ፤

ሀ) የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት፤

ለ) ወገን እንዳይጠቃ የመከላከያው ኃይል ኃላፊነት፤

ሐ) የኃይማኖት አባቶች የማስታረቅና የመገዘት ኃላፊነቶች፤ ታላቁ መጽሐፍ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር፤ በባልንጀራህ ላይ በሀሰት አትመስክር፤ ባልንጀራህን እንደራስህ ዉደድ፤ የተራበዉን አብላ፤ የተጠማዉን አጠጣ፤ እንግዳ ተቀበል፤ የታረዘዉን አልብስ፤ የታመመዉን ጠይቅ፤ ወዘተ አለ እንጂ ግደል፤ አፈናቅል፤ ዝረፍ አላለም። የኦርቶዶክስ አከርካሪ ሰበርን ብለዉ በአደባባይ የሚፎክሩትን ሰይጣናዉያን እያያችሁ፤ እየሰማችሁ ዝም ማለት የለባችሁም፤ ማስተማርና መገዘት ግዳጃችሁ ነዉና፤

መ) የሀገር ሺማግሌዎች ኃላፊነት

ዉድ ወገኖች፤ የምታዉቁትን ላስታዉሳችሁ በማለት እንጂ ብዙ የጨመርኩት አዲስ ነገር የለም። ያለችኝን የማካፈልና የሚሰማኝን ስጋት የማጋራት  ኃላፊነት ግን አለብኝ ብዬ ስለማምን ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮለኔል አያናው መስፍን ቤተመንግስት ከሄዱት የወታደሮች ጀርባ አሉበት ተብለው ተጠርጥረው ታሰሩ

ቸሩ አምላካችን ጭቁን ህዝባችንና ዉድ ሀገራችንን ይጠብቅ

2 Comments

  1. ያኔ ወያኔና ሻቢያ በባድሜ ሲፋለሙ አንድ አሽሟጣጭ ነጭ ጋዜጠኛ የውጊያውን ቀጠና ከተመለከተ በህዋላ እንዲህ ብሎ ነበር። ጦርነቱ ሁለት መላጣ ሰዎች ለማበጠሪያ እንደሚጣሉ አይነት ነው ነበር ያለው። የአሁኑ ተነስ፤ መጣንብህ፤ እናሸንፋለን ጡሩንባ ሁሉ የሰው ልጆችን ህይወትና ኑሮ ከቁጥር ያላስገባ በወንድሞችና በእህቶች መካከል የሚደረግ እልቂት ነው። ይህም ህሳቤ በማበጠሪያ (ሚዶ) ከሚጣሉት ጸጉር አልባ ሰዎች ጎን ያሰልፈናል። ፍጽም እብደት ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ በ 27 ዓመት ገነባሁ ያለው ሁሉ የሚፍረከረክበት ሃገርና ህዝብን ለመከራ የሚዳርግ የእልቂት ጥሪ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል እየሰማን ነው። ግን በስልጣን ጥም ለሰከረ ሰው የሰው ደም ምኑም አይደለም። ለዚያ ነው የትግራይ ልጆች ዛሬም ባልገባቸው ጦርነት ከመንገድ እየታፈሱ የሚማገድት። ለዚህም ነው ጦርነት ኳስ ጫወታ መስሎት አውቶቡስ ሞልቶ ወዪላችሁ እያለ ከማህል ሃገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር የሚነጉደው። ይህ እብደት አይደለም የሚል ካለ ራሱ ያበደና ሌሎችን ያሳበደ እንደ ጌታቸው ረዳ ያሉ ሙታኖች ብቻ ናቸው። ምን ማንን ገድሎ ነው እልል የሚባለው?
    ኢትዪጵያ የእምነት ሃገር ናት ይሉናል። ይህ ውስልትና ነው። አይደለችም። እውነተኛ አማኝ በዘሩና በቋንቋው አይሰለፍም። ሰውን በሰውነቱ ለክቶ ለሰላምና መረጋጋት ይሰራል እንጂ። አሁን በምድሪቱ የምናየው ዳግመኛ የጣሊያን ጦር ሊወረን ሲነሳ የሮማው ጳጳስ ይቅናችሁ ብለው እንደላኩት ነው። በተናጠልም ሆነ በህብረት ተው ይህ ነገር የቆመን ያፈርሳል፤ መገዳደላችን ይብቃ በማለት በይፋ ወያኔንም ሆነ ጠ/ሚሩን ያስጠነቀቀ የለም። አውቃለሁ የሚሰማ የለም ምን አደከመን እንደሆነ ጉዳዪ። ወንጌሉ ጀሮ ያለው ይስማ አይደል የሚለው። አቋምን ከዘርና ከቋንቋ፤ ከሃይማኖትና ከክልል አስተሳሰብ ነጻ በማድረግ በዚህ ዙሪያ ላይ የእምነት ሰዎች (እናቶችና አባቶች) ወይም ሽማግሌዎች የት አለ የጮኹት?
    ወያኔ መላልሶ መሬታችን እስኪመለስ እንዋጋለን ይላል። ሰው በጦርነት ካለቀ ባዶ መሬት ምን ይረባል? ደግሞስ ለሁላችን የሚበቃ ሃገር አይደል እንዴ ያለን? ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። በውጭ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለምን ጦርነቱ እንዲቀጣጠል በፈጠራ ቱልቱላ ሰውን እንደሚያነሳሱ አይገባኝም። ያለተያዘ ቦታ ተያዘ፤ ያልተደመሰሰው ተደመሰሰ እያሉ ወገን ወገኑን እንዲገል መገፋፋት ቢራቅም ከደሙ ንጽህ አያደርግም። አውቃለሁ ወያኔ በደባ የተካነ ስንኩል ስብስብ ነው። የአሁንም ሆነ ያለፈ ታሪካቸው ይህን አጉልቶ ያሳያል። ሰሚ ግን የለም። የዶ/ር አብይ መንግስት ደግሞ ሳይታሰብ ትግራይን ለቆ መውጣቱ የሚያስገርም ነገር ነው። ተደመሰሰ፤ ንፋስ ላይ ያለ ድቄት ነው የተባለው ወያኔ እንዴት ነው አፋር ድረስ በመኪና ሰዎችን እያጋጋዘ የጅቡቲ አዲስ አበባ መንገድን እዘጋለሁ የሚለው? የወሬውና የዜናው መጣረስ የሚነገረን አንድ ነገር ቢኖር በግጭቱ ላይ እውነት ቀድማ መሞቷን ነው። ሁለቱም ሃይሎች አይታመኑም። ለዚህ ማስረጃው ከላይ የተለጠፈው ፎቶ ነው። ስንቶች አለቁ በዚያ የመኪና ክምር ውስጥ? የስንቶች አስከሬን ወድቆ ቀርቷል? ስንቶችሽ ቆስለው እርዳታ እየጠየቁ አሸልበዋል። ይዘገንናል።
    በመጨረሻም በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ፈጣሪ የለበትም። የችግሩ ምንጮች እኛው ነን። ወንድምና እህቶቻችን እግርና እጃቸውን አስረን ገድለን በአስከሬናቸው ላይ የምንጨፍር የቁም ሙት ስብስቦች ራሳችን ነን። ፈጣሪ የሃበሻዋን ምድር ከተዋት ቆይቷል። ዝም ጭጭ ብሏል። እንድናስብበት የተሰጠንን ጭንቅላት መጠቀም ያቃተን እኛ። ምን አውርድ ነው የምንለው ፈጣሪን። ምህላው፤ ጸሎቱ፤ ጾሙ ሁሉ የውሸት ነው። ባይሆንማ ኑሮ የ3 ሺ ዘመን ነጻነት አለን የምንል እኛ ዛሬ ህዋ ላይ ነበር ቤታችን የምንሰራው። ግን አቋራጭ መንገድ አግኝተናል። እየተገዳደሉ ማለፍ። የዓለም መሳለቂያ መሆን። ሁሌ የልመና ኮሮጆ ይዞ እርድኝ ማለት። በሃበሻው ምድር ሃበሳ የሚቆጥረው ህዝቧ ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ጭምር ናቸው። ስለሆነም የትግራይ ግጭት ሁሉን የሃገሪቱን ቤት የሚያንኳኳ የመከራ ማእበል እንጂ በአማራና በፌዴራል መንግስቱ ጥምረት ብቻ የሚደረግ ፍትጊያ አይደለም። ጻድቃን መቼ አዲስ አበባ እንደሚገባ የሚያውቅ አለ? እንዴት ተብሎ ነው ሲኦል የምትወርደውን ሃገር እንደገና ወያኔ መግዛት የሚፈልገው? ለነገሩ አሁን ራሱ ህዝባችን በኑሮ ውድነት፤ በኮሮና ቫይረስ፤ በጦርነት ወዘተ የመከራ ኑሮ አይደል እንዴ የሚገፋው? ሲኦል እኮ ምድር እንጂ ሌላ እሳት የሚነድበት ቦታ የለም። ባጭሩ አሁንም እርቅ ለማውረድ ጊዜው አልመሸም። ከምንተላለቅ የህዝባችን መከራ ታይቶን በክብ ጠረጴዛ ላይ ልዪነታችን መፍታት ወይም ማርገብ ተገቢ ይሆናል። በቃኝ!

  2. በጣሙን አመሰግናለሁ ጌታዬ። የዓማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰበርን እያሉ ሲያቅራሩ ማንም አልተቃወማቸዉም፤ ማንም የመንፈስ አባት ወጥቶ አልገዘታቸዉም። ሰዉ በጎሳዉና በኦርቶዶክስ እምነቱ ምክንያት ሲጨፈጨፍ ብዙዎቹ ዝም ብለዉ ይመለከታሉ፤ የዘር ጭፍጨፋም የለም ብለዉ የሚክዱ ሰዎች ታይተዋል።

    ዘመኑ ዘመነ ፊዳና ዘመነ ኩነኔ ነዉ። እምነት ላልቶዋል። በገዳማት ዉስጥ የቅጠልና የስር ቁዋርፍ እየቀመሱ በሚፀልዩላት አባቶች ምክንያት እንጂ ሀገሪቱዋን ለማጥፋት ከተነሱ ብዙ ጊዜ አለፋቸዉ። ሥልጣንና ገንዘብ እንጂ የህዝብ ደህንነት አይታያቸዉም። በአንዱ ጥፋት አንዱ የሚነግሥ ይመስለዋል። ተያይዞ መጥፋትን እየረሳ።

    ‘አትዋል ይዋሉብህ፤ አትምከር ይምከሩ፤
    በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀሩ’
    ቸሩ አምላካችን ፍርዱን ይስጥ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share