ገጣሚ: በላይ በቀለ ወያ
አቅራቢ: አልማዝ አሰፋ – ዘረ ሰው
======================================================
ደራሲውን ባላወቀውም ግጥሙ ስለጣመኝ የዘሐበሻ ድረገፅ አንባቢዎች አንዲካፈሉት አቅርብያለሁ::
ደራሲው ይህንን ግጥሙን በዘሐበሻ ዳት ኳም (Zehabesha.com)ና በሳታናው ዳት ኳም (Satenaw.com) ካነበበ እራሱን በሌላ ግጥም ቢያስተዋውቅ ደስ ይለኛል:: ይህን ግጥም ስለሰጠንም ባለበት ሙሉ ጤናና ረጅም እድሜ ይስጥልን::
======================================================
ትናንት የጨቆኑት ፣ ጨቋኙን ለመጣል
“ሁላችን አንድ ነን ፣ አንድነት ይበልጣል
አንድነት ኋይል ነው ፣ አንድነት ያዋጣል
የኔ ደም ያንተ ነው ፣ ያንተም ነው የኔ ደም
ዘረኝነት ይውደም
ጎጠኝነት ይውደም
ፍሪደም ፍሪደም
ቅደም ቅደም ቅደም
ፍጠን ተባብሎ
አደባባይ ውሎ
ሰላም እንዲመጣ ፣ ሰላም ባስ አቃጥሎ
በከፋፈለው ፊት፣ ሀገር ህብረት ፈጥሮ
አንድ ነን እያለ ፣ ለአንድ ሀገር ዘምሮ
መንገድ እየዘጋ ፣ ድንጋዮች ደርድሮ
ጠብመንጃ ለማስጣል ፣ ድንጋይ ተወራውሮ
ጥይት ሲያዘንቡበት
ገዳይን ሲቃወም ፣ እጆቹን አጣምሮ
ጨቋኙን ለመጣል ፣ ተገርፎ ተወግሮ
አምስት ሊትር ውሃ ፣ ብልቱ ላይ ታስሮ
የተሰቃየ አምና
ፍርሃት በሚያጠፋ ፣ ወኔ ባለው ቃና
“ዘልአለም ከምትኖር ፣ በግፍ በጭቆና”
ለአንዲት ቀን ነፃነት ፣ መሞት ይሻላል ና
እያለ ሲጠራኝ ፣ ትግሉን እንዳስቀጥል
ፍቅርሽ አሸነፈኝ
መንገዶች ሳይዘጋ ፣ ባሶች ሳያቃጥል
ጭቆናሽ ፍትህ ነው ፣ ለጨቋኞች ማይጥል
ነፃነቴ አንቺ ነሽ ፣ ያገኘሁሽ በጥል
ቀንና ለሊቴ ባንቺ ነው የሚያልፈው
እያልኩ በስምሽ ፣ግጥም የምፅፈው
ለምን ይመስልሻል?
።።።
ተጨቆንን ብለው ፣ ትላንት ያለቀሱ
ጨቋኙን ለመጣል ፣ በህብረት የተነሱ
በአንድነት ኋይል ፣ ዛሬ ላይ ሲነግሱ
ህግ ለማስከበር ፣ ሰው እያፈረሱ
መብት ለመጠየቅ ፣ ሽመል እያነሱ
እኔ ብቻ ታገልኩ
የሚል ትምክህት ይዘው ፣ ሌላውን ሲረሱ
ሁሉም ነገር የኔ ፣ በሚል ክፉ አምልኮት
የተረኛ ስሜት ፣ ልባቸውን ማርኮት
ካለእኔ ፈቃድ ፣ እንዳትከፍቱ በር ፣ እንዳትዘጉ መስኮት
እንዳትለብሱ ኮት
እንዳታጨሱ እጣን
ቤት ንብረታችሁን ፣ ልቀቁና ውጡ ፣ እኛ ከተቆጣን
የእኛ ነው ፈጣሪ ፣ የእኛ ነው ሴይጣን
አዳኝም ገዳይም ፣ የእኛ ነው ስልጣን
ያለእኛ ፈቃድ ፣ አትዝሩ አትረሱ
መሬቱ የኛ ነው ፣ እግራችሁን አንሱ
የኛ ነው አየሩ
እኛ ካልፈቀድን እንዳትነፍሱ
ገለመሌ እያሉ
ጭቆናን የጠሉ
በተረኛ ስሜት ፣ ሲጨቁኑ በጣም
አዲስ ንጉስ እንጂ ፣ አዲስ ህዝብ አልመጣም
ነፃ አውጪ ነኝ ባዪ ፣ ራሱ ነፃ አልወጣም
ብሎ ሲተች ህዝቡ ፣ እየበላ ነገር
የባሰ አለና
ሀገርህን አትልቀቅ ፣ ሚል ተረት ሲናገር
ለኔ አንቺ ነሽና
የኔ ናት ቢሉኝም ፣ የማለቀው ሀገር
ለሌላ አልሰጥሽም ፣
ጊዜ ቢከዳኝም ፣ ቀኔ ቢጎድልብኝ
ሁለ ነገሬ ነሽ ፣ ፍቅርሽ ያደረብኝ
እኔ አንቺን ካገኘሁ
ቀረሁብት እንጂ፣ ከአለም ምን ቀረብኝ
ብዬ የማዜመው
የማንጎራጉረው የምደጋግመው
ለምን ይመስልሻል?
።።።።
በዚህ በጭንቅ ቀን
ለምን ባዮች ሁላ ለሞት ተሰልፈው
ሚዲያው ስለኳስ የሚለፈልፈው
እኔ ስላንቺ ጭን ፣ ግጥም የምፅፈው
ስለከንፈርሽ ጣም ቅኔ የምዘርፈው
ለምን ይመስልሻል?
።።።
በዚህ ጭንቅ ጊዜ
ድፍን ሀገር ታሞ ፣ ሀኪም ሲቸግረው
መድሀኒቴ አንቺ ነሽ ስል ማንጎራጉረው
አንዴ ላስነጠሰሽ
ይማርሽ እያልኩኝ ፣ ስጨነቅ የማድረው
ሀገር እያነባ
ለምን ይመስልሻል
ሰላሜ ነሽ እያልኩ ፣ ላንቺ ምዘምረው
ለውጡ እንዳይቀለበስ ነው
️️