የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ አማራዊ ማንነቴን በትግሬነት አለውጥም፣ ትውልዴን አላስጠፋም፣ ከትህነግ/ወያኔ ጋር ተባብሬ ኢትዮጵያ ሃገሬን አላፈርስም፣ አላስፈርስም በማለት ለ40 ዓመታት ሲታፈን፣ ሲገረፍ፣ ሲዘረፍ፣ ሲገደል፣ ሲሰደድ፣ በጀምላ ሲጨፈጨፍ ኖሮ በከፈለው እጅግ መራራ መስዋዕትነት እነሆ ሃገርህን ከእነ ሙሉ ክብሯና ዳር-ድንበሯ በክብር አስረክቧል።
እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራ ወገኖችህ እስከ ትላንቱ የማይካድራ ጭፍጨፋ ድረስ በጅምላ ስንታረድና በገፍ ስንሰደድ የኖርነው ማንነታችን ቀይረን ትግሬ አንሆንም በማለታችን፣ ኢትዮጵያን አዳክመንና በታትነን ታላቋን ትግራይ እንገነባለን ከሚል ፋሽስት ቡድን ጋር ተመሳጥረን ሃገራችንና ህዝባችንን ባለመክዳታችን፣ ይልቁንም ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከሚጠሉ ጠላቶች ጋር በተረዳነው መጠን ቀድመን እየተደራጀን አንድ ጊዜ “ከፋኝ” ሌላ ጊዜ “አርበኞች ግንባር”፣ በመቀጠል “ልሳነ ግፉዓን”፣ እንዲሁ በቅርቡ ደግሞ “የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ” በማለት በሄድንበት ሁሉ እውነትን ይዘን በኢትዮጵያዊ ጀግንነትና ኩራት በመታገላችን ምክንያት የከፈልናው ክቡር መስዋዕትነት ነው!
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!
ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከተቋቋመበት እለት ጀምሮ የትህነግ/ወያኔን እኩይና ፋሽታዊ ሴራ፣ አላማና፣ ራዕይ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለመላው ዓለም ያለመታከት አጋልጧል። ሴራውንም ለማክሸፍና ህዝባችንና ሃገራችንን ከተደገሰላቸው ጥፋትና መበታተን ለመታደግ ታግሎ አታግሏል።
እንደ ዛሬ ሳይሆን ፋሽቱ ወያኔ ከነሙሉ አቅሙና ስልጣኑ በነበረበትና መላውን አፍሪካ እጨፈልቃለሁ በሚልበትና የኢትዮጵያን ህዝብ በፋፁም አፈና ውስጥ በጣለበት በእነዚያ የእብሪት ዘመኖቹ ላይ እንኳን ሆኖ ልሳነ ግፉዓን በትህነግ/ወያኔ መወገድ ላይ ግልፅና የማያሻማ አቋም ከነበራቸው ጥቂት ድርጅቶ መካከል ዋነኛው ነበር።
ዛሬ ትህነግ/ወያኔ የቀደመውን የማስመሰል ጭምብሉን አውልቆ ኢትዮጵያን የመበታተንና ህዝቧን ለእልቂት የመዳረግ እኩይ አላማውን በይፋ በቃል-አቀባዩ ጌታቸው ረዳ በኩል የሚደሰኩርበት ግዜ ላይ ደርሰናል።
ዛሬ ጉደኛው ትህነግ/ወያኔ ለ25 ዓመታት የኢትዮጵያን መንግስታዊ ስልጣን፣ መከላከያ ሰራዊት፣ ሃገራዊ ሃብትና፣ ንብረት በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በነበረባቸው በእነዚያ ዘመናት እንኳ ከተመፅዋችነት ያላወጣውን የትግራይ ህዝብና ያልገነጠላትን ትግራይ እገነጥላለሁ በማለት በየአደባባዩ ሲደነፋ ይውላል።
ዛሬ ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ሃብት በውጭ ሃገር ተንደላቀው የሚኖሩና በኢትዮጵያ ኢንባሲዎችና በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ የትህነግ/ወያኔ ሰዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ሲክዱና ኢትዮጵያን ሊወጉ ከባእዳን ጋር ሲዶልቱ ማየትና መስማት ዜና መሆኑ ቀርቷል።
በአጠቃላይ ዛሬ ትህነግ/ወያኔ የእናት ሃገራችን ኢትዮጵያና የህዝባችን ቁጥር አንድ ጠላት መሆኑ በአፍም በመጣፍም የተረጋገጠ የአደባባይ እውነት ሆኗል።
ውድ ወገኖቻችን!
ያለን ምርጫ አንድና አንድ ነው! ይሃውም የትግራይ ህዝብ ውስጥ መሽገው ሃገርና ህዝብ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱትን ጥቂት ወንጀለኞች የገቡበት ጉድጓድ ገብቶ ለፍርድ ማቅረብ ነው። ወይም እነ ጌታቸው ረዳ እንደሚዝቱት ኢትዮጵያ በእነሱ ወታደራዊ ወረራ ስትፈርስና ህዝቧ ለከፋ እልቂትና ባርነት ተላልፎ ሲሰጥ ቁጭ ብለን መመልከት ነው።
የልሳነ ግፉዓን ምርጫ በትግራይ ህዝብ ውስጥ መሽገው ሃገርና ህዝብ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱትን ጥቂት የትህነግ/ወያኔ ወንጀለኞች የገቡበት ጉድጓድ ገብቶ ለፍርድ ማቅረብ ነው። ስለሆነም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን የአማራ ክልላዊ መንግስት ያቀረበውን የክተት አዋጅ በመቀበል በማንኛውም ግዳጅ ለመሰማራት ዝግጁነቱን ሲገልፅ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ኩራትና ክብር ነው።
ጀግናውና ታጋሹ የአማራ ህዝብ ሆይ!
ጥንተ ጠላትህ ትህነግ/ወያኔ ለአንተ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ኑና አፈር አልብሱኝ እያለ ነውና አደራ እንዳትቀር! ጠላትህን ከአማራ ጠል ማንነቱና ከ 1968ቱ ድሪቶው ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምትገላገልበት የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰሃል እንኳን ደስ ያለህ።
በዚህ አጋጣሚ የአማራ ክልላዊ መንግስት ያቀረበልህን ይህን ታሪካዊ የክተት አዋጅ ተቀብለህ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ታሪክህን በደማቁ ትፀፍ ዘንድ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከታላቅ አደራ ጋር ጥሪውን ያቀርባል!
ጀግናው የጎንደር! የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ሆይ!
ገዳይህ፣ የልጆችህ ደም መጣጭ፣ የርስትህ ወራሪ፣ አሳዳጅህ፣ ሴት ልጆችህን ያረከሰ፣ ህፃናቶችህን ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያንን ያለጧሪና ቀባሪ ያስቀረ፣ ይልቁንም የውድ ሃገርህ ኢትዮጵያና የህዝቧ ጠላት የሆነው ፋሽቱ ትህነግ/ወያኔ ግብዓተ መሬቱ እየተፈፀመ ይገኛልና እንኳን ደስ ያለህ!
እነሆ ያ! የብቸኝነት ዘመንህ አክትሞ፣ የኢትዮጵያ አምላክ በግፍ ለ40 ዓመታት የፈሰሰው ንፁህ ደምህን ሊበቀል የኢትዮጵያን ልጆች ከዳር-ዳር አሰባስቦ በቀዬህ እንዲከትሙ አድርጓልና እንኳን ደስ ያለህ!
ይህ ሰርግ የማንም ሳይሆን የአንተ ነውና እወቅበት! ወገብህን ታጥቀህ የኢትዮጵያን ልጆች አስተናግዳቸው! እንቅፋት እንዳያገኛቸው መንገዱን ምራቸው! እንዳይጠማቸው የተመረጠውንና የተወደደውን ወይን አቅርብ! እንዳይርባቸው ሰንጋህን ከጊደሯ ጋር አረድላቸው! ማረፊያ መኝታቸውን በአማረ ስጋጃ እንጥፍላቸው! ጊንጡን፣ ጉንዳኑንና ተባዩን አጥፋላቸው!
ከሁሉም በላይ በራስህ ሰርግ ላይ እንዳታረፍድ! ከአሁኑ ቀድመህ ዝመት! አደራ!
እኛ ልጆችህ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከጎንህ ነንና አይዞህ!
የኢትዮጵያ ህዝብ ውሀ ሙላት ሆኖ ጠላትህን ጠራርጎ እየወሰደው ነውና እንትፍ ብለህ ጨምርበት!
ድል ለኢትዮጵያ! ድል ለህዝባችን!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ሐምሌ 19/ 2013 ዓ.ም
ኦሃዮ/አሜሪካ