April 29, 2021
4 mins read

በምርጫ ወቅት የኔ ወገን ነው በሚል የሚደረግ ውሳኔ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚያቀጭጭ ነው – ምሁራን

በምርጫ ወቅት የኔ ወገን ነው በሚል በጭፍን በሚደረግ ውሳኔ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን አዙሪት የሚደግም እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚያቀጭጭ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር በዕውቀቱ ድረስ እና የህግ ባለሙያው አቶ ዳንኤል አሰፋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በምርጫ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዶክተር በዕውቀቱ ምርጫው የታለመለትን አላማ ይመታ ዘንድ ዜጎች በሂደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አሳታፊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ዜጎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተር በዕውቀቱ፣ ለዚህም በቀጣይ የሚያስተዳድራቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ከመውሰድ ይጀምራል ይላሉ፡፡

ዜጎች በቀጣይ ያስተዳድረናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ከመምረጣቸው በፊትም ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አማራጭ የፖለሲ ሃሳቦች በትኩረት መረዳት እንዳለባቸው ነው ዶክተር በዕውቀቱ የሚናገሩት፡፡

ለዚህም ፓርቲው ቢመረጥ ለሀገሪቱ  ግንባታ ያለው አስዋፅዖ፣ ለኢኮኖሚ መሻሻል፣ ለማህበራዊ ፍትህ እና ለሌሎች ጉዳዮች የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችን በአንክሮ መገምገም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የህግ ባለሙያው አቶ ዳንኤል አሰፋ በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች  ያቀረቧቸው  የፖሊሲ አማራጮች ዋጋ ሊኖራቸው የሚችለው ዜጎች እነዚህን ሃሳቦች በንቃት መርምረው ውሳኔ ላይ መድረስ ሲችሉ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቀረቡትን የፖሊሲ አማራጮች ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ የኔ ወገን ነው በሚል በጭፍን የሚደረግ ውሳኔ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ያቀጭጫል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ምርጫው ያለምንም እንከን ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መራጩ ማህበረሰብ በሂደቱ የሚከሰቱ አላስፈላጊ ድርጊቶችን በማጋለጥ በንቃት መሳተፍ እንደለበት ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ዜጎችን ለግጭት የሚዳርጉ ሀሰተኛ መረጃዎች የጥላች ንግግሮች ሲያጋጥም በፍጥነት ከማሰራጨት እና እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ቆም ብሎ መመርመር እና ማጣራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

የምርጫ ካርድ ከወሰድን እና የቀረቡ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን ከመረመርን በኋላም  በምርጫው ዕለት ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፅን መስጠት ይገባል  የሚሉት ዶክተር  በዕውቀቱ፣ በድህረ ምርጫ  የሚገለጸውን ውጤት አምኖ መቀበልም ሃላፊነት ከሚሰማው ስልጡን ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ/ኤፍ.ቢ.ሲ

Go toTop

Don't Miss

የምርጫ ህጉን፣ የምርጫ ዘመቻ መመሪያን የሚተላለፉ ንግግሮችን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሂደት ተግባራት መካከል ትገኛለች። የምርጫ