ከባልደራስ-መኢአድ ሰለኮረና፣ ሰለ ጦርነት እንቅስቃሴና ሰለኃይማኖት አባቶች የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ 

የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሥጋት ድባብን ፈጥሯል፡፡ የዓለም ተመራማሪዎች የዚህን በሽታ መድኃኒት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ምንም ዓይነት ሁነኛ መድኃኒት አልተገኘም ፡፡ በመሆኑም፣ የዓለም ማህበረሰብ የበሽታውን መስፋፋት መከላከሉ ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
እኛ ኢትዮጵውያን ካለን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብርና ድህነት አንፃር፣ በሽታው በሀገራችን የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በሸታውን ለመከላከል የሁላችንንም ትልቅ ትብብርና መተሳሰብ፣ እንዲሁም ንቁ መሆንን ይጠይቃል፡፡
ይህንን ክፉ ቀን የምናልፈው “አንተ ትብስ ፣ አንቺ ትብሽ” በመባባል፣ በመተሳሰብና ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የጤና ባለሞያዎች ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ ነው። ከሁሉም በላይ ልዩነቶቻችንን ሁሉ ለጊዜው ተወት አድርገን፣ ትኩረታችንን የጋራ ጠላታችን በሆነው የኮረና ቫይረስ ላይ ማድረግ አለብን፡፡
በዚህ መንፈስም፣ ባልደራስ-መኢአድ ለአባላቱ፣ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለገዢው ፓርቲ፣ ለሲቨክ ተቋማትና ብሎም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሚከተለውን መልዕክት ያስተላልፋል
1ኛ. የኪራይ እፎይታን በሚመለከት
እንደሚታወቀው የብዙ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዜጎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ ሲመከሩ፣ እንዲሁም የሥራ እድሎች እየጠበቡ ሲመጡ ብዙ ዜጎች የቤት ኪራይ ለመክፈል እንደሚቸገሩ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የግል አከራይና ተከራይ እንዲተሳሰቡ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ፣
1/ሀ
መንግሥት ለግል አከራዮች ያቀረበውን ጥሪ እራሱም መተግበር ስለሚጠበቅበት፣
1/ሀ/1
በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት ለሚያከራያቸው ቤቶች የሚሰበስበውን ኪራይ ምህረት እንዲያደርግ
1/ሀ/2
የኮንደሚኒየም ቤቶች ወርሃዊ ክፍያ ምህረት እንዲያደረግ፣
1/ሀ/3
የስልክ፣የውሃ፥ የመብራትና የኢንተርኔት ተመኖች ቅናሽ እንዲያደረግ
1/ሀ/4
ለህክምና ባለሙያዎች የአበል ክፍያ እንዲደረግላቸውና የትራንስፖርት ችግሮቻቸው እንዲቀረፍላቸው እንዲያደርግ
2ኛ. የጦርነት እንቅስቃሴን በሚመለከት
በዚህ ወቅት ሙሉ ትኩረታችን ቫይረሱን በመከላከል ላይ መሆን ስላለበት፣ የተኩስ ድምፅ የምንሰማበትና የምንዋጋበት ጊዜ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) አባል ሀገራት አንዷ ናት፡፡ የተባበሩት መንሥስታት በዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኩል ባስተላለፈው ጥሪ፣ በመላው ዓለም የተኩስ ማቆም እርምጃ አንዲወሰድ ጠይቋል። ይህን ጥሪ በተለይ መንግሥታት እያከበሩት ይገኛል። በዚህም መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በወለጋና በአማራ ክልል ባሉ ታጣቂዎች ላይ ውጊያ የሚከፍትበትን ቀነ ገደብ እያስቀመጠ፣ ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮችን እያሰማራ ይገኛል። በዚህም እንቅስቃሴው ግጭት የሚፈጠርበትን ዕድል በእጅጉ ከፍ አድርጎታል ። መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ፣ ችግሮችን በድርድርና በትዕግስት ለመፍታት እንዲተጋ በአፅኖት እናሳስባለን።
ባልደራስ- መኢአድ ማንኛውንም የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያወግዝ ሲሆን፣ ታጣቂዎች አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈቱና ከተኩስ እንዲታቀቡም ጥሪ ያደርጋል፡፡
3ኛ. አላስፈላጊ እንቅስቃሴን በሚመለከት
ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር መላ ኢትዮጵያውያን ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
4ኛ. ምሥጋና ለኃይማኖት አባቶች
ለሀገራችን ሰላምና ጤና እንዲፀልዩ የሃይማኖት መሪዎች በጋራ የወሰዱት እርምጃ በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው፣ የሚደነቅና የሚደገፍ ሲሆን፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናስተላልፋለን።
ባልደራስ- መኢአድ
ሚያዚያ 2/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከትም አግሳ አንበሳ!

3 Comments

  1. የ ኮሮናቫይረስ ሰውነት ውስጥ ሊገባ የሚችለው በ አፍ ወይም አፍንጫ ወይም ደግሞ አይን ነው። ስለዚህ እነዚህን አካላቶቻችንን በ እጃችን አለመንካት ዋነኛው መከላከያ ዘዴ ነው። በዚያም ላይ ሁሉም ሰው ፊቱን ከሸፈነ አንዱ ለሌላው የማስተላለፍ ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው። ሁለት ሜትር ርቀት ከ ሰው መራቅ ቫይረሱ እንዳይደርስብዎት በማሰብ ነው።
    እጅ ታጥቦ የተበከለ ነገር መንካት የማይቀር ነው። ስለዚህ መፍትሔው ፊትን አለመንካት ነው። ልብ በሉ።

  2. ጥሩ ነው። ሀሳባችሁን ወድጀዋለሁ። አንድ ቅር ያለኝ ነገር የባልደራስ ከመኢአድ ጋር መዋሀድ ነው። ኩበት ወደዘመድህ ሂድ ሲባል ከበረት ገባ ይባላል። እስክንድር ነጋ ዘመዶቹን ፈልጎ ከነማሙሸት ጋር ተቀላቀለ። ማሙሸት ማለት የተጉለትና ቡልጋ ስልጣን አስመላሽ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው። እንኳን መላው ኢትዮጵያውያንን መንዝን እና ይፋትን አይወክልም። ስለምናውቀው ነው። ማሙሸትን ማነው አማራ ወይም ማነው ኢትዮጵያዊ ወይም ማነው ታማኝ ብላችሁ ብትጠይቁት ተጉለትና ቡልጋ ነው ነው የሚላችሁ። ከዚህ በፊት እንደምንም መኢአድን ከተጉለቶች እጅ ለማውጣትና ኢትዮጵያዊ መልክ ለመስጠት ብዙ ተደክሟል። ግን አልተቻሉም። እነማሙሸት የተጉለትን የበላይነት ለማረጋገጥ ተግቶ የሚሰራውን ድርጅታቸውን ለማስመለስ ባደረጉት ተጋድሎ መልሰው ተቆጣጠሩት። አሁን ደሞ የአዲስ አበባ ተሟጋች ነው ብለን ስንደግፈው የነበረው ባልደራስ ዘሩን ፈልጎ መኢአድን አጠናከረ። ለውነተኛ ትግል ቢሆንማ የነልደቱን ወይም የኢዜማን ድርጅት ነበር መቀላቀል የነበረበት።
    ሌላው በመግለጫችሁ መንግስት በጎንደር ፋኖወች ላይ እያደረሰ ያለውን ማሸበር አስመልክታቹ ምንም አለማለታችሁ ትልቅ ግድፈት ነው። የታገቱት ተማሪወችንም ጉዳይ ረስታችሁታል።ቤንሻንጉል ክልል በአማሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አላወገዛችሁም። ትልቅ ጥፋት ነው። ሀገራዊ ፓርቲ ሆናችሁ ሳለ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢወች ስለተፈጸሙ ጉልህ ነገሮች አለመናገር ያሳፍራል። በምርጫ ጊዜ ምን ይዛችሁ ልትቀርቡ ነው።

  3. ኮሮናቫይረስ አካል ውስጥ የሚገባው በ አፍ፣ አፍንጫ እና አይን አድርጎ ነው።
    ይህ እንዳይሆን ፊትን በ ሆነ ጭምብል (mask) መሸፈን እና ፊትን ፈፅሞ አለመንካት ነው። ሁልጊዜም ከ ሰው ሁለት ሜትር መራቅ አስፈላጊ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share