ኢትዮጵያ ከኣፍሪካ ሀገሮች ቀደምትነት ያላት ሀገር መሆኗን ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግና ለመመጻደቅ ሳይሆን ታሪክ የመሰከረላት ናት። ቀደም ያሉ ታሪኮቿ እንደሚመሰክሩትላት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ከወርቅ፣ ከብርና ከነሓስ የተሠሩ የገንዘብ ሽርፍራፊዎች በመጠቀም የመጀመሪያዋ ሀገር የሆነች፣ ኃይማኖቷን ከኃይማኖቶች ውዝግብና ከፖለቲካ ቀውሶች ጠብቃ የቆየች፣ በኣፍሪካ የመጀመሪያዋ የሥልጣኔ ጮራ የፈነጠቀባትና መንግሥት ለመመስረት የመጀመሪያዋ የሆነች፣ ከኣፍሪካ ሀገሮች ብቸኛ የሆነውን ኣፍሪካዊ የግዕዝ ቋንቋ ባለቤትና ለጽሑፍም ያበቃች፣ በታሪክም ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ያስመዘገበችና እንደ ሉሲ የመሳሰሉ የሰው ዘር መገኛ ቅሪተ ኣካል የተገኘባት ሀገር ናት። ለምን? ለምን ሌሎች የኣፍሪካ ሀገሮች ኣልፈጸሙም? ኢትዮጵያውያን ከኣፍሪካውያን የተለዩ ናቸው? ዘራቸው የተለየ ነው? ወይስ የያዙት ቦታ የተለየ ነው? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ናቸው ሀገሪቷን በውጭ ሀገራት ዕይታ ውስጥ የከተታትና በተለያዩ ዘዴዎች እየገቡ ሊበታትኗትና ሊቦጠቡጧት የሚፈልጉት።
የግብርና ክንውኖች በኢትዮጵያ መተግበር የጀመሩት ቀደም ካሉ ጊዜት ጀምሮ እንደነበር ታሪክ ሲያስረዳ በ1520ዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በመስኖ በመጠቀምም ጥሩ ምርት ያመርቱ እንደነበር መረጃዎች ይመሰክራሉ። ይኸ መረጃ የሚመሰክረው የግብርናን ተግባር የጀመሩት ከዚያ በጣም ቀደም ብለው መሆኑንና ተደላድለው መኖር በመጀመራቸውም ኣፈሩ የተፈጥሮ ለምነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ወይም የኣንድ ወቅት ዝናምን በመጠቀም ኣንድ ጊዜ ብቻ ከማምረት በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ማምረት እንደሚቻል በመረዳታቸው የወንዝ ውሃን እየጠለፉ መጠቀም መጀመራቸውን ነው።
ኢትዮጵያውያን ውጭ ሀገራትን መጎብኘት ከጀመሩ ረዘም ያለ ጊዜ ያላቸው ቢሆንም ጣሊያንን መጎብኘት የጀመሩት ግን ከ1306 ዓ. ም. (እኣኣ) ጀምሮ ነበር። ከኢጣሊያ ወገን ግን የኢጣሊያ ተወላጅ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘው ፒትሮ ሮምቡሎ ሲሆን ጊዜውም ከኢትዮጵያውያኑ ጉብኝት ከኣንድ መቶ ዓመት በኋላ በ1407 ዓ. ም. (እኣኣ) ነበር። ጉብኝት ኣድርገው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ብዛታቸው 30 ሲሆን በጉብኝታቸው ወቅት ንጉሣቸው ፕሪስተር ጆን ይባል እንደነበረ፣ የሀገሪቷም ፓትሪያርክ ይኸው ንጉሥ እንደነበረና ከርሱ ሥር 127 ኤጲስቆጶሳት እንደነበሩ ለኢጣሊያው መሪ ገልጸውለት ነበር። ኤጲስቆጶሳቶቹም እያንዳንዳቸው 20 ጳጳሳት የነበሩዋቸው ሲሆን በጠቅላላው 2540 ጳጳሳት ነበሩ ማለት ነው። ፕሪስተር ጆን ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሥሩ 74 ንጉሦች ነበሩት። ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ልዑላንና ልዕልቶችም ነበሩ።
ፕሪስተር ጆን ዛሬ ካለነው በጣም የላቀ የሀገር ስሜት የነበረው ንጉሥ መሆኑ ከሚመሰከርለት ኣንዱ የዓባይ ወንዝ ችግር በዚያን ጊዜም የነበረ ስለሆነ የውሃው ተጠቃሚዎች ነን ባዮች ችግር የሚያመጡ ከሆኑ የውሃውን ፍሰት ኣቅጣጫ እንደሚለውጥ ኣስጠንቅቆ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የዓባይ ወንዝ ጣጣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የቆየ መሆኑን ነው።
ነጮች ኣፍሪካን ከተቀራመቱና ሀብቷን መጥጠው ከጨረሱም በኋላ ለቀው ለመውጣት የሞት ሽረታቸውን ከነፃ ኣውጪዎቹ ጋር ሲዋጉና ከለቀቁም በኋላ የኣፍሪካ ታጋዮችንና መሪዎችን ሲወጉ፣ ሲማርኩ፣ ሲያሰድዱና ሲገድሉ ነበር። ኢትዮጵያዊው ዳግማዊ ምኒልክ ግን በተለየ መልኩ ሕዝባቸውን ኣቅፈውና ደግፈው እንዲሁም በሕዝባቸው ታቅፈውና ተደግፈው ለነጮች ኣልተንበረከኩም ነበር። ይባስም ብለው ኃያሉን የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ኣዋርደው መልሰዋል። የኢጣሊያ መሸነፍና መዋረድ ለኣውሮፓ ሀገሮችም ውርደት መሆኑን በጊዜው ጽፈውታል፣ ተጸጽተዋልም። ይኸም በመሆኑ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች ምን ቢያገኙና ቢሰማቸውስ ነው የማይንበረከኩት በማለት ለኣያሌ ዓመታት ሲያሴሩና ሲያደቡ ነበር፣ ናቸውም። John Reader Africa በተባለው መጽሐፍ፣ በገጽ 208፣ 210፣ 265፣ 350-351፣ 583-585 ላይ ከላይ የተዘረዘሩትን መረጃዎች በማቅረብ ኣትቷል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ታሪካዊ መረጃዎች የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ማንነት በጉልህ የሚገልጹ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የሆንና በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታችን የምናምን ከሆን ይኸንኑ ስሜታችንን የምንገልጸው ኢትዮጵያን ስንወዳትና ስንሞትላት እንጂ ስናስማማት፣ ስንሸጣት፣ ስንጠላት፣ ስንገላትና ስናስገድላት ኣይደለም። መውደድ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መገለጽና መታየትም ኣለበት። ወላጆቻቸውን የሚወዱ ግለሰቦች በወላጆቻቸው ላይ ለሚደርሰው ችግር ሁሉ ቀድመው መድረስና መከላከል መቻል የልጅነት ግዴታቸው እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለሚወዷት ሀገራቸው ዘብ በመቆም ከማንኛውም ችግሯና ኣደጋ የመጠበቅና የመከላከል ግዴታና ኃላፊነትም ኣለባቸው።
ኣንዳንድ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንኳ መጥራት የሚጠየፉ፣ ስሟን ከዓለም ካርታ ላይ ለመሰረዝና ለማስሰረዝ ትግል የሚያደርጉ ያሉ ሲሆን በስሟ ደግሞ ሲነግዱና ሲጠቀሙ ይታያሉ። ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ሲወጡ በኢትዮጵያ ስም የተሠራና በኢትዮጵያ መንግሥት ማኅተም የታተመበት የይለፍ ወረቀት (ፓስፖርት) ይዘው ይወጣሉ፣ በዓለም ሀገራት ይሽከረከራሉ፣ ይጠቀሙበታል፣ ይከበሩበታል። በእንቅስቃሴኣቸው ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ሴራ ሲጎነጉኑና ሲሸርቡ ይታያሉ፣ ይሰማሉ። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለያይቶ ማስቀመጥ ኣይቻልም። ኢትዮጵያን የሚወዱ ኢትዮጵያዉያን ናቸው። ኢትዮጵያን የማይወዱ ደግሞ ፀረ ኢትዮጵያ ስለሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊባሉ ኣይችሉም።
ኢትዮጵያ ስትጠራም ኢትዮጵያዊ የሆኑ በርካታ ቅርሶች ኣሉዋት። እነዚህ ቅርሶች በኢትዮጵያዊነታቸው ለሚያመኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ማንም ሊከለክላቸው የማይችል ሀብታቸው ናቸው። ለኣንተ ይኸንን ያህል፣ ለኣንተ ደግሞ ይኸንን ያህል ተብሎ በመጨመርና በመቀነስ የሚደለደል ሳይሆን ለሁሉም እኩል የሆነ ድርሻ ኣላቸው። ቅርሶቹም ለዛሬዎቹ ትውልዶች ብቻ ሳይሆኑ ለሚመጡት ትውልዶችም የሚተላለፉ እንጂ የሚሸጡና የሚለወጡ ኣይደሉም። የኣክሱም ሐውልቶች፣ ባሁኑ ወቅት ላገሯ ሳይሆን ለሌላ ሀገር ገቢ እንዲታስገኝ የምትሽከረከሯ ሉሲ ቅሪተ ኣካል፣ ሶፎማር፣ ብርቅየ ኣዕዋፋትና እንስሳት፣ ተራሮችና ሸንተረሮች፣ የእህል ዘሮች፣ ቡና፣ ኣበቦች፣ የመሳሰሉ ማንም በግል የማያዝባቸው ሳይሆኑ የሁላችን የጋራ ሀብታችን ናቸው።
ቸሩ ላቀው ነኝ። ወላጅ ኣባቴን ላቀውን የማልወደውና የማልፈልገው ከሆነ የልጅ ከሃዲ ነኝና በላቀው መጠራት የለብኝም። በራሴ ስም ብቻ ኣባት ኣልባ ሆኜ መጠራት ኣለብኝ። በማልወደው ኣባቴ ከተጠራሁ ወንጀለኛ ነኝ። ሁላችንም ኢትዮጵያን የማንወድና በኢትዮጵያዊነታችን የማናምን ከሆነ በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ያለን መብት የተሰረዘ ስለሆነ በማንኛውም የኢትዮጵያ ቅርሶች ስም የመጠቀም መብታችን የተሰረዘ በመሆኑም መጠቀም ኣይቻልም። ኢትዮጵያ እንደ ሆቴል፣ ቡና ቤት፣ የንግድ ድርጅት በመሳሰሉ ለንግድ መጠቀሚያ መዋል የለባትም። ሊጠቀሙ የሚችሉት ልጆቿና ወገኖቿ ናቸው። ለምሳሌ ሉሲ፣ ኣክሱም፣ ላሊበላ፣ ግዮን፣ ዓባይ፣ ኒያላ፣ ኣደይ ኣበባ፣ ኣዲስ ኣበባ፣ ከፋ፣ ጂማ፣ ወለጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ኣዋሳ፣ ኣሰላ፣ ባሮ፣ ባሌ፣ ዲላ፣ ጎሬ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ላኮ መልዛ፣ መቀሌ፣ ትግራይ፣ ጎጃም፣ የመሳሰሉ ስሞችን ከኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲባል መጠቀም የለባቸውም። ኢትዮጵያን የሚወዱና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ ቢሆኑ ኖሮ እግረ መንገዳቸውን ሀገርን ማስተዋወቅ ስለሆነ በተደገፈ ነበር። ግን ዓላማውና ዒላማው የማይገናኝ ስለሆነ ከማታለል ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው ኣይችልም።
ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ከመበታተን፣ ከማፈራረስ፣ ከማስማማትና ከመሸጥ ተቆጥበን ለእናት ሀገራችን ዘብ እንቁም። የበጎ ሥራ ተምሳሌት ሆነን ፀንተን በመቆም ሀገራችንን እንጠብቅ።
ቸሩ ላቀው ነኝ። ቸር ይግጠመን። abatemsas@gmail.com.