በጾም በፀሎት ቀዳሹ በሰላም ጊዜ አምራቹ፣
በጦርነት ወቅት ዘማቹ የአገር ዘበኛ ተኳሹ፣
መገፋትህን አጢኖ መለኮት ይርዳህ አራሹ፡፡
ሙሴ ሕዝቡን እንዲያድን በጽላቶቹ የረዳው ያ ጌታ፣
አንተንም በታቦቶችህ ያጅብህ ትውልድ ለማትረፍ ስተጋ!
ጥበብ ዘዴውን ላላዩት አርሶ መብላትን ባስተማርክ፣
እህሉን ዘርተህ አርመህ አገሩን ምድሩን በቀለብክ፣
እንደ ባይተዋር ቆጥረውህ ታገርህ ነቅለህ ውጣ አሉህ፣
እግዚአብሔር ይህን ግፍ አይቶ የዳዊት ወንጭፍ አስያዘህ፡፡
እኛ ገንዘብ ለማውጣት ስንሳሳ አንተ ነፍስህን የሰጠህ፣
እንደ ክርስቶስ ለትውልድ ለመሞት ቆርጠህ የዘመትክ፣
ተፈሪሳዊ ቁማር ጠብቆ ያባቶች አምላክ ያበርታህ፡፡
ስንቶች ሆድን ቆዝረን አፍን ለጉመን ስንተኛ፣
አንተ በባዶ ሆድህ አገር ልታድን ስትለፋ፣
በመላእክቱ ያጅብህ የማያንቀላፋው ያ ጌታ!
ወራሪ ጠላት ተስፋፊን ወደ መጣበት መልሰህ፣
ለአምስት ሺ ዘመናት በከንች በማገር ገንብተህ፣
አገርን ለቀጣይ ትውልድ በኩራት በክብር ያስረከብክ፣
የግፉዓን አምላክ አሁንም የድልን ሸማ ያልብስህ፡፡
የዳዊት መዝሙር ሻጥ አርገህ እንደ ነበያት ስላዩህ፣
ባልተገረዘ ላንቃቸው ጠንቋይ እያሉ የሚያሙህ፣
ሐፍረት መሸፈን ተምረው ዛሬ ገልብጠው የሚያዩህ፣
ሳትበላ ሌሎች ባለበስክ በባዶ እግሩ ሃጅ የሚሉህ፣
በሌጣ እግሮቹ የሄደው ክርስቶስ ዛሬም ጥናትን ይጋትህ፡፡
ለብዙ ዓመታት ታግሰህ ሳትድርስባቸው ሲደርሱ፣
እንደ ፋሽሽቶች ጣሊያኖች ተደጅህ ሞፈር ሊቆርጡ፣
ተባእድ ጀርባ ተጣብቀው ጉልት እርስትህን ሲወሩ፣
የጎብዝ አለቃን አብዝቶ ባንዳን አጥፍቶ ተምድሩ፣
እንደ አምስቱ ዘመን አርበኞች አገሬ ወይ ሞት ባዮቹ፣
የድል ባለቤት ያድርግህ መለኮት ይርዳህ አራሹ፡፡
በላይነህ አባተ (Abatebelai@yahoo.com)
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ. ም.