July 20, 2023
14 mins read

መፍጠንና መፍጠር፡ የብልጽግና ፓርቲ አዲስ ጸረ-አማራ ዘመቻ – በደሳለኝ ቢራራ

Abiy Ahmed 5 1 1ብልጽግና ፓርቲ የህወኃት መቁረጫ እና የኦነግ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ ከሁለቱም ወላጆቹ በወረሰው ክሮሞዞም የተገነባ የራሱ ማንነትና ባህርያት አሉት። በመሆኑም ዘውገኝነት፥ ሴራ፥ ውሸትና አማራ ጠልነት ከሁለቱም ወላጆቹ በቀጥታ የወረሳቸው እና ፊት ለፊት የሚታይ ገጽታው መገለጫዎች ናቸው። ሰሞኑን እያካሄደው ያለው ደንባራነትና “ዐይናችሁን ጨፍኑልኝና ላሞኛችሁ” የሚሉት ነገር፡ እንዲሁም ቀንድ ያስነከሳቸው ችኮላ ደግሞ የድቅልናው ሂደት መስተጓጎል የፈጠረው ስናዳሪነት ይመስለኛል።

ብልጽግና ስልጣን እንደያዘ በዘመቻ መልክ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየጠራ በቤተመንግስት ልዩ ግብዣ ያደርግ ነበር። አንጋፋ አንጋፋ የኪነትና ስነጥበብ ባለሙያዎች፥ ምሁራን፥ ባለሀብቶች፥ ታዋቂ ሰዎች፥ የሀይማኖት አባቶች፥ ባለሙያዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ወዘተ እየተጠሩ ተጋብዘዋል። ግብዣውም ፓርቲው በቀጣይ ሊሰራው ላቀደው ጥፋት፡ እነዚህን አካላት በይሉኝታ ዝም ለማስባል የታቀደ ዝምድና ነበር። ብዙ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በሚናገረው ዲስኩር ትክክለኛ ሀገር ወዳድ መሪ የመጣ መስሏቸው ነበር። ታክቲክ መሆኑ እየተገለጠ የመጣው በሂደት ነው። በእርግጥ አሁንም አብይን ከኦነግ-ሸኔ ለይተው የሚያዩ አሉ፤ እራሱ በመጥረቢያ የነፍሰጡር ሽል ቀዶ ሲያወጣ ካላዩ የሚገለጥላቸውም አይመስለኝም። አንዳንዶቹ ደግሞ “መፈንቅለ-መንግስት ተሞከረብኝ” ብሎ ወታደሮችን ፑሽ አፕ አሰርቶ ሲመልስ ነው ጉዳዩን መመርመር የጀመሩት። መቼም በሲኒማቶግራፈር እና ሳውንድ ሲስተም ተስተካክሎ ከፍተኛ ጥራት ባለው ቪዲዮ የሚቀረጽ ድራማ እንጅ መፈንቅለ መንግስት ሊሆን አይችልም። ያንን ድራማ ካዩ በኋላ ብዙ ሰዎች ተነጋግረዋል። የሰውየውን የማምታታት ዝግጅት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ በዚህ ድራማ ነበር የተረዱት። የሚያነቡ ሰዎች ግን ገና ሳይሾምም “እርካብና መንበር” በሚል ርዕስ የጻፈውን መጽሐፍ አይተው ማንን ተረግጦ ወደ ዙፋን ለመውጣት እንዳሰበና በምን አይነት ስልቶች ድጋፍ ማግኘት እንደሚችል በስሱ ያስቀመጠውን ተረድተውታል። በኋላም አከታትሎ ያሳተማቸው መጻህፍት ዋና አላማቸው ማወናበድ ቢሆንም በመሰረታዊነት ይዘታቸው ጸረ-አማራ መሆኑን ማንም ሊያስተባብለው አይችልም።

ከድራማው በመቀጠል ሰውየው የቀትር ጋኔን መሆኑን በገሀድ የገለጠው “በአዲስ አበባ ጉዳይ ከእስክንድር ነጋ ጋር ወደ ግልጽ ጦርነት እንገባለን” ያለ ጊዜ ነበር። በራሱ አንደበት ስለ አዲስ አበባ ጉዳይ ለፌደራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጥ፦

“ማንም አስተዳደራዊ አካልና ፖለቲካ ፓርቲ መፍትሔ ሊሰጠው ባለመቻሉ ችግሩ እየተንከባለለ መጥቶ ከእኛ ደርሷል። እኛም ችግሩን ከስሩ አንስተን በማጥናት በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ መስተዳድር መካከል ከፍተኛ ክርክር እና ድርድር በማድረግ፡ ማንም የፖለቲካ ፓርቲ ሊፈታው የማይችልን ችግር፡ ምናልባትም እኛ ባንፈታው ኖሮ ወደ ፊትም ማንም ሊፈታው የማይችልን ችግር ፈትተናል። ብልጽግና ፓርቲ ከሰራቸው ጉልህ ተግባራትም ሁሉ ትልቁ የአዲስ አበባ ዙርያን ጉዳይ ቋሚ መፍትሔ መስጠታችን ነው” ብሎ ነበር፡ አብይ አህመድ።

እንግዲህ በአንድ አመት ውስጥ፡ ቋሚ መፍትሔው የተባለውን ስምምነት ለማየት ችለናል። ታዲያ ቋሚ መፍትሔ ተብሎ ከስምምነት የተደረሰበት ምን ነበር? አማራውን ጠራርጎ ማስወጣት አልነበረም!? በእርግጥ አዳነች አበቤና ሽመልስ አብዲሳ ተከራክረውና ተደራድረው የሚያመጡት መፍትሔ ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል በወቅቱ በርካታ ምሁራን ሀሳብ ሰንዝረዋል። ክርክሩ “አማሮቹን በቤታቸው እንዳሉ ከበባ አድርገን እንግደላቸው’ እና ‘አይ ቤታቸውን አፍርሰን ካባረርናቸው በኋላ ለምነው ይተዳደሩ” የሚል እንደነበር፡ የሸገር ከተማ ከንቲባው በቅርቡ በሰጠው ቃለምልልስ ‘ህጋዊ ለማኝ አድርገናቸዋል’ በማለት አረጋግጦታል።

በመሆኑም በተመሳሳይ ስልት ሙቅና ቀዝቃዛ ፕሮፓጋንዳ በየተራ እየቸለሱ ህዝቡን በማደናገር አዲስ አበባ ላይም ሊታሰብ የማይችል የስርአት መሰረት ለማስያዝ የማይናቅ ስራ ሰርተዋል። ምናልባትም በቀጣይ አጭር ጊዜ አማራውን ከሸገር ቤቱን አፍርሰው እንደበተኑትና ከወለጋ ጨፍጭፈው እንዳጠፉት ሁሉ ከአዲስ አበባም ውጣ ሊሉት ይችላሉ። አሰራራቸው እጅግ በሚቀፍ ደረጃ ፈጣን፥ ሀፍረት የለሽ እና አረመኔአዊ ነው።

ብልጽግና ፓርቲ በሚቀጥለው ምርጫ ቢያልፍም ባያልፍም ግድ እንደማይለውና ማሳካት የሚፈልጋቸውን አላማዎች በሙሉ ከምርጫው በፊት ለማጠናቀቅ መወሰኑን ተናግረዋል። ቁልቁለት ላይ ፍሬን የበጠሰ ሲኖ በሚመስል አስፈሪ ፍጥነት ወደ መቀመቅ እየተምዘገዘገ ያለውም “ቀሪ ስራዎችን በሁለት ዓመታት ውስጥ ማጠናቀቅ አለብን” ተብሎ በፓርቲ ደረጃ እቅድ በመያዙ ነው። ቀሪ ስራዎች የተባሉትን አላማዎችም ለማስፈጸም ፓርቲው አሁን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ባሉ ዞንና ወረዳዎች አጠቃላይ አመራሮቹንና የፓርቲ አባላቱን “መፍጠንና መፍጠር” በሚል ርዕስ ስልጠና እየሰጠ ነው። “መፍጠንና መፍጠር” የኢንዶክትሪኔሽን ነው።

በአማራ ክልል ሲሰጥ የሰነበተው “የመፍጠንና መፍጠር” ስልጠና ትኩረት ያደረገው በክልሉ እየተደረገ ያለውን የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ መበተን የሚቻልባቸውን ፕሮፓጋንዳዎች እና የሀሰት ክሶች በፍጥነት እና በብዛት መፈልፈል ነው። “መፍጠንና መፍጠር” የሚለውን አገላለጽ ህዝቡ ከዚህ ቀደም “ቆርጦ ቀጥል” በሚል የሀሰተኛነት መገለጫ ሀረግ ነበር የሚያውቀው። ቆርጦ ቀጥልነት መደበኛ የፓርቲ አሰራር ተደርጎ ዘመቻ ተወጥቷል። በዚህ ዘመቻ ከሆዳም የብልጽግና ካድሬ አማራዎች እስከ ፊልድ ማርሻሉ ድረስ ያሉት የሽብር መሩ ስርአት ደጋፊዎች የተለያዩ ሴራዎችን በመፍጠርና በማሰራጨት ላይ ናቸው። ለዚህ ዘመቻ የአሰልጣኞች ስልጠና በሰጠበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንደተናገረው “ውሸት፥ ክህደትና መሀላ የትግል ስልት እንጅ የፖለቲካ ነውር አይደሉም፤ የግድያ ዘገባና የአማራ ሞት ሳያሸማቅቀን ስራችን መስራት ይጠበቅብናል፤ ስለጭፍጨፋ ዜና አትጨነቁ that is the new normal” በማለት የአማራ እልቂት ገና የሚጠበቅና የሚቀጥል መሆኑን አሳውቋል። ይሰመርበት! “የአማራ ሞት፥ ግድያ፥ ስደትና ጩኸት . . . is the new normal”! የአገዛዙ ግልጽ አቋም ‘ከዚህ የተለየ ችግር እስካልተፈጠረ ድረስ ለአማራ እልቂት መልስ ስለመስጠት አትጨነቁ፡ መደበኛ ጉዳይ ነው’ የሚል ነው።

በዚህ የመፍጠንና መፍጠር ዘመቻ ዐይናቸውን በጨው አጥበው ስማቸውንና ደረጃቸውን በማይመጥን የወረደ የሴራ ቅሌት ውስጥ ከታዩት መካከል ደግሞ ዋናው ብርሃኑ ጁላ ነው። የአምስት ዓመት ህጻን እንኳን ሊምታታበት የማይችል ዝርው ሴራውን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ፊት ቀርቦ ሲለፋደድበት፡ “ምናለ በጣም የወረደውን ሴራ እንኳ ቢያንስ ዝቅተኛ ሚና ባለው ካድሬ እንዲነገር ቢያደርጉት!” ያስብላል።  ሁሉም ሰው እንደርሱ ጅል ይመስለዋል እንዴ? በብል[ጽ]ግና ዘመን “የወታደር ጀነራል ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ አያቡካ” የሚል አስተያየት ለመስጠት ቅንጦት እንደሚሆን ይገባኛል። ቢያንስ ግን ወሰብሰብ ያለውን ሴራ መርጦ ለምን አይናገርም? ብርሃኑ ጁላ በንግግሩ ማስረጽ የፈለገው ሴራ፡ በመጀመሪያ “የአማራ ልዩ ኃይልን እንዲፈርስ ያደረጉት በክልሉ መስተዳድር ውስጥ ያሉና ለፋኖ የሚወግኑ አመራሮች ናቸው” ሲሆን ለጥቆ ደግሞ “የተበተነውን ልዩ ኃይል ፋኖ እያሳደደ ጨፍጭፎታል” በማለት ሁለቱን የዐማራ ኃይሎች የሚወግን የተከፋፈለ ህዝብ መፍጠር ነበር። ሰገጤው የዘነጋው ነገር ግን፡ ልዩ ኃይሉ ካንፑን ትቶ ሲወጣ “እኔ ፋኖ ነኝ!” እያለ መሆኑን እና ያንን ትዕይንት ደግሞ ሁሉም ሰው ማየቱን ነው።

በአጠቃላይ የኦሮሙማው አገዛዝ በአፍጢሙ ለመደፋት ሚጢጢየ ጠጠር ብቻ የሚፈልግ ዐይኑን ጨፍኖ የሚምዘገዘግ ደመነፍስ ነው። እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የሚያቆየው ነገር የለም። እስከዛ ድረስ ጊዜ ከተሰጠው ግን የሚያደርሰውን ውድመትና ኪሳራ ለማስተካከል ቢያንስ የአምስት ምርጫ ዘመናትን እድሜ የሚፈጅ ይሆናል። በመሆኑም ከአማራ ፋኖው የትጥቅ ትግል በተጨማሪ በሁሉም ክልሎች ያለው ኢትዮጵያዊ የተሰናሰለ ፈጣን እርምጃ ወስዶ በአስቸኳይ ከስርአቱ መገላገል ይጠበቅበታል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop