August 7, 2019
9 mins read

ማለቂያ የሌለው ጉዳችን – አንዱዓለም ተፈራ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፩ ዓመተ ምህረት

የኛ፣ የዐማራዎች፣ የራሳችን ያለመሰባሰብና ባንድ ላይ ያለመቆም ችግር፤ ለሌሎች መጫወቻ እንድንሆን አደረገን። ዐማራው ለኢትዮጵያ ለሀገሩ ያደረገውን አስተዋፅዖ መዘርዘሩ ትርጉም የለውም! ለራሱ ያደረገው ነውና! አሁንም ቢሆን ዐማራው ከኢትዮጵያ ሌላ ሀገር የለውም። እንኳንስ ቀደምቶቻችን፤ እኛም አሁን ያለነው ልጆቻቸው፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለን ለሀገራችን ሙሉ ለሙሉ ሕይወታችን ሠጥተን ታግለናል፣ ተሰውተናል፣ ለወደፊቱም ይሄ ይቀጥላል። ሌሎች እኛና እነሱ እያሉ፤ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ሊያደርጉ ይችላሉ። ያ፤ ራሳቸውን ማሳነስና ሌሎች ብሎ ከፋፍሎ፤ ከሌሎች ጋር ለመወዳደር መሞከር፤ የራሳቸው ችግር ነው። ክፋቱ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ሀገር ሲገዛ፤ ሀገሪቱን በጁ ጨብጦ፤ ነገር ግን በጠባብ ወገንተኝነቱ ተጠምዶ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን፤ እንደ ትግሬነቱ ብቻ ሌሎችን ኢትዮጵያዊያንን መግዛት ስለያዘ፤ በሀገራችን የዘራው የመከፋፈል መርዝ፤ አሁን ቅርሻቱ ሀገራችንን በክሏታል። እናም በተለይ በዐማራው ላይ የተደረገውን በደል አስመልክቶ፤ በኢትዮጵያዊነቴ ተሰምቶኝ፣ በዐማራነቴ ፤ “በኢትዮጵያዊነት መታገል ነው መልሱ!” የሚሉ አሉ። ይሁንላቸው። ለኔ ደግሞ፤ ዐማራውን ከጥፋት ማዳን የአሁን ግዴታዬ ነው ብያለሁ።

እናም የራሳችንን ጉዳይ እኛው ራሳችን እንጂ፤ ሌላ ወገን እንዲፈታልን መጠበቁ ከየዋህነት አልፎ ጅልነት ነው። የኛ አለመተባበርና ተስማምቶ ባንድ አለመሰለፍ፤ አሁን በወገናችን ላይ ሌሎች በየተራ እንዲረባረቡብን መንገድ ከፍቷል። ዛሬ ደግሞ የሰማሁት ሌላ ዘርፍ ጨምሮበታል። ፋሲል ደሞዝ ያጎቴ ልጅ፤ ወንድሜ ነው። ሰሞኑን በሱ ስም የተለቀቀ ዘፈን አለ። ከመንገድ ወጥተው ይሄንን ተንኮል እንደሠሩ ሳስብ፤ በዐማራው ላይ እየተደረገ ያለው የተቀነባበረ የመከፋፈል ዘመቻ ምን ያህል ሥር እንዳለው ተረዳሁ። አዎ! ሁሌም ቢሆን የራስ ቁስል ያንገበግባል። የሱን ቅንጣቢ ድምጽ ጨምረውበታል። አብላጫው ግን የሱ ድምጽ እንዳልሆነ አብዛኛዎቻችሁ ታውቁታላችሁ። ከደረሰብን የመሪዎቻችን ሕይወታቸውን ማጣት አልፎ፤ እኛ ርስ በርሳችን በጠበበ ጎጠኝነት እንድንከፋፈል፣ ለነሱ እንድንመች፤ አንዳችን ከሌላችን እንድንጋጭ፣ ከቁስላችን ላይ ስንጥር ሰነቀሩብን።

ፋሲል የተዋጣለት የባሕላዊ ሙዚቃ ጉምቱ ተጠሪ ከመሆኑም በላይ፤ ለወገኑ ተቆርቁሮ ከፈተኛ ግፍና በደል ደርሶበታል። በዛብኝ ስይል ለወገኑ ቁሞ፤ በሚያውቀው ሙያው የሚችለውን ከማድረግ አላረፈም። አሁን በዚህ መሰሪ ቅንብራቸው፤ ፋሲልን ረግጠው በላዩ ላይ ቆመው መጠቀሚያ አድርገው፤ ዐማራውን ለማጥቃት ተነስተዋል። ፋሲል በሕግ መሠረት ማስኬድ ያለበትን ያደርጋል። ይህ መሰሪ ተንኮል ግን፤ ሁላችንን ሊያስቆጣን ይገባል። እያንዳንዳችን የሕግ ባለሙያ፣ የዜና ማዕከል፣ የትንታኔ ባለቤት፣ የሀገር ፖለቲካ አዋቂ፣ ሕግ አውጪ፣ ዳኛና ፖሊስ በሆንበት የድረገጽ፣ የዜና መድረኮችና ባጠቃላይ በሕዋው መድረክ ዓለም፤ ንጉሥ ሆነናል። ስነ ሥርዓት፣ መከባበር፣ ትክክለኛ ካልሆነ ነገር መታቀብ፣ ከብልግናና ከስድብ መራቅ፣ የሚሉትን “የኅብረተሰባችን ዕሴቶች!”፤ ገደል ተጥለዋል። እኔን ብቻ ስሙኝ በሚል አደናቋሪ ትርክት ማዋከቡ ሙያ ሆኗል። በመሐል ቤት፤ ሃያ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚችለውን ያደርግ የነበረው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ዛሬ አጋዥ አግኝቶ፤ አሁንም ሀገራችንን በመከፋፈል ማጥቃቱን ይዟል።

በፋሲል ደሞዝ ስም የተለቀቀው ዘፈን ግን፤ ዐማራው ላይ ያተኮረ ነው። በርግጥ እስካሁንም፤ “ዐማራውን በማጥቃት ኢትዮጵያን ማጥፋት!” በሚል መመሪያ፤ ዐማራውን በዐማራነቱ ማጥቃቱ የገዥው ክፍል መመሪያ ነበር። ይህን የጻፍኩት፤ ዘፈኑን አቀነባብሮ የበተነውን አካል ተው ለማለት አይደለም። ሌሎች የሚሠሩትን ያውቃሉ። እኔ፤ ዐማራዎች ምን እያደረግን ነው? ብዬ ልጠይቅ ነው።

በርግጥ ኢትዮጵያዊነታችን የሚያጠያይቅ አይደለም። ከሌሎች ጋር በኢትዮጵያዊነታችን የሀገር ባለቤትነታችን አያጠያይቅም። ተነጥለን በዐማራነታችን ስንጠቃ ግን፤ በዐማራነታችን መከላከል ይገባናል። እኔ ካገሬ የወጣሁት በኢትዮጵያዊነቴ ነው። ያን ማንም ሊነጥቀኝ አይችልም። ለኢትዮጵያዊነቴ አልታገልም። ኢትዮጵያዊ ነኝ። አሁን በዐማራነቴ ነው ጥቃቱ እየደረሰ ያለው። በመሠረቱ ማንም ኢትዮጵያዊ በዐማራነቴ ለሚደርስብኝ ጥቃት፤ አብሮ” ኢትዮጵያዊ ጥቃት ደረሰበት!” ብሎ ሊረዳኝ በተገባ ነበር። ከሌሎች የበለጠ ኃላፊነት ስላለብኝ፤ ግንባር ቀደም በመሆን በዐማራነቴ ልከላከል የሚገባኝ እኔው ነኝ። ይሄ ግዴታዬ ነው። እከሌ እንዲህ ስላለ ወይንም ስላላለ ሳይሆን፤ ጥቃት ስለደረሰብኝ መከላከሉ ግዴታዬ ነው። ትናንት አኙዋኩ ሲበደል ጮኼያለሁ። ኦጋዴኑ ሲበደል ጮኼያለሁ። ኦሮሞው ሲታሰር ጮኼያለሁ። በኢትዮጵያዊነቴ ብቻ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጮኼያለሁ። አልፎ ተርፎ ለኢትዮጵያዊያን ነፃነት በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከባድ የጥይት ጉዳት ደርሶብኛል። አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያዊያን ነፃነት፤ ትግሬ ወይንም ኦሮሞ፣ ኦጋዴኒ ወይንም አኝዋክ ብዬ አልመርጥም፤ ለሁሉም እቆማለሁ። ነገር ግን፤ በዐማራነቴ፤ ዐማራው አሁን ያዘመመበት አደጋ፤ ከሁሉም በላይ አሳስቦኛል። ይሄን አደጋ ተገንዝበን፤ ዐማራዎች፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ለማንምና ለምንም ነገር መደራደሪያ ሳናደርግ፤ ባንድ ተሰባስበን ለወገናችን መድረስ አለብን። ነገ ለቁጭት የሚያደርስ የምቾት ጊዜ የለንም። ከበራችን ሞፈር እየተቆረጠ ነው። እኛው እየተመቸናቸው ነው። ወደሌሎቹ ሳይሆን ወደራሳችን እንመልከት።

Go toTop