November 4, 2022
11 mins read

የደቡብ አፍሪካው ድርድር የጨረባ ተዝካር – ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር)

312178335 3406879756249870 1646905368792867560 nከሁለት ዓመታት ጦርነት በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ሕይወት ለህልፈት የዳረገው፣ ከቀያቸው ያፈናቀለውና ረሃብ አፋፍ ላይ ያደረሰው የኢትዮጵያ መንግስትና የትግራይ ክልል አማፂ ሃይል አረመኔያዊ የእርስ በርስ ጦርነት “ለዘለቄታው ጦርነት ለማቆም” መስማማታቸውንና በኅብረተሰቡ እየተወራ ያለውን አሉባልታ መሰል ወግ ስሰማ በአንድ ወቅት የሰማሁት ተረት ትዝ አለኝ፡፡

“ሁለት መነኮሳት ወደ ገዳም ለመሄድ በጉዞ ላይ ሳሉ ከፊታቸው ወንዝ ያጋጥማቸዋል። ያን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ሌላ ጥሩ ልብስ የለበሰች አንዲት ሴት ወንዙ ልብሷን እንዳያበላሽባት ፈርታ ግራ በመጋባት ከዳር ቆማ አዩአት። ከሁለቱ መነኮሳት አንዱም ያቺን ሴት በጀርባው ተሸክሞ አሻገራት። ከዚም መንገዳቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ አንደኛው መነኩሴ “እንዴት ከሴት ልጅ ጋር ያን ያህል ትቀራረባለህ? እንዴትስ እርሷን በመሸከም የምንኩስናን ሕግ የሚቃረን ነገር ታደርጋለህ? እንዴት…?” እያለ ተቃውሞውን ማሰማት ጀመረ። ይሁን እንጂ ያ መነኩሴ ግን ምንም መልስ ሳይሰጠው በዝምታ ይሄድ ነበር። አሁንም ወቀሳው ቀጥሏል “እንዴት የሴትን ሰውነት ትነካለህ? እንዴት ትሸከማታለህ?” እያለ ደጋግሞ እየተቆጣ ይጠይቀዋል። በስተመጨረሻም ያ መነኩሴ እንዲህ ሲል መለሰለት “እኔ ያቺን ሴት ቅድም ከወንዙ ዳር አውርጃታለሁ። አንተ ግን እስከ አሁን ድረስ ተሸክመሃታል? ለምን አታወርዳትም?”

አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር ይገጥመናል። ሌሎች ለደቂቃ የሠሩትን ጥሩ ያልሆነ ድርጊት እኛ ቀኑን ሙሉ በማሰብ ውስጣችንን እናረክሳለን። ወንድማችን አንድ ጊዜ የፈጸመውን በደል እኛ ኅሊና ውስጥ ሺህ ጊዜ እየደጋገምን እናየዋለን። ምናልባትም ያ ሰው ያንን የበደል ሸክም ፈጥኖ በንስሐ አራግፎት ይሆናል። እኛ ግን ለዚያ ኃጢአት በልባችን የተሻለ ቦታ በመስጠት ከፍ አድርገን እንሰቅለዋለን። ሠሪው ቶሎ ያወረደውን የኃጢአት ሸክም እኛ ታዛቢዎቹ ግን በኅሊናችን ተሸክመን በየሥፍራው እንዞራለን።

ያም አለ ያም አለ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱ እንዲቆም በይፋ መስማማታቸውን ድርድሩን ከአንድ አመት በላይ የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴን ኦባሳንጆ ናቸው፡፡

ድርድሩ የሰላም ሂደቱ ማብቂያ ሳይሆን የሂደቱ መጀመሪያ እንደሆነ ብንገነዘብም በ1960ዎቹ በናይጄሪያ በተነሣው የባያፍራ ግዛት የመገንጠል አመፅ የኛን ያህል ዜጋ አልቆባት ነበር። ያኔ ኦሉሴን ኦባሣንጆ የአገሪቱ መሪ ነበሩ። በመንግስትና አማፅያኑ መካከል ስምምነት እንዲደርስ፣ የናይጄሪያ ሪፐብሊክ ሳይፈርስ ጫፍ ደርሶ እንዲቀለበስ ያደረጉት ባለግርማ ሞገሱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ እንደነበሩ ታሪክ ቢነግረንም ኦባሳንጆ የኢትዮጵያን ውለታ ለመመለስ ያደረጉት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት በእስርና ያለእስር ከመደበኛ ሥራቸው የተፈናቀሉ፣ የታገቱ፣ የቆሰሉ፣ ቤተሰባቸው የተበተነ፣ የተደፈረ፣ በጅምላ ግድያ ወገናችሁን ያጣችሁ፣ አካላችሁ የጎደለ፣ ቤታችሁ የተቃጠለ የተዘረፈ፣ የተሰደደ በገዛ ወገናቸው የተዋረዱ፣ የተፈናቀሉ፣ መዘባበቻና መሳለቂያ፣ የስነልቦና ጉዳት የደረሰባቸው፣ የእለት ምግብ አጥትው ጎዳና የወጡ፣………ብዙ ግፍ የደረሰባቸው….በተለይ የአማራና የአፋር ተወላጆች የዘነጋ ድርድር መጨሻው አያምርም፡፡

ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም እ.ኤ.አ. በህዳር 2020 የጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመትና አሰቃቂ ድርጊቶችን አስከትሏል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ወይም ለአካል ጉዳት ከመዳረጉም በላይ ሚሊዮኖችን ማፈናቀሉና በርካቶችን በርሃብ አፋፍ ላይ መዳረጉ እየታወቀ በድርድሩ ላይ ምንም ዓይነት ነጥብ አለመስፈሩና ተጠያቂ የሚያደርግ ሐረግ አለመስፈሩ ስመለከተ ደርድሩ ከጨረባ ተዝካር ብዙም ያልዘለለ ለኦባሳንጆ ውለታ መክፊያ የተዘጋጀ ውል ነው፡፡

“የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” እንዲሉ በደቡብ አፍሪካ የታካሄደዉ ድርድር ነገ ለመተግበር ወደ ሥራ ሲገባ የሚያስከትለው ጉዳት ከእርስ በርስ ጦርነቱ ያልተናነሰ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

በአጠቃላይ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደዉ የዘላቂ ግጭት ማስቆም ድርድር ገበያ በዋናነት ትህነግ ማትረፍ ችሏል፡፡ የቤታችን ተደራዳሪ ባሪያዎች ዥዋዥዌ ከመጫወት ዉጭ ምንም ሚና እንዳልነበራቸው የተፈራረሙበት የስምምነት ሰነድ ስለሚያመላክት መጨነቅ የለብንም፡፡ ከስምምነቱ በኋላ ወደኋላ እያዩ መነዛነዝ፣ መጨቃጨቅ፣ መበጣበጥ ባያስፈልግም በቀጣይ ከራሳችንና ከቀጠናው ጥቅም አንፃር ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

  1. በዚህ ድርድር ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጠዉ ዋና አቅጣጫ ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ነዉ፡፡ ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ፀረ- አማራ መሆኑ ስለሚታወቅ የዚህ መርህ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ትህነግና ኦህዴድ/ኦነግ እንደሚሆኑ፣
  2. ይሄ ድርድር ዋናዉንና ወሳኙን የማንነትና የወሰን ጉዳይ (ወልቃይት፣ጠለምትና ራያ) በማድበስበስ ያለፈዉ በመሆኑ ችግሮች መቀጠላቸዉ የማይቀር መሆኑ፣
  3. በዚህ ጦርነት ብዙ ጉዳት የደረሰባቸዉ አማራና አፋር በድርድሩ ባለመወከላቸዉ የሰላም ስምምነቱን ዘላቂነት ጥያቄ ዉስጥ ይከተዋል፡፡ በድርድሩ የኤርትራ አለመሳተፍም ነገሩን ማወሳሰቡ አይቀርም፡፡ በዚህም የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ጉዳይ አደጋ ዉስጥ ይገባል፡፡
  4. የዚህ ጦርነት ዋና ግብ ትህነግን ማክሰምና ምልክቱን፣ አስተሳሰቡንና ስሙን መጠቀም ወንጀል የሚሆንበትን ስርዓት ማስፈን ሲገባዉ ትህነግ ህልዉናዉ እንዲቆይ መደረጉ፡፡ ትህነግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ተሳተፎዉ እስከቀጠለ ድርስ ለኢትዮጵያም ሆነ ለምስራቅ አፍሪካ የሰላም ስጋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ትህነግ በምርጫ አሸንፎ ክልሉን ማስተዳደሩ ስለማይቀር ለአማራ ህዝብ የስጋት ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
  5. ትህነግ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ለፈፀመዉ የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ ለፈፀመዉ ወንጀል ተጠያቂ ስለማይሆንና ካሳ ስለማይከፍል ቁርሾዉ ከህዝባችን ጋር አብሮ ይቀጥላል፡፡
  6. በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ የደረሰዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ተገቢዉ ትኩረት ባለመሰጠቱ እነዚህን አከባቢዎች መልሶ የማልማትና ማህበራዊ ምስቅልቅሉን የማስተካከል ስራዎች ዝቅተኛ ይሆናሉ፡፡
  7. የአማራን ህዝብ ጥያቄ በሚያነሱ ሀይሎች ላይ ትህነግ፣ ብአዴንና ኦህዴድ/ኦነግ በመተባበር ርምጃ ስለሚወስዱ እነዚህን ነጥቦች የሚቀለብስ አቅጣጫ ካልተከተልን ታጥቦ ጭቃ እንደሚሆን ስጋቴን ለመግለጽ እገደዳለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop