ሁለት ቦታ ቀብርህ
ቀብርህ ሁለት ቦታ
የት ይቁም ሐውልትህ
ተዝካርህ የት ይሁን
አመድ ሆኗል ቤትህ
ዝክሩን ማን ይደግስ
ታርደው ልጅ እናትህ
ቀብርህ ሁለት ቦታ
ደም ሥጋ አጥንትህ
ከፊሉ ጅብ ሆድ ውስጥ ከፊሉ ጉድጓድ ውስጥ
የት ይቁም ሃውልትህ?
በምድር አልተመቸም
በኢዮር ይደረግ አርባና ፍታትህ።
አርባህን ማን ያውጣ?
ሞትህ በገጀራ
ፍታትሕ ባሞራ
ቀብርህ በጅብ ጎሬ
ርስትህን ሊቀሙ
ማተብክን እያዩ
ያረዱህ ገበሬ።
አርባህ ነገ ማልዳ
ማን ያወጣልሃል
ሚስትህ ልጅህ ታርዳ?
ወገን ያልከው ነስቶህ
በገዛ ሃገርህ መቀበሪያ ጉድጓድ
ከውቅያኖስ ማዶ
ሐዘን እንድረስህ
እንባችን ውቅያኖስ ለቅሷችን ነጎድጓድ
አንተም ቋሚው ምዉት
ተንቀሳቃሽ በድን
እኩልህ ተገድሏል እኩልህም ቢድን
ሰማንያህ ተቀዳ ቆንጨራው ሲቃጣ
አርባዋን አወጣህ አርባህን ማን ያውጣ
የቁርባኗ ሚስትህ እሷ ሳትከዳ
ተለይታህ ስትሄድ በገጀራ ታርዳ
የሞቷ ሰቆቃ የእርዷ ሰቀቀን
ባርባ ዓመት አይጠፋም ይቅርና ባርባ ቀን
አይዞህ እንዳንልህ እኛም እንዲህ ርቀን
ከሩቅ ሥጋ ዘመድ ጎረቤት ይበልጣል ይሉን ነበር አበው
ጎረቤት ናቸው ወይ የሚያስጨፈጭፉህ ቤተሰብህን ከበው።
ንብረትም ይዘረፍ ሕንጻንም ያቃጥሉ ምን አገኙ ገድለው
የትኛው ጣዖት ነው የዚህ ሁሉ ክርስትያን ደም ይምጣልኝ ያለው?
ለገዳይ እንጸልይ
ባንቺ አልተጀመረም የመስቀል መከራ አርሲ ሻሸመኔ
ክርስትያን ሲሳደድ ሲሰየፍ ሲታረድ ኗሯል በአረመኔ
ጻድቁን የዋሁን ቸሩን ምስኪኑን ሰው ሲነግረን ስንክሳር
ቆርጠው ፈልጠውታል በጨካኞች ደቦ አይቷል ብዙ አሳር።
የክ/ርስትያን ቅዱስ ይሄ ነው ታሪኩ ተገልጦ ሲነበብ
በምድራዊ ሕይወት ስለ እምነት ጎስቁሎ በሰማይ ቤት ማበብ።
ስለዚህ አማኞች እውነትና ጽድቅን እንያዝ አጥብቀን
ፍትህ የሌለውን የምድራዊ መንግሥት ከንቱ ተስፋ ንቀን
በይቅርታ እንጽና ያምላካችንን ፍርድ በላጩን ጠብቀን።
ወገናችን ታርዶ
እስካንገት ብንሰጥምም በደሙ ማእበል
ይቅር ባይሉንም እኛ ይቅር እንበል
ክርስትና ማለት ይኸው ነው እውነቱ
በቀል አንፈልግም አያዝም እምነቱ
ይልቅስ ለገዳይ እንጸልይ እኛ
ጌታ እንዲያላቅቀው
ከኅሊና ደዌ ከዲያብሎስ ቁራኛ።
አንተም አይቀርልህ
የወንድም ርስት አምሮህ ገጀራ አንስተህ ደሙን አፍሰሃል
ባንተው ብሶ ደግሞ እስካለም ዳርቻ በለቅሶ ጮኸኻል።
ገለህ ስታለቅስ ፈረንጁን ቻይናውን ያሞኘህ መስሎሃል
በዚያው በገጀራህ ያንተም ጉድጓድ ማልዶ ተቆፍሮልሃል።
እንኳንስ ልትጨምር ያንተም ርስት ይሰጣል ለሌላ ተላልፎ
ምን ሲሻ መሰለህ በሀገርህ ዳርቻ ያለው አሰፍስፎ?
ይልቅ ከወንድምህ ተቀመጥ በሰላም
ሊነቅሉህ ቀርበዋል ክርስትያን ሆንክ እስላም::
ይሻላል ማስተዋል
ክርስትያን ሆንክ እስላም ሊነቅሉህ ቀርበዋል
ሀገርህን በሞላ ዙሪያዋን ከበዋል።
ዛሬ በገጀራ ብትጨፈጭፍ ወንድም
ከባሕሩ ዳርቻ እያዩህ ነው አግድም
አንተም በበሽታ በጦር ስትወድም
በሰሰትክለት ርስት ቆሞ አይቀርም አንድም።