March 7, 2013
27 mins read

“ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቆች ሆነዋል..” ስማቸው ያልተገለጸ እናት

ከሉሉ ከበደ

ሰሞኑን ከአገር ቤት አንዲት እናት ልጃቸውን ሊጠይቁ መተው ነበር። ልጃቸው የባለቤቴ ጓደኛ ነች።..የኔም ጓደኛ!…እኒህ አናት አንደበተ ርቱእና ተደምጠው የማይጠገቡ ጨዋታ አዋቂ ቀልደኛም ናቸው። ሑሉም ነገር የገባቸው ፍጹም ፖለቲካ አዋቂ ብሩህ እናት ናቸው። ጨዋታቸው ንግግራቸው ሁሉ ይማርካል። ሰማንያ አመት አይሞሉም። ጥንክር ያሉ፤ የነቁ ፍጹም ጤናማ እናት ናቸው።
ወይን ቢጤ ገዛሁና ባለቤቴ ድፎ ዳቦ ጋግራ ( እናቶች አዚህ አገር ሲመጡ ድፎ ዳቦ ሲቀርብላቸው ደስ እንደሚላቸው ታውቃለች) እንኳን ደህና መጡ ልንል ሄድን።
ለሁለት ሰአት ያህል አብሬ ስቆይ ከናታችን የገበየሁት ትምህርትና ቁም ነገር በቀላል የሚገመት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ እየጠላቸው ዛሬ ስልጣን ላይ የተጣበቁት የወያኔ ደናቁርት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ምንም አያውቅም ብለው፤ የሚገምቱትና የሚንቁት፤ወደ ታች ወደ ህብረተሰቡ ዝቅ ብለው፤ስለነሱ አገዛዝ፤ ስለ መልካም አስተዳደር ያለውን ግንዛቤ ቢረዱ ምን ያህል ከህብረተሰቡ ኋላ ኋላ እየሄዱ እንመራሀለን እንደሚሉ በተረዱና ባፈሩ ይበጃቸው ነበር።
እኒህ እናት ድህነትን እኩል ያካፈለን ደርግ ተሻለ ነው ነው የሚሉት፤ “እነዚህ ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቅ ሆነዋል። ደርግ አንዱን ልጅ አንዱን እንጀራ ልጅ አላደረገንም። ቢበድለንም አልለያየንም።”
ጎዳና ላይ ለፈሰሱ ለማኝ ህጻናትና ወላጆች ዘወትር ያለቅሳሉ። ኑሮአቸውን የከተማው ቆሻ ክምር ላይ የመሰረቱ ወላጆችና ልጆች ያስለቅሷቸዋል። “ይሄ ሁሉ ፎቅ ይገነባል። የእያንዳንዱን ፎቅ ባለቤት አስር አስር ልጅ ከጎዳና ወስዶ እንዲያሳድግ ቢያስገድዱት ጽድቅ ነበር። ላለው ሰው ምንም ማለት አይደለም” ይላሉ።
ስለቤተሰብ ስለዘመድ አዝማድ፤ስአየርንብረትና ሌላ ትንሽ ከተጨዋወትን በኋላ ወዲያው ነበር ስለ ሀገር ጉዳይ የተነሳው።
“ኑሮ አንዴት ነው?.. እትዬ… አገር ቤት ” አልኩ ።
“…አየ… ልጄ .. ምን ኑሮ እንዴት ነው ትለኛለህ? …ወያኔው እንዴት አደረጋችሁ በለኝ እንጂ? …”
አነጋገራቸው ያስቃል። ሁላችንም ሳቅን። ሳቄን ገታ አደረኩና.. “ወያኔው ምን አደረገ?.. እስቲ ያለውን ነገር ያጫውቱኝ…” አልኩ።
“ ከየቱ ጋ እንደምጀምርልህ አላውቅም ልጄ….ያላየነው ታሪክ የለም …በነዚህ ሰዎች ዘመን ያየነው ጉድ ብዙ ነው።”
“ ምን ጉድ አለባቸው?”
“ደግ ጠይቀኸኛል ልጄ…ምን ጉድ አለባቸው አልከኝ? …. ይሔውልህ እኔ ያንተ እናት… ሶስቱንም መንግስት በልቻለሁ።.. አንድ ነገር ልንገርህ ..ጃንሆይን ክፉ …አድሀሪ ስትሉ.. ክፉ መንግስት ስትሉ …ደርግ መጣና ክፉ መንግስት ምን አይነት እንደሆነ አሳየን.. ደርግን ክፉ ስንል ስንጠላ..ስንጠላ..እነዚህ መጡና የባሰ ክፉ መኖሩን አሳዩን..” ድንገት አቁዋረጥኳቸውና…
“የነዚህ ክፋት ምንድንው?”
“ደግ ብለሀል ልጄ… የነዚህ ክፋት.. ደርግ ወንበሬን ቀና ብላችሁ አትዩ ብሎ ነበር ያን ሁሉ ሰው የፈጀው፤…አማራ አላለም፤… ትግሬ አላም። እስላም ክርስትያን አላለም። ደርጉ ይል የነበረው፤ አገራችሁን ጠብቁ፤ ተስማምታችሁ አንድ ሆናችሁ ኑሩ፤ ወንበሬን ግን ቀና ብላችሁ አትዩ…”
ፊቴን ትኩር ብለው እያዩ
“..ያኔ እናንተም በየከተማው ጦርነት ከፈታችሁበት..እሱም ጦርነት ከፈተ…ያሁሉ በልቶ ያልጠገበ ልጅ አለቀ። ቀድሞውንም ያኔ ወይ ጫካ ሂዳችሁ በተዋጋችሁት ደግ… ወይ አርፋችሁ በተቀመጣችሁ… ያንን ሁሉ የልጅ ሬሳ አናይም ነበር..በኢሀፓ ጊዜ…”
“..እነዚህ መጡ …ያገሬ ሰው ተረተ። … ‘ምንሽር ልገዛ ወይፈኔን ሳስማማ፤መጣ የትግሬ ልጅ በነጠላ ጫማ’… ገና ሲመጡ ጀምሮ የወደዳቸውም የለ… እግዚአብሄር ያመጣውን ፍርጃ መቀበል እንጂ የሚደረግ የለም… መጡልህና ወንበራችንንም ቀና ብላችሁ እንዳታዩ፤ ለራሳችሁም እንዳትትያዩ… በየዘራችሁ ተበታተኑ አሉ። ለሁሉም በየዘሩ ማህበር አበጀለትና ሁልህም በዚህ ቀንበር ውስጥ ትገባለህ..ግባ አለው።”
“ማን ነው ያለው?’’
“ሟቹ…”
“አልገባም ያለ፤ እነሱን የሞገተ፤ የጥይት እራት ይሆን ጀመር። አንድም ሰው ጠመንጃ አንስቶ የተኮሰባቸው የለም። በያለበት ሰው መግደል ሆነ ስራቸው። አንዱን ካንዱ ማባላት፤ አሉባልታ ውሸት በራዲዮን፤ በቴሌቭዥን ሲነዙ መዋል ሆነ። እንዲህ እንዲህ አድርገው ሰዉን ሁሉ አደናግረው ሲያበቁ፤ አስፈራርተው ሲያበቁ፤… የራሳቸውን ሰው ሁሉ ቦታቦታውን አስያዙ። ዛሬ ያለነሱ ነጋዴ የለም። ያለ እነሱ የቢሮ አለቃ የለም። ያለነሱ የቀበሌ አለቃ የለም። ያለ እነሱ ፎሊስ የለም። ሰው ሁሉ ሀሞቱ ፈሶ እነሱን እየፈራ መኖር የዟል። ….ወንዱም ሴቱም….ታዲያ ልጄ ደርጉ እንደዚህ ባይተዋር አድርጎናል?” አሉና በንዴት እራሳቸውን እየነቀነቁ ጠየቁኝ።
“ልማቱስ እትየ?…አገሩን አልምተዋል ይባል የለ እንዴ?”
“ሀሰት!.. ሀሰት ልጄ!…አገር ቢለማ፤ አገሬው ሁሉ ከነልጁ ለልመና ጎዳና ላይ ይፈስ ነበር?…ልማቱንስ ቢሆን እነሱ እንጂ ሌላው ሰው የታለ?..የታለ ጉራጌ ባለፎቅ ?..የታለ አማራ?..የታለ ኦሮሞ?….ያ ፎቅ የማነው ስትል… እነሱ….ያፎቅ የማነው ስትል እነሱ…..ልጄ ከየት አመጡት ያሰኛል እኮ? እነሱና አላሙዲ እንጂ ሀብታም አለ እንዴ ዛሬ?..”
“ዛሬ አንድ ሺህ ብር ይዘህ ገበያ ወተህ….. አንዲት ዘንቢል ሞልተህ አትመለስም እኮ!…ልማት ማለት ድህነትና እራብ ነው እንዴ?… ጦሙን የሚያድረው ህዝብ ተቆጥሮ አያልቅም እኮ…. እዚችው አዲስ አበባ…..”
“…ጭራሽ ጥጋባቸው… ቤት ዘግተው፤ ዊስኪ አውርደው ሲጨፍሩ የሚያድሩ እነሱ… ጠግበው በሽጉጥ ሲታኮሱ የሚያድሩ እነሱ… መጠጥ ቤት የፈለጋቸውን ደብድበው አድምተው የሚሄዱ እነሱ….”
“…የኛ ሰፈር መደዳውን ቡና ቤት ነው።…አንድ ቀን ጠዋት ወደ ክፍለ ሀገር አውቶብስ ተራ ልሄድ አስር ሰአት ተነስቼ ታክሲ ስጠብቅ….አንዲቷን ድሀ ጸጉሩዋን ይዞ መሬት ለመሬት እየጎተተ በግንባሯ ያዳፋታል፤ ከቡና ቤት አውጥቶ አስፋልት ላይ ይረግጣታል።..ኡ ኡ እያለች…ገደለኝ እያለች…ሊገላግላት የመጣ ወንድ ጠፋ። ሰው ሁሉ ሰምቶ እንዳልሰማ እየሆነ ብቅ አላለም። በስካር መንፈስ እንኳ እነዚህን ሰዎች የሚደፍር ጠፋ? አልኩና እንባዬን እርግፍ አድርጌ አለቀስኩ። ልጄ ድሮ ሴት ልጅ ድረሱልኝ ብላ ስትጮህ እንዲህ ነበር እንዴ?..”
“..ወዲያውኑ አንድ ታክሲ ሲበር መጣ… አስቆምኩና ገብቼ… እንዳው ልጄ ይህን ሰውየ እላዩ ላይ ንዳበት!…ንዳበት!…ገደላት እኮ…ንዳበት! አልኩት። ለካንስ ያም ባለታክሲ የነሱ ሰው ኖሯል…አንዳንድ ደግ መቸም አለ…ሽርርር አደረገና መኪናዋን እላዩ ላይ አቁሞ፤ ወርዶ፤ እንደብራቅ ጮኸበት አልኩህ።ተጯጯሁ..ተጯጯሁ..ተሰዳደቡ፤ተሰዳደቡ..በግርግር እሷ እመር አለችልህና ደሟን እያዘራች ተነስታ አመለጠች…ያም ከባለታክሲው ጋር እየተሰዳደበ ወደ መሄጃየ አቀናን …”
“..ዛሬ አሁን የፈለገ ነገር ቢመጣ የአዲስ አበባ ሰው ቤት ለነሱ አያከራይም….”
“ለምን?” አልኩ።
“ለምን ማለት ደግ..ይኽውልህ ልጄ ቤት ታከራያቸው የለም?…ልቀቁ ስትል አይለቁም፤ …ወደየትም ሄደህ ከሰህ አታስለቅቃቸውም።…አንዲቷ እንዳደረገችኝ ልንገርህ..” አሉና ፎቴው ላይ እየተመቻቹ፤ የተደረበላቸውን ብርድ ልብስ ወደላይ እየሰበሰቡ፤ “… እግዚአብሄር ብድሩን ይክፈላቸውና ልጆቼ ቤት ሰሩልኝ ብየህ አልነበር?…”
ውድ አንባቢያን ወደጨዋታችን መጀመሪያ ላይ ልጆቻቸው ቤት እንደሰሩላቸው ነግረውኝ ነበር። አምስት ልጆች አሏቸው። ሁሉም በየአለሙ ተበትነው ይገኛሉ። ኖርዌይ፤ ጀርመን፤ አሜሪካ፤ካናዳ..እና ሁሉም እንደየአቅሙ አዋቶ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ከየመኝታ ቤት ያላቸው ባለ አንድ ፎቅ ሰርተውላቸው ነበር። እሳቸው አሮጌው ቤት እየኖሩ ይህን ቤት አከራይተው በሚያገኙት ገቢ ስድስት የእህት የወንድም ልጅ ከገጠር አስመጥተው እያስተማሩ ያሳድጋሉ። እናም ልጆቻቸው እንደገና ገንዘብ እንስጥሽ ብለው እንዳይቸገሩ በማለት ለነሱ ያልነገሯቸው፤ ነገር ግን ከቤቱ ኪራይ ቆጥበው ምድር ቤት ባንዱ ክፍል ምግብና መጠጥ ሊነግዱ ሀሳብ አላቸው። ዛሬ ነገ እጀምራለሁ ሲሉ አንዱን ቤት አላከራዩትም ነበር። ኋላ ላይ ግን ለማከራየት ወሰኑ።
“…ቤት ሰሩልኝ ብየህ አልነበር?…ታዲያ ያችን አንዷን የቀረችውን ለአምስት ወርም ቢሆን ላከራይ አልኩልህና….አንዱ ደላላ አንዲቷን ወያኔ ሴት ይዞ መጣ። ቤቱ መንገድ ዳር ነው ለንግድ ይመቻል …አንባሻና ሻይ ቡና ልሸጥ ነው አለችኝ።…..አይ ልጄ እኔም እንዲህ፤ እንዲህ ላደርግ ሀሳብ አለኝ። …ባከራይሽም ለአምስት ለስድስት ወር ነው። ከፍተሽ የምትዘጊው ንግድ ምንም አያደርግልሽም። ሌላ ብትፈልጊ ይሻልሻል አልኳት።”
“…ሞቼ እገኛለሁ። ልቀቂ ባሉኝ ቀን እለቃለሁ። እንደው እትዬ..እትዬ..” አለች።
“ኮሎኔል ወንድም አላት አሉ። እሱ ነው ካገሯ ያስመጣት። ላገሩም እንግዳ ነች። አይ እንግዲህ እለቃለሁ ካለች ትግባ ብየ በሰው ፊት ተዋውለን ገባች።”
“እርግጥ ጎበዝ ሴት ናት። የኛ ሰፈር አላፊ አግዳሚው ይበዛል። በጠዋት ተነስታ ቄጠማውን ጎዝጉዛ፤ አጫጭሳ፤ ቡናውን አቀራርባ፤ ሞቅ ሞቅ ስታደርገው፤ መንገደኛው ሁሉ ቁርሱን በልቶ ቡናውን ጠጥቶላት ወደየስራው ይሰማራል።”
“..እንዲህ እንዲህ እያለ ያች አምስት ወር ደረሰች። አይ ይች ሰው አሁን እንዲህ ገበያው ደርቶላት ልቀቂ ብላት ትቀየመኝ ይሆን? አልኩልህና እኔው ተጨንቄ አረፍኩት። …እሷም ቤት ልፈልግ አላለች፤ እኔም ትንሽ ትቋቋም ብየ ሶስት ወር ጨመርኩላት። ከዚያ በኋላ ደሞ ሶስት ወር አስቀድሜ ቤት እንድትፈልግ ነገርኳት። እሺ አለች። ወር አለፈ። ሁለተኛውም አለፈ። ሶስተኛው ተገባደደ። እየፈለኩ ነው ትላለች። ወሩ አለቀ። ቤቴን መልቀቅ የፈለገች አትመስልም። …በይ እንግዲህ ካጣሽ እኔው እፈልግልሻለሁ አልኩና ከኔ ቤት ወረድ ብሎ ሌላ አገኘሁላትና በይ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ቤቱን እፈልገዋለሁ አልኳት። ወሩ ሲሞላ ደህና የነበረችው ሴትዮ ድንገት ተለዋወጠችብኝና አልወጣም ሂጂ ክሰሽ አትለኝ መሰለህ?…አበስኩ ገበርኩ…አልኩና ያዋዋሉንን ሰዎች ጠራሁና ይችን ሽፍታ ገላግሉኝ አልኩ። ጭቅጭቋን ቀጠለች። አንድ አስራ አምስት ቀን ስታምሰን ከረመች አልኩህ…በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ወደዚሁ ቤት ስመጣ ሌሊት እቃ ታግዝ ነበር ሲሉኝ አምላክ በሰላም ሊገላግለኝ ነው አልኩና ገብቼ ቤቴን አየዋለሁ….ልጄ አፍርሳዋለች አልኩህ…ግርግዳውን ሁሉ ቧጣ፤ቧጣ ቧጣ…..እንደው ልጄ በምን ይሆን ስትቧጥጠው ያደረችው?…ሸንትራ፤ሸንትራ፤ ግርግዳውን ልጅ ያረሰው መጫወቻ ደጅ አስመስላዋለች። ሽንት ቤቱን ሰባብራ አግማምታ፤ አበስብሳው፤ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ሳትከፍለኝ ኮተቷን ሰብስባ ውልቅ አለች። ክሰሻት አሉኝ። ማን ላይ ነው የምከሳት?…ጭራሽ አሸባሪ ትብየ እኔው ልታሰር?…”
የእናታችን ጨዋታ ፈርጀ ብዙ ነበር። አንዱን ጨርሰው ወደ ሌላው ሲያልፉ አንደበተ ርቱእነታቸውና ለዛቸው አፍ ያስከፍታል።
“..አንድ ጉድ ደሞ ላጫውትህ….ስራ አጥተው ችግርርርር ያላቸው አስር የሚሆኑ የሰፈራችን ወጣቶች ተሰበሰቡልህና ስራ ፈጠሩ። ምንድነው ስራው ብትለኝ…ሆቴል ቤቶች ሞልተዋል ብየሀለሁ ሰፈራችን….ከባለቤቶቹ ጋር ይነጋገሩልህና በቀን ሶስት ጊዜ ቆሻሻ መድፋት፤ በቀን አንድ ጊዜ ግቢ መጥረግ፤ ይህን ለመስራት ተዋውለው ….ባለ ሆቴሎቹም ሁሉ ደስ ብሏቸው….ሲሰሩ የሚለብሱት ልብስም ገዝተውላቸው…ጋሪም ገዝተውላቸው ስራ ጀመሩ። የሰፈሩ ሰው ሁሉ ደስ አለው። ልጆቹ ገንዘብ አገኙ፤ እናትና አባታቸውን ማልበስ ለራሳቸውም ደህናደህና ነገር መልበስ ጀመሩ። ስራቸውንም እያስፋፉ በቁጥር አስራ አምስት ደርሰው፤ በሰላም ተረጋግተው በመስራት ላይ እንዳሉ፤ ህገ ወጥ ስራ ነው የምትሰሩት አቁሙ ይላቸዋል አንዱ…”
“ ማን? “
“ እዚያው ቀበሌ ውስጥ ….የምንትስ ሀላፊ ነው ያሉት ትግሬ…”
“ ለምን አስቆማቸው?”
“ ስራውን ቀበሌው ሊሰራው በእቅድ የያዘው ስለሆነ በቀበሌ ታቅፋችሁ ነው መስራት ያለባችሁ። ቀበሌ ለናንተ ይከፍላል። ግብር ለመንግስት መክፈል አለባችሁ፤ ፍቃድ ያስፈልጋችኋል….አለና አስቆማቸው። ልጆቹም ለምንድነው እኛ የፈጠርነውን ስራ የምንከለከለው ብለው ሲጨቃጨቁ ሁለቱን አስረው፤ የቀሩትን አስፈራርተው በተኗቸው።”
“…ትንሽ ቆየት ይሉልህና… ልጆቹን አደናግረው አስፈራርተው ከበተኗቸው በኋላ ያንኑ ስራ በቀበሌው የማይኖሩ የራሳቸውን ወጣቶች ሰብስበው ….”
“የራሳቸውን ወጣቶች ማለት?” አቋርጨ ጠየኩ።
“ትግሬዎቹን… ሰበሰቡና ከመጀመሪዎቹ ሁለቱን ቀላቅልው ስሩ አሏቸው …እነዚያ ሁለቱ ደሞ ጓደኞቻችን ተባረው እኛ አንሰራም ብለው ትተውላቸው ሄዱ። ባለሆቴሎቹ ቀድሞ የሚያስጠርጉትን ልጆች ሲያጡ፤ ምንድነው ነገሩ ብለው ቢያጠያይቁ፤ የመጀመሪያዎቹ ልጆች የሆነውን ሁሉ ነገሯቸው። ባለሆቴሎቹም አደሙ ። ቆሻሻችንን እኛው እንደፋለን እንጂ አናስጠርግም አሉ። የተተኩትን ልጆች ስራ የለንም እያሉ መለሷቸው። ”
“ያ አለቃ ተብየው ቀበሌ ሰዉን ሰብስቦ አሉ… ጸረ ልማት ሀይሎች እያለ ሲሳደብ ከረመ አሉ። ባለ ሆቴሎቹም እንዳደሙ ቀሩ። ሗላ ላይ ሥሰማ በመጀመሪያ ያጸዱላቸው የነበሩትን ልጆች ሁሉንም ተከፋፍለው ቀጠሯቸው አሉ። እነዚያም ጋሪያቸውንና ጓዛቸውን ይዘው ወዴት እንደሄዱ አላውቅም እልሀለሁ …..ልጄ..ወያኔ እንዲህ እያመሰን ነው እልሀለሁ…..” እንደ መተከዝ አይኖቻቸውን ወለሉ ላይ ተክለው ለአፍታ ዝምም አሉ።
ውድ አንባቢያን የህብረተሰብ ደህንነት የሚረጋገጠው፤ እያንዳንዱ ክፍለ ህዝብ ከህዳጣን እስከ ብዙሀን ምልአተ ህዝቡን የገነቡ ብሄረሰቦች ሁሉ እኩል መብትና ነጻነት ሲኖራቸው፤ በሀገራቸው እኩል የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው፤አንባ ገነንም ይሁን ዲሞክራሲያዊ ..ያለውን መንግስት የኛ ነው ሲሉት፤ በባህላቸው፤ በቋንቋቸው፤ በሀይማኖታቸው፤ የተነሳ ምንም አይነት መገፋት እንደሌለ ሲያረጋግጡ ዜጎች ደህንነት ይሰማቸዋል።
የናታችንን ጨዋታ ለማጫር ይችን ጥያቄ ጣል አደረኩ።
“ወያኔ..ወያኔ ይባላል… ኢህአደግ ነው መባል ያለበት… አይደለም እትየ?”
ከት አሉና ሳቁ ። ሳቃቸው አስቆን ሁላችንም ፍንድት አለን።
“አየህ ልጄ…በቆሎ እሸት ታውቃለህ አይደል?..በቆሎ እሸት..” አሉ እጃቸውን ቀና ቀጥ አድርገው፤ “..በቆሎ እሸት የምትሸለቅቀው ልባሱ አለ። ያ ልባሱ ገለባ ነው። ይጣላል። ዋናው በቆሎው ነው። ፍሬው። እነዚህ ኢህአደግ ያልካቸው ገለባ ናቸው (ሶስቱን የወያኔ ፍጡራን ድርጅቶች ማለታቸው ነው፡ ኦህዴድ፤ ብአዴን….) ዋናዎቹ ትግሬዎቹ ናቸው። ገባህ ልጄ…”
በአዎንታ ራሴን ነቀነኩ።
“..የአማራው ነን፤ የኦሮሞው ነን፤ ማነው ይሄ ደሞ የበየነ ጴጥሮስ አገር…ብቻ ሁሉም ከነሱ ጋር ያሉት ገለባዎቹ አሽከሮቻቸው ናቸው። ማፈሪያዎች ናቸው፤…..እንዳይመስልህ ልጄ…ጌቶቹ ትግሬዎቹ ናቸው፤….የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እነዚህ ኢህአደግ ያልካቸው ከምንም አያስጥሉንም……”
ውድ አንባቢያን ያለፈ አንድ አመት አካባቢ አንዲት ሌላ እናት እንዲሁ መተው ለመጠየቅ ሄጄ ዘጠና በመቶ ማለት ይቻላል ተመሳሳይ አይነት ጨዋታ አጫውተውኝ ነበር። ካንድ ሰው ብቻ የተገኘ ኢንፎርሜሽን ለሌላው ማስተላለፍ ያስቸግራል፡፡ ሁለት ይማይተዋወቁ ሰዎች፤ የተለያየ አካባቢ የሚኖሩ፤ በተለያየ ጊዜ አንድ አይነት ነገር ከተናገሩ እውነትነት ያለው ጉዳይ አለ ማለት ነው።
ይህ ስርአት መለወጥ እንዳለበት ዜጎች ይስማማሉ። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚታሰብ ነገር አልሆነም። እንዴት ነው እነዚህን ሰዎች ከስልጣን የምናስወግደው ነው ጥያቄው፤ መላ መምታት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታና ፈንታ ነው። እናታችንን ጠይቄአቸው ነበር።
“ይህንን መንግስት ለመለወጥ ምን ቢደረግ የሚበጅ ይመስሎታል እትየ?”
“መተኮስ….መተኮስ ነዋ!…እነሱ ተኩሰው አይደል ለዚህ የበቁት?…..ግን እኮ ልጄ… ወንዱ ሁሉ ሀሞቱ ፈሰሰ…በጥቁር አህያ ነው አሉ ያስደገሙብን…የሱዳን መተት ቀላል እንዳይመስልህ ልጄ…ሱዳን አልነበረ የሚኖሩት…ያኔ አሉ…. ሲገቡ፤ ሕዝቡ ሁሉ እንዲፈዝላቸው……ወንዱ ሁሉ ወኔው እንዲሰለብ…. በጥቁር አህያ አድርገው አስደግመው ገቡ አሉ። ይኸው ሀያሁለት አመት….አገር መሬቱን ሲሸጡ፤ እስላም ክርስቲያኑን ሲያምሱ፤ ሲገሉ ….ቤት ሲያፈርሱ.. ንብረት ሲቀሙ…ማን ወንድ ሸፍቶ አስደነገጣቸው?…..ሀያ ሁለት አመት…ሀያ ሁለት ዓመት… መተኮስ … መተኮስ ነው ልጄ…” lkebede10@gmail.com

Go toTop