ታሪኩ አባዳማ – መጋቢት 2009
የኦነግ መስራች ከነበሩት አንዱ አቶ ሌንጮ (ዮሐንስ) ለታ ከወራት በፊት ስለ ባንዲራችን ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ ‘እስከ ዛሬ ሁላችንም ተስማምተን የተቀበልነው ባንዲራ የለም’ የሚል መልስ ሰጥተዋል። አባባሉ ስለ ባንዲራችን ዕጣ ፈንታ ወደፊት ሁኔታው ሲመቻች እንመክራለን በሚል በይደር የተያዘ አጀንዳ እንዳላቸው ያመለክታል። እንደ ጭብጥ የሚያነሱት መከራከሪያ ደግሞ ባንዲራውን ለመቀበል ጥንት ስላልተመካከርን ለጊዜው አሁን አንቀበለውም የሚል አይነት ነው።
ዘር ላይ ብቻ የተመረኮዘ ባንዲራ ኖሮን ስለማያውቅ ፖለቲካውን በዘር መንፅር ለሚያዩ ወገኖች የባንዲራው ፋይዳ ሳይታያቸው ቢቀር ሊደንቅ አይገባም። ኦነግ ያነገበውን ወይንም ዛሬ እሳቸው የሚያውለበልቡትን ባንዲራ የዛሬ አርባ አመት ግድም ሲቀርፁት እና ሲያሰራጩት በየትኛው የህዝብ ሸንጎ ምክር ተደርጎበት እንደፀደቀ ባላውቅም ጥንታዊው የኢትዮጵያ ባንዲራ ግን ከመንግስት ምስረታ ታሪካችን እና ባህሪ ጋር የተቆራኘ ተፈጥሮ እንዳለው ለማሳየት ሞክራለሁ።
ስለ ባንዲራችን ጉዳይ እንነጋገር ማለቱ ባይከፋም እንደምናየው ገና ከመነጋገራችን በፊት ሌላ አዲስ ባንዲራ እያውለበለቡ (ቀድሞውኑ አቋም መውሰዳቸወን የሚያረጋግጥ) ሰለ ጥንታዊው እና ታሪካዊ ባንዲራ እንወያይ ማለት ማላገጥ ይመስለኛል። ውይይት በንፁህ ህሊና እስካልተካሄደ ድረስ ባንዱ ጉዳት ሌላው ለመጠቀም እያደባ መሆኑን ያሳብቃል።
በቅድሚያ ስለ አቶ ሌንጮ ጨዋነት ላመሰግናቸው ይገባል ፤ አገራችን ውስጥ ለሚነሳ ማናቸውም ፖለቲካዊ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በጋራ መስራት እና በጋራ መምከር ጨዋነት ነው። ከአነጋጋራቸው እንደተገነዘብኩት የባንዲራውን ህልውና አልካዱም ፣ ባንዲራውን ማንጓጠጥ አላስፈለጋቸውም። ስለ ባንዲራው ጉዳይ የሚከነክናቸው ነገር እንዳለ ግን ጠቁመዋል። አቶ ሌንጮ ዛሬም የሚመሩት ድርጅት አለ። ድርጅታቸውን ወክለው ማናቸውንም ኢትዮጵያን ይመለከታል የሚሉትን ለዘላቂ ሰላሟ እና ዕድገቷ ፣ ለህዝቧ ዕድገት እና ብልፅግና ይበጃል የሚሉትን ሀሳብ መሰንዘር ፣ መምከር ፣ መመካከር ሊከለክላቸው የሚችል የለም – እናም ያነሱት ሀሳብ ይከነክናል።
ባለጌ ያሳደገው ጎጠኛ ስንቶች የተሰዉለትን ባንዲራ “ጨርቅ” ብሎ እንደ መናኛ እቃ ሲያጥጥለው አልነበር? በዚህ አልበቃ ብሎ በመለስ ዜናዊ ዲስኩር የሰከሩ (እነ አቶ ሌንጮ በእማኝነት በተገኙበት) ባንዲራው ላይ ስንት ሳምንት ሙሉ በቅብብሎሽ ተዘባብተው በመጨረሻ እንደ ጉሮሮ አጥንት እንዳይተፉትም እንዳይውጡትም ሆኖባቸው አንዳች ድሪቶ ለጠፉበት።
የኛ ባንዲራ አመጣጥ ታሪክ ከአገራችን የቅርብ እና የሩቅ ዘመን ታሪክ በተለይም ከማዕከላዊ መንግስት ምስረታ ታሪካችን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። በብዙ አገሮች እንደሆነው ሁሉ በፖለቲካ እና ወታደራዊ መስክ መንግስታዊ ስርአት እየተጎናፀፈ የመጣ ህብረተሰብ ራሱን የሚገልፅበት ፣ ህልውናውን የሚያንፀባርቅበት ባንዲራ ይኖረዋል። ባንዲራ ለምን ተውለበለበ ብሎ መጠየቅ መንግስት ለምን ተመሰረተ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው። የቆየ ታሪክ ያለው መንግስታዊ ስርዓት እንደነበረን መቀበል ከዚህ ተነጥሎ የማይታየውን ባንዲራ እንደመቀበል ነው። ሁለቱ ተነጣጥለው የሚታዩ ነገሮች አይደሉም።
ጥቂት ምሳሌዎች ከሩቅም ከቅርብም ላክልበት – የአሜሪካ መንግስት ሲመሰረት እና ባንዲራ ሲያወለበልብ ከኛ እጅግ በተሻለ መልኩ ግን ውሱን በሆነ ተሳትፎ በምክር በፀደቀ አዋጅ ነበር። ይኸውም ጁን 14 ቀን 1777 (እአአ) ‘አገርአቀፍ ሁለተኛው ጉባኤ’ (Second Continental Congress) በወቅቱ ከነበሩት 13 ግዛቶች የተውጣጡ ተወካዮች ባደረጉት ውይይት ድንጋጌው ፀድቆ ወጣ። በዚህ ጉባኤ ላይ ጥቁር አሜሪካውያን (ባርያ ነበሩ) ፣ የሁሉም ዘር ሴቶች እና ቀይ ህንዶች ተሳታፊ አልነበሩም። እነኝህ የህብረተሰብ አካላት በጅምላ ከውይይቱም ከውሳኔውም ውጪ ነበሩ ማለት ነው።
እንግዲህ በአቶ ሌንጮ ስሌት ከሄድን የማይናቅ ድርሻ የነበራቸው አነኝህ የህብረተሰብ አካላት ሳይሳተፉበት ወይንም ሙሉ ለሙሉ ተመክሮበት የተቀረፀ ባለመሆኑ የዛሬው የአሜሪካ ባንዲራ ተቀባይነት የለውም። ይሁንና ‘ሁላችንም’ እንደምንረዳው አሜሪካ ዛሬ የምትወከለውም ፣ መላው ዜጋ የኔ ብሎ የሚያውለበልበውም ይህንኑ ባንዲራ ነው። በነገራችሁ ላይ የአሜሪካ ባንዲራ ከዘመን ወደ ዘመን ቅርፁ እንደ ግዛቶች ብዛት እየተለዋወጠ መምጣቱን (ይዘቱ እንደተጠበቀ) መገንዘብ ተገቢ ነው።
ለመሆኑ ያኔ በ1777 እኛ የት ነበርን?
አፄ ሱሰንዮስ እና ተክለሀይማኖት 2ኛ (የአፄ ዮሐንስ 2ኛ ልጅ) መንግስታቸውን ለማጠናከር የሚዳክሩበት ዘመን መሆኑን የኢትዮጵያ ታሪክ ቀመር ያመለክታል። እንደሚመስለኝ ከግራኝ መሀመድ የጥፋት ወረራ እያገገምን ነበር። ቁምነገሩ መንግስት ነበረን ፤ ባንዲራም ነበረን። የባንዲራችን ቅርፅ ማለትም የሶስቱ ቀለማት ቅደም ተከተል መለዋወጡን አሁንም ታሪካዊ ሰነዶች ያመለክታሉ። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቅርፁን ያገኘው በንጉስ እያሱ ዘመን በ1914 ግድም ቢሆንም ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሶስቱ ቀለማት ቅንብር የታጀበ ባንዲራ ሲውለበለብ እንደነበር ይታወቃል።
በቅርቡ ከኛ ‘ቅኝ አገዛዝ’ ነፃ የወጣችው ኤርትራ አዲስ ባንዲራ ቀርፃ እያውለበለበች ነው። የራሷ መንግስት ኖሯት የማታውቅ በመሆኑ ባንዲራውም ከአዲሱ መንግስት ጋር አዲስ ነው። ይህን ባንዲራ ለመቅረፅ ኤርትራውያን (በብሔረሰብ መነፅር ስናሰላው) ትግሬው ፣ ትግረው ፣ ቢለኑ ፣ ቤጃው በብሔረሰብ ተወካይ ተጋብዘው ሀሳባቸውን እንዲገልፁ አላስፈለገም። ካንድ ‘ነፃ አውጪ’ የፖለቲካ ድርጅት ሌላ የማታውቀው ኤርትራ እንኳን ስለ ባንዲራ ስለ መሰረታዊ ፖሊሲ የምትመክርበት ስርዓት ገና ዛሬም አልዘረጋችም። መንግስት የመሰረተውም ፣ ባንዲራ ቀርፆ ያወጣውም አንድ ሻ’አቢያ ነው። ይሁንና የጫካውን ባንዲራ እና የፖለቲካ ፕሮግራም ህግ አድርጎ ሲያውጅ ሁሉም ኤርትራውያን (በአገዛዙ ያኮረፉት ጭምር) በነፃነት መንፈስ ተቀብለው እያውለበለቡት ነው።
በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የሁሉንም አፍሪካ አገሮች ታሪክ ካየን ባንዲራቸው ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጥቶ መንግስት ከመመስረት ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለ መንግስት ምስረታ ታሪክ ዝርዝር ጉዳይ ልፅፍ ስላልተነሳሁ እዚህ ላይ ይብቃኝ።
በመግቢያው ላይ ‘ሁላችንም’ የምትለውን የአቶ ሌንጮ ቃል ከጊዜ ፣ ከዘመን እና ከታሪክ አንፃር አንስተን ብናየው እኛ አገር የተካሄደው ማዕከለዊ መንግስት ምስረታ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁላችንንም የሚነካ መሆኑን ያመለክታል። ‘ሁላችንም’ የሚለው አባባል ጎሳ ፣ ብሔር/ብሔረሰብ ሳይለይ መላ ዜጎችን ለማመልከት ከሆነ ማለቴ ነው።
ያሳለፍነው ንጉሳዊ የዘውድ ፍፁማዊ አገዛዝ ለምዕተ አመታት የዘለቀ መንግስታዊ ስርዓት የሰፈነበት አገር ነው። የነገስታቱ ታሪክ ብጥብጥ ፣ አመፅ ፣ ስልጣን ሽሚያ ፣ ስልጣን ነጠቃ ተለይቶት የማያውቀውን ያህል የውጪ ወራሪ ሲመጣ ደግሞ በጋራ ተሰልፎ አገሩን ሲታደግ ቆይቷል። ይኼ የተወሰኑ ብሔረሰቦች ብቻ የተሳተፉበት ሂደት አይደለም። የነገስታቱ ታሪክ የህዝቡ ተሳትፎ ታሪክ ነው።
ህዝብ ይሁንታ ባይሰጣቸው ኖሮ እነኝህ መሪዎች ለንግስ መብቃት ፣ ስርዓታቸውንም ማቆየት ባልቻሉ ነበር። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማምጣት ተሳትፎ ያላደረገ ብሔረሰብ እንደሌለ በውጪም በውስጥም ታሪክ ተመራማሪዎች ያረጋገጡት ሀቅ ነው።
ከሶስት ዓመታት በፊት የኦሮሞ ታሪክ ፀሀፊ አቶ ታቦር ዋሚ “የውገና ድርሰቶች እና የታሪክ እውነቶች” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ባለ 663 ገፅ የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን ያዘለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። መፅሀፉ ብዙ ዋቢ ሰነዶችን እያጠቀሰ ያሳየን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በዘውድ አገዛዝ ስር ያሳለፈችው ዘመን የህዝቡን ንቁ ተሳትፎ ያካተተ መሆኑን ነው። የታሪክ አቀራረቡ ኦሮሞ ላይ ደረሰ የሚባለውን በደል ለመተረክ ያዘነበለ ቢሆንም በማይሻር የታሪክ እውነቶች አሰገዳጅነት ኦሮሞ ራሱ የማዕከላዊ ዘውድ ስርዓቱ ተቀናቃኝ እንደ ነበር የወሎ ነገስታት እነ ንግስት መስተዋት እና ወርቂትን በመጥቀስ ይተርካል። ይህን ለምሳሌ ያህል ነው ያመጣሁት እንጂ መፅሀፉ ራሱን የቻለ ግምገማ የሚጋብዝ ብዙ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።
ታዲያ አቶ ሌንጮ ‘ሁላችንም’ ሲሉ አባባሉ ይህን እና ከዚህም የሰፋ ነገር ለማመልከት የፈለጉ ይመስለኛል። ሁላችንም ተባብረን ገና ድሮ መንግስታዊ ስርዓት እንዲኖር ማድረጋችን ሊያስመሰግነን ይገባል። ከነብዙ ጉድለቱ ቢያንስ የባዕዳን ወራሪዎች ቅኝ ተገዢ አለመሆናችን ያኮራል።
ሀሳቤን ማንም ተራ ሰው ሊረዳው በሚችል መልኩ እያቀረብኩ ነው…
‘ሁላችንም’ እንደምናውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ባለ-አገር የሆነው ዛሬ አገር ተብለው ባንዲራ ከሚያውለበልቡት አገሮች ውስጥ አብላጫው አገርም ፣ ባለ ባንዲራም ባልነበሩበት ዘመን ነው። አፍሪካ “ጨለማው አህጉር” ይባል የነበረበት ዘመን…
ይሁንና በዚያን ፣ እኛ ባለ ባንዲራ መሆን በበቃንበት ዘመን የሁላችንም ድምፅ የሚወከልበት ዘመናዊ መልክ ያለው በምርጫ ወይንም በውክልና የሚመራ መንግስታዊ መዋቅር አልነበረም። የዘመናዊ አስተዳደር ጭላንጭል መፈንጠቅ የጀመረበት ዘመን ነበር። ከፊል የአገራችን ህዝብ እንደ ዛሬው ሁሉ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተውጦ ውሱን ከሆነው ቄየው በስተቀር ከአድማስ ባሻገር በውጪው አለም ምን እየተካሄደ መሆኑን አያውቅም። ጣጣውን ሁሉ ነገስታቱ ላይ ጥሎ ዕለት ህይወቱን ሲከውን የቆየ ህዝብ።
ለገዢዎች በዚያን ዘመን አሳሳቢው ጥያቄ ዳር ድንበርን ሳያስደፍሩ ፣ ጉልበተኛ በየመንደሩ እየተነሳ ደካማውን ሳያማርር ፣ ህዝብ ሰላም ወጥቶ ሰላም እንዲገባ… የመሳሰሉት መሰረታዊ ነገሮች በመንግስታዊ ተቋም ዳኝነት ስር ስርአት እንዲይዙ ማድረግ ነበር። ጠንካራ መንግስት መገንባት – እንደ ወታደር ፣ ፖሊስ (አራዳ ዘበኛ) ፣ ፍርድ ቤት ፣ ፖስታ ቤት… መዘርጋት።
ሌላው አለም ከደረሰበት የስልጣኔ እርከን ባንደርስ እንኳ በሳይንስ እና ምርምር የቀደመው ህዝብ የፈበረከውን ቁሳቁስ ለመጠቀም ሙከራ አድርገዋል። ባቡር ፣ ስልክ ፣ መብራት ፣ መኪና ፣ ጋዜጣ… (ሞባይል?) እኛ አገር አልተፈለሰፉም። ቀደምት ነገስታት ሆኑ የዛሬ ገዢዎቻችን ግን እነኝህን ቴክኖሎጂ ወለድ ለኑሮ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ለህዝባቸው ለማስተዋወቅ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ተወካይ ሰብስበው እየመከሩ እና ውሳኔ እያሳለፉ ሳይሆን እንደ ጊዜው እና ዘመኑ አጠገባቸው ካሉ ሹማምንት ጋር በመምከር አጋጣሚው በፈቀደ ለመጠቀም ተችሏል። ጊዜው ሲፈቅድ ወይም ሲያስገድድ ፓርላማ መስርተው አገራዊ ጉዳዮች በምክር ቤት እንዲብላሉ ማድረግ ተጀምሯል። ለዘመናዊ አስተዳደር መዋቅር የበቃነው በ20ኛው ክፍል ዘመን አጋማሽ ገደማ መሆኑን ሳንዘነጋ።
በጨለማው ዘመን አውሮፓውያን አገር እየወረሩ በሌላው ምድር ላይ ባንዲራቸውን ሲተክሉ ያንን መክቶ ልክ እንደነሱ የራሱን ባንዲራ በራሱ ግዛት ማውለብለብ የቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ዳር ድንበርህ የተከበረ ሉአላዊ ህዝብ መሆንህን ብሎም ድንበርህ የት ላይ መሆኑን ለውጪ ወራሪም ሆነ ለዜጋህ በይፋ ለማሳየት በጊዜው የነበረው ብቸኛ ምልክት ባንዲራ ነበር።
ባንዲራ ደሙን አፍስሶ ባስከበረው ዳር ድንበር ላይ ለምስክርነት የቆመ የህዝብ ህያው መታሰቢያ ነው።
ባንዲራህን ተክለህ ከዚህ ወዲህ ማለፍ አገሬን ፣ ክብሬን ፣ ነፃነቴን እንደመድፈር ነው የሚል መልዕክት አለው። ባንዲራውን ረግጦ ድንበር የጣሰ ጠላት የሚመከተው በዜጎች ደም ነው። ደሙን አፍስሶ እየወደቀ ባንዲራውን መልሶ ያቆማል። ይኼ አጠቃላይ ግንዛቤ ነው – የትምክህተኛ ወይንም የጠባብነት ዝባዝንኬ አይደለም። ባንዲራ አገራዊ ፋይዳ ፣ አገራዊ ማንነት ትርጉም አለው።
አገር ሊቀማ የመጣ ጠላት የመጀመሪያ የጥቃት ኢላማው ባንዲራን መርገጥ ነው ፣ በባዕድ ባንዲራ መተካት ነው። መልሶ በማጥቃት ዳርድንበሩን በደሙ የሚያስከብረው ዜጋም ድሉን ሲያበስር መጀመሪያ የሚያደርገው ባንዲራውን ከድሉ ማማ ላይ መትከል ነው። ስለ ባንዲራ ጠለቅ ብለን እንመርምር ከተባለ ብዙ ማለት ይቻላል። ዋናው ቁምነገር ግን ባንዲራ በአዝጋሚው የህብረተሰብ ታሪክ ጋር እየተንከባለለ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የማንነት መግለጫ ቅርስ ነው።
አፍሪካን ለመቀራመት እንደ አራስ ነብር እየተወነጨፈ የመጣውን ወራሪ በማሳፈር ለአኩሪ ተጋድሎ የተሰለፈ ህዝብ ድሉን የሚያበስርበት አንድ ባንዲራ ማውለብለቡ ብሎም ያንን ታሪካዊ ባንዲራ ለመጪው ትውልድ ኩራት ማቆየቱ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ? ኢትዮጵያ ብቸኛዋ አፍሪካዊት የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሆና ወንበር ያገኘችው ነፃ መንግስት ያላት በመሆኗ ነው። ባንዲራዋን እያውለበለበች ከሌሎች ነፃ አገሮች ጎን ጉብ ብላ ተቀምጣለች። ይህን ታሪካዊ ባንዲራ ለመለወጥ መነሳት ያንን የደመቀ ታሪካችንን ጭምር እንደ መካድ አይቆጠርም?
በመሰረቱ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ዘመናዊ ቅርፅ እየያዘ በመጣባቸው ታሪካዊ ዘመናት እንኳንስ ስለባንዲራ ስለምንም ጉዳይ ተሰብስበን ያፀደቅደነው ነገር አለመኖሩ አቶ ሌንጮም ሆኑ መሰል አቋም የሚያራምዱ ይጠፋቸዋል ብዬ አልገምትም። ይህ ትውልድ ከመፈጠሩ በፊት የነበሩት ዜጎች በነገስታት መሪዎቻቸው ጥላ ስር በተመሰቃቀለ ትግል ውስጥ አልፈው የአገር ባለቤትነት እንዲሰፍን ማድረጋቸው ግን የሚካድ አይደለም።
ባንዲራ ሉአላዊነቱ የተረጋገጠ አገር መኖሩን ማረጋገጫ አንዱ ምልክት ነው። ድንበርህ ላይ ትተክለዋለህ ፣ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ታውለበልበዋለህ ፤ አገርህን ለመጠበቅ አባቶችህ እና አንተ የከፈልከውን ክቡር ዋጋ በምታስብበት ጊዜ ሁሉ ከፍ አድርገህ ትሰቅለዋለህ። ተራራ ተቆጣጥሮ ጠላት ድል መሆኑን የምታበስረው ባንዲራህን ተክለህ ነው። ባንዲራ ከሌለህ ግን ድል የተጎናፀፍክበት መሬት ሳይቀር ዘላን ያለፈበት አውድማ ይመስላል…
ባንዲራ ተዋርዶ ለማን ይበጃል።
ባንዲራ ይናገራል – ለአገር ደህንነት ሲባል የፈሰሰውን ደም የተከሰከሰውን አጥንት ይመሰክራል። በህልውና ያለፉትን ውጣ ውረድ ቆጥሮ ዘመናት ይናገራል ፤ ወገን ሲተክለው ጠላት ሲረግጠው ወድቆ መነሳቱን ፤ ክብርህ ሲዋረድ አብሮ መዋረዱን ይነግረሀል። ባንዲራ የጠለቀ አንደምታ ያዘለ የአገር ቤዛ ነው።
የሱማሊ ሚሊሻዎች ባንዲራቸውን ኦሮሚያ ክልል ተከሉ የሚል ነገር ሰሞኑን ያነበብኩ መሰለኝ።
ይህን ጉድ አቶ ሌንጮም ሳይሰሙ አይቀርም። ብሔራዊ ባንዲራውን የተቀማ ዜጋ በየጎጡ የጦር አበጋዞች በፈጠሩት ባንዲራ ስር ይራኮታል። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረጓት ብሔረሰቦቿ የተሳሰሩበት ፣ የተዋወቁበት ፣ የተከባበሩበት ድር እና ማግ ተበጣጥሶ ፣ ደብዝዞ ይልቁንም ወደ ጨለማው ክፍለ ዘመን እንዲመለሱ ተገደዋል። በህግ ጥላ ስር ሳይሆን የጦር አበጋዞች በፈጠሩት ማንነት ስር እንዲጨፋጨፍ እየተበረታታ ነው።
ወለጋ ነዋሪ የሆነው ኦሮሞ ቦረና ካለው ኦሮሞ ጋር የተሳሰረው አንድ ኦሮምኛ ቋንቋ ስለሚናገር ሳይሆን አገራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነትን) ስለሚጋራ ነው። ይኼ ትንሽ ሊያነጋግር ይችላል። በቀላሉ ለማስረዳት ከተፈለገ – የቦረና ኦሮሞ በንግድ ፣ በአስተዳደር ፣ ባኗኗር ወይንም በመልክአ ምድር ከወለጋ ኦሮሞ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አልነበረም። ሰፋ አድርገን ካየነው ይኼ ሁሉንም አካባቢዎች ይመለከታል።
ሰሜን ምስራቅ ኬንያ ኢትዮጵያን በሚያዋስኑ ወረዳዎች ኦሮምፋ ተናጋሪ ዜጎቿ አሉ። ኬንያውያን ናቸው። እንዳጋጣሚ አካባቢውን ለመጎብኘት ፣ ከህዝቡም ጋር የመተዋወቅ መልካም ዕድል አግኝቻለሁ። እነዚህ ኦሮምፋ ተናጋሪ ኬንያውያን ራሳቸውን ቦረና ፣ ገሪ እና ጋርባ ብለው ይጠራሉ። በቋንቋ ጭምር በብዙ ባህላዊ ጉዳዮች ዙርያ ይመሳሰላሉ – ግን በመካከላቸው እንኳ ሰላም የላቸውም። ያስተሳሰራቸው አንድ በጎ ነገር ቢኖር ኬንያዊነታቸው ብቻ ነው።
እዚህ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር ካለ እንግሊዝኛ ፊደል ለኦሮምፋ ቋንቋ (ቁቤ) ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በኬንያ ኦሮሞዎች መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን።
የኬንያ ብሔራዊ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ኪስዋሂሊ እና አንግሊዝኛ ናቸው። ኬንያ ከ42 አይነት በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰቦች ያላት ትንሽ አገር ናት። ማናቸውም ኬንያዊ ብሔረሰብ የራሱን ቋንቋ በፅሁፍ መጠቀም ቢፈልግ ከእንግሊዝኛ ፊደል ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም። እናም ቁቤ በወያኔ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈለሰፈ አድርገው የሚነግሩን (የኦሮሞ ሊሂቃን) የኬንያ ኦሮሞዎችን ድካም እንደ መመንተፍ ቢቆጠርባቸው የሚቆጡ አይመሰለኝም።
ቁቤ የኦፒዲኦ ወይንም የኦነግ ስራ ውጤት አይደለም። እነኝህ ድርጅቶች ከመመስረታቸው አያሌ ዘመናት በፊት የኬንያ ኦሮሞ አገልግሎት ላይ አውሎታል። መፅሐፍ ቅዱስ ሳይቀር በቁቤ ተተርጉሞ ከብዙ አሰርት ዓመታት በላይ የኬንያ ኦሮሞ ህዝበ ክርስቲያን ጥቅም ላይ አውሎታል።
በመሰረቱ ኦሮምፋ ተናጋሪ የሆነውን ህዝብ ባንድ አገራዊ ጥላ ስር የገዛ የኦሮሞ ንጉስ ኖሮ አያወቅም። ወደ ዝርዝር እንግባ ከተባለ ባሌ ከሸዋ ፣ አርሲ ከከፋ ኦሮሞዎች ጋር የተሳሰሩበት ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ወይንም ስነልቡናዊ መሰረት አልነበረም። ተበታትኖ ህይወቱን በተለያየ ቦታ የገነባው ኦሮሞ በራሱ ውሱን ክልል የጎሳ መሪው (እንደ አባገዳ) በሚሰጠው ባህላዊ አመራር ስር ሲኖር የቆየ ነው። ይህን የምለው እኔም ተወልጄ ፣ አፌን ፈትቼ ያደኩት በኦሮሞ ባህል በመሆኑ ከራሴ ህይወት በመነሳት ነው።
በትናንሽ ጎጥ ተበታትኖ አንዳንዴም እርስ በርሱ ከብት ሲዘራረፍ የነበረውን ኦሮሞ ወደ አንድነት የሰበሰበው ፤ ደህንነቱን ያረጋገጠለትም ኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ነው። በስልጣን ተዋረድ እያንዳንዱ አካባቢ ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ መንግስት እንዲሆን ፣ ጥቃት ቢደርስበት ፣ ፍትህ ቢጎድልበት አቤት የሚልበት ሸንጎ ያገኘው በኢትዮጵያዊነቱ ነው። አካባቢው ከተማ ቢቆረቆር ፣ ትምህርት ተቋም ቢከፈት ፣ ሀኪም ቤት ቢገነባ… ባለቤትነቱ ያንድ ጎሳ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ቤት መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያዊነት ነው። አንድ ዩንቨርሲቲ ቢኖር ከአራቱም ማዕዘን የመጡ ዜጎች ጥበብ የሚቀስሙበት ማዕከል የሆነውም በኢትዮጵያዊነት የተነሳ ነው።
ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰው ኦሮሞ ለመንደር ማንነት ሳይሆን በጋራ ለኢትዮጵያዊነቱ ተሰለፈ ፣ ሞቶ ዳርድንበሩን ማስከበር አገራዊ ማንነቱን ማስረፅ ተልዕኮውን ተወጣ። አንድ ባንዲራ ባይኖረው ኖሮ ከተለያየ አቅጣጫ የተቃጣበትን የባዕድ ጥቃት አንድ ሆኖ መመከት ባልቻለ ነበር። ያንን አገራዊ ማንነት መግፈፍ ለኦሮሞም ሆነ ለየትኛውም ብሔረሰብ ህልውና የሚበጅ አይደለም። እዚህ ላይ ዛሬ አማራ ነን የሚሉ አዳዲስ የጎጥ አበጋዞች እየተነሱ መሆኑን ያጤኗል። የጎጥ ፖለቲካ ገበያው ደርቷል።
የሶማሊ ኢትዮጵያውያን በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን መንደሮች ወረራ ፈፅመው ‘ባንዲራቸውን’ ተከሉ የሚለው ዜና አገራዊ ማንነትን ለመፋቅ የተደረገው ሴራ ውጤት ነው። የጎሳ ግጭት በየትኛውም ሁዋላ ቀር ህብርተሰብ ውስጥ ሊከሰት ይችላል (ከብት ዘራፊ ባንዲራ የለውም) – በድል አድራጊነት የጦር አበጋዞችን ባንዲራ መትከል ግን ዛሬ እንደዋዛ በሚብጠለጠለው ታሪካዊ ባንዲራችን ላይ ተቀነባብሮ የተከፈተ ግልፅ ጦርነት አካል መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
አገራዊ ባንዲራችንን አርክሰን የብሔረሰብ ክብራችንን ማስጠበቅ አይቻልም።
አቶ ሌንጮ እንዳሉት ጉዳዩን በሰከነ አይምሮ ማጤን ብልህነት ነው። ራሳችንን ከታሪካዊ ሀቅ ጋራ ማላተም አይበጀንም።
ያንዲት አገር ዜጎችን በዘር ሸንሽኖ በበታች እና በላይ መፈረጅ ብሎም ከዚህ ፖሊሲ በመነጨ ኢኮኖሚውን ፣ መገናኛ አውታሩን ፣ መከላከያውን ፣ ቁልፍ የመንግሰት ስልጣን ብሎም አጠቃላይ የፖለቲካ ህይወት ከዚያ ‘ወርቅ’ ብሎ ከሸነገለው ዘር ተመርጦ በተመለመለ ሀይል ሙሉ ቁጥጥር ስር እንዲውል ማረጋገጥ የለየለት የፋሺዝም መለያ ባህሪ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም። በተጨማሪ በመገናኛ አውታሮች ደጋግሞ መዋሸት (ደጋግሞ መዋሸት ውነት ይሆናል ከሚል እምነት) ፤ እመቃ እና ማስፈራራት ፣ እኔ ከምለው ሌላ ውነት የለም ማለት ፣ የፈጠራ ውንጀላዎችን እንደ ጭብጥ አድርጎ በ’ዶክመንተሪ’ ስልት ማቅረብ እና መስበክ… ከፋሺዝም ባህሪያት የተወረሱ ናቸው። ፋሺዝም መንግስታዊ ተጠያቂነት እና ግልፅነት የሌለበት ፣ ህግ አውጭ ፣ ተርጓሚ እና አስፈፃሚ አካላት የተደበላለቁበት ፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ህግ የሆኑበት የፖለቲካ ስርዓት ነው።
በዘር ልዩነት የተነሳ እንዲሁም ተነጥሎ በዘር መደራጀት ፣ የሌላውን ዘር ነጥሎ ማጥቃት እና ተነጣጥሎ መባላት የመንግስት ዋና መርህ ሆኖ እየተሰራበት ያለ አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት።
የኦሮሞ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን መንደሮች በሱማሌ ኢትዮጵያውያን ወራሪዎች እጅ ፍጅት ተፈፀመ፤ ሱማሊዎቹ ባንዲራቸውን በኦሮሞ መንደሮች ተከሉ የሚለው ጉዳይ ካንቀላፋንበት ጥልቅ መኝታ የሚያባንን ፣ የሚያስበረግግ ደወል ነው። ለያንዳንዱ ዜጋ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ በወያኔ የተሰነቀው ምን እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን አጋጣሚ ነው።
ላለፉት ሀያ አምስት ዓመታት የአንድ ህወሀት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እንዴት በአይናችን ስር እያበጠ እንደመጣ ለመመስከር የበቃን ይመስለኛል። ዛሬ በደረስንበት ደረጃ ማንም ኢትዮጵያዊ በነፃነት መናገር መፃፉ ይቅርና ከማን ጋር በስልክ እንደተነጋገረ ፣ ከማን ጋር ቡና እንደጠጣ ፣ ከማን ጋር ኢሜይል እንደተፃፃፈ ፣ የትኛውን ራዲዮ ጣቢያ እንዳዳመጠ … ክትትል ይደረግበታል ፣ እንደ ወንጀል ይጠየቅበታል ብሎም ላልተወሰነ ግዜ እንዲታሰር ይፈረድበታል።
ወያኔ ትግራይን ለመገንጠል ሲል የተኮሰው ጥይት እና ያፈሰሰው ደም በሚያሳፍር ደረጃ ዋጋ ቢስ መሆኑን ለመመስከር የበቃንበት ዘመን ላይ ብንሆንም ቅዠቱ ግን አሁንም እንዳወከን አለ – በዘር ተፈርጀን መፈናቀል ፣ ከስራ መባረር ፣ መታሰር ፣ ስደት ፣ ሞት… የግንጠላ ፣ የጥላቻ እና የጥፋት ፖሊሲ መንሰራፋት። አፈና ፣ ንቅዘት ፣ ብኩንነት ከዘር መድልዎ ጋር ቶቆራኝተው የእለት ኑሯችንን እያናወጡት መሆኑን ስናጤን በሰብአዊነት መለኪያ ምን ያህል ቁልቁል በዘቀጠ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ያስገነዝባል።
ስለዚህ ሁሉም ዜጋ አንገቱ ላይ በተጋደመ ሰይፍ ስር እየተነፈሰ ያለበት ዘመን ላይ ነን ማለቱ ይቀላል – ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየ መጠን አፋናውን ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። መፈናፈኛ እያሳጣ ዜጎችን እንዳሻው እያሰረ – እየፈታ ፤ የገጠር መንደሮችን ብቻ ሳይሆን በርዕሰ ከተማዋ ወታደሮችን እያዘመተ ህፃናት እና እናቶችን እያስበረገገ እና በተኩስ እና ግድያ እያሸበረ አገዛዙን መቀጠሉ የሚያጠራጥር አይመስለኝም።
ኢትዮጵያ ነፃ የምትሆነው ደግሞ ማንኛውም ዜጋ በህግ ፊት እኩል መሆኑ ዋስትና ሲያገኝ ብቻ ነው። አንደኛ ደረጃ ዜጋ ፣ ወርቅ ዜጋ ፣ ነሀስ ዜጋ እየተባለ በብሔረሰብ ምሽግ ሌላውን ህዝብ ለማዋረድ እና ለመቀማት መሰለፍ የወያኔ ተግባር ብቻ መሆኑን ማስመስከር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርቶ አገራችን ለወያኔ ጥፋት ተልዕኮ ሰለባ ከሆነች እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ተጠያቂ እንሆናለን።
‘ሁላችንም’ የወያኔ አገዛዝ ለአገር ዘላቂ ጥቅም አይበጅም እንላለን፤ ጎጠኝነት ብሔራዊ ጥቅም ይፃረራል ፣ አገራዊ የባለቤትነት ስሜት ይሸረሽራል ፣ ህዝብ ይከፋፍላል ፣ ያዳክማል እንላለን። በፅኑ ብሔራዊ ስሜት ላይ ያልተገነባ አገር – አገሩም አገር ህዝቡም የባለቤትነት ስሜት ያለው ህዝብ አይሆንም እንላለን። የተከፋፈለ እና የተዳከመ ህዝብ በቀላሉ ለጠላት ጥቃት ይጋለጣል ብሎም ለስግብግብ አምባገነን ገዢዎች ሰለባ ይሆናል እየተባለ ሲነገር ሲዘከር እዚህ ደርሰናል።
ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከምንጊዜውም በላይ በማንነቱ ኮርቶ ፣ የቆመበትን ምድር ቆንጥጦ ከጠላት ጋር የሚፋለምበት ዘመን ላይ የደረስን ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ጠላት ከውጪም ከውስጥም ተነስቶ ግዝገዛውን ማቀላጠፍ ከተነሳ ከራርሟል። እንደ አመጣጡ መክቶ እና አሳፍሮ ታሪካዊ ማንነታችንን ለመጪው ትውልድ ማውረስ ደግሞ ይደር የማይባል ግዴታችን ነው።
ቁስለኛ ፖለቲካችን ግን የዝንብ መጫወቻ አድርጎናል።
ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ አንድ ሉአላዊ አገር የሚታወቅበት የሚገለፅበት መለያ መታወቂያ አምድ ነው። ሁሉም ዜጎች ራሳቸውን ከብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ጋር የሚያስተሳስሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ አለ። ባንዲራችን የማይደለዝ የማይሰረዝ ነው ስንል ባንዲራውን ተሸክመው ያገራችንን ነፃነት ፣ አንዲት አትዮጵያ ብለው ዳር ድንበር እና ክብር ሲጠብቁ ፣ ሲያስከብሩ ለነበሩ ጀግኖች ያለንን ክብር ማረጋገጣችን ነው።
እኔ ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በስተጀርባ የሚታየኝ ባልቻ አባነብሶ መድፉን አነጣጥሮ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ሰፈር ሲያነውጥ ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ እምቢኝ ለአገሬ ብሎ ማይጨው ላይ በመርዝ ጪስ የተጠበሰው ዜጋ ነው – ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ የዚያድ ባሬን ወረራ ለመመከት ሳያሰልስ ቆርጦ የተመመው ከሁሉም የአገሪቱ ክልል የፈለቀው ጀግና ሰራዊት ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ መሬት ላራሹ ብሎ ፍትሀዊ አስተዳደር እንዲሰፍን የታገለው ትውልድ ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ የዕውቀት ብልጭታን ለመፈንጠቅ በመላ ገጠር ኢትዮጵያ የዘመተው የእድገት በህብረት ዘማች ነው… እኔ ከባንዲራው በስተጀርባ ደርግም አፄውም አይታዩኝም – አበበ ቢቂላ በሉት የጥቁር አንበሳው ጦር መሪ ኮለኔል በላይ ገብረአብ ወይንም በላይነህ ዴንሳሞ ባንዲራችንን በኩራት ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ የነበረው የአንድነታችን እና የነፃነት ክብራችን መግለጫ ስለሆነ ብቻ ነው።
ከብሔራዊ ባንዲራ በስተጀርባ ያለው ህዝብ እና አገር ናቸው። ባንዲራ ለድሀው ሆነ ሀብታሙ ፣ ለገዢው ሆነ ተገዢው ፣ ለገበሬው ሆነ ወዛደሩ ፣ ለተማረው ሆነ ለማይሙ ፣ ጠግቦ ለሚያድረው ሆነ ለተራበው ሳይቀር ለሁሉም እኩል ትርጉም ሊኖረው ይገባል። አለበለዚያ ካንድ ያገሪቱ ጫፍ የተነሳ የጦር አበጋዝ እሱ የመሰለውን ጨርቅ ጠቃቅሞ በብረት ያስገበረውን ሁሉ ይሔ ባንዲራህ ነው ቢል ውሎ አድሮ የሀይል ሚዛን ያጋደለ ጊዜ ውጤቱ አያምርም…