መስከረም 8 ፣ 2009 ዓ.ምየወቅቱ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ችግር መዘዝ (Root Cause) አበራ ቱጂአገራችን ኢትዮጲያ አስቸጋሪና የሚያስጨንቅ የፖለቲካና የአገር አመራር ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት፣ የተለያዩ የመፍትሄ ሃስቦች በፍትህ ፈላጊወችም ሆነ በገዥው ህውሃት መራሹ ኢህአድግ ይሰነዘራሉ። ብዙ ሰዎች የችግሩን መዘዝ (root cause) በተወሰኑ የመንግስትን ስልጣን፣ ደንብ ወይንም ህግ ለግል ወይም ለተውሰነ ቡድን ጥቅም ማግኛ በተጠቀሙ ግለሰቦች ወይም ቡድን የተፈጠረ ችግር አድረገው በተሳሳተ መንገድ ይመለከቱታል።የሚሰነዘሩት የመፍትሔ ሃሳቦች በእውነት ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመንቀልና ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ በማድረግ በአገራችን ዘላቂ ፍትህ የሰፈነበት ስርዓት ለማምጣት ይረዳሉን ብሎ መጠየቅ ከሁሉም ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባዉ ጥያቄ ነው። ወያኔ ኢህአዲግ የችግሩን መዘዝ የተወሰኑ ባለስልጣኖች የፈጠሩትነው በማለት የተወሰኑ ባለስልጣኖችን በማተካካት የጥገና ለውጥ በማድረግ አሁንም አረመኒያዊ አገዛዙን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተዘጋጀ ነው። ችግርን ለማስወገድ፣ የችግሩን መዘዝ (root cause) በዘዴ መመርመርና ማወቅ ያስፈልጋል። አሁን አገራችን የገባችበት ችግር መዘዝ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይገባል። መዘዝ (root cause) የችግሮች መሰረት ሆኖ ችግሮች ወይንም ችግሮችን የሚያስከትሉ ሰንሰለታዊ ሁነቶችን የሚቀሰቅስና ልናስውግደው የምንችል የችግሮች ስርዎ-መንሴ ነው። መዘዝን ካስወገድነው የፈጠራቸው ችግሮችና ችግሮቹን ተከትለው የሚመጡ መጥፎ ወይም የማይፈለጉ ሁነቶች ለዘለቄታው ይጠፋሉ ወይም ተመልሰውአይመጡም። መዘዙን ሳናስወግድ፣ ሰበብ (triggering event) ወይንም ከላይ ከላይ ያሉ ችግሮች ወይንም የመዘዙ ምልክቶች ወይም መገለጫወች (manifestation) ላይ ብናተኩር፣ ችግሩ ተመልሶ መምጣቱ ወይንም ሌላ መልክ ይዞ መከሰቱ አይቀርም።በሌላ በኩል፣ ይህ አገራችን የገባችበትን ችግር፣ ኢትዮጲያ በተሻለ አቅጣጫና አስተዳደር ለመመራት የምትዘጋጅበት ጥሩ እድል ይዞልን እንደመጣ በመቁጠር፣ ይህን የቁጣና የቁጭት ሃይል ወደ አዎንታዊ ጉልበት በመቀየር፣ ከችግሩ አዙሪት መውጣት እንድንችል የአገራችንን የፖለቲካ መዘዝ በማስወገድና፣ አገራችን የህግ የበላይነት የሰፈነባትና የቂም-በቀል ፖለቲካ የማይኖርባት ሆና፣ እንድትቀጥል መስራት አለብን። አሁን ያለውን ችግር ከስፋቱና ጥልቀቱ የተነሳ በተወሰኑ ዓርፍተ ነገሮች መግለጽ ያስቸግራል። ዋናው ችግር ግን ኢትዮጲያዊያን እንደ አንድ በአገሩ በነጻነት ሰርቶ የመኖር መብት እንዳለው ሰብዓዊ ፍጡር ሳይሆን፣ የወያኔ መንግስትና የፈጠረው ስርዓት፣ ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ያለፍርድ ይገድሏቸዋል፣ሰቆቃ ይፈጽሙቧቸዋል፣ንብረታቸውን ይቀማሉ፣ እንዳይናገሩና አንዳይደራጁ ያፍኗቸዋል፣ የወያኔን ብልሹ መርህ፣ ‘ፖሊሲ’ ወይም ‘ዶክትሪን’ እንዲቀበሉ ያስገዲዷቸዋል፤ ሰወች በሰብዓዊ ሃይላቸው በነጻነት መስራትና መጣር ማደግና መጠቀም ይከለከላሉ። በአጭሩ የኢትዮጲያ ዜጎች በወያኔወችና ወያኔወች በፈጠሩት ስርዓት ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብታቸው ተገፎ ወንጀል እየተፈጸመባቸው ነው።የዚህን የአገራችንን ዘርፈ-ብዙ ችግር መዘዙን ለማወቅ “ችግሩ ለምን ተፈጠረ ወይም ምን አመጣው’ በማለት የችግሩን ስር ወይም መዘዝ እስከምናገኝ ተከታታይ ጥያቄወችን ማንሳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል አንድ የችግሩን ሁነት (event) እንመልከት። በሰላም የመብት ጥያቄ ያቀረቡ ሰለማዊ ሰልፈኞች ለምን በመንግስት አነጣጥሮ ተኳሾች ይገደላሉ? ለዚህ የሚጠበቀው መልስ የመንግስት ባላስልጣን የግድያ ትዕዛዝ ስለሰጠ ነው እንበል። ይህን የግድያ ትዕዛዝ የሰጠ የመንግስት ባላስልጣን ከቦታው ቢነሳ፣ ሰለማዊ ሰልፈኞችን መግደል ያቆማል ወይ? ለዚህ ምሳሌ ማየት ያለብን፣ አቶ መለስ ዜናዊ የ 1997 ምርጫ ተክትሎግድያ አዘው ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ሰለማዊ ሰልፈኞችን አዲስ አበባ ዉስጥ ብቻ በግፍ አስገድለዋል። እሳቸው በሞት ሲለዩ የተኳቸውና እግዚአብሄርን ይፈራሉ ይባል የነበረው የወላይታው ተወላጅ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ትዕዛዝ በመስጠት በመቶወች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን እያስገደሉ ነው።የክልል መሪወችም ሆነ የተውሰኑ የጦር ጄኔራሎች የወያኔን አጥፊ ተልዕኮ ከፈጸሙ በኋላ ተተክተው አይተናል። የህዝብ ሃብት ዘረፉ የተባሉና፣ በዘረኛ ቅስቅሳ ህዝቡን በጠላትነት ያነሳሱ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ተተክተው አይተናል። ሰወቹን በመቀያየር መንግስት የበለጠ ችግር ሲፈጥር እንጂ ሲያሻሽል አልታየም። የህግም ማውጣት ችግሩን አልፈታም። ለዚህ የሚጠቀሰው የጸረ-ሙስና ህግ የሚባለው ማስመሰያ ነው። የችግሩ መዘዝ የተጻፈ ህግ እጥረትም አይደለም፣ ያለው ህግ ይህን ግልጽ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል የሚችል ነበር። ስለዚህ ተጨማሪ ህግ በማውጣት ወይንም ሰወችን በመቀየር ብቻ ችግሩን ማጥፋት ወይም ተመልሶ እንዳይከሰት ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም የችግሩ መዘዝ የተወሰኑ ስልጣን ላይ ያሉት ሰወች ወይንም የህግ፣የብልሹ አስተዳደር፣ የሙስና፣ የህዝብ ንብረት ምዝበራ፣የችሎታ ማነስ ወይም የአፈጻጸም ጉድለት አይደለም። እንዚህ መዘዙ ያመጣቸው የችግሩ ምልክቶች ወይም ሁነቶች ናቸው።ዛሬ የሚገድሉትና የሚያስገድሉት የወያኔ ባለስልጣኖች ከስልጣን ቢወገዱና የመሰረቱት ዘረኛ፣ አድሏዊና አፋኝ ስርዓት (system) እስካለ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል ወይንም መልኩንና ሰወችን እየቀያየረ በድጋሜ ይመጣል። ስርዓቱ የወያኔን መሰሪና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ተልዕኮ ለመፈጸም ሲባል የረቀቀ መዋቅር ተዘጋጅቶለታል። ስርዓቱን እንዳይወድቅ ደግፈው የያዙ፣ የተሳሰሩና እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ፣ ብዙ ምሶሶወች አሉት። ስርዓቱን ቀጥ አድርገው የያዙት፣ እያደሱና እየጠገኑ ያቆሙት የሚከተሉት ዋልታወች ናቸው።1. በዘርና ቋንቋ ከፋፋይ መርህ፤ የዚህ ስርዓት የመሃል ምሰሦ የሆነው አገሪቱን በዘርና ቋንቋ መከፋፈሉና የፈጠረው የዘር ጥላቻ ፖለቲካ ነው። ይህ ወያኔወች የኢትዮጲያን ታሪክ በማጥፋት ህዝቡን ለመቆጣጠር ያመጡት የጎሳ ፖለቲካ ለወያኔው ስርዓት ከሁሉም በላይ መድህኑ ሁኗል። ኢትዮጲያኖች የአገራቸውን ችግር በጋራና በሰለጠነ መንገድ ተወያይተውና ተቀራርበው እንዳይፈቱ፣በአገር አቀፍ ጉዳይ ላይ ከማትኮር ይልቅ በመንደር ድንበርና በጥላቻ ፖለቲካ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።2. አፋኝ ጦርና የስለላ ድርጅት¤ ስርዓቱን የሚቃወሙትን ሁሉ ለማፈን በወያኔ ታማኞች በበላይነት የሚመራ አገርና ህዝብን ሳይሆን ወያኔወችንና ስርዓቱን የሚጠብቅ የጦርና የፖሊስ ሃይል አለ። ዜጎችን ለመቆጣጠርና የመንግስትን ተቃዋሚወች ለማጥፋት ወያኔወች ከሚመሩት የስለላ ድርጅት በተጨማሪ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩና ቴሌኮሙኒኬሽን ይጠቀማል።3. በፖለቲካ ድርጅቱ ቁጥጥር ስር ያለ ምጣኔ ሃብትና የዕምነት ተቋማት፤ ስርዓቱን በገንዘብ ሃይል ለመደገፍና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመስጠት ደጋፊውችን ለማብዛትና ተቃዋሚወችን ለማዳከም የኢኮኖሚ አውታር የሆኑትን ያአገሪቱን መሬት፣ ባንክ፣ የንግድ ተቋማትን እንደ አየር መንገድ፣ ኤፈርት፣ ሜቴክ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ መብራት ሃይልና የመሳሰሉትን በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል። የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በወያኔ ደጋፊወች ብቻ በመሙላት የስርዓቱን እድሜ ለማራዘምና የዜጎችን ዕለት ከዕለት ኑሮ ለመቆጣጠር ይጠቀምባቸዋል። የዕምነት ድርጅቶችን በወያኔ ታማኞች እንዲመሩ በማድረግ ህዝብ ሲበደል አንዳይነሱ አድርጓል።4. ተቃዋሚወችን የሚያጠፋ የይስሙላ የፍትህና የምርጫ ድርጅቶች፤ ካለው የአንድ-ድምፅ ፓርላማ በተጨማሪ ለይስሙላ ያሉ የፍትህ መስሪያ ቤቶች የወያኔን ስርዓት “ህጋዊ” ጠለላ ይሰጣሉ። አፋኝ ህጎችን እንደ ጸረ-ሽብርና፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግ በማውጣት መንግስትን የሚቃወሙትንና የመብት ጥያቄ ያነሱትን በእስር ያሰቃያል፣ ሰቆቃ ይፈጽማል። ዜጎችን የመናገር፣ የመሰብሰብ፣የመደራጀት መብታቸውን ይነፍጋል።ለይምሰል ያህል ምርጫ ያካሂዳል፣ ከወያኔ በስተቀር ተመራጭ እንዳይኖር ያደርጋል። ምርጫን ያጭበረብራል።5. አማርጭ ሃሳብ የሚዘጋና ጥላቻ የሚነዛ የመገናኛ ብዙሃን፤ በወያኔወች የሚመሩትን በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን፣ በህዝቡ መሃል ጥላቻን ለመዝራት፣ ውሸትን ለማሰራጨት፣ ህዝቡን የመንግስትን አቋም ብቻ እንዲከተል ለማድረግ፣ አማራጭ ሃስቦችን ዝግ ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል። የግል መገናኛ ብዙሃንን፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን፣ የዝቡን ችግርና በደል እንዳያሳውቁ ፣ህዝቡን እንዳያነቁ ያጠፋል። የትምህርት ተቋማትን ወጣቱን በዘር ለመከፋፈል የጥላቻ ማስተማሪያ በማድረግ የወያኔ ካድሬ መፈልፈያ አድርጓቸውል።እነዚህ እርስ በእርስ የሚደጋገፉና የተሳሰሩ ምሶሶወችና፣ምሶሶወቹ የቆሙለት መሰሪ ተልዕኮ፣ መዋቅሩና ስርዓቱን የሚመሩትና የሚያገለግሉት ሰወች፣ በአንድ ተዋህደው ነው አሁን የደረስንበትን ችግር የፈጠሩት። ለዚም ነው ችግሩ ስርዓታዊ (systemic) ነው ወይም የችግሩ መዘዝ ስርዓቱ ነው የምንለው።ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ያለው አደገኛ ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት ማንፌስቶ እንደሚገልጸው ወያኔውች በደደቢት የጀመሩት በይበልጥ በአማራ ላይ በአላቸው ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ በልዩተንኮል የተዘጋጀ፣ ከፋፋይ፣ አድሏዊና አፋኝ ስርዓት ነው። አሁን ያለው ችግሩ በተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የተፈጠረ ወይም በተናጠል የሚታይ አይደለም። በአገራችን ያለው ችግር ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ይቀጥላል። የችግሩ መዘዝ (root cause) ይህ ወያኔ የፈጠረው ስርዓት ነው። የችግሩን ወቅታዊ ሁነቶች፣ለምሳሌ አንደ የአዲስ አበባ ድንበር መስፋፋት ወይም የወልቃይት ጉዳይ ለጊዜው መልስ በመስጠት ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት አይቻልም። ወያኔወች ዛሬ የፖለቲካ እስረኞችን፣ ምህረት ጠየቁ እያሉ ካደነዘዙና የአዕምሮ ሰቆቃ ከፈጸሙባቸው በኋላ ቢፈቷቸውም ነገ ደግሞ ባለተራወች ይገባሉ። ዛሬ ግድያቸውን ለጊዜው ቢያቆሙ ከተውሰነ ጊዜ በኋላ ይጀምራሉ። ወያኔወች በሃያ አምስት ዓመታት አገዛዛቸው ያሳዩን ሃቅ ይህን በደል ተራ በተራ መርሃ-ግብር አውጥተዉለት በተለያየ የህብረተሰቡ ክፍል ላይ መፈጸማቸውን ነው። ከሁሉም በላይ አገር ሊመሩ የሚችሉዜጎችንና ድርጅቶችን ገና ሲያቆጠቁጡ ያጠፋሉ። ዜጎችን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ እንዲዘጉባቸው በማድረግ ተስፋ በማስቆረጥ ወደጦርነትና ሃይል አማራጭ ይገፋሉ። በአገሪቱ የዘር ጥላቻን ይዘራሉ። እኛ ካልገዘናችሁ ህዝቡም አገሪቱም ትጠፋለች በማለት ህዝቡን ያሸብራሉ። በመግደል፣ በመዝረፍና በማሸበር መግዛት ከአገዛዙ ስርዓት እምነትና ተልዕኮ የመጣ እንጂ የተወስኑ አምባገነኖች ፍላጎት ብቻ አይደለም። ሰወቹ ቢቀያየሩም ይህ ስር የሰደደና በተንኮል የተዘጋጀ አፋኝ ስርዓት፣ ባለው አጥፊና የማያፈናፍን የድርጅትባህል (organizational culture)፣በስፋት በተደራጀው የስለላ ድርጅትና ሌሎች ከላይ የተጠቀሱ ዋልታወቹ ጋር በመሆን፣ አዲስ የሚቀላቀሉትን ግለስቦች ባህሪ ስርዓቱ በተቃኘበት መንገድ ይለውጠዋል። አቶ ኅይለማሪያም ደሳለኝ ከአነጋገራቸው ጭምር ዳግማዊ መለስ ዜናዊ ሆኑ እንጂ ራሳቸውን አልሆኑም።ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለመግደል ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት ወያኔወች የተለመደ ድራማቸውን ይዘው ለመቅረብእየተዘጋጁ ነው። የታዘዙትም የክልል ባለስልጣኖች ትዕዛዙን ተቀብለዋል። ወያኔወች “በጥልቀት እንታደሳለን” እያሉ የሚያላዝኑት፣ ችግሩን የሚያዩበት መነጸራችው ያው ሃያ አምስት ዓመታት የገዛን ወያኔየዘረጋው መሰሪ ስርዓት ነው። የሚመሩበትም ፍጹም የተማከለ፣ ሚስጥራዊና ከፋፋይ፣ የማያፈናፍን፣ በተወሰኑ የህወሃት ሰወች የሚመራ፣ ስርዓት ነው። ወያኔወች ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥማቸው በሚስጥር በመወሰን፣ ከስራቸው ያስጠጓቸውን ተለጣፊወች ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሰሞኑን በረከት ስምኦን ይህን ነበር ያለው። “በኢትዮጲያ ዉስጥ ፈደራል የሚባል ህዝብ የለም ክልላዊ ህዝብ ነው ያለው ኢህአዲግ ለብልሽት ብሄራዊ ካባ ልንደርብለት አይገባም የሚል በጣም ጠንካራ አቋም ነው ያለው፣ በጣም ጠንካራ፣እያንዳንዱ ክልል፣ እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት የራሱን ብልሽት ራሱ ይታገል።” ይህም ወንጀሉን የሚፈፅመዉን የፌደራል መንግስት ከደሙ ንጹህ እንደሆነ ማቅረብ፣ አፋኙን ስርዓት ለማዳንና ለማጠናከር የተወሰኑ የአማራና የኦሮሞ ተለጣፊ መሪወችን፣ ህዝባቸውን ካስጨፈጨፉ በኋላ ሊወረዉሯቸው መሆኑን ሲገልጽ ነው። የወያኔ ኢህአዲግ ሰወች ማሰብና መጓዝ የሚችሉት ይህ ስርዓት ባሰመራላቸው ቀጭን መስመር ብቻ ነው። አንዳንድ የሚባንኑ የኢህአዲግ ሰወች ቢኖሩም እንኳ፣ ከዚህ ነገሮችን የመመልከቻ ዘይቤ (paradigm) ዉጭ ሊያስቡ አይችሉም። ሌላ አዲስ ነገር እንዳያስቡ ይህ ስርዓት አፍኖ ይዟቸዋል። በወያኔ የአዕምሮ ማደንዘዣና አስገዲዶ ማሳመን (indoctrination and brainwash) ያልተረቱ አንዳንድ የስርዓቱ አባላት ቢኖሩም እንኳን ከዚህ ወጭ ማሰብ ከጀመሩ ስርዓቱ በተለያየ ዘዴ ያጠፋቸዋል። ይህ የችግሮቹ ሁሉ ዋና ምንጭ የሆነ ስርዓትና፣ የችግሩን ሁነቶች የፈጠሩት ግለስቦች፣ ችግሩን በፈጠሩበት አስተሳሰባቸው፣ አገራችንን አሁን ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ሊያወጧት አይችሉም። እንዲያውም የህወሃት መንግስት ተጠናክሮ ለመቀጠል ይህን አጋጣሚ እየተጠቀመበት ነው።መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአለባት ኢትዮጲያ ይህን ለሃያ አምስት ዓመታት እየገደለ በሰቆቃ የገዛንን ስርዓት አዝለን እንድንቀጥል የሚያስገድደን ምን ሁኔታ አለ? ወያኔ ለህዝብ ባለው ንቀት፣ ይህን ሁሉ ወንጀልና ግፍ በረቀቀ ዘዴ አቀነባብሮ እየፈጸመ፣ አሁንም ለኢትዮጲያ ከኔ በላይ አሳቢ የለም ይለናል። ከዘረፉት በተረፋቸው የብድርና እርዳታ ገንዘብ መንገድ ሰርተናል ከሆነ የሚሉን፣ ጣሊያንም እየጨፈጨፈን በአምስት ዓመታት የበለጠና እስካሁን እያገለገለ ያለ መንገድ ሰርቷል። የበደለ ቢረሳ የተበደለ አይረሳም። የኢትዮጲያ ህዝብ በዚህ ስርዓትና በወያኔ የደርሰበትን ግፍ ፍጹም አይረሳም። አገር ለመገንጠልና ለማስገንጠል አቅዶ የተነሳው የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ብዙ ሺህወችን ጨፍጭፎና አስጨፍጭፎ ስልጣን ላይ ወጥቶ በኢትዮጲያ ላይ ያደረሰውን በደል በዚህ አጭር ጽሁፍ ጨርሶ መዘርዘር አይቻልም። በመሃል አዲስ አበባ የተገደሉት እነ አሰፋ ማሩ፣ የእነ ሽብሬ ህይወት በግፍ የተጨፈጨፉት የጋምቤላ፣ ኦሮምያ፣ሲዳሞ፣ ኡጋዴን፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወገኖቻችን ደም አሁንም ወደሰማይ ይጣራል። በገደሉት ልጇ አስከሬን ላይ አንድትቀመጥ አስገድደው የደበደቧትን የወለጋዋ እናት ሰቆቃ እግዚአብሄር ያያል። በወያኔ እስር ቤት የሚሰቃዩ በሺወች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፣ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እምባ ወደአምላካቸው ይፈሳል። ይህንና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ በደሎችን የፈጸመብንን ስርዓት ተሸክመን የምንጓዝበት ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? አሁን ለደረስንበት የፖለቲካ ችግርና የህዝብ እምቢተኝነት መዘዙ ይህ አፋኝና ጨፍጫፊ ስርዓት ነው። ይህ ስርዓት ለሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ የፈጸመው ወንጀል ራሱን ገፍቶ ሊያጠፋው ተቃርቧል። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጲያው በዘር በሃይማኖት ሳይከፋፈል በአንድ ላይ ተነስቶ ይህን ግፈኛ ስርዓት ያስውግድ። ከዛ ዉጭ በችግሩ ምልክት ወይም ግለሰቦች ላይ ያተኮረ ትግል ወያኔወች የመሰረቱትን ስርዓት ዕድሜ ያራዝማል። ወያኔና ስርዓቱ አንገፍግፎናል። ይህ መሰሪ ስርዓት ፈርሶ በህግ የበላይነት የሚመራና ለዜጎች መብት የቆመ ስርዓት መመስረት አለበት። ትግላችን የጥላቻን ፖለቲካ የሚዘጋና የችግሩ ስርዎ-መንሰኤ ላይ ያተኮረ ይሁን። የኢትዮጲያ ህዝብ የአጋዚን ‘ስናይፐር’ ሳይፈራ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው፣ የተውሰኑ ትንንሽ ሌቦችን ከስልጣን ለማባረር ሳይሆን፣ ሃያ አምስት ዓመታት እየጨፈጨፈ የገዛንን ስርዓት ለማስወገድ ነው። ይህን ስርዓት ለመጣልና ትግሉን ግብ ለማድረስ፣ ኢትዮጲያኖች በመተባበርና ጥቃቅን ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው፣በችግሩ መዘዝ ላይ የተቀነባበረና ስልታዊ እርምጃወችን ሊወስዱይገባል። አንድነት ሃይል ነው