March 31, 2017
6 mins read

የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

ሦስት የኖክ ነዳጅ ማደያዎችን ጨምሮ ዘጠኝ የነዳጅ ማደያዎችን በእሳት ለማቃጠል፣ በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉ ዘጠኝ ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ ሊያቃጥሏቸው ነበር የተባሉት ሦስቱ የኖክ ነዳጅ ማደያዎች ቦሌ ኤርፖርት አካባቢ፣ መገናኛ አካባቢና ባምቢስ አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡ ስማቸው ያልተጠቀሱት ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ መካኒሳ ጀርመን አደባባይ አካባቢ፣ መርካቶ ጭላሎ ሆቴል አካባቢ፣ አየር ጤና፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ኮልፌ አጠና ተራና አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የሚገኙ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ በቅጽል ስሙ ሁሴን መሐመድ የሚባለው ክንዱ መሐመድ፣ መሐመድ ካሳ (ቅጽል ስም ሁሴን አህመድ)፣ ደረጀ አያሌው፣ ኤፍሬም ሰለሞን፣ አብርሃም ሰለሞን፣ ጴጥሮስ ጉግሳ፣ ዘሪሁን አግዜ፣ ተመስገን አልማውና ግሩም ወርቅነህ እንደሚባሉ ተገልጿል፡፡

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 35፣ 38፣ 32(1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ከላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የሥራ ክፍፍል በማድረግ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡

ክንዱ መሐመድ ወይም በቅጽል ስሙ ሁሴን መሐመድ በመባል የሚጠራው አንደኛ ተከሳሽ፣ በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. የግንቦት ሰባት አርበኞች አመራር ዳዊት በሚባል ግለሰብ ተመልምሎ የወንጀል ድርጊቱን እንዴት መፈጸምና ማስፈጸም እንዳለበት በ‹‹ዋትስ አፕ›› በመገናኘት ተልዕኮ ሲቀበል እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ‹‹አሻጥር›› የሚል መመርያ ዳዊት የሚባል የግንቦት ሰባት አርበኞች አመራር ለአንደኛ ተከሳሽ ከላከለት በኋላ፣ ተከሳሹ ሌሎች ስምንት ግለሰቦችን (ስማቸው የተጠቀሱትን ተከሳሾች) በመመልመል በመመርያው ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ዘጠኝ የነዳጅ ማደያዎች መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማቃጠልም ቁርጥ ቀን መያዛቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ዘጠኙንም የነዳጅ ማደያዎች መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ላይ ለማቃጠል በጠርሙስ ውስጥ ቤንዚን በመሙላት፣ በጠርሙሱ ውስጥ ጨርቅ በማስገባትና ጫፉን በክብሪት በመለኮስ የነዳጅ ማደያዎቹ ላይ እንዲወረውሩ ተስማምተው እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡

ድርጊቱን ከመፈጸማቸው በፊት የነዳጅ ማደያዎቹን የጥበቃ ሁኔታ እንዲያጠኑ ወይም ማረጋገጥ እንዳለባቸው በ‹‹አሻጥር›› መመርያ ስለተነገራቸው፣ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ተንቀሳቅሰው ሲያጠኑ የጥበቃ ሠራተኞች በትጋት ሲጠብቁ በመመልከታቸው ዕቅዳቸው ሳይሳካ መቅረቱን ክሱ ይገልጻል፡፡

የግንቦት ሰባት አርበኞች አመራር ነው ለተባለው ዳዊት በተሰጣቸው ‹‹አሻጥር መመርያ›› መሠረት ድርጊቱን መፈጸም እንዳልቻሉ አንደኛ ተከሳሽ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ደውሎ ሲነግረው፣ የጥበቃ ሥራው መላላቱን እንደሰማ ነግሮት የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ በድጋሚ ድርጊቱን ለመፈጸም መዘጋጀት እንዳለባቸው የነገረው ቢሆንም፣ እንዳልተሳካለት ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ሊሳካላቸው እንዳልቻለና ድርጊቱን ሳይፈጽሙ በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳትና ሙከራ ወንጀል ክስ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መሥርቶባቸዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

Go toTop