September 13, 2016
7 mins read

የአማራ ክልል የወያኔ መቀበሪያ

ከአይናዲስ ተሰማ

ኢሕአዴግ አዲስአበባን እንደተቆጣጠረ አቶ መለስ ዜናዊና ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ስለአማራ ማንነት ያደረጉት ክርክር እንደነበረ ብዙወቻችን እናስታውሳለን:: በዚህ ክርክር ላይ ፕሮፌሰር መስፍን አማራ የሚባል ብሄር የለም ብለዋል:: እሳቸው እንደሚሉት አማራ በደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረው የክርስቲያኑ ሕዝብ መጠሪያ ስም እንደሆነ ነው::

እኔ በበኩሌ ፕሮፌሰሩ የተነሱት ከትክክለኛ ጭብጥ ነው ብየ አምናለሁ:: እስከማውቀው ድረስ በቅድመ-ወያኔ አማራ በመባል የሚታወቅ ብሔረሰብ እንዳልነበረ ነው:: ከወያኔ በፊት በነበሩት አስተዳደሮች ጎጃሜ: ወሎዬ: ጎንደሬ: የሸዋ ሰው ተብለው የሚጠሩ ሕዝቦች እንጅ እኒህን አራቱን የያዘ አማራ የሚባል ጥቅል (package) መጠሪያ አልነበረም:: እንዲያውም አማራ የሚለው ስም የክርስትና ዕምነት ተከታይ ለሆኑ ሰዎች የተሰጠ ስያሜ ነበር:: ቢያንስ እኔ በተወለድሁበት አካባቢ የነበረው ግንዛቤ ይህ ነው:: አማራ የሚለው ቃል ክርስቲያን የሚለውን ቃል የሚተካ ለመሆኑ በጎጃምና በጎንደር አካባቢ የሚኖሩትን አባቶች ጠይቆ መረዳት ይቻላል:: የአንድን ሰው ሐይማኖት ለማወቅ የፈለገ ሰው “እስላም ነህ አማራ?” የሚል ጥያቄ ነበር የሚቀርብለት:: ይህ የሚያሳየው የክርስቲያን ዕምነት ተከታይ የሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ አማራ ተብሎ ይጠራ እንደነበረ ነው::

በድህረ.ወያኔ ጊዜ አሁን ያለው የአማራ ክልል ተፈጥሮ በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ አማራ በሚል የወል ስም መጠራት ጀመረ:: በመጀመሪያወቹ የወያኔ የግዛት አመታት አማራ የሚለው መጠሪያ ብዙሀኑን ያደናገረ እንደነበር ብዙወች ይመሰክራሉ:: በአራቱ ክፍላተሀገሮች ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች ብዙም ባይሆንም የየራሳቸው ስነቦናዊ ማንነትና የአኗኗር ዘይቤ የነበራቸው ነበሩ:: እንደግል የየራሳቸውን ክ/ ሀገር እንደሀገር ደግሞ የጋራ የሆነችውን ኢትዮጵያን በማልማትና በመከላከል ይኖሩ የነበሩት እኒህ ሕዝቦች በአቶ መለስና በድርጅታቸው በተፈጠረው አማራ በሚባለው የጋራ መጠሪያ መጠራት ከጀመሩ በኋላ የነበሩትን ልዩነቶች በሂደት እያጠበቡ የጋራ ማንነትን ማለትም አማራነትን እያዳበሩ ለመምጣት ብዙም አልተቸገሩም::

አቶ መለስና ድርጅታቸው እኒህን በአራት ክ/ሀገሮች ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች በአንድ ጨፍልቀው “አማራ” የሚል ስም ሰጥተው በአንድ ክልል ሊያካልሏቸው የተነሱበት የሆነ ተንኮል መኖር አለበት:: ወያኔ መለያየትን እንጅ መተባበርን የሚጠላና የሚፈራ ድርጅት መሆኑን የማያውቅ ማንም የለም:: የአማራን ክልል ሲመሰርት አመራሩ በቀድሞ ማንነት ላይ ያተኮሩ ትናንሽ ቡድኖችን እየፈጠረ ለስልጣንና ለጥቅም መናቆሩ ስለማይቀር ክልሉን የብጥብጥ ቀጠና ያደርጉትና ሕወሀት የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ያመቸዋል የሚል አላማ አንግቦ ሊሆን ይችላል:: በአንድ ክልል የተሰባሰበ ግን ውስጡ የተከፋፈለ ሕዝብ ለጥቃትና ለብዝበዛ የተጋለጠ መሆኑ እውነት ስለሆነ ማለት ነው::

ነገር ግን የታሰበው የተሳካ አይመስልም:: ወያኔ “አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው:: አማራው ካልጠፋ ትግራይን ማልማት አንችልም” ብሎ በፕሮግራሙ ያስቀመጠውን ንድፈ-ሀሳብ ወደተግባር ሲተረጉም ተጠቂ የሆኑት ዱሮ ወሎየ: ጎጃሜ: ሸዬና ጎንደሬ ተብለው ይጠሩ የነበሩት ሕዝቦች ናቸው:: ከነዚህ አካባቢ የተገኙ ሰዎች አማራ ናቸው ተብለው በየአካባቢው እየታደኑ ተገድለዋል: ታስረዋል: ሀብት ንብረታቸውን ተቀምተው ተባረዋል: ተሳደዋል: ተደብድበዋል: ተዋርደዋል:: ይህ ሁሉ እየተደረገባቸው ያለው አማራ ናቸው በሚል ነው::

የወያኔ የጥቃት ኢላማ የሆኑት እኒህ ሕዝቦች ከታሪካዊ ማስረጃ ይልቅ በመገፋትና በመጠቃት የተነሳ ፍጹም አንድ ሕዝብ ሆነው እየደረሰባቸው ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥቃት ለመመከት አማራነትን ተቀብለው ላይለያዩ አንድ ሆነው ተነስተዋል:: ህልውናን ለማስቀጠል ለህልውና ጸር የሆነውን ነገር ማስወገድ ግድ ይላል:: ተወደደም ተጠላም ከምንም በላይ ችግር አንድ አድርጎናል:: የአማራ ክልል መመስረት አማራ ተብሎ እየተጠራ ላለው ሕዝብ ጥንካሬን ሲያላብስ ለወያኔ ግን ያልታሰበ ዱብ ዕዳ ፈጥሯል:: ገደብ የለሽ ስልጣን ለማስጠበቅ ይጠቅማል ተብሎ የተመሰረተው አማራና የአማራ ክልል የዘረኞች መጥፊያ ሊሆን እንደሚችል አለመጠርጠሩ የወያኔን የመሞቻ ጊዜ አቅርቦታል::

Go toTop