February 13, 2022
9 mins read

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊና ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳለፈ

5617fadf643edc214073408bc4558f8b

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አስቸኳይ ትኩረት በሚሹ ሀገራዊና ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተሉትን ውሳኔዎችና ቀጣይ የአፈፃፀም አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡

  1. ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ፣

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሀገራዊ ፖለቲካችን አልፋና ኦሜጋ ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑባት፣ ሰላምና ደህንነት የተረጋገጠባት፣ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዬጵያዊ እውንነት ማረጋገጥ እንደሆነ በጥብቅ ያምናል፡፡

በዚህም መሰረት አብን ግጭትና ጦርነት ምርጫ ሆነው የማይቀርቡበት የሠለጠነ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ባህል በመገንባት ሰላማዊ ፣ ህጋዊና ፍትሃዊ ተዋስኦን መርህ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የምትገኝበትን ፅኑ ቀውስና ምስቅልቅል ለመግታትና በህዝባችን ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ በመቀልበስ ሀገርንና ህዝብን ወደ አስተማማኝና ዘላቂ ማህበራዊ ሰላምና ህብር፣ ጥቅል ሀገራዊ መግባባት፣ አንድነትና ልማት ለማሸጋገር ብሔራዊ ምክክር ከምንጊዜውም በላይ አንገብጋቢ መሆኑን ይገነዘባል፡፡

ለዚህም ሲባል የተጀመረው የብሔራዊ ውይይት ሂደት ከቅድመ ዝግጅቶቹ ጀምሮ ተአማኒነት፣ ግልፅነትና አካታችነት እንዲኖረው፣ በጋራ መረዳዳት፣ በመግባባትና ፍትኃዊ አማካኝ ላይ እንዲመሰረት እና በውጤቱም ሁላችንንም አትራፊ የሚያደርግና ድል የሚያጎናፅፍ እንዲሆን አብን በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል፡፡

የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሀገራችን የምታልመው የምክክር ሂደትና ማደማደሚያ የሚሆን አዲስ ብሔራዊ ውል ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ሂደቶች በአሸናፊዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ፍላጎት ነፀብራቅ ሆኖ የጋራ ይሁንታ እንዲያገኝ፤ በተለይም በአማራው ህዝባችን ላይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የተፈፀሙ ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጥቃቶች ፍፁም እንደማይደገሙ ማረጋገጥ እንደሚገባ በአፅንኦት ተወያይቷል፡፡

በህዝባችን ላይ ሲፈፀሙ የቆዩትና የቀጠሉት ጥቃቶች መዋቅራዊና ስርዓታዊ ገፅታና ድጋፍ ያላቸው መሆኑን፣ በከፍተኛ ቅንጅትና ዕቅድ የተፈፀሙ መሆናቸውን፣ በርካታ ምድብና ዝርዝር እንዳላቸው በማስመር እውቅና መሰጠት፣ እውነት እንዲወጣ ማድረግ፣ ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ ካሳ መከፈል እና አጠቃላይ ፍትህ መስፈን አለበት የሚለውን አቋሙን አፅንቷል።

ስለሆነም የብሄራዊ ውይይትቱና ማዕቀፉ ለህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች እልባት ማስገኘት በሚያስችል ሁኔታ መከናወን እንዳለበት በማስረገጥና ከወድሁ ወሳኝ ዝግጅቶችን ማድረግ ይገባል የሚል አቋም በመያዝ የዝግጅትና የትግበራ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በዚህ ረገድ አብን የሚጠበቅበትን ሚና ባግባቡ ለመወጣት በአንድ በኩል የአማራን የፖለቲካ ኃይሎችና መላውን ህዝብ በጋራ ጥያቄዎቹ፣ ጥቅሞቹና ፍላጎቶቹ ዙሪያ በአንድነት ለማሰለፍ የተጀመሩ ስራዎችና ዝግጅቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ፣ ለብሔራዊ ድርድሩ የሚመጥንና አስተማማኝ የሆነ ጠንካራ አማራዊ አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ስልቶችን በመለየት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል ከመሰል ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኃይሎችና ማህበረሰቦች ጋር በሚያስተሳስሩን ሀገራዊ አጀንዳዎች፣ ግቦችና ራዕዮች ዙሪያ ተግባቦትና አስቻይ ትብብረሮችን ለመፍጠር የሚደረጉት ጥረቶች ተጠናከረው እንዲቀጥሉ ውሳኔ በማሳለፍ ተጨማሪ የስምሪት መመሪያዎችን ሰጥቷል፡፡

በዚህ ረገድ የአማራ ፖለቲከኞች፣ ማህበራዊ አንቂዎችና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ተፅእኖ ፈጣሪ አካላት የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ አጠቃላይ የማህበረፖለቲካውን አቅጣጫ የሚወስን ጉልህ አጀንዳ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በዚህ ልክ ኃላፊነት እንዲወስዱ፣ በጎና አወንታዊ ሚና እንዲጫወቱና ለሂደቱ ስኬታማነት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ታሪካዊ ጥሪ ያቀርባል።

  1. የንቅናቄውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ፣

የአብን ብሄራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሀገራችንና ህዝባችን የሚገኙበት ወሳኝ የታሪከ እጥፋት የሚጠይቀውን ጠንካራና ሁለገብ ትግል ለማድረግ የሚያስችል አጠቃላይ ድርጅታዊ አቋም ላይ መሆን አማራጭ እንደሌለው ያምናል፡፡

ይሄን ለማረጋገጥ በንቅናቄው የማዕከላዊ ኮሚቴ በተቀመጡና ስምምነት በተደረሰባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ ጥናቶች ውጤት በሰነድ እንዲቀርብ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ኃላፊነት የወሰዱ ኮሚቴዎች በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አጠናቀው እንዲያቀርቡ በማሳሰብ ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ምደባ አድርጓል፡፡

በመጨረሻ የጠቅላላ ጉባኤ አመቻች ኮሚቴው የጉባኤ ተሳታፊዎችን ምልመላ በማስመልከት አዘጋጅቶ ያቀረበውን ሰነድ አግባብነት ካላቸው ህግጋት፣ የንቅናቄው ደንብና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያዎች አንፃር በመገምገምና አስፈላጊ የማሻሻያ ሀሳቦችን በማካተት ለአፈፃፀም ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ረገድ የቅድመ ዝግጅት መርሃ ግብር ዝርዝሮችን በማውጣት የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲደረግ ውሳኔ በማሳለፍ የዕለቱን ስብሰባ አጠናቅቋል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ !

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

የካቲት 5 ቀን 2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop