ለዶከተር ዓብይ ዓህመድ
የኢትዮጵያ ፌድራልዊ ዴሞክራሲያዊ ሬፑብሊክ ጠቅላይ ምኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ጉዳዩ፥ እውቅና የሰጠዎትን ሃምሳ ሚልዮን ዓማራ ድጋፍ በከንቱ እንዳያባክኑ አደራ፣
በቅድሚያ ሰላምና ጤና ከመልካም የስራ ዘመን ጋር እየተመኘሁ ይህን ማስታዎሻ ያዘጋጀሁት ለወራት ኢትዮጵያ በቆየሁበት ጊዜ የዓማራው ሕዝብ ከርስዎ የሚጠብቀውን ተስፋና ያለውን ጥርጣሬ በወፍ በረር ከቃኘሁ በኋላ መሆኑን እንዲአውቁልኝ እፈልጋለሁ።
የዛሬ ዓመት በብዓለ ሲመትዎ ላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉት ንግግር ያላስደሰተው ኢትዮጵያዊ፤ ያልመሰጠው የዓለማችን ማህበረሰብ አልነበረም። ብዙዎቹ ከፕሬዚደንት ኦባማ የበለጠ ተናጋሪ፤ አሳቢና፤ መሪ በአፍሪካ በተለይ በተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያ መወለዱን በመገናኛ ብዙሃን አብስረው በደስታ ዘምረዋል። የሰው ልጅ መፈጠሪያ በሆነችው የኢትዮጵያ ምድር የርስዎ ዓይነት ኢትዮጵያዊ መገኘቱ ብዙ ባይደንቀንም የእኛ በመሆንዎ ድስታችን እጥፍ ድርብ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ማሕፀነ ለመለም መሆኗን በነገሩን ሃሳብ መሠረት ለምለሟ ማሕፀን እርስዎን የመሰለ መሪ ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋናችንን አቅር በናል። በነበረው የፖልቲክ ትኩሳት ምክንያት ብዙዎቻችን ኢትዮጵያ አለቀላት ብለን ተስፍ ቆርጠን ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምህላ ጊዜ ባወጀችው መሰረት በየቀኑ ቤተክርስቲያን እየሄድን ልመና አድርገናል። ቅዱስ መጽሃፋ ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’ ባለው መሰረት እጃችን ወደላይ ዘርግተን፤ በጉልበታችን ተንበርክከን ለወራት ምጥንታ አድርገናል። ፈጣሪም ልመናችንን ሰምቶ በርስዎ ተመስሎ ሙሴን ልኮ ሃገራችንን ከጥፋትና ከመበታተን አድኖልናል።
በግሌ በንግግርዎና ሃሳብዎ ከተመሰጡት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንዱ በመሆን ድጋፌን ለግሸዎታልሁ። እርስዎን ለማየትና ለመስማት ዘጠኝ ስዓት ነድቸ ዋሽንግቶን በመሄድ የሕዝባዊ ስብሰባ ው (Town Hall Meeting) ታዳሚ ሆኛለሁ። በአጋጣሚ ከፊት ለፊትዎ የመቀመጥ ዕድል ገጥሞኝ ስለነበር ከታማኝ በየን ጋር መሬት ወርዳችሁ በመተቃቀፍ በይቅርታ ስትላቀሱ ሳይ እንባ አውርጃለሁ። በሕይወቴ እንደዚህ ዓይነት መሪ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድማ ይገኛል ብየ አስቤ ስለማላውቅ በስሜት ከመቀመጫየ ተነስቸ አጨብጭቤአለሁ።
በኢትዮጵያ ቆይታየ እንደተገነዘብሁት ሰፊ ድጋፍ ያገኙት ከዓማራ ሕዝብ እንደሆነ ያውቁታል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ በመኪና ስጓዝ በየከተሞች ያለው ሕዝብ ለርስዎ ያለውን ድጋፍና አድናቆት አይቻለሁ፤ ሰምቻለሁም። በታክሲ፣ ባጃጅ፣ አውቶብስ መናህሪያ፤ ሆቴሎች፤ ምግብና መጠጥ ቤቶች፤ ገበያ አዳራሽ፤ ትምህርት ተቋማት፤ ወዘተ የተለጠፈውን የርስዎን ምስል ማየት ብቻ በቂ ምስክር ነው። የዛሬ ዓመት ዋሽንግተን በሄዱበት ጊዜ በነቂስ ወጦ የተቀበለዎት አብዛኛው አማራው ዲያስፖራ እንጂ ኦሮሞው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አልነበረም።
ባለው የዘር ፌድራሊዝም አወቃቀር ዓብይ ኦሮሞ ሆነው የአማራውን ድጋፍ እንዴት አገኙ የሚል ጥያቄ ብዙ ሰዎች ያነሳሉ። ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። በጥሩ አንደበትዎ ኢትዮጵያዊነትን አግዝፈው ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ታላቅነት አወድሰዋል፤ ሃገሪቱ በጎሳ አትፈርስም፤ እንደ ሃገርም ትቀጥላለች፤ ወደ ታልቅነቷም ትመለሳለች ብለው ባደባባይ ሰብከዋል። ዓማራው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ጽኑ እምነት ያለውና በጎሳ ፖለቲካ የማያምን በመሆኑ ቃልዎን አምኖ ድጋፉን የሰጠዎት ይመስለኛል። ለሶስት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን የሚአስመልስለት መሪ ሲናፍቅ የኖረው ዓማራ በእጅጉ ተደሰተ፤ ደገፈዎትም። ዓብይ ወይም ሞት ብሎ ተነሳ፤ የርስዎን አንደበትና ሃሳብ ወደደ፤ ቃልዎን አመነ፤ ሊከተልዎትም ወሰነ። በኢትዮጵያዊነት ከማመኑ የተነሳ የዓብይ የዘር ሃረግ፤ ሃይማኖትና ጎሰኝነት ሳያሸንፈው ከርስዎ ጋር ተሰለፈ።
በአንፃሩ የኦሮሞው ማህበረሰብ ዓማራና ሌሎች ሕዝቦች የሰጡዎትን ዓይነት ድጋፍና ፍቅር አልቸረዎትም። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ኦነጋዊያን፤ የኦሮሞ አቀንቃኞችና የፖለቲካ ልሂቃን የኦሮሞ የበላይነትን ከመፈለጋቸውና ብሎም ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል መስማት ባለመፈለጋቸው ድጋፉን ነፈገዎት። ብዙም ሳይቆይ የመንጋ ፖለቲካ መካሄድ ጀመረ። መንጋው በየክልሉ ችግሮችን እየፈጠረ የርስዎን፤ የዓማራውን፤ የሶማሊውን፤ የደቡቡን፤ የጋምቤላውን፤ የሀረሬውን፤ የዓፋሩን ወዘተ የኢትዮጵያዊነትና የዜግነት ፖለቲካ መውጫ መግቢያ አሳጣው።
አማሮች፤ ሶማሊዎች፣ ጉጅዎች፣ ኦረሞዎች በገፍ ተፈናቀሉ። የመንጋ ፖለቲካ ጥርስ አወጣና መናከስ ጀመረ። ለውጡ ኢትዮጵያዊነትን ማራመድ ሳይሆን ጎሳንና ዘርን ያማከለ ንቅናቄ ሆኖ ተስፋፋ። ሑሉም በሩን ዘግቶ ዘብ ቆመ። በየክልሉና በየጎሳው መደራጀትን መረጠ። ሁሉም እየተደራጀ የክልል እንሁን ጥያቄን በየፊናው አቀረበ። ይህን ዓጀንዳ የሚአራግቡ እጄቶ፤ ቄሮ፤ ፋኖ፤ ዘርማ ወዘት የመሳሰሉ የእግዚአብሔር አርበኞች (Soldiers of Allah) እና ቪጀላንቴ ብድኖች እንደእንጉዳይ ፈሉ። በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች እንደ ጃዋር፤ ህዝቄል ገቢሳ፤ ዳውድ ይብሳ፤ ወዘተ የመሳሰሉት እነዚህን ቡድኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየደገፉና እያበረታቱ የርስዎን የዜግነት ፖለቲካ ተገዳደሩት።
በዚህ ሁኔታ ነበር የዘር ፖለቲካ የትሊወስደን እንደሚችል ፍንጮች መታየት የጀመሩት። የመንጋ ፖለቲካ በሻሸመኔ ሰውን ከነሕይወቱ ዘቀዝቆ በመንጋ ፍርድ ገደለ። በተመሳሳይ ሁኔታ በዓማራውም ለምርምር የሄደን ተማሪ በመንጋ ንቅናቄ በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለ። በደቡብ የክልል እንሁን ጥያቄ ሳቢያ የብዙ ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ፤ አብያተ ክርስቲያንት ተቃጠሉ፤ የኢኮኖሚ አውታሮችና መዋቅሮች ወደሙ፤ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ሆነ። የሃገሪቱ እጣፈንታ እርስዎ ወደ ስልጣን ከመምጣትዎ ትቂት ወራት በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ ተመለሰ። በደቡብ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ እስከማወጅ ተደረሰ።
እምነትና ተስፋ የተጣለበት መንግሥትዎ ሕገ አራዊትን ማስቆም ተሳነው፤ የጥፋት ድርጊቶችን እያየ እንዳለየ ማለፍን መረጠ። በድምፀ ተአቅቦ አቋም በመቀጠልዎ የድርጊቱ ተባባሪ እስኪመስሉ ድረስ አዘገሙ። የመንግሥት ሃላፊነት የዜጉቹን ደህንነትና የሕግ የበላይነት ማስከበር መሆኑን የዘነጉትም መስለው ታዩ። መንግሥትዎ ውስጥ ውስጡን እየሰራና እርምጃ እየወሰደ ነው የሚል እምነት ቢኖረንም በቤተእምነት ቀኖና ሃገር ማስተዳደር የማይቻል መሆኑን መገንዘብ የተሳነዎት ሆነው ታዩ።
በሃይል ብቻ ሲታጀብ የኖረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በፍቅር እና በይቅርታ እንሻገር ፍልስፍና ለውጥ ለማምጣት ማሰብዎና መስበክዎ ሕሊና ያለው ዜጋ ሁሉ የሚቀበለውና የሚደግፈው ነው። በአንፃሩ የዘርና የመንጋ ፖለቲካ ከርስዎ በተቃራኒ የቆመና በግደለው፤ አፈናቅለው፤ ዝረፈው፤ አስወጣው፤ አግልለው ፅንሰ ሃሳብ የተመሰረተ በመሆኑ ከርስዎ ጋር ተጣጥሞ በለውጡ ጎዳን መጓዝ ተሳነው።
ይህ በእንዲህ እያለ ዓማሮች ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ዝምታን በመረጡበት ሁኔታ የዓማራው ማህበረሰብ ጥርጣሬ ወደቀ። ዓማራውም የኢትዮጵያዊነት ዓጀንዳን በይደር ገሸሽ አድርጎ ዓማራነትን መስበክ ጀመረ። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ባለቤትና ጠበቃ አጡ። ኢትዮጵያዊነት ለዓማራ መስበክና ማስተማር አይቻልም ብሎ እየተኮፈሰ ብሄርተኝነትን አክርሮ ያዘ። ገመድ መሳሳቡ በሁሉም ዘር ሥር ሰዶ አደገ። አሁን አማራው እየተጠቃ ስለሆነ መጀመሪያ መቀምጫየን ላስጠብቅ በሚል እራሱን አደራጅቶ ለሰላሳ ዓመት የተፀየፈውን የዘር ፖለቲካ አራገበ። ትዳር የሚፈርሰው በባለትዳሮች መካከል የነበረ መተማመን ጠፍቶ እርስ በርስ መጠራጠር ሲበዛ ፍቅር ይቀዘቅዛል ትዳር ይናጋል። የዓማራው ወጣት ትውልድ ቀደም ሲል ለእርስዎ የነበረው ፍቅር መቀዝቀዙን፤ በአመራርዎ ላይ የነበረው እምነትና ድጋፍ መሸርሸሩን በባህር ዳር ቆይታየ መገንዘብ ችያለሁ።
በቆይታየ ጊዜ የርስዎን መስተዳደር በቀጥታ የሚአወግዘውን የኦሮሞ ልሂቅ በቸልተኝነት ማለፍዎንም አስተውያለሁ። በአንፃሩ ለርስዎና ለመንግሥትዎ ሙሉ ድጋፍ የሰጠ ዓማራ ሲጠቃ፤ ሲፈናቀል፤ ብሔሩን ለማጥፋት ዘርፈ ብዙ ጥቃት ሲደርስበት እያዩ ዝምታን መረጡ። ምክንያቱ እስካሁን ሊገባን ባይችልም በኦነጎች ቁጥጥር ስር ሆኑ እስከማለት ተደርሷል።
ይሁን እና አሁንም ስላልመሸ ብዙውን ነገር ማስተካከል ይቻላል። ዋናው ከርስዎ የሚጠበቀው የሕግ የበላይነት እንዲስፍን ማድረግ ነው። በዘር ፌድራሊዝም ላይ ቆራጥ የቀዶ ጥገና ዘምቻ እንዲአድርጉ ዓማራውና ሌሎች ሕዝቦች በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ።
ብዙ ሰዎች በኦነግ አክራሪዎች ስለተጠልፉ እንጂ እንደርሳቸው አስተሳሰብ የሚሰሩ ቢሆን እዚህ ምስቅልቅል ውስጥ አይገቡም በለው ያወራሉ። በእኔ እይታ ሃያ ሰባት ዓመት የከሰረ ፖለቲካ ስለወረሱ የማጽዳቱ ስራ ከፍተኛ ሳንካ እንደሆነብዎት ይሰማኛል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት ወያኔን መጣል ቀላሉ ስራ ሲሆን፤ ከውድቀቱ በኋላ ወያኔ ለ30 ዓመት ያበላሸውን የማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ማስተካከል ከባድ እንደሚሆን ተንብየዋል። እርስዎን የገጠመዎ ችግር ይህ ይመስለኛል።
ያልተበላሽና ያልታመመ የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቀር የለም። ሑሉም መድሃኒትና ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል። እርስዎ ደግሞ ሃገር ማስተዳደር ከጀመሩ ገና አንድ ዓመትዎ ነው። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ በጎ ተግባራትን ፈጽመዋል። በሂደቱም የተበላሹ ጉዳዮች አሉ። እንዚህን እያስተካከሉ፤ ሕዝባችንን እያሰባሰቡ እንዲመሩ ዓማራው በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ዓማራውን በጥንቃቄ ይያዙት። ሙሉ ድጋፍ የሰጠዎት ማህበረሰብ ወደ መደገፍ ወይ አለመደገፍ ምርጫ እንዲገባ አይግፉት። ይህ ማሁበረሰብ ከደገፈዎት ለውጡ ይቀጥላል፤ ከተቃወመዎት የለውጡ ዓጀንዳ ይደናቀፋል፤ ሃገሪቱንም ወደ ክፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊአስገባት ስለሚችል በጊዜ ያስቡበት።
ለጊዜውም ቢሆን አሁን ላለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የእኔ ምርጫ ነዎትና ማስተካከያዎችን እያደረጉ ይምሩን። ግን በቁልቁለት ጎዳን መሄድ በሚጀምሩበት ጊዜ የድጋፍ ካርዴን ወደ ሰገባው እመልሰዋለሁ። ድጋፍና እውቅና የሰጠዎትን ሃምሳ ሚልዮን ዓማራ አንዱ በመሆኔ ድጋፋችንን እንዳያጡ በጥንቃቄ እንዲመሩን ከአደራ ጋር አስታውሳለሁ። አመሰግናለሁ
በርስዎ ተስፋ ያልቆረጠው
አቢቹ ነጋ
July 25, 2019