አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ለኢትዮጵያ የሚገባትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ በሰላማዊ የትግል መስመር ለማረጋገጥ ትግል ከጀመረ አራት ዓመታት አሳልፏል፡፡ በነዚህ ዓመታትም ፓርቲያችን ወደ ፍፁም አምባገንነት እየነጎደ ያለውን ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ አካሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጠቃ እንዲቆም አጥብቆ ታግሏል፡፡ በትግሉ ሂደትም ስርዓቱ በግልፅና በስውር ፓርቲያችን ላይ ጥቃት ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ይገኛል፡፡ አመራሮቻችንና አባሎቻችንም ስለ ቁርጠኛ ዓላማቸው ያለምንም ማፈግፈግ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ስለ ዴሞክራሲና ነፃነት ሲሉ ጨለማ ክፍል ውስጥ የተጣሉትን ወጣት አመራሮች አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን እና ሌሎችንም፤ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ እስር ቤት የተጣሉ ጉምቱ ጋዜጠኞችና የዕምነት ጣልቃ ገብነትን ስለተቃወሙ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን መጥቀስ ይቻላል፡፡
አንድነት በሆደ ሰፊነት የፖለቲካ ለውጦች እንዲደረጉ፣ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንዳይታሰሩ፣ እንዳይገረፉ፣ እንዳይሳደዱ፣ መንግስት በኃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባና የኃይማኖት ነፃነት እንዲረጋገጥ ስለጠየቁ በጅምላ የድራማ ክስ እየተመሰረተ ወደ እስር ቤት እንዳይጋዙ፣ ጋዜጠኞች ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ እንደ መደበኛ ጠላት ተቆጥረው ሰብዓዊ መብታቸው ተገፍፎ እንዳይታሰሩና ለስደት እንዳይዳረጉ በተደጋጋሚ ገዥውን አካል ያለመታከት መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡ የሀገሪቱ ችግሮች በገዥው ፓርቲ ብቻ የሚፈቱ አለመሆናቸውን በመገንዘብ በሃገራዊ ጉዳዮችና የፖለቲካ መፍትሄዎች ላይ ከተቃውሞ ኃይሎች ጋር ድርድር እንዲያደርግ፣ የዘጋውን በር ለውይይት ክፍት እንዲያደርግ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር በተደጋጋሚ ጠይቀናል፡፡ ለነዚህ ዓብይ ጥያቄዎቻችን የተሰጠን መልስ እስራት፣ መፈረጅና ማዋከብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ገዥው ፓርቲ ለጭቆናው ሕጋዊ ከለላ ለመስጠት ጨቋኝና አፋኝ ህጎችን በማውጣት፤ የረጅም ዓመት የስልጣን ቆይታን በመናፈቅ ዜጎችን በየማጎሪያ ቤቱ እያሰቃየ ይገኛል፡፡ እኛም ይሄንን ዓብይ ችግር ለመፍታት ሰላማዊ በሆነ የትግል ስልት ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ አምነናል፡፡
ስርኣቱ ዜጎች ካላግባብ ከየመኖሪያ ቀያቸው በገጠርም ሆነ በከተማ በግፍ እንዲፈናቀሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄው ሀገራዊ ይዘት ያለው ማፈናቀል ሦስት አይነት መልክ ያለው ሲሆን በዘር ላይ ተመሰረተ ማፈናቀል፣ በልማት ስም ማፈናቀልና ለመሬት ወረራ ማፈናቀል ናቸው፡፡ ዘርን መሰረት ያደረገው ማፈናቀል በቅርቡ ብቻ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ በቤኒሻንጉል ክልልና ሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተው ነው፡፡ በልማት ስም የሚከናወነው ማፈናቀል በአብዛኛው በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው መሰረቱ የገዥው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡ መሬት በባለቤቱ ፈቃድ የሚሸጥና የሚለወጥ ባለመሆኑ ያለበቂ ካሳና ማስጠንቀቂያ ለማህበራዊ ትስስር ቁብ ሳይኖረው ልማት በሚል ስም ብቻ በማንሳት ዜጎች የሚፈናቀሉበት ነው፡፡ ሌላው የማፈናቀል አይነት ደግሞ ከመሬት ወረራ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና በእርሻ መሬት ሰበብ ዜጎች እየተፈናቀሉ ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በጥቂት ሳንቲም የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄም በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በስፋት የታየና እየታየ ያለ ነው፡፡ ፓርቲያችን ይህንን ጉልህ ሀገራዊ አደጋ ለማስቆምም የሚጠበቅበትን ትግል ለማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ መሆኑን ያምናል፡፡
ከመፈናቀሉ በተጨማሪም ቅጥ ያጣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ ያስነካው የዋጋ ግሽበት ዋና መንስኤው ስርዓቱ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ የወለደው ነገር ቢኖር ሀገራችን በታሪኳ አይታ የማታውቀው ስደት ነው፡፡ ዜጎች ከፊት ለፊት ሞት እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ተጋፍጠው ለስደት የመነሳታቸው መንስኤ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር የነፃነት እጦት ሲታከልበት የችግሩን መልክ ውስብስብ አድርጎታል፡፡
የንግዱን ማህበረሰብም ስንመለከት ከመቼውም በባሰ ሁኔታ ነጋዴ መሆን ወንጀለኛ መሆን የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ በተጨማሪም ገዥው ፓርቲ በአንድ በኩል ህግ አውጪና አስፈጻሚ፣ በሌላ በኩል ነጋዴ በሆነበት ሁኔታ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ይህም የግሉ ሴክተር በሀገሪቱ ዕድገት ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ሚና እጅግ አቀጭጮታል፡፡ ካላግባብና በግምት የሚጣል ታክስ መክፈል ሃገራዊ ግዴታ የመሆኑን ለዛ አሳጥቶታል፡፡ አንዳንዱ በብልጣብልጥነት ስርዓቱን እንደመታወቂያና ከለላ በመጠቀምና ከባለስልጣናት ጋር በመሻረክ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሀብት ማማ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን፡፡ ይሄም በንፁህ ንግድ ላይ ለተመሰረቱ በርካታ ዜጎች አደጋ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚያም ልቆ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሃዊ የንግድ አሰራር እንዲኖርና የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባውን ቦታ እንዲኖረው እንጠይቃለን፡፡
በዚህም መሰረት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ለማድረግ በአዲስ አበባና በመላ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ውይይትና ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን፡፡ ህዝቡንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍ፣ አባሎቻችንንና ደጋፊዎቻችንን ያሚያቅፍ፣ አፋኝና ጨቋኝ ህጎችና አዋጆች እንዲሰረዙ ጫና የሚያደርጉ፣ በመሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ውይይት ለማካሄድ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መደረግ እዳለባቸው እናምናለን፡፡ በዚህም መሰረት የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት (MILLIONS OF VOICES FOR FREEDOM) በሚል መሪ ቃል ተከታታይነት ያለው የሕዝባዊ ንቅናቄ ዕቅድ ይፋ አድርገናል፡፡
የዕቅዳችን ዋና አላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ አምባገነንነትን ማስፉት፤ በአንፃሩ ደግሞ ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብትን እየገፈፈ፣ ዜጎችን በፍርሃት ተዘፍቀው በምንደኛነት እንዲኖሩ ያደረገውን ስርዓት መቃወም፤ መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ስልጣን የህዝብ እንዲሆን፣ ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በዕምነታቸውና ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው የማይታሰሩባት ሃገር መፍጠርና ፍትሃዊነትን ማስፈን ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የሚሊዮኖችን ድምፅ በመሰብሰብ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጋጨውንና ፍፁም ነፃነት ነጣቂ የሆነውንና ማሰብ እንኳን የሚከለክለውን የፀረ ሽብርተኝነት ህግ እንዲሰረዝ ማድረግ ነው፡፡ ሚሊዮኖች የፀረ ሽብር አዋጁን በመቃወም የሚፈርሙበት ሰነድም እነሆ ይፋ አድርገናል፡፡ ሚሊዮኖችም የተቃውሞ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ሙሉ እምነት አለን፡፡ ይንንም መሰረት በማድረግ ለእስር የተዳረጉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የተቀየሰው የሠላማዊ ስልት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ህዝባዊ የአዳራሽ ስብሰባዎችን፤ የአደባባይ ስብሰባዎችንና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ያካትታል፡፡ በአዲስ አበባ ስድስት ህዝባዊ ስብሰባዎችን፣ በክልል ደግሞ ለመጀመሪያ ዙር ብቻ አስር ስብሰባዎችን እናደርጋለን፡፡ በሚሊዮኖች ድምፅ ነፃነትን ለማረጋገጥ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚሳተፉበት ይሆናል፡
የህዝባዊ ንቅናቄው ዓላማ
- የፀረ-ሽብር ህጉ የኢትዮጵያውያንን በርካታ መብቶች የሚገፍ በመሆኑና ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚፃረር በመሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የተቃውሞ ድምፅ በማሰባሰብ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ጥያቄ እናቀርባለን፡፡ የድጋፍ ፊርማ (ፔቲሽን) እናስፈርማለን፡፡ ይህንንም በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን፡፡ የሚሊዮኖችን ድምፅ በመያዝ ወደ ክስ እንሄዳለን፡፡
- በሀገር ዓቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው በገጠርና በከተማ የዜጎች መፈናቀልና የመሬት ቅርምት እንዲቆምና መፍትሄ እንዲያገኝ እንጠይቃለን፤
- የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እንዲቀረፍ፤ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች እንዲወሰዱ እንጠይቃለን፤
- የንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር፤ ማጥላላትና ማዋከብ እንዲቆም፤ ገዥው ፓርቲ ህግ አውጭና ነጋዴ የሚሆንበት ስርዓት እንዲያበቃና የግሉ ሴክር በልማቱ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው እንጠይቃለን፡፡
ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሳካት ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ለሀገር ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያንና የሀገርን ጥቅም ለማስቀደም የሚፈልጉ የኢህአዴግ አባላት እንዲሳተፉ ሀገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 12 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ