October 24, 2016
40 mins read

ኢትዮጵያን ከአደጋ ለመታደግ አስቸኳይ መፍትሔ ለመፈለግና ለሰላማዊ ሽግግር የሸንጎ ራእይ

ጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አገራችን ከፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተማግዳ የቆየችበት ወቅት ገደቡን አልፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለመውለድ በቅቷል። በሙስሊም እምነት ተከታዮች፣ በኦሮሞ ክልል፣ በአማራው ክልል በጎንደርና ጎጃም የተቀሰቀሰውና የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የዚሁ ነጸብራቆች ናቸው።

የህወሃት መራሹ የኢሕአዴግ አገዛዝ እንዳለፈው ሁሉ ያረጀ ያፈጀ የ25 ዓመት ስልቱን፣ ሃይልና ጭካኔን በመጠቀም ሕዝባዊ እምቢተኝነቱንና አመጹን ለማፈን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ደረጃ የሞት የሽረት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የሕዝቡ ትግል ግን እየከረረና እየተጠናከረ እንጂ እየተዳከመ አልመጣም። ይህ አዲስ ክስተትና አዲስ የፖለቲካ አካሄድ መጣኝ የሆነ ምላሽን ይጠይቃል። ይህንንም አዲስ አካሄድና አቅጣጫን ለመንደፍ ሁሉም የሚሳተፍበት የፖለቲካ ሂደት መወጠን ከምን ጊዜውም በላይ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚያ ውጭ ግን የህዝብን ጥያቄ በተለመደ መልክ አፍኖ ለመቀጠል መሞከር የበለጠ ትርምስና አቅጣጫውን መገመት ወደሚያስቸግር ቀውስ የሚወስድ ይሆናል።

በሚያሳዝን ሁኔታ አምባገነኖቹ መሪዎች ከተጠናወታቸው የክህደትና የጨለምተኝነት ባህሪ የተነሳ ያለውን ዕውነታ ማገንዘብና መረዳት ተስኗቸው የሕዝብን ተቃውሞና የለውጥ ፍላጎት በአግባቡ ለማስተናደግ የፖለቲካ ፍላጎትም ሆነ ብቃት አይታይባቸውም። ይህንን ማየት ቢችሉ ኖሮ ያለፉበትን መንገድና የሕዝቡን ጥያቄ ባጤኑና በጎ ምላሽም በሰጡ ነበር።

የ2005 ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ የተከሰተው እልቂትና ጭፍጨፋ በሽህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት፣ ለእስራትና ለስደት በመዳረግ የልዩነቱ ደረጃና ጥልቀት ጎልቶ የታየበት ሲሆን፣ መንግሥት ተብየው ቡድን ግን ለሥልጣኑ ሟችና ለሕዝብ ፍላጎት ግደቢስ መሆኑን በወሰደው እርምጃና በመረጠው መንገድ በገሃድ አረጋግጧል። የተከተለውንም አጥፊ አቅጣጫ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎበት በተወሰነም ደረጃ ቢሆን የተቃዋሚ ድርጅቶችን ለማሽመድመድ ችሏል። አሁንም የሚጓዝበት መንገድ ከዚያ ቢብስ እንጂ የተለዬ አይደለም። የነጻ ሚዲያ ዘርፎችን አፍኗል፣ ነጻ የሆኑ የሙያና የመብት ተከራካሪ ድርጅቶችን ዘግቷል፣ “የጸረ ሽብርተኝነት” የሚል ሕግ አውጥቶም ከሱ ጋር ያልተሰለፉትንና የሚቃወሙትን ሁሉ አጥቅቶበታል። ይህም አድራጎቱ ሲሰብክ የነበረውን የመድብለ ፓርቲ ልፈፋ ባዶነትና የኢዴሞክራሲያዊነት ባህሪውን አጋልጧል። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስምና ልማታዊ መንግሥት በሚል ካባ ታጅሎ የሚያጭበረብር ብቸኛ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን በገሃድ አሳይቷል። በዚህም አካሄዱ የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በርን በመዝጋቱ አሁን ወደምንገኝበት ሕዝባዊ ሰላማዊና ትጥቃዊ እንቅስቃሴዎች በየቦታው የተስፋፋበት ወቅት ላይ ተደርሷል። አገዛዙ በበኩሉ ይህንን ሕዝባዊ ተቃውሞና የለውጥ ፍለጋ ትግል ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል። ውጤቱ ግን ይበልጥ ስርዓቱን ከድጡ ወደማጡ ከመሄድ አላዳነውም።

የኢትዮጵያን ህዝብ ዛሬ ለለውጥ እንዲነሳ ያደረጉ አያሌ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና የማህበራዊ ምክንያቶች ቢኖሩም የሕዝቡን ቁጣና እምቢተኝነት ከቀሰቀሱት ውስጥ ዋናዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፥

  1. ላለፉት 25 ዓመቶች በተከታታይ በአገዛዙ የተከናወነው፣ ጭቆና፣ አፈናና ግድያ፣
  2. የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበራቸው፣
  3. ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት ቦታ መፈናቀሉ፣ ንብረትና መሬቱን መነጠቁ፣ ከሥራ ምድቡ ያላግባብ መባረሩ፣ እንደ ዜጋ ለደህንነቱ ዋስትና ማጣቱ፣ ሕገ አልባ ሥርዓት መስፈኑ፣
  4. ሕዝብ በብሄሩ በጎሳውና በቋንቋው መሠረት እየተነጠለ ለጥቃት መዳረጉ፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የጥላቻና ቅራኔ ቅስቀሳ አገዛዙ በኩል ሆን ተብሎ የፖለቲካ ስልት ተደርጎ መወሰዱ፣
  5. በገጠርና በከተማ ለመኖር የሚያስችሉ የሥራ ዕድሎችና መስኮች እንዲሁም ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች በቅድሚያ ለገዢው ፓርቲ አባላትና ለደጋፊዎቹ መሰጠቱ፣ ሌላውን በማግለል የዝቅተኝነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲዳብር መደረጉ፤
  6. ተቃዋሚውን በጎሳና በእምነቱ እየመነዘሩ ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ ጠባብ፣ አክራሪ፣ ትምክህተኛ፣ አሸባሪ…እያሉ መመደብና ያለማቋረጥ ጥቃት መፈጸሙ፤
  7. በተለያዩ ቦታዎች ያለህዝብ ፈቃድ ለፖለቲካ ተጠቃሚነትና ተስፋፊነት የሚደረግ ያስተዳደር ክልሎች ሽግሽግ ለምሳሌ(በወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ ኮንሶ ወዘተ.) ከፍተኛ ግጭትና ተቃውሞ ማስከተሉ፤

አሁን በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ ለሃያ አምስት ዓመት ሳያሰልስ የተካሄደው ተቃዋሚን ደምስሶ የማጥፋት ስልት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ሕዝቡ ተደጋግፎ በሙሉ ልብ የሚያካሂደው ትግል ማስረጃ ነው። ይህ ክልል፣ ዕድሜ፣ ጎሳና ሃይማኖት ያለየው ሕዝባዊ ትግል ያነጣጠረው የሥርዓቱ ዋልታ በሆነው ህወሓትና የሱ ኮረጆ በሆነው ኢሕአዴግ ላይ ነው። ሥርዓቱ የእኔ ናቸው ብሎ ይተማመንባቸው የነበረው ተቋማት ሳይቀሩ አሁን ተቃውሟቸውን በግልጽ እያሰሙ መጥተዋል። ቀን በቀን አቅሙ እየዛለ ሥልጣንም ከእጁ እያፈተለከ መውጣቱን የተገነዘበው የገዢ ቡድን የሞት የሽረት የመጨረሻውን ነብስ አድን እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል፤ ይህም አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ማወጅ ነው። ይህ እርምጃ በአገሪቱ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታል። ሁሉም እንደሚያሰታውሰው ተመሳሳይ አዋጅም የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት የ1997 ዓመት ምርጫ ተከትሎ አሳሳቢ ቀውስ ላይ በነበረበት ጊዜ አውጆ ነበር። በተቃዋሚው ጥንካሬ ማጣትና የእርስ በርስ ሽኩቻ ሕዝብ የሚሻው ለውጥ ሳይገኝ አገዛዙ እንደገና ሊያንሰራራ ችሏል። አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ተቃዋሚው የሕዝቡን ትግል ተከትሎ፣ ጥያቄውንም አዳምጦ፣ በይበልጥም አገራችን ያለችበትን አደገኛ ወቅት ተገንዝቦ የአገርን አንድነት የሚያስከብርና ለሚፈለገው ለውጥ የሚያበቃ የትግል አቅጣጫ መንደፍና የትግሉ አካል መሆን አለበት። በውሃ ቀጠነ ተለያይቶ ወይም ለሥልጣን ጉጉት ተነጣጥሎ መጓዙ በአገራችንና በሕዝቡ ላይ መቅሰፍት እንዲወርድ ወይም ያለው የተጠላ አገዛዝ እድሜ እንዲራዘም እንደመፍቀድ ይቆጠራል።

በታህሳስ 2008 ዓ.ም.(ኖቬምበር 2015) በኦሮሞ ሕዝብ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ አማራው ክልል ተሻግሮ አሁን በመልክና በይዘት የተለዬ አደረጃጀት የያዘ፣ ካለፈው የተሻለ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ትግል ይበልጥ የተጠናከረና ለሚፈለገውም ድል እንዲበቃ ለማድረግ ብሔራዊ አቀነጃጀትና ራዕይ ያለው አመራር ያስፈልገዋል።

የአሁኑን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ካለፈው የተለየ የሚያደርገው በከፊል በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፤

  1. ያለፉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በዋና ዋና ከተማዎች በተለይም በአዲስ አበባ ያተኮረና የተካሄደ ነበር፤ የአሁኑ ግን የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፣ የገጠር፣ ከተሞችና ወረዳዎችን ያጠቃለለ ነው።
  2. ያለፉት ትግሎች በዋናነት ከላይ ወደታች በፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያ የተካሄደ ሲሆን ገዢው ቡድን መሪዎቹን ነጥሎ በመምታት ለማዳከም የቻለ ነበር፤ የአሁኑ ግን ብዙሃኑን ሕዝብ ከታች ወደ ላይ የቀሰቀሰና ያሳተፈ በመሆኑ ለማፈንና ለመቆጣጠር ቀላል አልሆነም፣
  3. ባለፈው ጊዜ ከታየው ሁሉ በተለየ ሁኔታ አሁኑ ህዝቡ ይዟቸው የተነሳው ጥያቄዎች በመሬቱ ላይ የመኖርና ያለመኖር፣ መሰረታዊ ማንነት፣ ታሪክና የእለት ተለት ህይወት ጋር እጅግ የተቆራኙ በመሆናቸው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘት የህይወት መስዋእትነትም ቢሆን እየከፈለ እስከመታገል ቆርጦ እንዲነሳ አድርጎታል።
  4. ባለፈው አገዛዙ እንደ አንድ ማእከል በመንቀሳቀስ ሳይከፋፈል በሙሉ ልብ ጠንካራ ሆኖ የታየበት ወቅት ነበር፣ አሁን ግን የአገዛዙ ስርዓት በውስጡ ክፍተት ያለበት፣ አንድነቱን ያጣበትና የተጋለጠበት ወቅት ነው።
  5. ባለፈው ጊዜ ስርዓቱ ህዝብን ሃይማኖትን፣ ብሄርንና ጎሳን፣ የመለያያ ስልት ያደረገበትና የተጠቀመበት ነበር፤ አሁን ግን ሕዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመቆም አገዛዙን የጋራ ጠላት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝበት፤ የኦርቶዶክስ አባቶች ጭምር ድምጻቸውን ለማሰማት ደፍረው የተነሱበት ጊዜ ነው።
  6. አሁን የፍርሃት ድባብ ተገፎ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ለመታገል የደፈረበት ወቅት ነው።
  7. በቅርቡ በኢሬቻ ሕዝባዊ በዓል ላይ የተፈጸመው የጭፍጨፋ ወንጀል ሥርዓቱን በውስጥና በውጭ ይበልጥ አጋልጦታል። ይደግፉት የነበሩትም አንዳንድ መንግሥታት ጥያቄ እያነሱበት ነው። የጀርመን፣ የካናዳ፣ የስዊድን፣ የአውሮፓ ህብረት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የሕዝቡን ትግል ጥንካሬና የሥርዓቱን እየተዳከመ መሄድ ያበስራሉ። ህዝብም በስርአቱ ላይ እምነቱ ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠና በህወሓት/ኢህአዴግ ስር ለመገዛት በፍጹም እንደማይሻ እያሳየ ነው። ሆኖም ግን ሥርዓቱ አሁንም የክህደት፣ የማጭበርበር፣ የሰለቸና የተጋለጠ ፕሮፓጋንዳውን በማስተጋባት፣ ለለውጥም እንደተነሳ በማስመሰል የሕዝቡን የትግል ስሜት ለማኮላሸትና ትጥቅ ለማስፈታት እላይ ታች እያለ ይገኛል።

ህወሀት መራሹ አገዛዝ ከዚህ ወዲያ እንደተለመደው ለመቀጠል እንደማይችል ተረድቶ ለመሰረታዊ ለውጥ ፈቃደኛ ካልሆነ፤ ሁሉንም የሚያሳትፍ አገራዊ እርቅና ሰላም የሚያመጣውን በር ካልከፈተ አገራችን ወደባሰና እጅግ ወደተወሳሰበ ቀውስ መግባቷ የማይቀር ይሆናል፤ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ የሥርዓቱ ተጠሪዎችና አራማጆ ች ይሆናሉ።

ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ስለ አገሪቱ አሳሳቢ ሁኔታና መፍትሔ ማፈላለግ ላቀረቡት የውይይት ጥሪ የተሰጠው መልስ በሽዎች የሚቆጠሩ የጸጥታና የመከላከያ ኃይል አባላትን በማሰማራት በሕዝቡ ላይ ዘመቻና ጥቃት ማካሄድ ነው። በዚህም ሳቢያ በሽህ የሚቆጠሩ ህይወታቸው ሲያልፍ አያሌዎችም አካለስንኩል ሆነዋል፣ በሺዎቹ የሚመደቡ ደግሞ በእስር ቤት እየተሰቃዩ ይገኛሉ።

የህወሀት መራሹ አገዛዝ የያዘውን የአጥፍቶ መጥፋት፣ የእልህና የበቀል ጎዳና ካልቀየረ፣ ለሰላምና እርቅ ድርድር በሩን ካልከፈተ አገራችን የቀውስ መስክ ሆና ለተለያዩ የታጠቁ የሽብር ሃይሎች አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠር ያሳሰባቸው የውጭ ታዛቢዎች ሳይቀሩ ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። የሸንጎም ስጋት ከዚህ የተለዬ አይደለም። አገሪቱ ለተደቀነባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የመውጫ መንገድ ዛሬ ነገ ሳይባል መቀየስ አለበት፤ የመውጫ መንገዱም በሰጥቶ መቀበል መንፈስ፣ በረጋና በሰከነ አስተሳሰብ የሕዝቡን ጥያቄና ችግሩን ተገንዝቦ በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ መወሰን ነው። በመተማመን፣ ሁሉን ያቀፈና ያሳተፈ ፍትሃዊና ሃቅ የተመላበት፣ ይቅርታን መሰረት ያደረገ፣ ሁሉም የሚረካበት ሂደት መጀመር አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። በተለመደው መንገድ መንጎዱ ቀውሱን ያባብሰዋል እንጂ ማስወገድ ቀርቶ አይቀንሰውም።

ኢትዮጵያና አጎራባች አገሮቿ የሚገኙበት አካባቢ ውጥረትና ስጋት የሰፈነበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ በአገሪቱም በውጭም ያለውን አለመረጋጋት ይበልጥ ያባብሰዋል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ በአፋጣኝ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ለአካባቢው ቀጠናና ባጠቃላይም ለአህጉሩ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ስለሆነም አሁን ሀገራችንና ሕዝባችን ከሚገኙበት ሁኔታ ለመውጣት ሸንጎ የሚከተሉት ሦስት ነጥቦች መሰረታዊ ናቸው ብሎ ያምናል፤

  1. መረጋጋትን ለመፍጠር እውነተኛ፣ አስተማማኝ፣ ሁሉን አሳታፊ፣ በሁሉም ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ሂደት መጀመር፤
  2. ሁሉንም ባሳተፈ ውይይት የቀውሱን መንስዔ አስወግዶ ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚችል የሽግግር ሂደት ማካሄድ፤
  3. ጠንካራ መሰረት ያለው ሂደት ተግባራዊ በማድረግ፤ ዘላቂ የሆነ ለውጥና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋትና ተመሳሳይ ቀውስ ወደፊት እንዳይከሰት መስራት፤

ከላይ የተጠቀሱትን እውን ለማድረግም የሚከተሉት አብረው የሚታዩ ተጓዳኝ ተግባሮች ናቸው፤

ከአመጽ ይልቅ አመጽ አልባ የሆነ ሽግግር ይመረጣል

የሚቻል ቢሆን የሰው ሕይወት ሳይጠፋ፣ የአገር ንብረትና ሃብት ሳይወድም በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ቢመጣ የሚጠላ የለም። ይህም በመሆኑ ሰላማዊውን ሽግግር የሚመርጥ ሁሉ ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ለዚህም ነው ሸንጎ ሽግግሩ ሰላማዊ መሆኑ ለወደፊቱ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ያለውን ወሳኝነት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የትግል አካሄድን የሚከተለው።

አሁን ግን በአገዛዙ ጀብደኝነትና ጭካኔ የተሞላበት አካሄድ ሁኔታው ይበልጥ እየተካረረና ህዝቡም ሌሎች አማራጮችን እንዲወስድ አስገደዶታል። በኛ በኩል ሰላማዊ ሸግግር የተሻለና አስተማማኝ ውጤትን እንደሚያስከትል ስለምናምን አሁንም ቢሆን የበለጠ አደጋና ውድቀት ሳይመጣ የእስከአሁኑ በቅቶ አገዛዙ ወደ ህሊናው ተመልሶ ወደሚሻለው አቅጣጫ ፊቱን እንዲያዞር የመጨረሻ ሰዓት የአደጋ ጥሪያችን እናሰማለን። የወቅቱ ሁኔታ ከቀውስ የጸዳ፣ ሁሉን ያቀፈና ያሳተፈ፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ፣ የፖለቲካ አቅጣጫን ይሻል። ሕዝቡ ያለውን ስርዓት አንቅሮ ተፍቶታል። ለተመሳሳይ አምባገነን አገዛዝም እንደማይመች ይፋ አድርጓል።

የሚያስገርመው ጉዳይ ግን አሁንም የቀውሱ ባለቤት የሆነውና በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን እራሱን ብቸኛ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የእድገትና የልማት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ፈጣሪና አውታር፣ ሕዝብም ከዳር እስከዳር የሚደግፈውና የሚከተለው አድርጎ ማቅረቡ ነው። እዚህ ላይ “ለማያውቅሽ ታጠኝ” ከማለት በስተቀር እሰጥ አገባ ጊዜ ማባከን ይሆናል። በአጭሩ አገዛዙ የሚከተለው መንገድ አገሪቱን ከተዘፈቀችበት የቀውስ ማእበል የሚያወጣ ሳይሆን በቀውስ ላይ ቀውስ እየወለደ የኤኮኖሚና የማህበረሰብ ውድመትን የሚያስከትል ነው። ከዚያ ማዕበል ለመውጣት ያለው መንገድ አንድ ብቻ ነው። ሁሉን ያሳተፈ አዲስ የሽግግር ሂደት መጀመር!

ግልጽነት ያለው ሁሉን አቀፍ ሽግግር አስፈላጊና ወቅቱ የሚጠይቀው ነው

አሁን ያለውን ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ስርዓትን ለማምጣት በህዝብ ተቀባይነትና ከበሬታ ሊኖረው ወደሚችል መንግስትና ስርዓት መሸጋገርን የግድ ነው። ህወሀት መራሹ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ የህዝብን አመኔታና ክብር አጥቷል።

አሁን እየተካሄደ ያለው በአይነቱ በጣም የተለያየ አካሄድ ከቀጠለ ለሚፈለገው የተደላደለ አይነት ስርዓት የታደልን አንሆንም። ለዚያም የሚያበቃ ተስፋ የሚጣልበት ነጠላም ሆነ የቡድን ድርጅት አለመኖሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። የሕዝቡን ትግል የሚመራና የሚያስተባብር የጋራ የሆነ ድርጅት አለመኖሩም ሌላው ክፍተት ነው። እዚያና እዚህ ትግሉን እየመራነው ነው የሚሉ ባይጠፉም በገሃድ ግን በመሬት ላይ የሚታዬው እውነታ ከዚያ የተለዬ ነው። ስለሆነም አገር አቀፉን ሕዝባዊ ትግል ወክሎ በሁሉም ቦታ የሚመራ ብቸኛ ድርጅት የለም። አንዱ ድርጅት ባንድ አካባቢ የተሻለ ጥንካሬ ቢኖረው እንኳን በሌላ ቦታ ደግሞ ተመሳሳይ አቅምም ድገፍም ላይኖረው ይችላል።

ስለዚህም የሀገራችንን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ የሚሳተፍበት፣ የውድቀቱም የስኬቱም ሂደትና ውጤት ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታን ለመፍጠር ጉባኤ መጥራትና መወያየት አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመከላከልም ሆነ ለማስወገድ ከባድ ይሆናል፣ አገራችንም ወደማያባራ ቀውስና ምስቅልቅል ሁኔታ ልትገባ ትችላለች። ያንን መፍቀድም አይኖርብንም። የሽግግር ወቅት ከመፍጠር የተሻለ አማራጭ የለም። ለዚያ ደግሞ ወቅቱ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ሁሉን አቀፍ፣ በግልጽነት፣ በመተማመንና፤ በመግባባት የሚፈጠረው የሽግግር ሂደት (የሽግግር መንግሥት) የሕዝብ ድጋፍና እምነት ብሎም ከበሬታ ያገኛል።

የሽግግር መንግስትና የሽግግር ምክር ቤት

በኛ አመለካከት ይህ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ የሚወልደው የሽግግር መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የለውጡ አንቀሳቃሽ የሆኑ የጎበዝ አለቆችን፤ የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮችን፣ የሃይማኖት፣ የጾታ፣ የሙያ፣ የጎሳ፣ የምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ወጣቶችን የሚያካትት (ሁሉን ያቀፍ hybrid model) መሆን ይኖርበታል እንላለን። ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮ የጸጥታና የመከላከያ ክፍሎች እንዲሁም የፍትህ ተቋማት ከፖለቲካ ተሳትፎ ርቀው ለተሰለፉበት ሙያና ተግባር ብቻ ያደሩ ይሆናሉ። የሕዝቡንና የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት አስከባሪዎች እንጂ የአንድ ድርጅት ታዛዦችና አገልጋዮች አይሆኑም። ተጠሪነታቸው ሕዝብ መርጦ በሥልጣን ላይ ላስቀመጠው መንግሥትና ለሕዝባዊ ምክር ቤቱ ይሆናል።

የሀገሪቱን እለት ተለት ተግባር ከሚመራው የሽግግር መንግስት የበላይ ሆኖ የሚያገለግል “የሽግግር ወቅት የብሄራዊ አንድነት የጋራ ምክር ቤት” (Transitional Assembly of National Unity) መመስረት አለበት እንላለን።

ይህ የሽግግር ምክር ቤት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ድርጅቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው።

የሽግግር ሂደት(የሽግግር መንግሥት) በሚከተሉት ቁልፍ ተግባርና ግዴታ ላይ ያተኮረ ይሆናል።

  1. አገሪቱን ቋሚ መንግሥት ተመስርቶ እስከሚረከብበት ጊዜ ድረስ ይመራል፤ ያገልግሎት ዕድሜው ግፋ ቢል ከሦስት ዓመት አይበልጥም።

አፋኝና ጨቋኝ የሆነውን ሕገ መንግስት አስወግዶ በምትኩ በሽግግሩ ተሳታፊዎች የጸደቀ ጊዜያዊ የሽግግር ቻርተርን ተግባራዊ ያደርጋል፤ በሽግግሩ ወቅትም ሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን መስርቶ ህዝብን ባሳተፈ ሁኔታ አዲስ ሕገ መንግሥት ያረቃል ለሕዝበ ውሳኔ አቅርቦም ያስጸድቃል።

  1. ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያመቻቻል፣ አሁን ያለውን ቋሚ የምርጫ ቦርድ ሽሮ ሥራው በምርጫ ወቅት ብቻ በሚያገለግል በሕዝብ ምክር ቤት ስር በሚቋቋም አካል እንዲካሄድ ያደርጋል።
  2. የእርቅና መግባባቱ ሂደት እንዲጀመርና እንዲቀጥል ጥረት ያደርጋል። ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ በህግ የሚዳኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን እውን ስለማድረግ፣

ለሽግግሩ ዋነኛ መሰረት የሚሆነው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ነው። የመደራጀት፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ መደገፍና መቃወም፣ መምረጥና መመረጥ፣ ዜጋ በፈለገበት የአገሪቱ ግዛት የመኖር፣ የመስራትና ንብረትና ሃብት የማፍራት…ወዘተ ያካትታል። እነዚህን ለማረጋገጥና አስተማማኝ ሂደት ለመጀመር፤ ለሕዝቡና ለአገሪቱ መተማመንን የሚገነቡ ተግባራት በቅድሚያ መፈጸማቸው ወሳኝ ነው። ከነዚህም ውስጥ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ የጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጁን ማንሳት፣ የመገናኛ ተቋማትን ነጻነት ማክበርና የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን ነጻነት በተግባር ማረጋገጥ ዋናዎቹ ናቸው።

እኩልነትን፣ እራስን የማተዳደርና የአገሪቱን አንድነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ሁኔታን ስለመፍጠር

በቋንቋና ክልል ረድፍ የማንነት ጥያቄ መነሳቱ የአገሪቱን አንድነትና የሕዝቡን ተሳስሮ፣ ተዋልዶና ተስማምቶ መኖር የሚፈታተን ሆኗል። ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ በመወያየት ለሀገራችን ምን አይነት የአስተዳደር መዋቅር እንደሚበጅ መመካከሩና መወሰኑ የተከሰተውንና ወደፊትም ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችለውን የእርስ በርስ ግጭት ስጋት ሊያመክን ይችላል። ስለሆነም በሽግግር ሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ በሥልጣን ክፍፍል የመንግሥትና የአካባቢ አስተዳደር ተቀራርቦና የአገሪቱ አንድነት ተጠብቆ የሚሰራበት፣ የአካባቢ ነዋሪ ሕዝብ፣ መጤና ተወላጅ ሳይባል፣ በሁሉም አካባቢ መብቱ በእኩልነት የሚጠበቅበትና በተግባር የሚተረጎምበት አካሄድ አንዱ መፍትሔ ነው ብለን እናምናለን። የልዩነቱ ሳይሆን የአንድነቱና የጋራ እሴቱ እየጎላ የሚታይበት፣ ሁኔታ መፍጠር ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል። የእኔና የእኔ ብቻ የሚለው አስተሳሰብ የእኛና የጋራችን በሚለው አስተሳሰብ እንዲለወጥ ማድረጉ ለበለጠ እድገትና ጥንካሬ ይረዳል። ከክልል ፖለቲካ ወጥቶ አገር አቀፍ ፖለቲካ መከተሉ ያስከብራል፣ እድገትና ሰላምን ያስገኛል።

በሽንጎው በኩል በዚህ የሽግግር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ሁሉ ለእኩልነት፣ ለአካባቢ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ስልጣን በማጋራትና የሀገሪቱን አንድነት በማስጠበቅ ላይ ለመሰለፍ ቃል ሊገቡ ይገባል እንላለን።

ለእርቅና ለመግባባት የሚረዱ ተግባሮች

የማህበረሰብና የፖለቲካ እርቅ ለማስፈን የአገራችን ህልውና ቀዳሚና ወሳኝ ነው። የነበሩና አሁን የተፈጠሩ ቁርሾዎችን እንደ ሁኔታው በሰላምና በውይይት ለመፍታት አለመቻል ችግሮቻችንን እጅግ የተወሳሰቡ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።

እነዚህን ቁርሾዎች ባግባቡ መመርመርና መፍታት ተፈላጊውን ብሄራዊ እርቅ ለማምጣት እጅግ አስፈላጊ እርምጃ ነው። ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ፣ በመከባበር፣ በቅን መንፈስ፣ በእውነተኛነትና፣ በግልጽ አሰራር ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት። ይህም እውን የሚሆነው በብሄራዊ እርቅ ሂደት ስንጓዝ ስለሆነ፣ የሽግግሩ መንግስት ይህን ሂደት በጥንቃቄ ግብ ይመታ ዘንድ መሰረቱን መጣል ስራውንም መጀመር ይጠበቅበታል።

ካለፉት የሽግግር ሂደቶች የሚቀሰመው ትምህርትና ተመክሮ

ኢትዮጵያ ካለፉት አርባ ሦስት ዓመታት ወዲህ በሁለት የተለያዩ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ፣ የማህበራዊ ሽግግር ሙከራ ሂደቶች ውስጥ አልፋለች። ከንጉሡ ቀጥሎ የሰፈነው ወታደራዊ አምባገነንና እሱን ጥሎ የተተካው የአሁኑ ብሄርና ጎሳ ተኮር ስርዓት መሆናቸው ነው። ሁለቱም የሚመሳሰሉበት አሏቸው፤ ሌላውን ያሳተፉ አይደሉም፣ የነጠላና የጠበበ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚተገበርባቸው ነበሩ፤ ሁለቱም የዲሞክራሲ ጸሮች ናቸው፣ በሁለቱም ስርዓቶች ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ የሆነባቸው፣ አለመተማመን፣ ስጋት፣ ግፍ፣ ሽብርና ጭንቀት የሰፈነባቸው ናቸው። በእነዚህ ስርዓቶች ሰፍኖ የኖረው አጥፊና ጠባብ የፖለቲካ ባህል ተወግዶ በቦታው የሁሉም በሁሉም ለሁሉም በሆነ የተሻለ ስርዓት እንዲተካ ካለፈው ድክመትና ውድቀት መማር ተገቢ ነው እንላለን።

በ1983 ዓ.ም. የተከሰተው የለውጥና ሽግግር ድክመት

  1. ግልጽነት የሌለው፣ የተዘጋ አግላይ ቡድን የጠነሰሰውና የተሳተፈበት ሌላው ተገፍቶ ከዳር የቀረበት ሂደት ነበር።
  2. የሕዝቡን ይሁንታ ሳያገኝ ቋሚ መንግሥት ሊሰራው የሚገባውን ነጥቆ በአገሪቱ ዘላቂና ከፍተኛ ጉዳዮችና ጥቅሞች ላይ ጎጂ ውሳኔ ያስተላለፈ ጠባብ የሽግግር ሂደት ነበር።
  3. ያንድ ድርጅትን ፕሮግራም ብቻ በሽግግር ቻርተርነት ስም አቅርቦ በሀገሪቱ ላይ መጫኑ።

አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ሁሉም መጣር አለበት።

ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመነጠል ውሳኔና ያስከተለው ጉዳት

የኤርትራ ከኢትዮጵያ መለየት ጉዳይና በአስመራ የተመሰረተው የሻቢያ መራሹ አገዛዝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ሚና እንዳለው ማየቱ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው። አሁን ባለው የሀገራችን የፖለቲካ መልክዓ ምድርም ቢሆን የኤርትራ ጉዳይ ሲነሳ ለየት ያለ ተጨማሪ ምስቅልቅልን ይጋብዛል።

አሁንም ቢሆን የኤርትራን በተመለከተ ያላለቀ ጉዳይ መኖሩን በመገንዘብ ይህን ጉዳይ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ ጋር ማደባለቅ ነገሮችን እጅግ ማወሳሰብና መፍትሄውንም እጅግ ማበላሸት እነደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው።

ስለሆነም በሁለቱም በኩል ያለውን ያልተዘጋ አጀንዳ በአዳሪ ማስቀመጥና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግር በቅድሚያ መፍታት አስፈላጊነቱን ተረድቶ መጓዝ ተገቢ ነው እንላለን።

Go toTop