“ሁሉ ከሆነ ቃልቻ ፣ ማን ይሸከማል  ሥልቻ ??”  (ሰው ዘ ናዝሬት)

ዛሬ እና አሁን በሀገሬ አውቃለሁ ባይ እጅግ  በዝቷል። ሁሉ ቃልቻ ሆኗል። አድምጡኝ የመፍትሄው አካል ነኝ እንጂ የችግሩ አካል አይደለሁም፣ ባይ ሥፍር ቁጥር የለውም።ዛሬ ጆሮ አልባ በዝቷል።የራሱን ሥሜት ያወራሃል እንጂ ያንተን ሃሳብ አያዳምጥም።አውርቶ ሲያበቃ ቻው ብሎህ ይሄዳል።አንተም ” የተጨቆነ ሃሳብህን ” ላገኘኸው ሰው  ገልፀህ ምላሽ ሣትጠብቅ እብሥ  ትላለህ።ያም፣ያቺም ይሄም እርሷም ግንድ የሚያህለውን የራሳቸውን ጉድፍ ከቶም አያዩም።ይዘባርቃሉ ሳይገባቸው፣ ሥለፖለቲካ፣ ሥለሃይማኖት፣ሥለቋንቋ፣ሥለጎሣ ወዘተ።
 በዚች ሀገር ዛሬ እና አሁን  ለማዳመጥ ዝግጁ ያልሆነ እጅግ በዝቷል።ወላ ጋዜጠኛ ሳይቀር።…  አንድአንድ   ጋዜጠኞች ፣ በአንድአንድ የግለሰብ ቴሌቪዢን ጣብያዎች  ሥለሌሎች ሰዎች ወይም ዜጎች ሥቃይ፣ መከራ  እንግልት፣  የፍትህ መጓደል ፣እሥር፣ቶርቸር፣ ወዘተ። እንደአሻቸው መተንተን እና ከጎሣና ቋንቋ አኳያ እየፈረጁ ችግሩ እንዲባባሥ እሳቱን ማቀጣጠል እንጂ ፣ የችግሩን ሰለባዎች አቅርቦ ፣ የጎሣ፣የዘር ፣የቋንቋ እና የኃይማኖት አክራሪነት  ጦስና ጥንቡሣሥን በማሳየት ዜጎች ከዘረኝነት ህሊናቸው እንዲፀዳ ሲያግዙ አናሥተውልም።
ይልቁንሥ “ያለቋንቋ ፖለቲካ” መኖር የማይችሉትን ወይም ሳይሰሩ” የቋንቋ ፖለቲካ ፊትአውራሪ  ” በመሆናቸው ብቻ ባለ አምሥት ኮኮብ ሆቴል እየተምነሸነሹ የሚሥተዋሉትን ፣ ” በቪ 8 የሚንፈላሰሱትን ለኢትዮጵያ     ህዝብ ፍትህ፣ነፃነት፣ዴሞክራሲ፣እኩልነት፣ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ደንታ የሌላቸውን  ነጋ፣ጠባ በማቅረብ ፣በማህበራዊው ትሥሥሩ ተፋቅሮና ተዛምዶ በየቀየው፣ ለመኖር በእጅጉ እየታገለ በሚኖሩው ” ጨዋ ህዝብ ” ውስጥ ጠብ በመጫር፣ጠቡም እንዳይበርድ ሲያደርጉ ይሥተዋላሉ። ….
ለመሆኑ የአንድ ” ቪ 8″ ዋጋ ሥንት ነው።ቻይና በእኛ ሀገር ደረጃ ባለችበት ጊዜ ይቅር እና ዛሬ ይሄ ለቻይና ኮምኒሥት ፖርቲ ፀያፍ ምግባር ነው።እዚህ በርሃብ አለንጋ የሚገረፍ ህዝብ እየጮኸ ፣ አንተ ሚሊዮን ብሮችን ለቅንጦት እያወጣህ የሚጮኽ መኪና መግዛት ጤነኝነት አይደለም።እናም ለጊዜው ነው እንጂ ፣ይህንን ሲገነዘብ ህዝብ፣ “ህዝቤ፣ህዝቤ፣”ብትለው ከቶም አይሰማህም። በገንዘብህ ግን አሸባሪዎችን ከሥራ አጡ ብቻ ሣይሆን ሥራ ካለው፣የመንግሥት ደመወዝ ከሚከፈለውም   መመልመል ትችላለህ።ምክንያቱም የገንዘብ አቅም አለህና!!”…..
      እርግጥ ነው፣ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ።እዚህ በምድር መሄጃ መንገድ ላጣነው ይብላኝ እንጂ።…የገንዘብ አቅም ካለህ ፣ ፍትህን ራሷን በረብጣ ብር ትገዛታለህ።
   ወደ መገናኛ ብዙሃኑ ልመልሳችሁ። እነዚህ የገንዘብ አቅም ያላቸው መገናኛ ብዙሃኖች በብሄር ሥም እየተጠሩ እንዴት መገናኛ ብዙሃን እንደሚሆኑ ለዛሬው ዘመናዊ  ዓለም ባይገባውም፣ ፣ ይህ የዘር የመገናኛ ብዙሃን አሰያየም፣ በራሱ ችግር ፈጣሪ ነው።እንደፖርቲ ሥሞች  ሁሉ። የአማራ ፣የትግራይ፣የአዲሥ አበባ፣ የኦሮሞ፣የሶማሌ፣ ወዘተ፣ቴሌቪዢን ጣብያዎች መቋቋማቸው ፣ ይህቺን ሀገር አጥር፣ባጥር አድርጓታል።ተጋብቶ እና ተዋልዶ የሚኖረውን ህዝብም ግራ እንዲጋባ አድርጎታል። (የትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያዎች ይመሥል ፣ዘር በማይመርጠው አያሌ ተመልካች ባለው የቴሌቪዢን መሥኳት እጅግ የጠበበ ሥያሜ መሥጠትም፣ዓለም ባለችበት ደረጃ፣   ተገቢ አይመሥለኝም።ሥያሜውም ሆነ አደረጃጀቱ መቀየር አለበት ብዬ አምናለሁ።)
   ይህም ብቻ አይደለም፣ሚዲያው በፍላሎት የተሞሉ ፣”ወዶ ገብ” ጋዜጠኞችን ፈጥሯል።ያለ ጋዜጠኝነት ትምህርትም በድፍረት ማይኩን ጨብጠው፣ እንዳሻቸው በመናገር እና ለሆዳቸው ወይንም ጥቅም ለሚሰጣቸውና ለሚከፍላቸው ወገን በማድላትና በግብዝነት ከኛ በላይ ላሳር በማለት ፣ ለአንድ የፖለቲካ ቡድን ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩና እየተቀጣጠለ ባለው የዘር ፖለቲካ እሣት ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ  ይሥተዋላሉ።
          ቋንቋው ቢለያየም ሰው እና ወንድማማች የሆነውን ገና ለጋ እና ሎጋ የሆነውን ፣ ” በፍላሎት የተሞላውን” ሥራ አጥ  ወጣትንም (ቄሮ፣ፋኖ፣ኤጄቶ ወዘተ ) ያለ ዘር ፖለቲካ መኖር የማይችሉት እና በዘር ፖለቲካ የበለፀጉ፣በሥውር እጅ   የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉለት፣ በሀገሪቱ እውነተኛ ፍትህ፣ዴሞክራሲ ፣ሠላምና ልማት እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ  በቴሌቪዢን መሥኮታቸው፣እያቀረቡ ፣ ሰውነቱ ላይ ሳይሆን ቋንቋው ላይ አተኩረው ፣አፈር የሆነ ያለአዋቂዎች ታሪክ ከመቃብር ቆፍረው በማውጣት ፣ የዛን ዘመኑን ግፍ እንደገና እንዲፈፅም ይቀሰቅሱታል።
      በዚህ አድራጎታቸውም አውቀውም ሆነው ሣያውቁ  የኢትዮጵያን ጥፍት እንጂ ልማት ለማየት ከማይፈልጉ  ኃይሎች ጋር ተባብረው ይህቺን ሀገር ሶሪያ ለማድረግ እየጣሩ ነው።
   እነዚህ የዘር ፖለቲካ አራማጆች ሚዲያውን  ፣ይልቁንም ቴሌቪዢኑን በመቆጣጠር፣ ለግል ጥቅምና ምቾታቸው ብቻ በማሰብ እና ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን በሚሊዮን የሚቆጠረውን ህዝብ በመዘንጋት ፣በፕሮግራማቸው ፣ ከከብት ጋር እኩል ውሃ የሚጠጣውን ፣ዘመናዊ አኗኗር ይቅርና በቂ ምግብ ፣ልብስና መጠለያ የሌለውን ዜጋ ፣ በማሳየት ” ሀገሬ እንዲህ ናት፤ እናም ከድህነት ለመውጣት ሰው መሆናችንን ተገንዝበን በዚች አጭር ዕድሜያችን ለእነዚህ ወገኖቻችን ከድህነት መውጣት የበኩላችንን አሥተዋፆ እናድርግ። ” ከማለት ይልቅ፣ሰው፣ሰው መሆኑን እንዳይገነዘብ እና የራሱን ቋንቋ ከፍ፣ከፍ፣በማድረግ በቋንቋው እና በባህሉ ሰው ሳይሆን መለአክ እንደሆነ ራሱን እንዲቆጥር የሚያደርጉ ሆነው እናገኛቸዋለን።
   አንዳንዶቹም አሜሪካ ትሻለናለች፣ቻይና እና ሩሲያ ይቅሩብን  ወይም በተቃራኒው በማለት መንግሥትን ለመምከር ይዳዳሉ።እነዚህ ሰዎች፣ የትኛውም ኃያል ሀገር የራሱ ጥቅም እንዳይጓደልበት ሁሉንም ወዳጅ እንደሚያደርግ ከቶም የተገነዘቡ አይደሉም።
      አንዳንዶችም ይህንን ተገንዝበው ሢያበቁ፣ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል መንፈስ የህዳሤው ግድብ ሣይራዘም እንዲገነባ ሀገሬ የምታደርገውን ታላቅ ጥረት ለማደናቀፍ በብርቱ ከሚጠረው የውጭ ኃይል ጋር የተሰለፉ ሆነው እናገኛቸዋለን።
  ያም ሆነ ይህ፣የጋዜጠኛ ሚና እውነትን ፣ማሳወቅ፣መዘገብ፣መሥተማር እና ህብረተሰብ ለበጎ ነገር እንዲነቃ ማድረግ ነው።እናም ከዚህ አንፃር፣    መፍትሄ ለማቅረብ  ብዙ ከማውራት ይልቅ የጉዳዩ ባለቤቶች    እንዲያወሩ መድረኩን መስጠት ነው።ይሁን እንጂ በቴሌቪዢናችን  እየተቀነጫጨበና እያተጎማመደ  የሰዎች ሃሳብ በዜና መልክ ይቀርባል።…
      ከህዝብ የተደበቀ ሳይኖር ሚዲያው ከህዝብ መደበቁ ሰዎች እንዳይማሩ ከማድረጉም በላይ ፖለቲካው እንዲከር አድርጓታል።      ጋዜጠኞቻችን ነፃነት ሥለሌላቸው፣ የምኖረውን ህይወት ድጋሚ ለእኛው  ሊያስረዱን የሚጥሩ ሆነው እናገኛቸዋለን።ማድረግ የነበረባቸው በሥፍራው ተገኝተው እውነትን መዘገብ እና አሥተያየቶችን ያለ ድራማ ከማንኛውም ሰው መቀበል እና ሚዛናዊ መሆን ነው።
   ዛሬ እና አሁን የምናሥተውለው፣ሚዛናዊነት መጥፋቱን ነው። ሥለ ዓለም ና ሰው አፈጣጠር፣ሥለሀገሮች ምሥረታ፣ሥለ ተለያዩ  ፖለቲካዎች፣ሥለቋንቋ አመጣጥ ፣ሥለባህል በወጉ የማያውቅ፣ወይም የጠለቀ እውቀት የሌለው ሁሉ ፣የወቅቱን ፖለቲካ ሲተነትን እናሥተውላለን።
     በየሚዲያው ግለሰቦች እና ጋዜጠኞች  በኢሕአዴግ ክሥመት …. አጋር ድርጅቶችን ያካተተ አንድ ግዙፍ ፖርቲ ምሥረታ … የዘር፣የቋንቋ፣የጎሣ እና የወንዘኝነት ፈተና  … ሥውር ሽኩቻ…በነፃ አውጪ ሥም በመታገል ባአረጁ እና ባአፈጁ…   ዛሬም ይህንኑ አቋማቸውን  የሙጥኝ ባሉ … በግንቦት 7፣በአዳርጋቸው ሥብዕናና በብርሃኑ ነጋ ቦገር፣የዕውቀት  የኃብት ባለፀግነት ና የሌበራል ሥርአት ናፋቂነት …በልደቱ” ፖለቲካዊ ከልት።” የመፍጠር ግላዊ ትግል…የኢሕአፖ ዛሬም አብዮታዊ ነኝ ማለት …
     የህዝብ መፈናቀል…በእርዳታ ማሰባሰብ ሰበብ የግል ሀብት ማካበት ወይም የ (Lord of conflict)  መብዛት። … የዚችን ዝነኛ እና ገናና  ሀገር፣ታሪክ ጠብቆ የሚያቆይ   ህግ የማስከበር  አቅም ያለው ሠራዊት ቢኖርም፣የክልል መንግሥታቱ ፣ባላቸው የታጠቀ ኃይል ምክንያት እና በህገመንግሥቱ ሰበብ መግቢያ ቀዳዳው በመጥበቡ ሰበብ፣ በደቦ ፣ በሻሸመኔ፣በቡራዩ፣በጎጃም (በጎንጅ ቆለላ)፣ ዛሬ ደግሞ በአዳማ፣ ሐረር፣ ድሬደዋ፣ሰበታ … የንፁሐን ህይወት መቀጠፍ …
      ቋንቋቸው የተደበላለቀባቸው እና ለመግባባት ያልቻሉ ባቢሎን ሰዎች የሚመሰሉ ፣የአላቅም፣ ያለዕውቀትና፣ ያለችሎታ፣ሰማይን በእርግጫ ለመምታት የሚፈልጉ እንደ አሸን መብዛት…ዳግም በኢትዮጵያ ፣ከ1967 -1971 ዓ/ም  እ/ኢት/አ   ያለው፣የደርግና የመሰል የማሌ(ማርክሲዝም ሌኒኒዝም)አቀንቃኞች ሹክቻ በሌላ አውድ፣መከሰት …ላይ የራሳቸውን ትንታኔ ይሰጣሉ።
     ይህም ብቻ አይደለም፣  የተመሰቃቀለ የፖለቲከኞች መጫወቻ ሜዳ፣በሜዳው ላይ ከመቶ በላይ የሆኑ ፖርቲዎች የተለያየ መልያ ለብሰው ከመቶ በላይ ኳስ  በየአንበሎቻቸው ይዘው መገኘታቸው …ጫወታውን የሚመራው ዳኛ ይሄን ዝብርቅርቅ አለባበስ ካላሶገዳችሁ፣ ጫወታውን ማስጀመር አይቻልም ማለቱ …የመስመር ዳኞችም በዋና ዳኛው ሃሳብ መስማማታቸው … ታዛቢዎችም  አንዱን ከአንዱ ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ድብልቅልቅ ያለውን የጫወታ ሜዳ ተመልክተው ለተመልካቹ ሪፖርት ማድረጋቸውን …ሥለእውነተኛ ህግ፣ሥለ ሚዛናዊ ፍትህ፣ተረድተው ” ይህማ ከሚያስበው የሰው ህሊና የማይጠበቅ ድርጊት ነው። “በማለት ፊታቸውን ማዞራቸው።…  በለው፣ቦቅሰው፣ሥበርና ጣለው…ልኩን አሳየው…እያለ በጡንቻው የሚያስበው፣ዛሬም እንደትላንቱ ኃይል፣ጡቻ እና ጠበንጃ እንዲገዛ የሚፈልገው …በጩኸት ጨዋታው እንዲጀመር፣ለጉልበተኛ ተወካዮቹ ድጋፉን እየሰጠ ነው።…በማለትም የሚፅፉ፣የሚናገሩና የሚያሥደምጡ እውነትን ገንዘባቸው አድርገው ፣  ህዝብ እውነቱን እንዲያውቅ የሚያደርጉ ፣ሚዲያዎችም አሉ (ሶሻል  ሚዲያዎችምንም ጨምሮ)
    የአንድ ሉአላዊ ሀገር ዜግነትን የየክልሉ መሪዎች ረስተው፣ራያ፣ ወልቃይት-ጠገዴ። ቅማት።ወዘተ።የማንነት እና የአሥተዳደር ጥያቄ።ለምን አነሱ ብለው፣በኃይል ጥያቄያቸውን ለመቀልበስ ለምን ይጥራሉ?  “በአንድ ሀገር ውስጥ እስከሆኑ ድረስ እኔ አስተዳዳሪያቸው ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ ለምን ይባላል?የምትበላንን አፈር ቀድመን መብላት እንጂ፣ሳንበላት ለምን ቀድማ ትብላን??”…እያለ፣እያለ…ሁሉም ካነሳኋቸው ነጥቦች፣በአውንታዊ እና በአሉታዊነት ተሰልፎ፣የበኩሉን አስተያየት ይሰጣል ።ሁሉም ትክክል ነኝ ባይ ነው።…
   ይሁን እንጂ፣ በዚች ሀገር   ለሥጋው እየተገዛ ያለመታከት የሚዘባርቀው ሥፍር እና ቁጥር የለውም።”  ሳይደወል ቅዱስ ባዩ፣አዛን ሳይባል ሰጋጁ ” ብዙ ነው። በዛው መጠን  ” የምፅዓት  ቀን ናፋቂው ” ሳያጣራ ጯሂው እንደአፈር ነው።
      እልፍአእልአፉ ራሱን ቃልቻ አድርጓል። ጎንበስ ብሎ በትህትና ሀገርና ህዝብን ለማገልገል ወገቡን የታጠቀው የሚከብደውን የሥራ ትጥቅ፣”ሥልቻውን”ተሸካሚ  ግን   ጥቂት ነው።ራሱን በራሱ ቃልቻ ያደረገው መብዛት፣  ሥልቻ ተሸካሚ አሳጥቶናል።ይህ ሁኔታ በጊዜ ካልታረመ ይህቺን ሀገር ወደማትወጣው መከራ ውስጥ እንደሚከታት መገመት ነብይ አያሰኘም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ጦር እየመዘዙ ድርድር ለማንም አይበጅም !! (ከተዘራ አሰጉ)

2 Comments

  1. Locust does not eat people but people can eat locust. Some say eating locust can cut money spent on food by half or more. Locust doesn’t chew through paper so all cash money or other documents are safe ,as long as the locust invasion doesn’t distract us from guarding our treasures from robbers. Locusts are blessings in disguise.

  2. እኔም ልጨምር፦ ሁሉ ካለ ዝም፣ ማን ይለቅማል ግም፤
    አገር አፍርሶ ሚል ቀደም ቀደም፤
    ወሬ ይብቃ አንሁን ደም በደም!

Comments are closed.

Share