የጥቁር ሕይወት ይገዳል (Black life matters) ቁማር! ለመሆኑ እኛስ? – ሰርፀ ደስታ

ለማስተዋል፡-ሰሞኑን በምድረ አሜሪካ ሚኒአፖሊስ ከተማ  በጠራራ ፀሐይ በሰላማዊ መንገድ ላይ ፖሊሶች ጆርጅ ፈሎይድ የተባለወን ጥቁር ጎልማሳ ሲገድሉ የሚያሳይ ፊልም ከተለቀቀ በኋላ ዓለም ዓቀፍ ይዘት ያለው የሚመስል የሕዝብ ተቃውሞ እየታየ ነው፡፡ ግፉ በተፈጸመባት አሜሪካ ከጎዳና ላይ ተቃውሞ አልፎ ኃይል ወደ ተሞላበት ሁኔታ ተለውጦም አይተናል፡፡ ሁኔታው እጅግ አሳዛኝም አስደንጋጭም እጅግ የሚያናድድም ስለሆነ ይሄ ቢሆን አይገርምም፡፡ እስካሁንም ሕዝብ ንዴቱ አልበረደም፡፡ እርግጥ ነው መሠረታዊ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ የሕዝብ የተጠናከረ ተቃውሞና ጥያቄው መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በምድረ አሜሪካ ጥቁሮች (ነባሮቹ በተለይ) ሆን ተብሎ እንደሚገፉና ጥቃትም እንደሚደርስባቸው ከብዙ ከምናያቸው ነገሮች እንረዳለን፡፡ ሆኖም ለእኔ የጥቁር ነፍስ ይገዳል አይነት ዘመቻው ከማይመቹኝ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ጉዳዩ ከነፍስ ግድያ ጋር ለመድረስ ብዙ የካበተ መሠረት ያለው ነውና፡፡ የጥቁር ሆነ የነጭ ነብስ በፍትህ እኩል ነው፡፡ ፍትህ ስል እውነተኛውን ማለቴ እንጂ የአሜሪካ ማለቴ አደለም፡፡ ይሄን የጥቁር ነብስ ይገድላልን አስተሳሰብ የሚያጮሁት ደግሞ አስመሳዮቹ ስለሚመስሉኝ የበለጠ በሁኔታው አዝናለሁ፡፡

ነገሩ እንዲህ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ልሳሳት እችላለሁ፡፡ የጥቁር ሆነ የነጩን ነብስ በፍትህ አግባብ ከመጠበቅ ይልቅ የጥቁር ነብስ በአክቲቪስት የነጭ ነብስ በስልጣን እንዲጠበቅ እየታወጀ ይመስላል፡፡  ሆኖም ግን ሄዶ ሄዶ ብያኔ ሰጭው ስልጣን ስለሆነ የጥቁር ነብስ በስልጣንና በፍትህ እስካልተጠበቀ ድረስ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ይሄ የጥቁር ነብስ ይገደኛለ ዘመቻ በኦባማ እንደተጀመረ እናውቃለን፡፡ ከዛ በፊትም እንዲህ ስያሜ አይሰጠው እንጂ እንዲሁ የጎዳናዎች ማሞቂያና የአስመሳዮች ዘፈን እንደነበር ይሰማኛል፡፡ በሚኒአፖሊስ የሆነው ክስተት በራሱ ብዙ ነገር ይነግረናል፡፡ ይሄ ዓለምን ጉድ ያሰኘ ነውር በፊልም ባይለቀቅ ኖሮ ዋና ገዳዮን ጨምሮ ፖሊሶቹ እንኳን መከስስ ያቺ መጀመሪያ የተደረገች እርምጃ ከሥራ መባረርም እንደማይገጥማቸው ታዝበናል፡፡ ምን አልባትም በውስጥ ጥሩ አደረግህ ተብለው ባይሸለሙ ማለት፡፡ በሕዝብ አደባባይ እናወግዛለን እያሉ የሚያቅራሩ ባለስልጣናት ያንን ሂደት ላይ መነካካት አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም ትኩረቱ የአገሪቱ ፕሬዘደንት ላይ እንዲያነጣጥር እያደረጉ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን በምንም መለኪያ ከትረምፕ ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ ስለዚያ እመጣበታለሁ፡፡ ጉዳዩ የሚኒሶታዎቹ ባለስልጣናትና የፍትህ ሰዎች ጋር ያለ ነው፡፡ ፊልሙ ይፋ መሆኑ ስለታወቀ ገዳዮች በሥራ መባረር ብቻ ሊታለፉ ነበር፡፡ ከሶስት ቀን በኋላ ዋና ገዳዩን በሶስተኛ ደረጃ ግድያ ከሰሱት፣ ቆይተው የሕዝብ ተቃውሞ እያየለ ሲመጣና አንዳንድ ሰዎች ስለ ሆኔታው ጠንከር ያለ አስተያየት መስጠት ሲጀምሩ የዋና ገዳዩን ክስ ከሶስት ወደ ሁለት በማድረግ ሌሎች ሶስቱም በተባባሪነት ተከሰሱ፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋር እየሰራ ያለው ሕግና ፍትህ ወይስ የሕዝብን አመጽ ፍራቻ ቢባል መልሱን ለአንባቢ ልተወው፡፡

አስመሳይነትና ዘራፊነት፡-ሌላው በዓመፁ ብዙ ንብረት መውደምና ምን አልባትም በሰዎችም ላይ አደጋ የደረሰ መሰለኝ፡፡ አሁንም እነዛ አስመሳዮች ነብረትና አደጋ የሚፈጥሩትን አዎ ትክክል ናቸው ስለተናደዱ ነው በሚል ነገሩን ሌላ መልክ እንዲይዝ ሲያበረታቱ ነበር፡፡ እንበል ስለተናደዱ የመንግስትን ንብረት የፖሊስ መኪናን ሊያወድሙ ይችላሉ፡፡ ይሄ ሊጠበቅ የሚችል ነው፡፡ ለፍትህ ወጣሁ ያለ በንዴትና በአመጽ ተጀቡኖ ዘረፋና የግለሰቦችን ንብረት ማውደምን ግን እንዴትና በምን መስፈርት ከአሳዛኙ የፈሎይድ ግድያ ፍትህ ጥያቄ ጋር ሊገኝ ይችላል፡፡ ይልቁንም በመንገድ ላይ በጨካኝ ፖሊሶች ሊያውም ሲያጭበረብር በሚል የተገደለውን የፍሎይድን ሞት በዘረፋ ሲያራክሱት ታዝበናል፡፡ በመንገድ ላይ የወደቀው ሳይገዳቸው ጫማና ሶፍት ለመዝረፍ እርስ በእርስ ሲጋፉ አይተናል፡፡ እንግዲህ የጥቁር ነብስ ይገደኛል የሚል ዘግናኙ የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ እንኳን ከጫማና ከሶፍት በላይ እንዳልገደደው ታዝበናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጃዋር ቃለምልልስ በፓልቷክ

የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችስ፡-ሁሉም ያስተውል ይሄ ለጥቁሮች ለየት ያለ ጥበቃና ፍትህ ያስፈልጋል አይነት ነገር ምን ማለት እንደሆነ በደንብ አጢኑት፡፡ እኛ ስላገዝናችሁ ነው መብታችሁ የተጠበቀው አይነት አንድምታ እንዳለው አስተውሉ፡፡ የጥቁሩ ማሕበረሰብ ዋነኛ ችግር በስነልቦና የበታች እንዲደረግና የተረጅነት አስተሳሰብ እንዲኖረው በሚያደርግ ልዩ የተሳለጠ አሰራር እያኖሩት እንደሆነ አስተውሉ፡፡ በወሳኝ መዋቅሮችና በምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች ሱታፌው እንዲወሰን በማድረግ ሁሌም እነሱ በሠሩለት ልክ እንዲኖር ነው የተደረገው፡፡ ኑሮው በስራና በሌሎች የአገሪቱ ጉዳዮች በመሳተፍ የተጠመደም ስላልሆነ በጎጂ ሱስና በወንጀል ተግባር እንዲባክን ተደርጓል፡፡ ቁልፉ ያለው እዚህ ጋር ነው፡፡ እርግጥ ነው ጥቁሩ ከቁጥሩ አንጻር ብዙ ወንጀል ይፈጽማል፡፡ ለብዙ ሱሶችም ተጋልጧል፡፡ በአጠቃላይ መጥፎ የተባሉ ነገሮቹ ሁሉ በጥቁሩ በዝተው እናያለን፡፡ ለምን? ለእኔ ምክነያት ብዬ የምለው ሆን ተብሎ ጥቁሩ ማህበረሰብ ከኢኮኖሚውና ከመንግስታዊ መዋቅሩ እንዲወጣ ተደርጎ በተረጅነት እንዲያድር የተሰራበት ሤራ ነው፡፡ ፍትህ ለጥቁር ለነጭ ለሴት ለወንድ ብሎ ነገር ባለስፈለገ ነበር፡፡ ግን ይሄን አስተውሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ስለአሜሪካ ጥቁሮች ያስባል እስኪ የደቡብ አፍሪካዊያኑን ጥቁሮች አስተውሉ፡፡ በአገራቸው በቁጥረም ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም እንዴት አድርገው ከሰው አስተሳሰብ እጅግ ዝቅ ወደ አለ ሁኔታ እንዳወረዷቸው ታዝበናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ነጮች ዛሬም ጌታው ናቸው፡፡ በነጮች የተገነባ ጭንቅላት ስለሆነ ማለት ነው፡፡ የሌላውን አፍሪካዊ ጥቁር ግን በምን አይነት አረመኔያዊ ግድያ ሲገድሉ እንደነበር ከፍሎይድ በከፋ ሁኔታ ታዝበናል፡፡ አንድ አደለም በብዙ መቶዎች ምን አልባትም በሺዎች እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መልኩ በእሳት በማቃጠልና በሌሎች ዘግናኝ ሁኔታ ሲገድሉ ታዝበናል፡፡ ፍትህ!!!! ሥነልቦታ!! እንግዲህ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በእኛው አድሜ እነኳን ነጭን በጫንቃቻ ተሸክመው መጓጓዣ እንስሳ ሆነው አይተናል፡፡ ብዙዎች አፓርታይድ በሚል ቃል ነገሩን ሊሸፍኑት ይሞክራሉ፡፡ ጉዳዩ ከዘር ልዩነት በላይ የሆነ የሰውን ልጅ እንደ እንስሳና እቃ መቁጠር ነበር፡፡ የነበረው እውነት ግን በቀጥታ የባሪያ ሥርዓት እንደነበር አንድም ደፍሮ ሲናገረው አልሰማሁም፡፡

ትረመፕና ባይደን፡- በምድረ አሜሪካ በዲሞክራሲ ሥም ተጀቡኖ ያለው ጉድ ከዛ ከደቡብ አፍርካው ትንሽ ከፍ ብሎ ምን አልባት የአፓርታይድ ሥም ሊስማማው ይችል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ከሰሞኑ እንዳየንው በዘረፋና ወንጀል ተሰማርተው ያሉትን ሲያበረታቱ ታዝበናል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚደንት የሆኑት ትረምፕ ነገር ማስመሰል ብዙም ስለማይሆንላቸው ብቻም ሳይሆን ድርጊቱም ፍትህን ለማምጣት ሳይሆን ፍትህን ለማጠየም እንደሆነ ስለተረዱ ሁኔታውን በይፋ አወገዙ ወታደሮችም ልከው በሀይል ተቆጣጠሩት፡፡ በተቃራኒው ብዙ የዲሞክራት መሪ ነን የሚሉት ተፎካካሪው ፕሬዚደንት ባይደንን ጨምሮ ድርጊቱን በማበረታትና ፍትሕን ለማጠየም ለዘመናት ሲጠቀሙበት የነበረውን ሴራ ዛሬም ሲደልሉበት እያየን ነው፡፡ የሚኒአፖሎቹን ባለስልጣናት አይን ያወጣ ወንጀልን መተባበርን አቅጣጫ ለማስቀየር ዛሬ ሁሉም ትረምፕ ላይ ተሰልፎ አይተናል፡፡ ባይደንን ጨምሮ ለዘመናት በመንግስቱ መዋቅር ነበሩ ይሄንኑ ዛሬ የሚሰሩት ቁማር እየቆመሩ ዛሬም ጥቁሩ በራሱ ሙሉ መብት እንዳለው እንዳያስብ እኛ ነን ያንተ ጠባቂ የሚልን አስተሳሰብ እንዲኖረው ሙጥኝ ብለውበት እናያለን፡፡ እዚህ ላይ ትረምፕ ለጥቁሮች ከነጭ አኩል ያስባል የሚል አስተሳሰብ ያለች የቧህ አደለሁም፡፡ ሆኖም ግን የትረምፕ መንግስት ጥቁር ነኝ ከሚለው የኦባማ አስተዳደር በላይ ለጥቁሮች በራሳቸው እንዲተማመኑና ተሳታፊ በአገሪቱ የሥራ ድርሻም ትልቅ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ልንክደው የማንችለው እውነት ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ትረምፕ ጉዳዩን ከቁማር ይልቅ ጆርጅ ፍሎይድ ላይ የተደረገውን የግፍ ግድያ በቀጥታ ትኩረት እንዲኖረው ነው የፈለጉት፡፡ የዘር የሀይማኖት የምናምን ከሚለው በፊት ፍትህ የሚለው ፊት ለፊት ስለነበር፡፡ ገዳይ በዘረኝነት ገደለው ግን የሚኒአፖል የፍትህና ሌሎች ባለስልጣናት ለምን ፍትህን ለሟች አላሰቧትም፡፡ ትረምፕ በቀጥታ የፍሎይድ ደም ደመ ከልብ ሆኖ አይቀርም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ጉዳዩንም የፌደራሉ መንግስት ሳይቀር ገብቶ ሊመረምር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩ ወደፌደራል ሄደ ማለት ደግሞ በገዳዮች ከነበራቸው ክስ በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ እንግዲህ ትረምፕን በማውገዝ የነገሮችን አቅጣጫ ለማስቀየር የሚሞክሩት የዘመናት ቁማርተኞቹ ትረምፕል ወሮበሎችንና ዘራፊዎች ለምን ዘራፊዎች አለ የሚል ነው፡፡ ለምንስ ወታደር አዘምቶ ወሮበሎችን ተቆጣጠረ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ከጥፋትና ወንጀሉ በላይ የፍሎይድን ደም ማርከስ ነው፡፡ እንግዲህ በሰው ፊት ማስመሰላቸውን ለዘመናት የተካኑት የሚሉን ይሄ ነው፡፡ ፍትህ እንጂ የጥቁር የነጭ በሚል ሌላ ዘረኛ የሆነ ዘመቻ አሁንም የጥቁሩን ማህበረሰብ በስነልቦና የበታች ለማድረግ የሚሞከር ቁማር ቢቀር እላለሁ፡፡ ይሄ ቁማር በትክክል የማይረዳው አብዛኛው ጥቁር በዚህ ሊደሰት ይችላል፡፡ አካሄዱ ግን ያው የኖረ ቁማር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ህወሓት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቆመ እጅግ መሰሪ የፖለቲካ ኃይል ነው” - አቶ አገዘው ህዳሩ፣የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፤

የፍሎይድ ጉዳይና እኛ፡-ለፍሎይድ የሚያጫፍረው ኢትዮጵያዊስ እራሱን ከየት ይመድብ ይሆን፡፡ ከላይ የደቡብ አፍሪካውን አረመኔያዊ ግድያ ቀደም ብለን በቴሌቪዥን በራሳችን ወገኖች ሲደርስ ምን እንሰሶች ናቸው ብለን ነበር፡፡ ብዙም አልቆየንም የእኛዎቹ ከተሞች ያን በቴሌቪዥን ያየንውን አረመኔነት በተግባር አሳይተውናል፡፡ አዎ የፍሎይድ አሟሟት ዘግናኝ ነው ሆኖን ከእኛው አረመኔነት ጋር በፍጹም አይወዳደርም፡፡ አሜሪካ በጥቁሮች ላይ አድልኦ ይደረግባቸዋል አልፎ አልፎም ይገደላሉ፡፡ በእኛው አገር ግን በዘሩ ምክነያት የዘር ማጥፋት ግፍ ለወሬ ቀፋፊ ግድያዎች እናያለን፡፡ እዚህ ላይ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስቴር ቱርዶ የተናገሩት በሳል ንግግር እጅግ መሰጠኝ፡፡ በዙዎች በዛ ንግግራቸው አሁንም እንዴት ትረምፕን ማውገዝ ትቶ በእኛ ውስጥ ሥር የሰደደ የዘረኝነት ችግር አለ ይላል ብለው ተበሳጭተውበታል፡፡ አስቂኝ ነበር የተችዎቹ ንግግር፡፡ ትሩዶ ግን በራሴ ያለ ምሰሶ እያለ የሰው ጉድፍ ለማውጣት የምምክር እኔ ማን ነኝ ነበር መልሱ፡፡ ተወዳጅ ነው፡፡ እርግጥ ነው በካናዳ እንደ አሜሪካው ያለ ነገር የለም ሆኖም በስልታዊ ሁኔታ የከፋ አድልኦ እንዳለ ይታወቃል፡፡ መንግስት ግን ይሄን ለመስቀረትና ሁሉም ካናዳዊ እኩል የሚታይበትን ብዙ ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ፍትህ ቦታም ሲደርስ ጉዳዩን እንዲህ በቀላል አያዩትም፡፡ እንግዲህ ቱርዶን የራሴ ምሰሶ የሚያህል ጉድፍ በአይኔ እያለ ያሰኘው በእንዲህ ያለቸው ብዙ ፍትህ ያለባት ካናዳ መሪ ሆኖ ነው፡፡ እኛስ ሰውን በአደባባይና በፖሊስ ታጅበት ቁልቁል ሰቅለን የምንገድል ፈሎይድ በዘሩ ምክነያት ጥቃት ያደረሱበት ለፍርድ ይቅረቡ ለማለት ምን ሞራል ይኖረን ይሆን? ለፍሎይድ ከሌሎች ጋር ያዳመቅንውን ያህል በእኛው ሲሆን ብዙዎች ምንም አልመሰለንም፡፡ አሁንማ የተለመደ ሆኗል ደንዝዘናል፡፡ በአስራዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከመንግስት ዩኒቭርሲቲ ታፍነው ተወስደው ዛሬም ድረስ ምን እንደሆኑ ሳይታወቅ እንዳታነሱብን የሚሉ ባለሥልጣናት፣ በዩኒቨርሲቲው በዘሩ ምክነያት ከፎቅ እየተፈጠፈጠ የመገደል ተማሪ ያለባትን አገር የሚመሩ የእኛዎቹም መቼም አያፍሩምና የፍሎይድን ሞት ሊያዳምቁ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በሕገመንግስት ሳይቀር ዜጎችን በዘራቸው ምክነያት የተለያየ ምደባ የሰጠ መንግስት ስለዘረኝነት አወግዛለሁ ሲል ልንሰማ እንችላለን፡፡ መቼም እንደቱርዶ አይነት ነግግር ይወጣቸዋል ብዬ አልጠብቅም፡፡ መሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም እንደእውነቱ ይሄን ባየንበት አይናችን ወደራሳችን ብናይ መልካም ነው፡፡ እርግጥ ነው ግፍ ማውገዝ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም ይሄን ስናወግዝ ቢያንስ የእኔስ ጉድ ብሎ ማሰብ እጅግ ለሕሊና ይጠቅማልና ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አክራሪነት በኢትዮጵያ - ጥያቄዎች ለሃጂ ናጂብ

ኮረና በኢትዮጵ፡-ዛሬ የተነሳሁበት ጉዳይ ባይሆንም በአገራችን አሁን የኮረና በሽታ አሁን ብዙ ሕዘብ እያጠቃ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ ብዙ ነገር ይቆጫል፡፡ ሀምሳ ዓመት ፖለቲካ፣ ሰላሳ ዓመት ዝርፊያነ ዘረኝነት ፖለቲካ፡፡ ብዙ ጊዜ ነበር፡፡ ቢያንስ ከዚህ በተሻለ ፈቀቅ የምንልበት፡፡ በ50 ዓመት ዛሬ ያለችበት ቦታ የደረሰችውን ኮሪያን በአይኔ አይቻለሁ፡፡ ኧረ ምን ኮሪያ ብቻ ታላቋ ቻይናስ ብትሆን የዛሬ 50 ዓመት ምን ነበረች? ሕንድስ ብትሆን? ቻይናና ሕንድ በአንድ ወቅት በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ በረሀብ አልቆባቸዋል፡፡ ቻይና ከ30-40 የሚሆን ሕዝብ የዛሬ 70 ዓመት ገደማ፣ ህንድ እስከ አረንጓዴው ዘመቻ ድረስ፡፡ እኛም ዊ አር ዚ ዎርልድ የተዘመረልን ዘመን ሩቅ ነው፡፡ እኛ ግን ዛሬም በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ይራብብናል፡፡ የሚራበው ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሆኖ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል፡፡ አሁን በእንቅርት ላይ ደግፍ እንደሚባለው ይሄው ሌላ ተጨማሪ አደጋ ተጋርጦብናል፡፡ በክርምት የአንበጣ መንጋ ብዙ ቦታዎች ሲያጠቃ ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ዘመን ከኮቪድ ጋር ምን ያህል እንደሚራብ አናውቅም፤፡ ዛሬ ሁሉም አገራት የራሳቸው ችግር ስላለባቸው እንደድሮው እንኳን ዳረጎት ይጥሉብናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ አዝናለሁ! ከእኛ እየመነጩ ሌሎች አገራት ባለቤት የሆኑባቸው ወንዞች ምንጭ ኢትዮጵያ ከ እስከ የማይባል መደበኛ የረሀብ ሀገር፡፡ ይሄን የሚያስብ ባለስልጣም ሆነ ሙያተኛ ጠፋ፡፡ ያኔ ሪፎርም ተብሎ ሰሞንኛ ሆኖ በቀረው ጊዜ ብዙዎች ትልልቅ ሀሳብን ይዘው ወደ አገራቸው ሊገቡ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ በኋላ ሥልጣን ላይ ያሉት ያን እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚፈሩት ታዘብን፡፡ አስቦ በማቀድና በጥበብ ሳይሆን በዘመቻ እየወጡ ነብረት ማውደም የአንድ ሰሞን የአበልና የወርክሾፕ ዳረጎት እንጂ ማን ለአገርና ሕዝብ ይጨነቃል? ይቆጫል! ዛሬ ግን እጅግ አስከፊ ነገር መጥቷል፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይታደግ! ለዓለሙ ሁሉ ምህረቱን ያውርድ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share