በአዲስ አበባ በ5 ክፍለ ከተማዎች በ25 ቦታዎች ላይ 213900 ካሬ ሜትር ቦታ በህገወጥ ወረራ ተይዟል-ኢዜማ

በአዲስ አበባ ከተማ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ እንደተካሄደ ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ ፓርቲ (ኢዜማ) ተናገረ፡፡

ዜማ ዛሬ ይፋ ባደረገው የጥናት ግኝት ሪፖርት፣ ‹‹የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታ እና ፕላን ተሠርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበር እና በግል፣ ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉም ተደርገዋል›› ብሏል፡፡

‹‹በዋናነት የመሬት ወረራው ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ‹ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸው› እና ‹በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል› የሚሉ ግለሰቦች እና ወረራ በተፈፀመባቸው ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ናቸው›› ሲል የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹ጉዳዩን በማፋጠን ሕገ-ወጥ ደላላዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ›› ብሏል፡፡

‹‹በጠራራ ፀሐይ፣ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ አመራሮች እና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን የነበሩበት ነው›› ብሏል ኢዜማ ይፋ ያደረገው የጥናት ግኝት ሪፖርት።

‹‹በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች በተለያየ መልኩ ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወርረው እንዲይዙ አመቻችተዋል፣ የመንግሥትን ሥልጣን ለሕገ-ወጥ ተግባር ከለላና ሽፋን አድርገው ተጠቅመዋል፤ ከዚህም ባስ ሲል ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ራሳቸው ወረራ ፈፅመዋል›› ብሏል ሪፖርቱ።

‹‹ሕገ-ወጥ የሆኑ የግንባታ ፈቃዶች፣ ካርታ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሕጋዊ መስለው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋልም›› ብሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  «ፍልስፍና የሚጀምረው ከመደነቅ ነው» - የሞረሽ ወገኔ አዲስ መግለጫ

‹‹በአጠቃላይ በመሬት አስተዳደር በግንባታ ፈቃድ እና በደንብ ማስከበር እንዲሁም በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ግዴለሽነት እና የወንጀል ተባባሪነት ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ተዘርፏል›› ብሏል የጥናቱ ግኝት ሪፖርት።

‹‹ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በሀገራችን አዲስ ያልሆነና በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ግን በዚህ ደረጃ እና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም›› ብሏል፡፡

‹‹የመሬት ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች እንደሚስተዋለው በአገልግሎት ላይ የሚውሉት ቦታዎች ስፋት ከፍተኛ ከመሆናቸውም በላይ ወረራው የከተማ አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የወንዝ ዳርቻዎችን እንዲሁም ለመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል›› ብሏል፡፡

‹‹ከጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተገናኘም በግልፅ የታየው የመንግሥት ሕገ-ወጥ ተግባር ነው›› ያለው ሪፖርቱ፣ ‹‹ኢ-ፍትሐዊ ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣትና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችን እና ደንቦችን በማሻሻል ለካቢኔውና ለከንቲባው በተሰጠ ልዩ ሥልጣን (መመሪያ ቁጥር 1 እና 2/2011፣ ክፍል 2 አንቀጽ 12/2) ከንቲባውም ሆኑ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት ሆኗል›› ሲል አክሏል።

‹‹በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ፈፅሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት የማስተላለፍ ተግባር እንደፈፀመና እየፈፀመ መሆኑን አረጋግጠናል›› ብሏል የኢዜማ የጥናት ግኝት ሪፖርት።

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ያለበትን ከፍተኛ ድክመትና የተንሰራፋውን ሙስና ዋነኛ ማሳያ የሚሆነው መስከረም 2012፣ 5000 ቤቶችን ለግንባታ አቅዶ በበጀት ዓመቱ ምንም የተገነባም ሆነ ግንባታቸው የተጀመረ ቤቶች አለመገኘቱ ነው›› ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ከአሁን ቀደም በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ቦታ እና ኮንዶሚኒየም ቤት የተሰጣቸው መሆኑን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ደግሞ ድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደሏቸው መሆኑን አረጋግጠናል›› ብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ተነሱ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በብዙ የከተማው አካባቢዎችና ሰፋፊ መሬቶችን ዒላማ ያደረገ በተናጠል የሚደረግ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧልም ተብሏል።

ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የጥናት ቡድኑ በዋናነት ጥናት ያደረገው በአዲስ አበባ 5 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መሆኑን ጠቅሶ በዚህም መሠረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 88,100 ካሬ ሜትር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 63,000 ካ.ሜ.፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 15000 ካሬ ሜትር፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 23,600 ካሬ ሜትር፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 23,000 ካሬ ሜትር ቦታዎች በወረራና ከሕግ አግባብ ውጪ እንደተያዙ በወረራ ተይዟል የተባለው ቦታ የሚገኝበትን እያንዳንዱን አካባቢ በዝርዝር በመጥቀስ አመልክቷል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከታሰበለት ጊዜ በጣም ዘግይቶ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉ ሳያንስ ቤቶቹን ለመረከብ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከ15 ዓመታት በላይ የቆጠቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ሳያገኙ ግንባታቸው ያለቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላልተመዘገቡ እና ቁጠባ ላልፈፀሙ ሰዎች ተላልፈው እየተሰጡ መሆኑን በጥናት ደርሼበታለሁ ብሏል ኢዜማ።

በሥልጣን ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ በመቀየር በግለሰብ ትዕዛዝ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በጥናቱ ተረጋግጧልም ብሏል።

እነዚህ ሕገ-ወጥ ተግባሮች ያላቸው ተፅዕኖ ዛሬን የሚሻገር፣ ለነገም የሚተርፍ እና የህብረተሰቡን ቀጣይ ሕግን የማክበር ባሕሪ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ በመሆኑ ጥፋቱ የከፋ ነው ብሏል የጥናቱ ሪፖርት፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችና ድምዳሜዎችን ተመልክቶ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር የጠየቀው ኢዜማ፣ የመሬት ወረራውና ከሕግ አግባብ ውጪ የተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ባለስልጣናት እጅግ ሲከፋ ቀጥተኛ በሆነ የጥቅም ተጋሪነት ሲያንስ ደግሞ ኃላፊነታቸውን በትክክል ካለመወጣት በተሰጠ ሽፋን የተፈፀመ በመሆኑ፣ በዚህ ተግባር ውስጥ እጃቸው ያለበት ኃላፊዎች ላደረሱት ጉዳትና ለፈፀሙት ወንጀል በሕግ የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል ብሏል

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዲስ አበባ በተረጋጋ ሁኔታ ዋለች | ፌዴራል ፖሊስ ቴሌን እና ኢቲቭን ተቆጣጥሮ ነበር

4 Comments

  1. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሁን ምን እንደምትሉ መስማት እንፈልጋለን ። ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ሰው ሲሞት ብቻ ሳይሆን ሊገድሉን ሲሉም ድረሱልን ።

  2. EZEMA!
    You are playing the right role of opposition parties .It is an exemplary deed for those who cried out loud for what happened 100+ years ago.
    You are also helping Abiy take corrective measures before it is too late .
    The Abiy Administration should embrace such responsible parties instead of those who voiced to erect statue for what happened forty years back.
    Keep up raising the political bar of Ethiopian backward and shameful political activities.
    God bless you !

  3. መቼም ቢሆን እንዲህ አይነት ድረጊት መጥፋት አይችልም፡፡ የመሪዎች ትልቁ ድክመታቸው ማዳላታቸው ነው፡፡ በእድሜዬ እንደ ማንዴላ፣ ቼኮቪራና ማርቴን ሎተር ኪንግ አይነት ለሌሎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ያስተማሩኝ ናቸው፡፡ የህንዱ ማህተመ ጋንዲ፣ ዳግማዊ አጼ ምንሊክ፣ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴና መንግስቱ ኃይለማርያም ደግሞ የአንድ ሀገር ዜጋ ሁሉም እኩል መሆኑን ተምረባቸዋለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share