January 17, 2015
6 mins read

የሰሜን አሜረካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር አንድነት ፓርቲ የምጫ ቦርድ ትዕዛዝ እንደማይቀበለው መግለፁን እንደሚደግፍ አስታወቀ

ከአንድነት ድጋፍ ማህበር በሰሜን አሜሪካ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ጉዳዩ፡ ፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና በአንድነት ፓርቲ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ በተመለከተ፡፡

እንደሚታወቀው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት ከምርጫ ቦርድ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ በ4 ቀን ውስጥ እንዲጠራና የፓርቲውን መሪ በድምፅ አሠጣጥ መመሪያው መሠረት እንዲመርጥ ስለተገደደ አንድነት ፓርቲም በሆደ ሰፊነት በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ባያምንበትም ሕግ ለማክበርና የሠላማዊ ትግሉን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ስለሚረዳ በሌለ አቅሙ በ4 ቀን ውስጥ በአስቸኳይና በታላቁ በገና በዓል ሣምንት የጉባዔ አባላትን ከክ/ሃገር ጭምር ጉባዔ ጠርቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፋ በ4ቀን ጉባዔ እንዲጠራ ካዘዘ በኋላ በጉባዔው ተገኝቶ ምርጫውን ታዝቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጋብዞ ሣይገኝ ቀርቷል፡፡ ይህ ዓይነት የምርጫ ቦርድ ሕገ-ወጥነት በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ምርጫ ቦርድ አሁንም እጅግ በጣም በሚያሳፍርና ይሉኝታ በሌለው አካሄድ አንድነት ፓርቲንና መኢአድን በድጋሜ ጉባዔ እንዲጠሩ ሕገ-ወጥ ትዐዛዝ ለማስተላለፍ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን ውስጥ ጉዳይ የመፈትፈት: ውሣኔ የመቀልበስ እንዲሁም የፓርቲዎችን አመራር የማፅደቅ ወይም ያለማጵደቅ መብት ጨርሶ ሊኖረው አይገባም፡፡ ምከንያቱም እንደዚህ ዓይነት ጣልቃ ገብነት ካለ የፓርቲዎች የበላይ አካል የሚሆነው የአባሎቻቸው ጠቅላላ ጉባዔ ትርጉም አልባ ይሆናልና፡፡

አንድነት ፓርቲ በምጫ ቦርድ በድጋሜ የተላለፈውን ጉባዔ የመጥራት ትዕዛዝ እንደማይቀበለው መግለፁን እኛም የሰሜን አሜረካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ሙሉ በሙሉ እንደምንደግፍ እናረናገግጣለን፡፡ ምርጫ ቦርድ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ ለአገዛዙ ወገናዊነት በማረጋገጥ በአስተዳደሩ ኃላፊዎች በመታዘዝ በአንድነት ፓርቲና በሌሎች ተቃዋሚ አጋር ፓርቲዎች የሚያደርገውን ሕገ-ወጥነት አስተዳደራዊ ክፋ ሰራ እንቃወማለን! አንቀበለውም:: አገዛዙ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ ከፈለገ ህጋዊ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በህገ-ወጥነት ሣይሆን በስርዓት :በአግባቡ የጨዋታ ሜዳውን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ የተደጋጋሚ ጉባዔ ጥሩ ትዕዛዝ ህገወጥነት ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም አገዛዙ እንደዚህ ዓይነት እጅግ የዘቀጠ ፀያፍ ስራ ውስጥ ተነክሮ ያለው መጪውን ብሔራዊ ምርጫ ያለተቀናቃኝ ብቻዉን ተወዳድሮ ለማሸነፍ ካለው ጭፍን ፍላጐት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም ግን ይህ አካሄዱ ሃገሪቱን ወደ ባሰ ምስቅልቅል ይወስዳታል እንጅ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡

በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ማለትም መኢአድ: ሰማያዊ: መድረክና ሌሎችም ፓርቲዎች ተቀራርበው ትግሉን በጋራ እንዲመሩት ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ፓርቲዎቹ አገዛዙን በመቃወም ለሚያደርጓቸው ማንኛውም የሠላማዊ እንቅስቃሴዎች ከጐናቸዉ እንደምንቆም በዚህ እጋጣሚ ማሣወቅ እንወዳለን፡፡ አንድነት ፓርቲ በሚያደርጋቸው የትብብር ጥሪዎችና የአመራር ስልቶች በተናጠልም ወይም ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር ለሚያደርጋቸው ትግሎች ሙሉ በሙሉ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብም የአገዛዙን ተንኮል በመረዳት ከአንድነትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጐን በመሰለፍ የነፃነት ትግሉን እንዲያፋጥን ጥሪ አናቀርባለን፡፡

Go toTop