የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታና የአዋጁን አፈጻጸም ማምሻውን ገሞግሟል። ዕዙ ለኅብረተሰቡ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ፣ የአዋጁን አፈጻጸምና ወታደራዊ ርምጃዎች በመገምገም የተለያዩ ድሎች መመዝገባቸውን አረጋግጧል።
በዚህም መሠረት፦
1. የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ፣ የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልሎች ሕዝብ የተደረገላቸውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ወደሁሉም ግንባሮች ከትቷል። ሌሎችም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
2.በባቲ– አሳጊታ ግንባር የጥፋት ኃይሉ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ከ20 ያላነሡ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አድርጓል። ጀግኖቹ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀትና በንሥሮቹ የአየር ኃይል በመታገዝ፣ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሣራ በማድረስ፣ ሁሉንም የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አክሽፈው ወራሪው ሽንፈትን እንዲከናነብ አድርገውታል። ሚሌን ለመያዝ የነበረውንም ፍላጎት የሕልም እንጀራ አድርገውበታል።
3. በትግራይ እና አፋር ክልል ወሰን ላይ ቢሶበር አካባቢ ጁንታው ዛሬ የከፈተውን አዲስ የማጥቃት ሙከራ፣ አንበሶቹ የአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል የጠላትን አከርካሪ ሰብረው በዚህ ግንባር የመጣውን ጠላት አሳፍረው መልሰውታል።
4. በወረኢሉ ግንባር ለመስፋፋት አስቦ የተንቀሳቀሰው የጠላት ኃይል፣ በደቡብ ወሎ ሚሊሻና በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተመትቶ መክኗል።
5. በአቀስታ ግንባር ለመንቀሳቀስ አስቦ የነበረው የጁንታ ኃይል በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ወሎ ሚሊሻ ተመትቶ ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ተገድዷል።
6. በከሚሴ ግንባር ያሉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሞ ብሔረሰብና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ሚሊሻዎች ባለፉት አምስት ቀናት ባደረጉት ተጋድሎ፣ ወረራውን በመቀልበስ፣ ወደ ፀረ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተሸጋግረዋል።
7. በማይጸብሪ ግንባር የጥፋት ኃይሉ ተደጋጋሚ ፀረ ማጥቃት ቢያደርግም እንቅስቃሴው ከሽፏል።
በአጠቃላይ በአማራና በአፋር ክልሎች የክተት አዋጁን ተከትሎ በጠላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ አመርቂ ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህ መሠረቱ የሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ መነሣሣትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የፈጠረው ንቅናቄ መሆኑ ተረጋግጧል።
8.በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮጉድሩ እና በምሥራቅ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ፣ ሰላማዊውን ሕዝብ በመግደልና ንብረት በመዝረፍ፣ የጁንታውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረውን አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በመደምሰስና ግብር አበሮቹን በቁጥጥር ሥር በማድረግ ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ የጋራ ጥምረት፣ ከፍተኛ ድል ተጎናጽፈዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተደረገለትን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበልና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ይህ አኩሪ ድል እንዲመዘገብ አድርጓል። ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያደርጋል።
ድላችንን አጽንተን መቀጠል እንድንችል፣ ዕዙ የሚከተሉትን ሦስት ትእዛዞችን አስተላልፏል።
1. የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ባለፉት ቀናት አኩሪ ውጤቶችን አስመዝግቧል፣ ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፣ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችም ተይዘዋል። ይህ ያስደነገጠው ጠላት የጸጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት፣ ለማሸማቀቅና ሥራቸውን በሙሉ ዐቅም እንዳይሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካለት መኖራቸውን ዕዙ አረጋግጧል። በእነዚህ አካላት ላይ በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ተሰጥቷል።
2. የጸጥታ ኃይሎች ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ ይህ መግለጫ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዲያስመዘገብ ታዟል። ይህን በማያደርጉት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ተላልፏል።
3. ሕገወጥ ግለሰቦች ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ደንቦችና የአፈጻጸም መመሪያዎች፣ እንዲሁም ከባንኮች ሕጋዊ አሠራር ውጭ፣ በተጭበረበረ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እያካሄዱ መሆኑ ተደርሶበታል። ለዚህም በጊዜው ተገቢው ርምጃ ተወስዷል። በመሆኑም ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎችና መመሪዎች ውጭ ሲሠሩ በሚገኙት ባንኮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድ ታዟል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማንኛውም የተጭበረበረ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሰነድ ይዘው በተገኙ ላይ ከወትሮው በተለየ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድ ታዟል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ