ፂዮን ዘማርያም (ኢት-ኢኮኖሚ /ET- ECONOMY)
‹‹ ጊዜው ጎዳኝ እንጂ እኔ ሰው አላማ
የአህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ!!!››
‹‹ምነው እማምዬ ለምን ታለቅሻለሽ
በወፍጮው ላይ መጁ ሲጨፍር እያየሽ!!!››……………አለማየሁ እሸቴ
በብልፅግና ጉባዔ ዕጩ ተመራጭ አስመራጭ ሆኖ መሰየሙ ትክክል እንዳልነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከስድስት ወር በኃላ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከስድስት ወራት በኃላ የወረወረው አለሎ ተንከባሎ የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተላትሞ፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አመራረጥን በተመለከተ፣ ዕጩ የሆነ ሰው አስመራጭ የሚሆን ከሆነ፣ በተለይ አስመራጭ የነበሩት የአገር መሪ ዶክተር አብይ አህመድ በመሆናቸው በምርጫው ሒደት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር አሠራር መሆኑን አስታውቆል፡፡ ጠቅልይ ሚንስትር አብይ አህመድ ራሳቸው አስመራጭ ሆነው ጥቆማ በመቀበል ‹‹ዓብይ ዕጩ መሆን አለበት ወይስ የለበትም ›› ከተሳታፊዎች ፊት ለፊት ተቀምጠው ምርጫውን ሲያካሂዱ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ የምርጫ አካሄዱን አስመልክቶ ለምርጫ ዕጩ ሆኖ የሚቀርብ ሰው፣ አስመራጭ እንዳይሆን የሚከለክል አንቀፅ በማስፈር ፣ መተዳደሪያ ደንቡን አስተካክሎ ወደፊት በሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያፀድቅ ምርጫ ቦርድ አሳስቦል፡፡ ምርጫ ቦርድ የብልፅግና ፓርቲ የመተዳደሪያ ደንቡን አስቀድሞ አለመቀበሉን በገሃድ በሪፖርቱ ሠነድ አምነዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ የሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ማሞላት የሚገባቸውን ሲያሞሉ አድሎ በመፈፀም እንዳይወዳደሩ ያገዶቸው ፓርቲዎች ምስክር ናቸው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የመተዳደሪያ ደንቡ ሳይኖረው የምርጫው አካሄድና ሂደት፣ የምርጫ አሰፈፃሚ አካል እንዴት እንደሚመረጥ፣ የዕጩ ጥቆማ፣ በሚስጢር ድምፅ አሰጣጥ፣ ድምፅ ቆጠራ፣ ውጤት ማዳመር፣ ውጤት አገላለፅ የመሳሰሉት አንኮር የፓርቲ መተዳደሪያ ደብቦች እንደሌሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በፍርሃት ድፍረት ገልፃለች፡፡ ከፈረሱ በፊት ጋሪው ቀደመ ማለት እንዲያ ነው፡፡ ትላንት በሽመልስ ከማል ዛሬ በሽመልስ አብዲሳ አሳሮን አየች ብርቱካን ሚደቅሳ!!! ብለው ዘፈኑላት ወይ የሶ አበሳ፡፡ አበበ በሶ በላ አይ የህግ ሰው ያስተማረሽ ህዝብ አያውቅም ብለሽ፣ የጮኸልሽ ህዝብ አያውቅም ብለሽ የህሊና ሠላም አጣሽ፡፡ ‹‹ ጊዜው ጎዳኝ እንጂ እኔ ሰው አላማ፣ የአህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ!!!›› በማለት የአለማየሁ እቴን ዘፈን በገጠር እረኞች በከተማ አዝማሪዎች ያዜሙት ለዚያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ለህዝብ በመቆም የህዝቡን ብሶት በማስተጋባትና ርሃብ፣ ስደት፣ እስራትና ጦርነት በማጋለጥ ሲያዜሙ ዘመናት ተቆጥሮል፡፡ ከዛሬ ያረጡ ፖለቲከኞች ሙዚቀኞች መንግሥትን በማጋለጥ በህዝብ ዘንድ ለሠላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት በመስበክ ትልቅ ተሰሚነት አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዬ) እንዳይቀርፁ ተከልክለው ነበር፡ የብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ጊዜ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ስብሰባው እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር፡፡ የሌሎች ፓርቲዎችን ከግር እስከ ራሱ ስትቀርፁ የብልጽግና ፓርቲን ዝም ማለታችሁ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባችሁ እንደሆነ ህዝብ ያውቃል፡፡ ድኃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት ይገለው ነበር ይላሉ አበው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሹማምንቶች ቪላ ቤት ተሠጥቶችኃል፣ ሦስት መኪና ተመድቦላችኃል፣ በቦዲጋርድ በቀይ ኮፍያ ኮማንዶች ትጠበቃላችሁ፣ ረብጣ ዶለር የደም ወዝ ይቆረጥላችኃል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ገና ካመሠራረቱ የአንድ ፓርቲ ሥነምግባር መመዘኛዎች ሳያሞላ የተመሠረተ መሆኑንና ምክትል ፕሬዜዳንት ያልመረጠ፣ የፓርቲው ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት ያልመረጠ እንደነበር ምርጫ ቦርድ ያውቅ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት ለጠቅላላ ጉባዔ ብቻ ቀርበው የተሸሙ መሆናቸው ህገወጥ አሰራር መሆኑን ባርዱ እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ አሳልፎል፡ በማጠቃለያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ህሊናቸው ለጥቅም የሸጡ ቅጥረኛ በመሆን የሙያ ስነምግባራቸውን ያላሞሉና የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ያቀጨጩ በመሆናቸው በሚቀጥለው ትውልድ ሙያቸውን በማርከስ በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡
ምንጭ
(1) በብልፅግና ጉባዔ ዕጩ ተመራጭ አስመራጭ ሆኖ መሰየሙ ትክክል እንዳልነበር ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ሴፕቴንበር 14 ቀን 2022