በቅድምያ፣የምንወዳትየአገራችንኢትዮጵያርዕሰ-ብሔርእንደመሆንዎመጠን ኢትዮጵያንለመታደግናከጠላትለመከላከልየሚያደርጉትንጥረትእንደምንደግፍለመግለጽእንወዳለን።
የጀግናው አርበኛ የሻለቃ ለማ ወልደጻድቅ መታሰብያ ድርጅት ዓለም ያወቃትን፣ ያከበራትን፣ የአፍሪካና የመላ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርማና መመክያ የሆነችውን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሰንደቅ ዓላማ ህጋዊ አግባብነት ባለው መንገድ ዳግም በመላው አገራችን በክብር ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እርስዎ ለሚመሩት መንግሥት ይፋዊ አቤቱታ ካቀረበ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነት በድል አድራጊነት ከአሸነፍን በኋላ፣ የኢትዮጵያ ትክክለኛና እውነተኛ ሰንደቅ አላማ፤ ንጹሁ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቃችን በመላው የአገራችን ክፍል ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተገቢውን ፖሊቲካዊ ትኩረትና ህገ -መንግሥታዊ መፍትሔ እንደማይነፍጉት በብዙ ሚሊዮን የምንቆጠር አገር ወዳድና ኩሩ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠላቶቿን ሁሉ ተመክታ ያሸነፈቻቸው በንጹሁ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዪ ሰንደቅ አላማችን ነው። በኢትዮጵያዊነት አርማና መንፈስ አባቶቻችን አድዋ ድረስ ዘምተው ጠላትን ድል ለማድረግ የቻሉት በጥንታዊው ሰንደቅ ዓለማችን ስር ተሰባስበው ነው። አሁንም የተነሳብንን ጠላት ለማንበርከክ፣ አስተማማኝ ድል ለመቀዳጀትና ጣፋጩን የኢትዮጵያዊነት ድል ጽዋ ለመቋደስ፣ ዛሬም ከንጹህ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ስር መሰባሰብ ግድ ይላል።
በተቃራኒው ወገን የተሰለፉ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ሃይሎች የሚመኩበትና ኢትዮጵያዊነትን የሚጻረር የራሳቸው መገለጫ አርማ አላቸው። እነዚህ እኩይ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሚወክሏቸው አርማ ስር ተሰባስበው አገራችንን ለማጥፋትና እርስዎን ከስልጣን ላይ ለማውረድ ቀን ተሌሊት እየተጉ እንደሆነ ለእርስዎ ማስረዳት የሚያስፈልግ አይመስለንም። ይሁን እንጂ፣ እርስዎ ኢትዮጵያን ለመታደግ እየጣሩ ያሉት፣ ወያኔ በፈጠረው ጸረ-ኢትዮጵያዊ ባንዲራ ስር ኢትዮጵያዊያንን ለማሰባሰብ በመሞከር ነው። ይህ በፍጹም ሊሆን የማይችልና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ሙሉ በሙሉ የሚጻረር መሆኑን ሳንጠቅስ አናልፍም።
የጸረ-ኢትዮጵያዊያን አላማ ከኢትዮጵያዊያን አላማ ጋር የሚጻረር መሆኑን የምናስረዳቸው እነሱን በመምሰል ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሆነን በመገኘት ነው። ጠላቶቻችንን የምናሽንፈው እነሱ እንድንገባላቸው በሚፈልጉት ወጥመድ ሳይሆን ወይም ደሞ እነሱ የቀደዱልንን ጨርቅ በመልበስ እንዳልሆነ ለእርስዎ ማስረዳት ያስፈልጋል ብለን አናስብምና የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ መላ ይመታለት!
ሶስቱ ቀለማት ያለው ባለኮከቡ የወያኔዎች ባንዲራ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስብና ለድል የሚያበቃ ስላልሆነ በአስቸኳይ ለሕዝባችን ብርታትና ጽናት ይሆን ዘንድ፣ ወያኔን የሚፋላሙ ቁርጠኛ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ የአገራችንን መለዮ ለባሾችና ሰራዊት በሁለም ቦታ፣ የአገራችንና የአንድነታችንን መገለጫ አርማችን የሆነው፣ ንጹሁ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዲሰቀልና ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያወጁ በዚህ ግልጽ ደብዳቤ፣ በምንወደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት፣ ከአባቶቻችን በወረስነው በማያወላውል የኢትዮጵያዊነት መንፈሥና ስሜት እንጠይቅዎታለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ ይሄን ደብዳቤ የምታነቡ መላው ኢትዮጵያዊያን በጥንታዊ ጀግናው አርበኛ በሻለቃ ለማ ወልደጻድቅ መታሰብያ ድርጅት ስም ሰንደቅ አላማችን እንዲመለስ የተጀመረውን ዘመቻ በመደገፍ፣ ከታች ያለውን ማስፈንጠራያ በመጫን፣ ፊርማችሁን እንድትፈርሙ በጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች፣ በኢትዮጵያ ሰራዊትና መለዮ ለባሽ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እንጠይቃለን።
https://www.change.org/RestoreEthiopianFlag
ድል ለኢትዮጵያ!
ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል!!
አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!!
ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!!!!
ነብያት አክሊሉ ደምሴ
የሻለቃ ለማ ወልደጻድቅ መታሰብያ ድርጅት