September 10, 2021
5 mins read

ሸበረኸ እንቁጣጣሽ! – በላይነህ አባተ

enk

ያለፉትን ልታስታውሽ፣
ያዘነን ልብ ልታበራች፣
የጠገበን ልታስታግሽ፣
የተራበን ልትመጸውች፣
በጷጉሜ ውኃ እድፍ አጥበሽ፣
አዲስ ተስፋ ምህረት ይዘሽ፣
እንንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፣
ሳምንት ወራት ዓመት ቆጥረሽ፡፡

ወፍ አሞራው የሚያደምቅሽ፣
ጅረት ወንዙ የሚያዜምሽ፣
ሜዳ ጋራው የሚያጅብሽ፣
ሁሉ እሚልሽ እንኳን መጣሽ፣
ጨለማ ክረምትን ፈንቅለሽ፣
ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፣
ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፡፡

ምድሩ በመስክ ተለብጦ፣
ሶሪት ላባ ከውስጥ ሽጦ፣
ፍንትው ብሎ ተንገልጦ፣
እንግጫ አድጎ ወጥቶ ወጥቶ፣
በፍልሰታ ተንሰራርቶ፣
ችብሃ መስሎ ወዙን ተፍቶ፣
ሸበረኸ ፊቱ ፈክቶ፡፡

ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፣
ባለም አምሳል ያላገኘሽ፣
ለየት ብለሽ የተሠራሽ፣
ልጅ አዋቂው የማይጠግብሽ፣
ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፣
ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፡፡

ወፏ በራ እየወጣች፣
ክረምት ቤቷን እየተወች፣
ስለት ፉጨት እያሰማች፣
ሸበረኸን ታዜማለች፣
ለእንቁጣጣሽ ትዘፍናለች፡፡

ወኔአም ጎብዝ ሃይ ሎጋው ሲል፣
ልባም ቆንጆ በለው ስትል፣
ዳገት ጋራው ያስተጋባል፣
ሸበረኸን ያዳምቃል፡፡

ምድሩ ጪቃን አወላልቆ፣
አደይ ለብሶ ባደይ ደምቆ፣
ከላይ እታች ፈነዳድቆ፣
እያሳቀ እሱም ስቆ፣
ይህን ከዚያ አንፀባርቆ፣
ጉብላልት አስደልቆ
ከንፈር ወዳጅ አስተዋውቆ፡፡

ወንዙ እንዲሁ ተጠራርቶ፣
አፈር ኮረት ማፈስ ትቶ፣
ዘና ብሎ ፊቱ ፈክቶ፣
ልጅ አዋቂ አስደስቶ፣
ኃጥያት አጥቦ አነጣጥቶ፣
እያዜመ በዋሽንቱ፣
ዳግም ያምጣሽ በያመቱ፣
ሸበረኸ የኛይቱ፡፡

ቤተክሲያኑ ባበባ አምሮ፣
በአገር ልጆች ዙሪያው ታጥሮ፣
ዓለም ሲቀልጥ በከበሮ፣
ካህን ቄሱ ሻሹን አስሮ፣
ፀናፅሉን ሿ! ሿ! አድርጎ፣
ወረብ ሲያደርስ ዘንጉን ሰብቆ፣
ሸበረኸ ሲል ሁሉ አብሮ፡፡

እንግጫውም ተጎንጉኖ፣
በአደይ ሶሪት ተሽቆጥቁጦ፣
ኮረዳ አንገት በዚያ አጊጦ፣
የጎበዝ ልብ አስደንግጦ፣
በሎሚ ኳስ ደረት መቶ፣
ከንፈር ወዳጅ ከዚያው ቀልጦ፡፡

እሸት ቆንጆ ተደጅ ወጥታ፣
ስትል ዘፍና ውብ አበባ፣
ተው አብራልኝ ሶሪት ላባ፣
ጎበዝ ወጥቶ ሲያስተጋባ፣
የፍቅር ችቦ ሲያበራ፡፡

የጦቢያ ልጅ ጥርን ንቆ፣
ከመስከረም ተቆራኝቶ፣
ዘመን ሲቆጥር በራስ ኮርቶ፣
ተዓለም ሁሉ ተለይቶ!

ያበባ ዓይነት ወጥቶ ፈክቶ፣
አደይ በምድር ፈነዳድቶ፣
የሶሪት ዘር ነቂስ ወጥቶ፣
ተእንግጫ ጋር ተዋህዶ፣
እንደ ድሪ በአንገት ገብቶ፣
ሸበረኸን አስጨፍሮ፣
ከንፈር ወዳጅ አስገብይቶ፣
በእንቁጣጣሽ ምኑ ቀርቶ!

የእኛ እመቤት እንቁጣጣሽ፣
እኛ እንደዚህ ስንወድሽ፣
አሲረዋል ጠላቶችሽሽ፣
ተውስጥ እርጉም ባንዳዎችሽ፣
ተመስከረም ሊያባርሩሽ፣
ተጥር ወሮች ሊወሽቁሽ፡፡

ቀናተኛ ቢንጨረጨር፣
ሸበረኸን ቆርጦ ሊጥል፣
ራስ ደጀን እምቢኝ ይላል፣
ላሊበላ ማት ያወርዳል፣
ያባይ ጋራ ይናወጣል፣
ቢጫ መልበስ አልተው ይላል፣
ጎበዝ ቆንጆን ያስደልቃል፣
አበባዬን ያስጨፍራል፡፡

ከሀዲያን ቢታገሉሽ፣
ግን አትወድቂ ተሸንፈሽ፣
መረጃዎች እስካሉልሽ፣
ሶሪት አብቃይ ሜዳዎችሽ፣
እንግጫ አጠጪ ወንዞችሽ፣
ሻደይ መጋቢ ጅረቶችሽ፣
አደይ ለባሽ ተራሮችሽ፣
ሸማይዋነ እንቁጣጣሽ፣
ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፤
ከርሞም ደሞ ትመጫለሽ!

በዓለም አምሳል ያላገኘሽ፣
ለየት ብለሽ የተሰራሽ፣
ልጅ አዋቂው የማይጠግብሽ፣
በደስታ የሚያዜምሽ፣
ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፣
ወሰን የለሽ ይሁን ዕድሜሽ፣
ሸማይዋነ እንቁጣጣሽ፣
ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop