July 30, 2022
4 mins read

የባልደራስ ተወካይ ከአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያየ

295922611 640027501021842 2363535761675940881 n 1ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከአሜሪካ ኢምባሲ በደረሰው ጥሪ መሰርት በ 22/11/2014 ዓ/ም ጠዋት ኤምባሲው በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ባዘጋጀው የዉይይት ፕሮግራም የፓርቲዉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አምሃ ዳኘዉ ከአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ከሚስተር ማይክ ሃመር ጋር ተገናኝተዋል፡፡

በዉይይቱ ወቅት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል የተገኙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካው መንግስት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ላቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልሰ የሰጡ ከመሆናቸዉም በላይ ወቅታዊ የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በማብራራት የአሜሪካ መንግስት የሚከተለዉ ወደ ህወሃት ያጋደለ ፖሊሲም ሆነ አማራዉን እና ሌሎች ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ ሃይሎችን በማግለል ህወሃትን እና የኦህዴድ ብልጽግናን ለማስታረቅ የጀመሩት ጥረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሊያስገኝ እንደማይችል ገልጸዉላቸዋል።

በአገራችን በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ያለዉ በአብዛኛዉ በአማራዉ ላይ እንዲሁም በሌሎች ህዳጣን ማህበረሰቦች ላይ እየተፈጸመ ያለዉ ማነነትን መሰረት ያደረገ የዘር ጭፍጨፋ የአሜሪካ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባ፣ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲረጋጋ ባልደራስ ሊወሰዱ ይገባቸዋል የሚላቸዉን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ገልጸዉላቸዋል።

በውይይቱ ወቅት የእናት ፖርቲ፣ የአብንና የኢዜማ ፓርቲ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን እነዚህም ፓርቲዎች የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን፣ ችግሩን ለማቃለልና ለማስወገድ ያስችላሉ የሚሏቸውን የፖለቲካ መፍትሄዎች ሰንዝረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የአሜሪካ መንግስት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ መንግስታቸዉ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን በተመለከተ የነበረውን ወደ አንድ በኩል ያጋደለን ፖሊሲ ትቶ ሁሉንም ወዳካተተ የፖሊሲ አቅጣጫ ለመቀየር መወሰኑን ገልጸዉ፣ ከፓርቲዎቹ ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ይሄን የአሜሪካ መንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ለማበልጸግ ጠቃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ የአሁኑ ጉብኝታቸዉ የተጣበበ በመሆኑ፣ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ከልዩ ልዩ ፓርቲዎች ጋር ዉይይት ለማድረግ ባይችሉም፣ ወደፊት በሚመጡበት ጊዜ ሰፋ ያለ ጊዜ እንደሚሰጡ ቃል በመግባት ውይይቱ ተጠናቋል። ከውይይቱ በኋላ ልዩ መልእክተኛዉ ካወያዩአቸዉ ፓርቲዎች ተዎካዮች ጋር አንድ ላይ በመሆን ፎቶ ተነስተዋል።

 ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop