June 13, 2013
8 mins read

Sport: የመሠረት ደፋርና ገንዘቤ ዲባባ የኦስሎ ፉክክር ዛሬ በጉጉት ይጠበቃል

ከቦጋለ አበበ
ከረጅም ርቀት ንግሥቶች መካከል አንዷ የሆነችው መሠረት ደፋር ከወጣቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ጋር በዛሬው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ተገምቷል፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በአምስት ሺ ሜትር የሚያደርጉት ፉክክር ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ሆኗል፡፡
መሠረት በአምስት ሺ ሜትር ርቀት የዓለም ቁጥር አንድ አትሌት መሆኗ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ርቀቶች ድንቅ አቋም ይዛ ብቅ ያለችው ወጣቷ አትሌት ገንዘቤ ዘንድሮ መሠረትን ሁለት ጊዜ አሸንፋታለች፡፡ አትሌት መሠረት ደግሞ ክብሯን ለማስጠበቅ ብርቱ ጥረት የምታደርግ በመሆኗ የዛሬውን የዳይመንድ ሊግ ፉክክራቸውን ጠንካራ ያደርገዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡
መሠረት ባለፈው ለንደን ኦሊምፒክ አስደናቂ ብቃት በማሳየት ከስምንት ዓመት በኋላ የአምስት ሺ ሜትር የቀድሞ ክብሯን ማስመለስ ችላለች፡፡ ይህም መሠረትን የርቀቱ ንግሥት መሆኗን ያስመሰከረላት ሆኗል፡፡ መሠረት በዛሬው ውድድርም ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ያስመለሰችውን ክብሯን ትደግማለች የሚል ግምት እንዲሰጣት አድርጓል፡፡
በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ ላይ የወጡ የተለያዩ ዘገባዎች የውድድሩ አሸናፊ ማን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ አልሰጡም፡፡ ይሁን እንጂ መሠረት በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ በገንዘቤ ከተቀደመች በኋላ ሰፊ የልምምድ ጊዜ ስላገኘት አቋሟን አስተካክላ ወደ ውድድር እንደምትገባ ተገምቷል፡፡
ምሽት ላይ ቢስሌት ስታድየም ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ውድድር በርቀቱ ሁለት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ የቻለችው መሠረት የተለየ ብቃት ይዛ ብቅ እንደምትል የስፖርቱ ተንታኞች እምነት አላቸው፡፡
ገንዘቤ በውድድሩ ብቃቷ ቀንሶ ትቀርባለች የሚል እምነት ባይኖርም ሰሞኑን በተለያዩ ርቀቶች እንደመሳተፏ መጠን ድካም ስለሚኖርባት መሠረትን እስከ መጨረሻ መታገል ላይሆንላት ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህም የተነሳ መሠረት የገንዘቤን ድካም ተጠቅማ የማሸነፍ እድል አላት፡፡
አትሌት መሠረት በአምስት ሺ ሜትር ከገንዘቤ የተሻለ ትልቅ ስም አላት፡፡ ከሁለት የኦሊምፒክ ድሎቿ በተጨማሪ አራት የዓለም ሻምፒዮና ሜዳሊያዎች(አንዱ የወርቅ ነው)፣ ስድስት የዓለም የቤት ውስጥ ሜዳሊያዎች (አራቱ የወርቅ ነው) እንዲሁም አራት የአፍሪካ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችላለች፡፡
እ.ኤ.አ 2007 ላይ መሠረት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ኦስሎ ላይ ወደ 14፡16፡63 ማሻሻሏ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም የመሠረት የአጨራረስ ብቃት በርካታ ደጋፊዎች እንድ ታፈራ አስችሏት ነበር፡፡ በዛሬው ውድድርም መሠረት ቢስሌት ስታድየም ውስጥ በርካታ ደጋፊዎች እንደሚኖሯት ይጠበቃል፡፡
መሠረት በወጣቶች ሻምፒዮና የርቀቱን ክብረወሰን ከአንድም ሁለት ጊዜ ያሻሻለች አትሌት ነች፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሦስትና አምስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ባለክብረወሰን ነች፡፡ ይህን የመሳሰሉት እውነታዎች ከመሠረት የርቀቱ ልምድ ጋር ተዳምረው የአሸናፊነት ሚዛኑ ወደ እርሷ እንዲያደላ ያደርጋሉ፡፡
በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የቀድሞ ጓደኛዋ አበባ አረጋዊን እየተፎካከረች የምትገኘው ገንዘቤ፣ በዘንድሮ ዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በሁለት ዓይነት ርቀቶች በመሳተፍ የእህቷ ጥሩነሽ ዲባባ ተተኪ እንደምትሆን አሳይታለች፡፡
ገንዘቤ የውድድሮች መደራረብና ድካም ከሌለባት የሻንጋዩን ድሏን በመድገም መሠረት ላይ የበላይ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ ገንዘቤ ይህን ውድድር ካሸነፈች በዳይመንድ ሊግ በአምስት ሺ ሜትር የሚኖራት የነጥብ የበላይነት ከፍ ይላል፡፡
በዓለም ወጣቶች የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማድረግ የቻለችው ገንዘቤ በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗ የተለየች አትሌት ያደርጋታል፡፡
የዛሬው ውድድር የመሠረትና ገንዘቤ ፍጥጫ ብቻ ሳይሆን የኬንያውያን አትሌቶች ጭምርም እንደሆነ የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ኬንያውያን አትሌቶች በተለይም በለንደን ኦሊምፒክ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተወሰደባቸውን የበላይነት ለማስመለስ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በለንደን ኦሊምፒክ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩ የኬንያ አትሌቶች በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል መነሳታቸውን ተከትሎ ትልቅ ቁጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህን ቁጭታቸውን የሚወጡበት ውድድርም በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው ውድድር የቁጭታቸው መወጫ ከሚሆኑ ውድድሮች መካከል ሊካተት ይችላል፡፡
በዛሬው ውድድር የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮኗ ሜርሲ ቺሮኖ በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው ከሚገመቱ ኬንያውያን አትሌቶች መካከል አንደኛዋ ነች፡፡ በሌላ በኩል የአገሯ ልጅ ቪዮላ ኪቢዎት የውድድሩ ተካፋይ መሆኗ ፉክክሩን ጠንካራ ያደርገዋል፡፡

Go toTop