June 29, 2022
10 mins read

አሜሪካ መንግሥት በወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ የያዘውን የተዛባ አቋም አጥብቀን እንቃወማለን!

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ሰኔ 22/2014 ዓ.ም

Lisanየአሜሪካ መንግስት ከፋሽቱና አሸባሪው ትህነግ/ወያኔ ጋር ያለው ግንኙነትና ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በተቃራኒ በመቆም የሚወስዳቸው አቋሞችና ለአንድ ቡድን ያደላ ኢፍትሃዊ ድጋፎች ትክክል እንዳልሆኑና የ ኢትዮጵያን ህዝብ በእጅጉ እንዳሳዘኑ በተደጋጋሚ ስንገልፅ ቆይተናል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግስትና በአሸባሪው ትህነግ/ወያኔ መካከል “ድርድር” ሊኖር እንደሚችል በሁለቱም ወገኖች እየተገለፀ ይገኛል። ይህን የ“ድርድር” መድረክ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዋናነት የሚዘውረው ደግሞ የአሜሪካ መንግስት መሆኑ ከኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተል ማንኛውም አካል የተሰወረ አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ መንግሥት /State Department/ የወልቃይትን ህዝብ የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ /Referendum/ ሽፋን ለትግራይ ወራሪ ሃይል ለማስረከብ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በተጨባጭ መረጃዎች ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን አረጋግጧል። በተለይም ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው “ድርድር” ውስጥ ቀዳሚው አጀንዳ የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምትን ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ /Referendum/ እንዲቋጭ አቅጣጫ ተቀምጧል። ይህ የአሜሪካ መንግስት አቋም በእራሱ ሶስት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት።

1ኛ. ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደ ማንኛውም ሀገር ሉዓላዊት ስትሆን የውስጥ ችግሯን የምትፈታበት የራሷ የሆነ ህግና ስርዓት አላት። የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ሲሆን የሚፈታውም በሀገራችን ህግና ስርዓት መሰረት ይሆናል። ከዚህ ውጭ በድርድር ስም የሚቀርብ ማንኛውም ተፅዕኖም ይሁን አስገዳጅ አጀንዳ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማያከብርና የሚዳፈር በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም።

2ኛ. ወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት የጎንደር/አማራ መሬቶች እንደሆኑና ህዝቡም ጎንደሬ/አማራ እንደሆነ በዘርፈ-ብዙ /All-inclusive/ ተጨባጭ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሀቅ ነው። ነገር ግን ትህነግ/ወያኔ በወረራ ከያዛቸውና በተለይም የኢትዮጵያን መንግስታዊ ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው የሚኖሩትን ቀደምት የአማራ ተወላጆች ማንነት በሚያጠፋ ደረጃና የህዝብ ስብጥሩን በሚያዛባ ሁኔታ /demographic change/ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው የትግራይ ሰፋሪ ከሱዳንና ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በማጓጓዝ ትልልቅ ህገ-ወጥ የሰፈራ ፕሮግራሞች አካሂዷል። በዚህም ምክንያት በህዝባቸን ላይ የዘር ማፅዳትና ማጥፋት ወንጀሎች /ethnic cleansing/ ተፈፅመዋል። ይህ የተዛባ የህዝብ ስብጥርና ህገ-ወጥ ወረራ በተካሄደበት ሁኔታ “ህዝበ ውሳኔ” ይደረግ ማለት “ከሰረቀህ ሌባ ጋር ንብረትህን እኩል ተካፈል” ብሎ እንደ መፍረድ የቆጠራል። ስለሆነም ይህን ኢፍትሃዊ ፍርድ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ነው።

3ኛ. አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ/ወያኔ በተለመደ የማጭበርበርና የውሸት ዘመቻው ከወልቃይትና አካባቢው የተፈናቀሉት ትግሬዎች /Internally Displaced People/ ቁጥር ላይ እጅግ የተዛባና የተጋነነ ቁጥር በማቅረብ ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ በማጭበርበር ይገኛል። የዚህ የቁጥር የማዛባትና የማጭበርበር ዋና አላማ በሕዝበ ውሳኔ /Referendum/ ሽፋን ከ 700 ሺ እስከ 1.2 ሚሊየን የሚደርስ ትግሬ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህጋዊ ነዋሪና ባለቤትነት ለማደረግ የሚደረግ አሻጥርና ሴራ አካል ነው። ስለሆነም የአሜሪካ መንግስት በሕዝበ ውሳኔ /Referendum/ ሽፋን ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ለትግራይ ወራሪ ሃይል ለማስረከብ ካልሆነም ከ 700 ሺ እስከ 1.2 ሚሊየን ለሚደርስ ትግሬ የባለ ዕርስትነት/ባለቤተነት ማረጋገጫ ለማሰጠት የሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴና ጫና ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት በድርድር ስምና በሕዝበ ውሳኔ /Referendum/ ሽፋን ወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምትን ለትግሬ ወራሪዎች አሳልፎ እንዲሰጥ በቀጥታ በአሜሪካ መንግስታት ልዩ መልዕክተኛ ወይም በአደራዳሪዎች በኩል የሚደረግበትን ህገ-ወጥና ለትህነግ/ወያኔ ያደላ ግፊትና ጫና ባለመቀበል ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል የማድረግ ታላቅ ታሪካዊና ትውልዳዊ ኃላፊነት አለበት።

ይልቁንም ከህዝብ አይንና ጆሮ የሚሰወር ምንም ነገር እንደሌለ ታውቆ የኢትዮጵያ መንግሥት የህዝብ እውነተኛ ወገንተኝነቱን በማሳየት፣ ህዝባዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት በተሞላበት ሁኔታ አቋሞቹንና ውሳኔዎችን በተገቢው ግዜና ሁኔታ ለህዝብ እንዲያውቅ በማድረግ፦

1ኛ. የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ወቅቱን የጠበቀ ፍትሃዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ለብዙ ውስብስብ ችግር ሀገርና ህዝብን እንደዳረገ የሚታወቅ ነው። አሁንም ቢሆን መንግስት በተቻለ ፍጥነት ለህዝባችን ጥያቄ ፍትሃዊ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ አበክረን እንጠይቃለን። መንግስት ፍትሃዊ ምላሽ ከመስጠት በዘገየ ቁጥር የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ እጅግ እየተወሳሰበና በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ተጨማሪ ጫናዎችና ችግሮች እየፈጠራ እንደሚሄድ ከወዲሁ ማሳሰብ እንወዳለን።

2ኛ. የማንም ሰው ወይም ህዝብ ማንነት እውቅና ይሰጠዋል እንጂ በድርድር የሚሻሻል ወይም የሚቀየር ጉዳይ አይደለም። ከዚህም በመነሳት የህዝባችን የአማራ ማንነት ጥያቄ ፍትህ ሊሰጠው የገባል እንጂ በድርድር ወይም በሽምግልና ሊዳኝ አይችልም። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ከትህነግ/ወያኔ ጋር በሚያደርገው ድርድር የወልቃይትን ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለድርድር ማቅረብ የለበትም።

3ኛ. በመጨረሻም የዚህ ሁሉ ሴራና ሸፍጥ ዋናው አላማና ግብ የአማራ ህዝብ በሰላም፣ በነፃነትና፣ በእኩልነት በሀገሩ ውስጥ እንዳይኖር ማድረግና ኢትዮጵያን ማተራመስና ብሎም መበታተን መሆኑ ታውቆ የአማራ ሕዝብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩንና የህዝቡን ጉዳዩን በንቃት መከታተልና ለማንኛውም ግዳጅ መዘጋጀት አለበት ብለን እናምናልን።

ወልቃይትን ለትግሬ ወራሪ ለመሸጥ የታቀደው ሴራ በትግላችን ይከሽፋል!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት

665565

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop