በፍቅር ለይኩን
እጅግ ሰፊ የሆነ እውቅናና ተደማጭነት ካላቸው ከጆን ፖል እረፍት በኋላ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የመጡት ጀርመናዊው ቤኔዲክት 5ኛ በመንበራቸው ላይ አሥር ዓመት እንኳን ሳይደፍኑ ነበር በቅርቡ እኔ ዕድሜዬ ገፍቷል፣ ድካም እየተጫጫነኝ፣ የጤናዬም ሁኔታ የሚያወላዳ አልሆነም፡፡ ስለዚህም በገዛ ፈቃዴ ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ ሲሉ አስታወቁ፡፡ በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸወቅን የሚገልጸውን የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለቫቲካን አስገቡ፡፡
ይህ የቢኔዲክት 5ኛ ያልተጠበቀ ውሣኔ ቫቲካውያን፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የካቶሊክ እምነት ተከታዮችንና መላውን ዓለም ያነጋረ አስደንጋጭ ዜና ነበር፡፡ ፖፑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ በሚገባ ለማካሄድ ከጸሎትና ከመንፈሳዊው አገልግሎት ባሻገር፣ በርካታ ውስብስብ የሆኑ አስተዳዳራዊ ውሣኔዎች የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ስላሉ ይህን በብቃትና በቅልጥፍና የሚሰራ ሌላ ብቁ ሰው ብትመርጡ ይሻላል፡፡
እኔ በተቀረው ዘመኔ በጸሎትና በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ብቀጥል ይሻላል በማለት ነበር ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በይፋ ያስታወቁት፡፡ ይህ ከታወቀም በኋላ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የካቶሊክ ካርዲናሎች ባደረጉት ምርጫ በትላንትናው ዕለት አርጀንቲናዊው ካርዲናል ቤርጎሊዮ ከአንድ ቢሊየን በላይ መእመናን ያሏትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲየንን ለመምራት የሚያስችላቸውን ድምፅ አግኝተው ተመርጠዋል፡፡
አርጀንቲናዊው ፖፕ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ከላቲን አሜሪካ የተመረጡ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ያልሆኑ ፖፕ ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ የ76 ዓመቱ ካርዲናል ፖፕ ሆነው መመርጣቸውን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ይጠባበቅ ለነበረው በሺህ ለሚቆጠሩ ካቶሊካውያንነ ምእመናን ሲታወጅ በሆታ፣ በደስታ እንባና ሲቃ ሆነው ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው ካቶሊክ በሚበዛባት ላቲን አሜሪካ ደስታው እጅጉን የተለየ ነበር፡፡ አንድ ምርጫውን በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኘ ካቶሊካዊ የምርጫውን ሂደት ልጅህ የሆነ ሕፃን ወደዚህች ምድር ሊቀላቀልበት ያለበትን ሁኔታ የመጠበቅ ያህል አጓጊ ነበር ሲል ነው ለኒዮርክ ታይመስ ዘጋቢ የገለጸው፡፡
አርጀቲናዊው የቦነስአየረስ ሊቀ ጳጳስ ቤረጎሊዮ በጵጵስና ስማቸው ፍራንሲስ በነጩ መነጋገሪያ መድረክ ላይ ሆነው ባስተላለፉት አጭር መልእክት፡- ‹‹መሪያችሁ አድርጋችሁ ስለተቀበላችሁኝ አመሰግናለሁ! ወንድሞቼ የሆናችሁ ካርዲናሎች ከእናንተ በሩቅ የምገኘውን ሰው መሪያችሁ እሆን ዘንድ መረጣችሁኝ፡፡ ይኸው አሁን ደግሞ ከእናንተ ጋር በዚህ ነኝ! እባካችሁ ጸልዩልኝ፣ በቶሎ እንገናኛለን፡፡ ሰላም እደሩ፤ መልካም እረፍትን እመኝላችኋለሁ!
አርጀንቲናዊው አዲሱ የካቶሊክ ፖፕ የሆኑት ቤርጎሊዮ ከኢጣሊያ ከተሰደዱ ቤተ ሰዎች የተወለዱ ካህን ናቸው፡፡ ካርዲናል ቤርጎሊዮ ተራ የሚባል ሕይወትን የሚኖሩ፣ ብዙም ለራሳቸው የማይጨነቁ፣ ቀለል ያለ ሕይወትን የሚኖሩ ሰው መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
የቦነስአየርስ ሊቀ ጳጳስነት ዘመናቸውም አገልግሎታቸውን ለመፈጸምና ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በሕዝብ አገልግሎት መስጫ አውቶቡሶችና መጓጓዣዎችን እንደሚጠቀሙ ነው የሚታወቁት፡፡ ፖፕ ፍራንሲስ ከተራው ህብረተሰብ የተለየ የአኗኗር ዘይቤ እንደሌላቸውም ነው ብዙዎች የሚመሰክሩላቸው፡፡
ቤርጎሊዮ ምግባቸውን እንኳን ሳይቀር ራሳቸው እንደሚያበስሉ ነው በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች የሚናገሩት፡፡ ቤርጎሊዮ ሌላው ሳይቀር በቦነሰአይረስ የነበረውን እጅግ ግዙፍና ውብ የሆነውን የመንበረ ጵጵስናቸውን ቤት ሽጠው እንደ ተራ ሰው በአፓርታማ ውስጥ ከሕዝባቸው ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ፣ ቀለል ያለ ሕይወትን የሚመርጡ ሰው መሆናቸውን ቶማስ ሮዚካ የተባሉ ካናዳዊ የቫቲካን ቃለ አቀባይ ለኒዮርክ ታይምስ ዘጋቢ ተናግረዋል፡፡
እኚህ አዲሱ የካቶሊክ ፖፕ ለመሆን የተመረጡት ፈራንሲስ ውሎአቸውና አደራቸው ከድሆችና ዝቅተኛ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መሆናቸው በእጅጉ ይነገርላቸዋል፡፡ ብዙም አጀብና ሽርጉድ የማይወዱት አርጀንቲናዊው ካርዲናል ከአገራቸው መንግሥት በተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ፊት ለፊት ሙግት የሚገጥሙና ምንም የማይፈሩ ሰው መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
የአርጀንቲና መንግሥት የተመሳሳይ ፆታን ጋብቻ ለማፅደቅ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም መንግሥታቸውን ፊት ለፊት በመቃወም እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ‹a war against God› ይህ ከአምላክ ጋር ጦርነት ማድረግ ነው! ሲሉ ነው፣ ያለ ምንም ፍራቻ ተቃውሞአቸውን በግልፅ በአደባባይ ያሰሙት፡፡
አርጀንቲናውያን በ1970ዎቹ ልክ በኢትዮጵያችን እንደተከሰተው ቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር እልቂት በተመሳሳይ ዜጎቻቸው ቀኝ ዘመምና ግራ ዘመም በሚል የፖለቲካ አመለካከት እርስ በርሳቸው በተጨፋጨፉበትና በአርጀንቲና ታሪክ ‹‹ቆሻሻው ጦርነት›› (the Dirty War) በሚባል በሚታወቀው ጦርነት ቀውጢ ወቅት በወታደራዊው ጁንታ ሲታደኑ የነበሩ ወጣቶችን መጠለያ በመስጠት፣ በመደበቅና ወደ ሌላ አገር እንዲሸሹ በማድረግ ትልቅ የሆነ መንፈሳዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውም በሰፊው ይነገርላቸዋል፡፡
አርጀንቲናዊው ካርዴናል ቤርጎሊዮ አዲሱ የካቶሊካውያን ፖፕ ሆነው በመመረጣቸው የመጀመሪያውን የደስታ መልእክት ያስተላለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለፖፕ ለፍራንሲስ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መግለጫቸው፡-
As a champion of the poor and the most vulnerable among us, he carries forth the message of love and compassion that has inspired the world for more than 2000 years-that in each other we see the face of God. በማለት ለመጪው ዘመንም ዓለማችን በእጅጉ የናፈቀችውን የፍቅርና የሰላምን መልእክት የሚናገር የድሆች ወገን፣ የድሆች ድምፅ በማለት ነው የጠቀሷቸው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሀሮ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ቀኖና ላይ ጥብቅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አዲሱ የካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ ፀንስ ማስወረድን/ውርጃን፣ የተመሳሳይ ፆታን ጋብቻ፣ የሴቶችን ለቅስና መሾም አጥብቀው የሚቃወሙ ናቸው፡፡
በዚህ ጽኑ ሃይማኖታዊ አቋማቸው የሚታወቁት አዲሱ ፖፕ ምናልባትም ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች፣ ምእመናንና ከዘመናዊው ዓለም የሚመጣባቸውን ግፊት ለመቋቋም ጠንካራ የሆነ መንፈሳዊና አስተዳዳራዊ ክህሎትን በእጅጉ እንደሚጠበቅባቸው ታዛቢዎች እየተናገሩ ነው፡፡ የፖፕ ፍራንሲስ በዓለ ሲመት በመጪው እሑድ እጅግ በደመቀ መንፈሳዊ ሥነ ስርዓት እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡
ሰላም! ሻሎም!