ለኢትዮጵያ በጋራ ከመቆም ልዩነት አያግደንም።
ኢትዮጵያ ሲመቸን የምንወዳት ሳይመቸን የምንተዋት ሳትሆን ሁሌም ከጎኗ መቆም የሚገባን የአደራ ምድር ነች። ባለታሪክና ለእሷ ነጻነትና ክብር ሲባል ሕይወታቸውን ሳይሳሱ የሰጡ የጀግኖች አገር ነች። ክብሯን በደም የጻፉ አባት እናቶቻችን ቀጣይነቷን እንድናረጋግጥ አደራ ያስተላለፉልን መተኪያ የሌላት አገር ነች። ምናልባትም ለዘነጉት እሩቅ ሳንሄድ የሶማሌን የግዛት መስፋፋት ለመግታት ካራማራ ላይ እራሳቸውን የሰው፤ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ በኤርትራ በረሃዎችና በየቀበሮ ጉርጓድ ውስጥ የቀሩትና የወያኔዎችን የከፋፍለህ ግዛ አላማ ለማምከን ሲታገሉ የተሰው ኢትዮጵያውያን ደም ይፋረደናል።
ለውጥ ከመጣ ወዲህ ለኢትዮጵያ ተስፋ በማየቱ ዳያስፓራው ከመቸውም ጊዜ በተለየ መንግሥትን ለማገዝ የተነሳሳንበት ወቅት ነው። የሚችለውንም በማድረግ ላይ ይገኛል። ለአገሩ ስኬት ከመቆርቆር እንጂ አብዛኛው በቡድንም ሆነ በግል ከኢትዮጵያ የሚሻው አንዳች ነገር የለም። መሻቱ ሰላሟ እንዲሰፍን፤ በእድገቷ እንድትራመድ የተፈጥሮ ሃብቷንና የሕዝቧን እምቅ ሃብት ተጠቅማ የብልጽግናና ስኬት ማማ ላይ እንድትወጣ ብቻ ነው።
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ መንግሥት በርካታ ጉልህ ስህተቶችን ፈጽሟል። ከብዙው በጥቂቱ የዜጎች ሕይወት ባስቃቂ ሁኔታ ሲጠፋ መከላከል አለመቻል። ለምሳሌ አጣዬን ሻሻመኔን መጥቀስ ይበቃል። የብቃትና የፈቃደኝነት ውሱንንነት ተደጋግሞ መታየት። የዲፕሎማሲ አቅሙም ማጥቃት ቢሳነው መከላከል እንኳን በሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም። አብዛኞቹ አምባሳደሮች በኢሃዴግ የዘር ፓለቲካ ተኮትኩተውና ተጠምቀው በማደጋቸው ሕዝብን ሲከፋፍሉ ሲያፈናቅሉና ዘላቂ ቁርሾ ሲተክሉ የኖሩት ናቸው። «ሀሰተኛ ያወራውን ፈረስ አይመልሰውም» እንዲሉ የወያኔዎች ጩሀቴን ቀሙኝ እርቃኑን የቀረ ውሸት እሩቅ የሄደው በዘረፉት ገንዘብ ሃይል ብቻ ሳይሆን በዚህም ምክኒያት ነው።
ይህ ሲባል የፈለገው የሃሳብ ልዩነት ቢኖር ባንስማማ ኢትዮጵያ አንዳች ክፉ ነገር እንዲደርስባት አንሻም። ባንዳም ሆነን ጠላትን አናገለግልም። በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ሰበብም የምእራባውያንን ችሮታ ፍለጋ ኢትዮጵያን አናሳጠም። መንግሥትን ለማስገደድ በሚልም ገመናችንን ብሄራዊ ማንነታችንና ክብራችንን አናራክስም። መንግሥት ይመጣል ይሄዳል። ስለሆነም ሂያጅ የሆነን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር አቻ አርጎ በማየት የአገርን ጥቅም መጉዳት ይቅር የማይባል ታሪካዊ ስህተት ነው ብለን እናምናለን።
ምንም የሃሳብ የአመለካከት ልዩነት ቢኖር ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል በአሁኑ ወቅት ከመንግሥትና ከተለያዩ የአንድነት ሃይሎች ጋር ከመቆምና ከመተባበር ውጭ ሌላ አማራጭ አለ ብለን አናምንም። ለጊዚያዊ የፓለቲካ ፍላጎትና ሥልጣን ጥም ኢትዮጵያን አደጋ ላይ መጣል ይቅር የማይባል የሀገር ክህደት ነው። ለመንግሥትም በአጽኖት ማሳሰብ የምንሻው ቆርጦና ዳተኝነትን በማስወገድ የውስጥ አርበኞችን አክራሪ መንደረተኞችንና ጠብ አጫሪዎችን ሥርአት ማስያዝ ይጠበቅበታል። የወያኔ ርዝራዦች ትንፋሽ እንዳያገኙ ተከታታይነት ያለውና የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ እንጠብቃለን። ኢትዮጵያ ከማንም ቡድን፤ ግለሰብና ብሄረሰብ በላይ ነች።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ ጫና ለማሳደር ያደረገው እገዳ የተለያየ ማእቀብና ሌሎች አገሮችን ለማግባባት የሚያካሂደው ደባ አሳሳቢና በጽኑ የሚወገዝ ተግባር ነው።
መንግሥት የግብጽና ሱዳንን ግርግር በመቋቋም የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ፤ እንዲሁም የአሜሪካኖችን ጫና ለማክሸፍ የሚያደረገውን ጥረት እያደነቅን ኢትዮጵያ ወደ አስተማማኝ ንጋት እስክትደርስ መበርታት እንዳለብን በጽኑ እናምናለን።
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!
ኢትዮጵያ ምንግዜም ታሸንፋለች!
የአውስትራሊያውያን ኢትዮጵያውያን የሰላምና ትብብር አድቮካሲ ግሩፕ።