የኮረና ቫይረስ ስርጭት እና ሰዋዊ ደህንነት በኢትዮጵያ

ታደሰ ብሩ

ሰዋዊ ደህንነት (Human Security) በተለምዶ ከምናውቀው የመንግስት ደህነት (State Security) በጣም ይለያል። ሰዋዊ ደህነነት ሰው-ተኮር እና ሁለገብ እሳቤ ነው። በስፋት የሚታወቁ 7 ዋና ዋና የሰዋዊ ደህንነት ስጋቶች አሉ፤ እነዚህም (1) የኢኮኖሚ ደህነነት፣ (2) የምግብ ደህነነት፣ (3) የጤና ደህነት፣ (4) የተፈጥሮ ከባቢ (environment) ደህነት፣ (5) የግለሰብ ዜጎች (ነዋሪዎች) (personal) ደህነት፣ (6) የማኅበረሰብ (community) እና (7) የፓለቲካ ደህነት ናቸው።

አሁን አገራችንን (ዓለምንም) እያስጨነቀ ያለው የኮረና ቫይረስ ስርጭት የጤና ደህንነት ስጋት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ አቅሙ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይህ ጥረት መቀጠል አለበት፤ ከዚህ በፊትም እንገለጽኩት በዚህ ዘመቻ ሁላችንም ከመንግስትን ጎን የመቆም ኃላፊነት አለብን። የመጣብን አደጋ በደካማ የመንግስት አቅም መቋቋም ሊያዳግት ስለሚችል መንግስትን ማጠናከር የጋራ ኃላፊነታችን መሆን ይኖርበታል።

የጤና ደህነት ችግር የጤና ችግር ብቻ ሆኖ አይዘልቅም፤ ሌሎች የደህነት ችግሮችን ይፈጥራል፤ ቀድሞ የነበሩትን የደህንነት ችግሮችንም ሊያባብስ ይችላል። የኮረና ቫይረስ ስርጭት የኢኮኖሚና የምግብ ደህንነታችን ላይ አደጋ እንደሚያመጣ በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤ ያለ ይመስለኛል።

የኮረና ቫይረስ ስርጭት ከጤና ችግርነቱ ባሻገር በኢኮኖሚና በምግብ ደህንነታችን ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች የደህንነት ዓይነቶች ላይ ስለሚያስከትለው ችግር ሲነገር ግን ብዙም አልሰማሁም፤ ይህ በጣም ያሳስበኛል። እንዲያውም በግልባጩ “የኮረና ቫይረስ ክስተት በማኅበረሰባችን ውስጥ ያለውን መልካምነት አጉልቶ አውጥቷል“ የሚሉ አስተያየቶችን ነው የምሰማው። ይህ በአጭር ጊዜ እውነት ሊሆን ቢችልም ለረዥም ጊዜ ስለመዝለቁ መጠራጠር ይበጃል። የጋራ ችግር መረዳዳትን የሚፈጥር የመሆኑ ያህል የወንጀሎችና የቅራኔዎች ምክንያትም ሊሆን ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕብር ራዲዮ ዕለታዊ ዜና | Ethiopia Feb 14, 2023

ተግባራዊ እርምጃዎችን ካልወሰድን የኮረና ቫይረስ ስርጭት በኢኮኖሚና በምግብ ደህነታችን ላይ ከሚያደርሰው አደጋ ባልተናነሰ (ምናልባትም እጅግ በባሰ) ሁኔታ በግለሰብ ዜጎች፣ በማኅበረሰቦቻችን እና በፓለቲካ ደህነታችን ላይ አደጋ ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ።

“የግለሰብ ዜጎች ደህነት” ስል በቅድሚያ የሚታየኝ በተለይ በከተሞች እየተባባሰ የመጣው የተደራጀ ዝርፊያ፣ ህገወጥነት እና ውንብድና ነው፤ በቂ ትኩረት ካልተሰጠው ኮረና ይህን የወንጀል ዓይነት በከፍተኛ መጠን ሊያባብስ ይችላል። “የማኅበረሰብ ደህንነት” ስል በአዕምሮዬ የሚመጣብኝ ”ማንነትን” መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ነው። የኮረና አደጋ በተራዘመ መጠን ዘርንና ሀይማኖትን ሰበብ የሚያደርጉ ግጭቶች ሊባባሱ ይችላሉ፤ እንዲያውም “አገር በቀል” የሽብር ድርጅቶች የሚፈጠሩበት እድል የሰፋ ነው። “የፓለቲካ ደህንነት” ስል የሚታየኝ የፍትህ እጦት፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እና አፈና ናቸው።

ምን ይደረግ?

የአደጋውን ስፋትና ጥልቀት በዚህ መልክ መረዳት ለመፍትሄ ፍለጋው የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ሁለተኛ፤ መንግስት (በተለይ የሰላም ሚኒስትር እና የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት) ሁለገብ የሀገር ደህንነት ጥናት እንዲያደርግ እጠይቃለሁ። ሶስተኛ፤ አሁን በተፈጠረው አጭር “አመቺ” ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ እርቅን መፍጠር፤ ለቅራዊዎች መፍቻ ተቋማዊ መፍትዎችን ማበጀት፤ የተደራጀ ውንብድናን የሚቋቋም ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠር ያስፈልጋል። የኮረና ቫይረስ ስርጭት ብዙ ከቆየ አሁን ያለው መልካም ስሜት አይቆይም፤ ስለሆነም መፍጠን ያስፈልጋል።

1 Comment

  1. All of the current Edirs in Ethiopia need to mend their policies together as one , inorder to give especial support to the families of those physicians who loose their lives while fighting Covid-19.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share