የቴዲ አፍሮ ‘ደሞ በአባይ ድርድር’ እና የኢትዮጵያ  ሉዓላዊነት

በደጀን የማነ መሠለ
(በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአለምአቀፍ ሕግ መምህር)
Email: [email protected]

በሙዚቃ ስራዎቹ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረጉ  የትውልዱ ምልክት የሆነው  የግጥምና የዜማ ደራሲው ድምፃዊ ቴዲ-አፍሮ(ቴዎድሮስ ካሳሁን) ስለ ታላቁ እና ስለገናናው የአባይ ወንዝ የተቀኘውን ደሞ በአባይ የተሰኘ  አዲስ  የሙዚቃ ስራ ለህዝብ ጀባ ብሏል፡፡  ሁሌም ስራው በጉጉት የሚጠበቅለት ይህ የትውልድ ድምፅ ይሄኛው ስራውም በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሚገባ እየተደመጠለት ነው፡፡ እኔም ይህንን የአርበኝነት ወኔን የሚያሰታጥቅ ሙዚቃ ደግሜ ደጋግሜ እያዳመጥኩ  በሙዚቃው ውስጥ ያሉ ስንኞች የሚያሰተላልፉትን መልዕክት  ከአለም-አቀፍ ሕግ አኳያ ለመመልከት ይህችን ፅሁፍ አዘጋጀሁ፡፡ ልብ አድርጉ  እኔ ኪነ-ጥበባዊ አስተያየት እየሰጠሁ አይደለም፡፡

እንዲህ ስል ልጀምር ቴዲ አፍሮ የታሪክ አዋቂ ብቻም ሳይሆን የአለም-አቀፍ ሕግን በሚገባ የተረዳ ሁለገብ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ቴዲ በዚህ ስራው የሙዚቃ ህግጋቶችን ብቻም ሳይሆን የሉዓላዊነት  ህግጋቶችንም ጭምር አክብሮ ነው የሰራው፡፡

ቴዲ ‘ማን ዝም ይላል ሆኖ ዜጋ ደሞ በአባይ ሲል በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ በሚገኙ ዜጎች እና በዚያች ሉዓላዊ ሐገር በሚገኝ ታላቅ ወንዝ መካከል ስላለ ግንኙነት እያዜመ መሆኑን በመግልፅ ይጀምራል፡፡ በዚህም አባይ ኢትዮጵያውያንን አንድ አድርጎ የሚያሰተሳስር እና አንድ ላይ የሚያስጮህ የማናገሪያ አንደበት መሆኑን እንደ ድምፃዊ ብቻም ሳይሆን እንደ ዜጋ እየጮኸ መሆኑን ይነግረናል፡፡

ሙዚቃው የወጣው ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ለመጠቀም እየገነባች ባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ አባይን ለዘመናት በኢ-ፍትሐዊነት እና በብቸኝነት ስትጠቀምና ስትደፋ ከኖረችው ግብፅ( ምስር) ጋር ድርድር ይሉት  ጦርነት ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው፡፡ ግብፅም ሆነች ሱዳን በኢትዮጵያ የግል ንብረት በሆነው ፕሮጀክት ላይ   የድርድር ጠረንጴዛን የተጋሩት ለአባይ ወንዝ ጠብታ ውሐ ሳያዋጡ ይልቁንም ለዘመናት ውሐውን ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት ሲጠቀሙ የኖሩ እና እየተጠቀሙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ ከሁለቱ ሐገራት ጋር ለድርድር መቀመጥ ሉዓላዊነቷን  የጣሰ መሆኑ እና በአለም-አቀፍ ሕግ ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት ሊያዙ የሚችሉበትን አንዳች መብት የማይሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቴዲ ደሞ በአባይ ድርድር ሙዚቃ የኢትዮጵያን በአባይ ላይ ያለን ፍፁማዊ  ሉዓላዊነትን የሚያስረዳ ነው፡፡ በሙዚቃው ውስጥ ያሉት ስንኞች የሚያስረዱት ይህንን እውታ ነው፡፡

ደሞ በአባይ ድርድር የሚለው ስያሜ በራሱ የኢትዮጵያ  በአባይ ወንዝ ላይ ያለን  ሉዓላዊ  መብት መሰረት ያደረገ እና በዚህ ሉዓላዊ መብት ላይ  ድርድር የማያስፈልግ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የአባይ ጉዳይ ለድርድር የሚበቃ ባለመሆኑም ምክንያት ‘አባቱም ገዳይ እናቱም ገዳይ ድርድር አያውቅም በሐገሩ ጉዳይሲል ይገልፃል ቴዲ፡፡ ቀጠለና ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ አመንጪ እና  ባለቤት ብትሆንም ከግርጌ ሐገራት ጋር በጋራ መጠቀም እችላለሁ የሚለውን ዘመናትን የተሸገረ አቋሟን እንዲህ ይገልፃል  ‘አባይ የግሌን ባልኩኝ ለጋራ፤ ካቃራት ምስር ግፍም ሳትፈራ ፡፡’ ይህ አገላለፅም ኢትዮጵያ የግሏ የሆነውን ወንዝ በአብሮነት መንፈስ  በጋራ መጠቀም እንችላለን ማለቷ ግብፅን (ምስር) ካልተስማማት(ካቃራት) የግብፅን ግፍ የአለመፍራት ጥግን የሚያመለክት መሆኑን ነው፡፡ እውነትም የአባይን ውሐ ለአያሌ ዘመናት በብቸኝነት እየተጠቀሙ ኖረው ዛሬ በኢትዮጵያ የግል ንብረት ላይ አብረን ካላዘዝን በሚል ያዙን ልቀቁን ማለታቸው የግፍ ግፍ ነው፡፡   ታዲያ ይህ የግብፅን የግፍ አለመፍራት አደገኛ አካሄድ የኢትዮጵያን የፍቅር እና የትዕግስት አካሄድ መፈታተኑ አይቀሬ መሆኑን ጥበበኛው ‘የተቆጣ እንደሁ ፍቅር ታግሶ የሚባላ እሳት ይሆናል ብሶ ‘ሲል  ያስጠነቅቃል፡፡ እውነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን የአልጠግብም-ባይ የግብፅን የግፍና የበደል በትር በፍቅር እና በትዕግስት የምንችልበት ጊዜ አክትሟል፡፡የግብፅን አደገኛ አካሄድም ህዝቡ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ እየተከታተለ ነው፡፡ እናም መንግስት  የዚህን ህዝብ ስሜት የሚጠብቅ ስራ የመስራት ታሪካዊ ሐላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህንን የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀምን ሂደት ለማደናቀፍ ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ደፍ ቀና ለምትለው ግብፅም ‘ሳንጃው ፀብ አይመርጥም፤ ልቁረጠው አለ እንጂ የራሴን ውሐ ጥም ‘ ሲል የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ ላይ ያለ ትክክለኛ ፍላጎት ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ መንገድ ከግብፅ መንገድ በተቃራኒው ውሀ ጥምን የመቁረጥ እንጂ ፀብ አጫሪነት አለመሆኑን ገልጧል፡፡ግብፅ ግን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በውሐ ጥምና በድህነት እንድትኖር የተቻላትን ሁሉ እያደረገች ያለች ሐገር መሆኗ በገሐድ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ  አቋም ወንዙን በጋራ መጠቀም ከተቻለ በሚል እንጂ የግብፅን ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከእቁብ በመቁጠር እንዳይደለ ‘ይሁን ይበጅ ለእኔም ለእሱዋም ብዬ እንጂ ማንንም አልፈራ፤ ‘ ሲል ሸልሏል፡፡

ቴዲ የአባይን ለዘመናት የግብፅ ሲሳይነትን በማውሳት ዛሬ ይህ የኢትዮጵያ ልጅ የእናት ሐገሩን ጭለማ ያበራ ዘንድ ወደ እናቱ መመልከቱ ግብፅን በእብሪት አሳብጦ አሻፈረኝ ካሰኘ እና የኢትዮጵያን በወንዟ የመጠቀም ትልም የሚያደናቅፍ ከሆነ ኢትዮጵያውያን የማንታገስ መሆናችንን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ይሄውና  ‘አባይ ለጋሱ ግብፅን አርሶ፤ አገሬን ባለ ልይ ተመልሶ፤ ብሎ አሻፈረኝ  ለሳበ ቃታ፤ እኔን አያርገኝ የነካኝ ለታ፡፡’ እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባን መሰረታዊ ጉዳይ ግብፅ አሻፈረኝ በማለት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና በአባይ ወንዝ ላይ የዲፕሎማሲ ጦርነት መክፈቷንና የድርድር ቃታዎችን ከሳበችብን ዘጠኝ አመታት መቆጠራቸውን ነው፡፡ በራሳችን ሉዓላዊ ሐብት ላይ ሰነድ ካልተፈራረምን በሚል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ይፈጥራሉ ያለቻቸውን መንገዶች ሁሉ እየተጠቀመች  ሲሆን ኢትዮጵያውያን ይህንን የእብሪት  ጉዞ በተለያዩ አማራጮች እየሞገትን እንገኛለን፡፡ ቴዲ ደግሞ ይህንን ወኔ በደንብ ሊያስታጥቀን ከች ብሏል፡፡ በለው ኸረ በለው እያለ፡፡ አዎ የግብፅ የእብሪት  ጎዞ በህዳሴ ሰበብ፤አባይን ለመክበብ በሚል የዲፕማሲ ጦርነት ስልት  ኢትዮጵያን አደገኛ የሕግ ሰነድ ለማስፈረም  እየተደረገ ያለ የሞት የሽረት ትግል መሆኑን አውቀን እኔን አያርኝ የነካኝ ለታ በሚል ወኔ የግብፅን አደገኛ ፍላጎት ማምከን አለብን፡፡ ይህን የማምከን ስራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየድርሻው የሚወጣው ሆኖ የተደራዳሪ ቡድኑ የመጀመሪያ ሀላፊነት አለበት፡፡ አዎ ቼ-በለው ኸረ-ቼበለው

ይህንን አደገኛ እና መርዘኛ  የግብፅ   አካሄድ  በመረዳትም እንደ ሐገር ቆፍጠን ያለ አቋም መያዝ እንዳለብን ቴዲ ይነግረናል ‘ከእንገዲህ አይኖርም ነገር ማለሳስ ከሞከሩንማ ደፍረው እዚህ ድረስ፡፡’  ለግብፅ የከረረ እና ድፈርት የተሞላበት አካሄድ እኛ ጆሮ-ገብ የሆኑና ተራ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ማለትም በራስ ሉዓላዊ ፕሮጀክት ላይ መተማመንን ለመፍጠር፤ ለቀጠና ትብብር ቅብጥርሶ ምንትሶ የሚሉ ተራ እና ብሔራዊ ጥቅምን የማያስከብሩ የመለሳለሻ ምክንያቶችን በመጥቀስ ከግብፅ ጋር የተጋራነውን ያልተቀደሰ የድርድር ጠረንጴዛ ትተን የመነሻ ጊዜው አሁንና አሁን መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡በአሁኑ እና በመጪው ትውልድ እጣፋንታ ላይ አደጋን ያረገዘ የድርድር ሂደት ቁጭ ብለን እንመለከት ዘንድ ታሪክ አይፈቅድልንም፡፡ አዎ ማለሳለሱ ይብቃ እና አይሆንም እንበል፡፡ አይሆንም ለማለት መጀመሪያ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ሉዓላዊ መብት አላት የሚለውን ሕጋዊ መርህ እንቀበል፡፡ ይህንን ሉዓላዊ መብት ለማስከበር ደግሞ ከግብፅ የተሰነዘረውን ሉዓላዊነትን የመጋፋት ሙከራ ባለን ተፈጥሮአዊ እና ሕጋዊ ራስን የመከላከል መብት ተጠቅመን እንመክት፡፡ ቴዲም የሚለን ይሄንኑ ነው፡፡   ተው ሲሉት ካልሰማ አሳደህ በለው፤ በአባትህ ጎራዴ በተሰቀለው፡፡ ይህ ተገቢ እና ሐገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ከተሰነዘረ ጥቃት ራሰቸውን ለመከላከል ይከተሉት ዘንድ የተቀመጠ መብት ነው፡፡ምንም እንኳን ግብፅ ጦር አዝምታ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሳ   ጦርነት ባትከፍትብንም የኢትዮጵያን  ሉዓላዊ መብት የሚነካ አደገኛ ሰነድ ለማስፈረም ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እና እየተፋለመችን በመሆኑ እና ተይ ስንላትም አልሰማ ስላለች ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር አባቶቻችን አልሰማ ያለ ነጭ ወራሪን ድል የነሱበትን ጎራዴ ከተሰቀለበት አውርደን እንፋለም ዘንድ ሕጋዊ መብት አለን፡፡አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የእቴጌ ጣይቱን  የውጫሌ ውልን ቀዶ የመጣል የጀግንነትን ጎራዴ ከተሰቀለበት አውርደን የግብፅን የአሳሪ የህግ ሰነድ ፈርሙልኝ ጥያቄ ድራሹን ማጥፋት ይኖርብናል፡፡ ግብፅን አሳዶ መምታት ማለት አባይ የኔ ነው በወንዜ ላይ ማንም ሊያዘኝ አይችልም ብሎ አቋም መያዝ ነው፡፡

ይህንን የተሰቀለ ጎራዴ ለማንሳት  የግብፅ የብቻይን ልጠቀም ባይነት ያሳደረብን ብሄራዊ ህመም የሚያስገድድን መሆኑን እያመመው እያመመው መጣ፤ አለፈ ገደፉን ትዕግስቴ ልክ አጣ ሲል ቴዲ ይነግረናል፡፡ አዎ በግብፅ ላይ ያሳዬነው ትዕግሰት ሞልቶ ፈሷል፡፡ግብፅ ከትላንት እስከዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆኑ መንዶች ሴራን ስትሰራ ከመኖሯም በላይ ዛሬ ከድሐ እናት መቀነት ተፈትቶ ፤ከእለት ጉርስ ተቀንሶ በሚገነባ ግድብ ላይ እጇን አስገብታ ለማደናቀፍ እና ኢትዮጵያ በቀጣይ በአባይ ወንዝ ላይ ሌሎች ልማቶችን እንዳታለማ በህግ ለማሰር የምታደርገው የተንኮል አካሄድ በቃን፤ ትዕግሰታችን ተሟጧል ማለት አለብን፡፡

ግብፅ ከህመማችን ላይ ሌላ ህመም እየጨመረች፤ ትዕግሰታችንንም እየተፈታተነች መቀጠሏን እንኳን ለጎረቤት ከወንዜ ለጠጣ፤ ቋያ እሳት ነው ክንዴ ከሩቅም ለመጣ ሲል ለነጭ ወራሪዎች  ያሳዬነውን አይበገሬነትና ድል አድራጊነት ያወሳል፡፡ ለነገሩ ግብፆችም ቢሆኑ የአያቶቻቸውን የሽንፈት ታሪክ ቢገልጡ ይህንን ቋያ እሳት የሆነ የኢትዮጵያውያንን እጅ መቅመሳቸውን አያጡትም፡፡ ቴዲ ይቀጥላል አስተምረዋለሁ ታሪኬን ከጥንቱ፤ እስኪፈራኝ ድረስ የሞተው አባቱ፡፡ ከታሪክ የወረስነው ተፈጥሮአዊ ሉዓላዊነትንና ለዚህ ሉዓላዊነትም አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል ወራሪዎችን አሳፍሮ መመለስ ነውና ከታሪክ በተቃራኒ ገፅ እንዳንቆም  ታሪክ ሀላፊነትን ጥሎብናል፡፡

ስለሆነም በአለም ላይ ካሉ ሐገራት ብቸኛ ተፈጥሮአዊ ሉዓላዊነት ያለን ህዝቦች መሆናችንን በማወቅ   ግብፅና ሱዳን እየጠየቁን ያለውን ሕገ-ወጥ ጥያቄ አሽቀንጥረን እንድንጥል የትውልዱ የጥበብ ንጉስ እና የኢትዮጵያዊነት አድማስ የሆነው የቴዲ-አፍሮን(ቴዎድሮስ ከሳሁን) ጥበባዊ የወኔ ስንቅ ይዘን እንፀና ዘንድ ከእንገዲህ አይኖርም ነገር ማለሳስ ከሞከሩንማ ደፍረው እዚህ ድረስ የሚለውን ስንኝ ደጋግመን እናስታውስ፡፡

 

4 Comments

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.