ፍልስፍና፣ ኃይማኖትና አዲስ ኪዳን 

ፍልስፍናና ኃይማኖት

ከክርስቶስ ልደት 361 ዓመት በፊት ፕላቶ (Plato) ከምዕራብ አቴንስ ትንሽ ራቅ ብሎ የሚገኘውን የግል ዘመናዊ ቤቱን ጓሮውን ጭምር ለአምልኮው ማህበር (cult association) በስጦታ አበረከተ። ትምህርት ቤቱን በአካባቢው ተወዳሽ በነበረው አካዴሞስ (Akademos) ስም ሰየመው። ይህ ትምህርት ቤት ለሚቀጥሉት መቶ ዓመታት መላውን ኅዋና ጠፈር በሚያጠናው ሥነትዕይንት (cosmology) ምርምርና የሥነአምላክ (theology) ትምህርት ማስተማርያ ሆኖ ቀጠለ። ከፕላቶ እልፈት በኋላ የእርሱ ተከታይ የሆኑት ስፔሲፖስና (Speusippos) ዜኖክራትስ (Xenocrates) ይህንኑ የፕላቶ ፈለግ ተከትለው ፕላቶናዊ (Platonism) ብለው የጠሩትን አስተምርሆ ቀጠሉበት። ከትምህርቶቹ መካከል የመናፍስት (demnology) ጉዳይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ትምህርት ሊሆን በቃ። ትምህርቱ ልዩ ልዩ የሆኑ በሠማይና በዓየር የሚገኙት መናፍስት በፍጡራን ዓዕምሮ ውስጥ ሳይቀር እንደሚሠርጹ ያስረዳል። ትምህርቱ በተጨማሪም መናፍስቶቹ በሰዎችና አምላኮች መካከል የሚገኙ መልዕክተኞች ናቸው ሲል ጥልቅ ግናዛቤ ያስጨብጣል። ከክርስቶስ ልደት 315 ዓመት በፊት ለኅልፈት የበቃው ዜኖክራትስ ጥሩና መጥፎ መናፍት እንዳሉም ጭምር አስረድቶ ይልቁንም መጥፎ (evil) የሆኑት ከጨረቃ በታች (sub-lunar) የሚገኙት አማልክት ይህችን ዓለም በጣር ያምሷታል ብሎ ነበር። እነዚህን የመሳሰሉ ሃሳቦች ናቸው ፍልስፍናዊ አስተሳሰብንና ኃይማኖታዊ ግንዛቤን በቅጡ ያስጨበጡት። በወቅቱ ፍልስፍናንና ሥነመለኮትን አስመልክቶ በርካታ ጽሁፎች ተሰራጭተዋል።

ፕሉታርክና (Plutarch) አዲሶቹ የፓይታጎራስ (Neo-pythagoreans) ተከታዮች የሮማ ዘመን ፕላቶናዊ በመሆን አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማከል ግንዛቤ ጨመሩ። ሃሳባቸውንም ጁስቲን ማርቲን (Justin Martyr) የመሳሰሉ ክርስትያኖችም ጭምር ተጋሩት። እነሆ አረማውያን የሚያምኑባቸው አማልክትም (gods) ገና ከመሠረቱ በርኩስነት የተሞሉ መሆናቸውን በአደባባይ ተናገሩ። ፍልስፍናን ተመርኩዘው አሳማኝ ሃሳቦችን ማንጸባረቅ የቻሉት አፖሎጀቲካውያንም (Apologetics) ዜኖክራትስን በመከተል እዚሁ አካዴሞስ ነበር የሠለጠኑት። አፖሎጃውያን በመናፍስትና (demons) አማልክት (gods) መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት አነጻጽረው ገንቢ ሃሳብ በማቅረባቸው ሲታወቁ፣ የሰው ልጅ ምግባሩንና ማህበራዊ ጉዳዮችን ጭምር (Anthropologicl) ለሚዳስስበት እንዲሁም ሥነትዕይንታዊ (Cosmological) ጉዳዮችን አስመልክቶ ይመራመር ዘንድ አዳዲስ መረዳቶች እንዲያገኝ በቂ አስተዋጾ አክለዋል። ሥነትዕይንት ከጨረቃ በላይ የሚገኙትን የማይነጥፉትንና (imperishable) የማይለወጡትን (immutable) ተፈጥሮዎች ያጠናል። ከጨረቃ በታች ያሉት ፍጥረታት የሚያልፉና የሚለወጡ (transitary and subject to change) ናቸው። ስቶይኮች (Stoic) መንፈሳዊ ጉዳዮችን የሚተነትኑት (method of exegesis) የወቅቱን አንኳር ትምህርቶች ተንተርሰው ነበር።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ሁለተኛውና ሶስተኛው ምዕት ዓመታት ገደማ ተንሰራፍቶ የነበረው የአካዳሚው አስተምርሆ እያደር ከስቶይኮች አስተሳሰብ ጋር ይጋጭ ጀመር። ፕላቶኒስቶቹ የሶቅራጥስ ሃሳቦች ላይ በመመርኮዝ አዲስ ምርምር ጀመሩ። ሶቅራጥስ አንድ ወቅት ላይ ለሶፊስቶች እውቀት በስሜት ሕዋሳት አማካኝነት አትገኝም” (No knowledge through sense perception) ያለውን ተንተርሰው ስቶይኮችን ይሞግቱ ጀመር። እውነትን ለማግኘት (truth Value) ልምድ (experiance)፣ አስተውሎና (observation) ሳይንሳዊ ምርምር (sceintific experiment) ጠቃሚ መሆኑን አካዳሚዎቹ ቢረዱም እንኳን በተወሰነ ደረጃ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተጠራጣሪዎች (skeptist) ሆኑ። ይህ እሰጥ እገባ የተጀመረው አርኬሲሎስ (Arkesilos) የአካዳሚው ዋና ሃላፊ ከሆነበት ከክርስቶስ ልደት በፊት 268 ዘመን ጀምሮ ለሚቀጥሉት አንድ መቶ ዓመታት ካርነደስ (Karneades) የትምህርት ቤቱ መሪ ሆኖ እስከተተካበት ድረስ ነው። እያደር ግን አካዳሚዎቹ ከተጠረጣሪነት ቅርቃር ራሳቸውን በማላቀቅ የሌሎችን ሃሳቦች መቀበል ጀመሩ።

ፊሎ (Philo) የእውቁ ኢጣልያዊ ገዥ የሲሴሮ (Cicero) አስተማሪ ነበር። የፊሎ ተከታይ የነበሩት አንቲኮስና (Antiochos) አሽኬሎን (Ashkelon) ስቶዓ (Stoa) የተባሉትን፤ ዓለምን ሁሉ በሚያጣምረው ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሚሰጡትንና (cosmopolitan) ፈጣሪን ከኅዋ ጋር የሚያመሳስሉትን፤ (pantheistic) ፈላስፎች መቃወም ጀመሩ። ስቶዓዎች አሪስቶትል ያነነሳሳት ተምኔታዊዋን የፖለቲካ ከተማ (polis – political community) አንቋሸው እትልቁ ህዋ (universe) ላይ መዋኘትን መረጡ። ስቶዓዎች የፊዚክስ (physics) እንቅስቃሴ ህግ ላይ በመንተራስ ኅዋ ራሷ አምላክ ነች አሉ።

እያደር አንቲኮስና (Antiochos) አሽኬሎን (Ashkelon “አካዳሚስቶች፡ መባላቸው ትተው ፕላቶኒስት” መባልን ሲመርጡ ፕላቶ የመሠረተው አቴንስ የሚገኘው ትልቁ አካዴሞስ (Akademos) ወደ መዘግቱ ደርሰ። ፕላቶኒስቶቹ በአንድ ቦታ መወሰንን ትተው በየሃገሩ እየተዘዋወሩ ማስተማር ስለጀመሩ አስተምርሆቻቸው ይበልጥ እየተስፋፋና እየተጋነኑ በመምጣት አጠቃላይ የዓለም ግንዛቤ ሆኑ። ከጂዊሹ ፈላስፋ ፊሎ እንዲሁም የጥንቱ የክርስትና አስተሳሰብ አዋቂ እስከነበሩት ጁስቲን ማርቲንና ቅዱስ አውጊስቲን (St. Augustin) ድረስ የፕላቶናው ፍልስፍና አስተምርሆ ጎልብተው የሰውን ልጅ፣ ምግባሩንና ማህበራዊ ተቋሞቹን የሚጠናበት (anthropology) እንዲሁም የሥነትዕይንት (cosmology) ምስጢሮችን መፍቻ ቁልፍ ሆኑ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዳይ እንደ ተበዳይ   !

ዜኖክራት ስለ መናፍትስ ምንነት ሲተነትን የፕላቶን ሃሳብ ተመርኩዞ በመሆኑ ጥሩ መንፈሶች የመልካም ምግባር አነሳሾች ሲሆኑ መጥፎ መንፈሶች ደግሞ መጥፎ ድርጊትን ያሰከውናሉ” ይላል። የስቶይኩ ፈላስፋ ፖሳይዶንዮስ (Poseidonios) ከፕላቶናዊው አስተምርሆ ውስጥ ለራሱ የሚስማማውን እየመረጠ በአዳዲስ ሃሳቦች አደመቀው። ግኖስቲሶችም የሃሳብ መንደርደርያ ያገኙት ከፕላቶ ሲሆን የሰው መንፈስ መሠረት ወይም መገኛ ፀሃይ ነች” ይላሉ። ግኖስትሶች በጨረቃ በኩል ዘልቆ የሚወረወረውን የጸሃይ መንፈስ በመጋራት ፍጥረታት መሻታቸውን (desire) ሁሉ ያገኛሉ” የሚል አስተሳሰብም ያራምዳሉ። ትምህርቱ – የሰው ልጅ ሲሞት ነፍሱ ከስጋው ተነጥላ በጨረቃ ውስጥ ዘልቃ እመገኛዋ ፀሃይ ትጠልቃለች – የሚለውንም ኃይማኖታዊ ሃሳብ ይጨምራል። ሲሴሮና ሰኔካም ይህን ተቀብለው ነበር። የስቶይኮች አንኳር አስተሳሰብ ቃል (logos) የፍጥረታት ሁሉ አንደርዳሪ መለኮታዊ ኃይል (divine power) ነው” የሚለው ነው። የአሌክሳንደሩ ፊሎ እምነት በብዙ ረገድ ከስቶይኮች ጋር ቢመሳሰልም፤ የሰውን ልጅ፣ ምግባሩንና ማህበራዊ ጉዳዮቹን የሚጠናበት እውቀትን (anthropology) አስመልክቶ ግን ፕላቶናዊ ነው።

የአሪስቶትል ፍልስፍና ከኃይማኖቱ ይልቅ በተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ነበር የሚያተኩረው። አሪስቶትል ሊሴ (Lyceum) ባለው የራሱ ትምህርት ቤት ፍልስፍና ሲያስተምር ቆይቷል። ጓደኛውና ተባባሪው ቴኦፍራስቶስ (Theophrastos) የአሪስቶትልን ፈለግ በመከተል ፐሪፓተቲክ (peripatetic) ብሎ በከፈተው ትምህርት ቤት መሪ ሆነ። ትምህርት ቤቱ በአብዛኛው ስለ እፅዋቶች (plants) ምርምር ሲደረግበት ቢቆይትም በመጠኑ ኃይማኖታዊ ጉዳዮችም ይዳሰሱበታል።

ከግሪኩ ዘመን መምጣት በፊት ሥራ የጀመሩት የፕላቶ አካዳሚና (Academy) የአሪስቶትል ሊሴ (Lyceum) ከሁለት ሶስት አስርት ዓመታት በኋላ በኤፒኩርያንና (Epicureans) ስቶይኮች (Stoics) ተተኩ። መስራቾቻቸው ኤፒኩሮስና (Epikouros) ዜኖ (Zeno) ሁለቱም አቴንስ ውስጥ ነው ማስተማር የጀመሩት። ኤፒስቴሚሎጂ (epistemology) በእውቀት ንድፈ ሃሳብ (theory of knowledge) ላይ መስራት ማለት ነው። ኤፒኩሮስ ከግምት (opnion, speculation) ወጥቶ ትክክለኛውን እምነት ለመፈለግ ኤፒስቴሚሎጂን ሲከተል ደስታና ግብረገብ (happiness and moral) ዋነኞቹ መሆናቸውን ተገነዘብኩኝ ይላል። ኤፒኩሮስ አሪስቶትል ያወደሳት ፖሊስ (polis) ደስታን አታመጣም ይልና በመልካም ምግባር ተሳሰረን የምንገናኝባቸው ማራኪዋ የአትክልት ቦታ ደስታን መቃረምያ ነች” ሲል ያደንቃታል። ከላይ እንደተመለከትነው ኤፒኩሮስ ፊሲክስ እንጂ አማክልት በሰዎች ጉዳይ ላይ ቦታ የላቸውም ይላል።

የፕላቶም ሆነ የአሪስቶትል፣የዚኖም ሆነ ኤፒኩሮስ ትምህርቶች ለአዳዲስ ኃይማኖቶችን ግኝት ምክንያት ሆኑ። ተከታዮቻቸው አስተውለው እንዲሰሟቸው ማራኪ ንግግርና ጽሑፍ (diatribe) የሚጠቀሙት ሲኒኮች (The Cynics) ዋና ፍላጎታቸው ሰዎችን ማስደሰትና ደስታን አብዝቶ መጨመር ነው። የመጀመርያዎች ክርስትያኖች ፊሎ፣ ሴኔካ፣ ሙሶኒዩስ፣ ማክሲሙስ እና ሐዋርያው ጳውሎስም ጭምር የአጻጻፍ ዘይቤአቸው (literary style) ሲኒካዊ ቢመስልም እውነትን ፍንትው አድርገው ከመናገር ግን ወደ ኋላ አይሉም። ባሁኑ ዘመን ውስጣቸው ባዶ የሆኑ አስመሳዮች ተከታዮቻቸውን ለማብዛት – ቀልብን የሚስቡ ነገር ግን ዓዕምሮን የሚያጨልሙ ማራኪ ቃላት እየተጠቀሙ በርካቶችን አስተኝነትው በድህነት አረንቋ ያስገርፋሉ፣ ያሰድዳሉ።

ስለ ቀድሞው ዘመን ኃይማኖትና ፍልስፍና ቢጽፉ ወረቀት አይበቃም። ሰዎች በጨረቃና ኮከቦች እንቅስቃሴ (astrlogy) እየተከተሉ እድላቸውን (fate) መፈለግ የጀመሩት፤ በተለይም ግብጽና ሶርያ ውስጥ የሚዘወተረው አምልኮ የተወለደውም ከጥንት ዘመን አስተሳሰብ ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰዎች እንደ ቅዱስ ቃል ወስደው የሚያመልኩበት ኦርፊዝም (Orphism) የተባለው እምነትም ኦርፌዎስ (Orpheus) የጻፋቸውን ግጥሞች እንደ መዝሙር በማነብነብ ይመለካል። አምልኮው (ritual) ግብረገባዊ በመሆብ ራስን ከክፉ ሃሳብ ማንጻት (moral purification) የሚለው ላይ ያተኩራል። እንዲህ እንዲህ እያልን ስለ አስክሌፖስ (Asklepios)፣ ስለ ድዮኒሶስ (Dionysos)፣ ሳራፒስና አይሲስ (Sarapis and Isis)፣ ስለ ሌሎችም ብዙ ልንጽፍ እንችላለን። አንድ ማወቅ ያለብን ጉዳይ አለ። በጥንታዊው ዘመን አንድ ወጥ ኃይማኖት ነበር ለማለት ያስቸግራል። አንዱ ኃይማኖት ከሌለኛው አንድ ማራኪ” የመሰለውን የአምልኮ ዘይቤ ስለሚወስድ ኃይማኖቶች ድብልቅ (syncretised) ነበሩ። የሰው ልጅ ጉጉ ስለሆነ ወይንም ፍላጎት ሲያድርበት አልያም ሲጨንቀው ቀልቡ የሳበውን ይከተላል። የኃይማኖት መደበላለቅ (syncretism) በጊዜ ብዛት የሚከሰት ሁኔታ ነው። በጥንት ጊዜ እርስ በእርስ ያልተወራርሰ አንድ ወጥ ኃይማኖት ለማግኘት ይከብድ ነበር።

የምሥራቹ ቃል – አዲስ ኪዳን

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህሊና  እስረኞችን  ፍቱልን!!!! - ፊልጶስ

ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ አመት በፊት አቴንስ በሜቄዶንያውያኑ ንጉሥ ፍሊፕ ተወረረች። የአሪስቶትል ተማሪ የነበረው የንጉሥ ፊሊፕ ልጅ ታላቁ እስክንድር ዓለምን ሁሉ ለመግዛት አስቦ ሃገሮችን በኃይል ሲያስገብር የግሪክኛ ቋንቋም አብሮ ተስፋፋ። ይህ ቋንቋውን ብቻ ሳይሆን ፍልስፍናውንም ያስፋፋው ዘመን የግሪክ ዘመን (Hellentistic Age) ይባል ነበር። በወረራው ወቅት የግሪክኛ ቋንቋ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ዝምድና ስላበጀ ኮይነ ግሪክ (Koine Greek) የሚል አዲስ ቋንቋ ተወለደ። ይህን ከዋነኛው ግሪክኛ (classical Greek) ቋንቋ የሚለየው አዲሱ ኮይነ ግሪክኛ እብራዊኛ (hebrew) እንዲሁም እየሱስ ክርስቶስ የሚናገረው አራማይክኛ (aramaic) ቋንቋንም በውስጡ ስላዘለ አንዳንዶች የመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ ነው ሲሉ አወድሰውታል። ዛሬ እጅግ አምሮ መንፈሳዊ ጸጋን የምንለብስበት አዲስ ኪዳን መጀመርያ ከተጻፈበት ኮይነ ግሪክኛ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመው አባቶች ባደረጉት ከፍተኛ ትጋትና ድካም ነው። አባቶች የእግዚአብሄርን እውነትና ብርሃንነት ጥበብ በተመላ እውቀት (knowledge of Wisdom) በማድመቅ አማኞች ደግሞ እምነታቸውን ትዕግስት፤ በጎነት፤ቸርነት ደግነትና ጥሩነት (exercise in vitrue) በተላበሰ ምግባር እንዲያንጸባርቁ ጥርጊያ መንገድ አበጁ።

መጀመርያ በኮይነ ግሪክኛ የተጻፉትን የምስራቹን ቃሉንም ሆነ ሌሎቹን መልእክቶችን መተርጎም ቀላል ሥራ አልነበረም። ያንዳንድ ጸሃፊዎች ቃላት (word) የተያያዙ ስለነበሩ ቃሉን ከቃል ለመለየት ብዙ ትጋት ተደርጓል። በስተኋላ ሁለት ነጥብ ማድረግ የተጀመረው ቃልን ከቃል ለመለየት ነው። በተጨማሪም የቃሉን (word) ትክክለኛ ሃሳብ አግኝቶ መንፈሳዊ አባባሉን በቅጡ ለመተንተንና ለማስረዳት (exegesis – critical explanation or interpretation) የወቅቱን – ከላይ በትንሹ ያቃረብኩትን – ዓይነት የግሪኩን ዘመን ታሪክ፣ ባህልና ኃይማኖትን (history, culture and religion of the Hellenstic Age) በሚገባ መረዳትን ይጠይቅ ነበር። አሁን የተነሳሁበት ዓላማ ስለዚህ ጉዳይ ለመጻፍ ስላልሆነ ለጊዜው አንድ ምሳሌ ብቻ እንመልከት።

ዮሐንስ ወንጌል ላይ ስለተጻው ቃል” (logos) አተረጓጎም ጥቂት ልናገር። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ ላይ ያለውን መጀመርያ ቃል (logos) ነበር፣ ቃልም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበር፣ ቃልም እግዚአብሄር ነበር” የሚለውን ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ኮይነ ግሪክኛው – καὶΘεὸςἦνΛόγος” – ካይ ቴዎስ ሄ ኦ ሎጎስ” – ቃልም እግዚአብሄር ነው – የሚለውን ትርጉም ሳቤልዮሳውያን (Sabellianism) “ካይ ኦ ሎጎስ ሄ ኦ ቴዎስ” ማለትም («and the Word was the God – i.e the Father) የሚል ትርጉም በመስጠት ቃሉ” እግዚአብሄር ነው አሉ። ይህ ማለት ሥላሴዎችን አለመቀበል (monotheism) ማለት ነው። አርዮሳውያውያን (Arianism) – “ካይ ኦ ሎጎስ ሄ ቴዎስ” ማለትም («and the Word was a god) የሚል ትርጉም በመስጠት ቃልን” አሳነሱት። ኦርቶዶክሶች (Orthodoxy) “ካይ ቴኦስ ሄ ኦ ሎጎስ” ማለትም (and the Word was God) “ቃልም እግዚአብሄር ነበር” በማለት ወልድ አብ ከለበሰው ባህርይ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በመግለጽ አወዛጋቢ ለነበረው የግሪክኛው ጽሁፍ ቀጥተኛ ትርጉም አገኙ። (William D. Mounce – Basics of Biblical Greek, page 29)

በኋላ ዘመን ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ድንግል የሚወለደው ቃል” (logos) የአብ የባህርይ ልጅ ነው። ከሶስት አካል ማለትም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንዱ የሆነው ወልድ ፍጡር ሳይሆን ፈጣሪ ነው። አርዮስ ሊያሳንሰው እንደፈለገው ወልድ እኛን ለመፍጠር የተወለደ አይደለም። የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ቁጥር ሶስት ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም ነው የሚለው። የቃል እግዚአብሄርነትን ያሳነሱት ሳቤላውያንና አርዮሳውያን ብቻ ሳይሆኑ የንስጥሮስና የፓፓሊዮን ትምህርት ተከታዮችም ጭምር ናቸው። ቃል ሥጋ ሆነ ሲባል ቃል ተለውጦ ሥጋ ሆነ ማለት ወይንም ሥጋ ወደ አምላክነት ተለወጠ ማለት አይደለም። በማይመረመር የተዋህዶ ምስጢር – የቃል ሃብት ለሥጋ – የሥጋ ኃብት ደግሞ ደግሞ ለቃል ሆነ – እንጂ። ይህም ማለት የመለኮት ገንዘብ በተዋህዶ የሥጋ ገንዘብ – የሥጋ ገንዘብ በተዋህዶ የቃል ገንዘብ ማለት ነው። ፊተኛና መጨረሻ መሆን የሚገባው ቃል ሲሆን ሥጋ ግን በተዋህዶ የቃልን ገንዘብ የራሱ አድርጎ – ፊተኛም መጨረሻም እኔ ነኝ – ሊል በቃ። እነዚህ የመሳሰሉ ምስጢሮች አቶ ብርሃኑ ጎበና በጻፉት ዓምደ ሃይማኖት መጽሃፍ ውስጥ ይገኛሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቁልቁለት መንገድ - አገሬ አዲስ

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የወንጌሉን ቃል በትክክል በመተርጎምና አማኞቿ ቀጥተኛና ያልተዛባ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ መንፈሳዊ ትግል ያደረገች የእግዚአብሄር እምነት ቅድስት ቤት ነች። ወደ ኋላ መለስ ብሎ ገድሏን በአትኩሮት ቢመረምሩ ቀጥተኛ፣ በግሪክኛው ኦርቶዶክስ የተባለችው ቤተ ክርስትያን ዛሬ ለሚነሱት ኃይማኖታዊ ውዝግቦች፣ የቀኖና ልዩነቶች፣ የኃይማኖት መከፋፈልና የወንጌል ነጋዴዎች ስውር ዓላማ ትክክለኛ ግንዛቤ ማስጨበጥ የምትችል ቤተ ክርስትያን ነች። እውነትን በመያዟ ምክንያት ነው ቤተ ክርስትያኒቱ ከጨረቃ በታች በሚርመሰመሱት ርኩሳን መንፍስት (bad demons) ሁካታና ሤራ ከዘመን ዘመን ጥቃትና በደልን የምታስተናግደው።

መደምደምያ

አንባብያን ሆይሁሉንም ሃሳቦች አንስቶ መጻፍ ቀላል ባይሆንም ከላይ የተመለክትናቸውን ሃሳቦች ጠቅለል አድርገን ስናይ ኃይማኖትን አስመልክቶ ፕላቶናዊስቶይካዊነት (Platonism- Stoicism) የግሪኩ (Hellenistic) ዘመን ዋነኛ የአስተሳሰብ መነሻና መንደርደርያ መሆኑን እንገነዘባለን። ግሪክ በታላቁ እስክንድር ወረራ ምክንያት ፍልስፍናን ወደሌሎቹ ሃገራት ወሰደች። ሮማም አውሮፓንና እስያን ስትገዛ ክርስትና በኃይል በያዘቻቸው አገሮች ሁሉ ተስፋፋ። ክርስትና በዓለም የተሰራጨው መሪዎች የሚያደርጉትን የግዛት መስፋፋት ተከትሎና በደቀመዛምርቱ ተጋድሎ ነው። ጥበብን የተሞላ እውቀትና ክርስትና ከጣዖት አምልኮ ባርነት ነጻ አውጥቶ የክርስቶስን ማዳን ያለብሳል እንጂ አንዳች ጉዳት አያመጣም። ኃያልነትን መሻትና ፍቅረነዋይ ጥበብን አነጠፈ እንጂ አውሮፓ ወደ ከፍተኛ እድገት የተመነደገችው ክርስትና ባስታጠቃት ጥበብ አማካኝነት ነው። አፍሪካውያን ለነጻነት ስትል ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከከችዋን የገናናዋን ኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት ሲወስዱ የአውሮፓ ስካንዴኒቭያ ሃገሮችም ወደ ሠላምና እድገት የመራቻቸውን ክርስትና ኃይማኖት ለማወደስ ባንዲራቸው ላይ የመስቀል ምልክት አድርገዋል።

ፕላቶ ማስተማር ከጀመረበት ዕለት ከሶስት ምዕት ዓመታት ገደማ በኋላ ከሰማይ ሠማያት ወርዶ ወደ ምድር የመጣው እየሱስ ክርስቶስ ፈላስፎቹ ያላገኙትን ሰባቱን ምሥጢሮች ራሱ ተናገረ። የዮሐንስ ወንጌልን ብንመለከት እየሱስ እንዲህ ይላል። ምዕራፍ 6: 35 “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፣ ምዕራፍ 8: 12 “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፣ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል፣ ምዕራፍ10:9 “በሩ እኔ ነኝ፣ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል…”፣ ምዕራፍ10:17 “…ነፍሴንም ስለበጎች አኖራለሁ። ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፣ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፣ ድምጼን ይሰማሉ…”፣ ምዕራፍ 11:25-26 “ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል…”፣ ምዕራፍ 14:6 “እኔ መንገድና እውነት፣ ሕይወትም ነኝ፣ ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም..”፣ ምዕራፍ15:5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ…”። የሚሉት ናቸው። እነሆ ብርሃን፣ እውነት፣ ጥበብ፣ የጨለማው መውጊያ፣ እረኛ፣ አስተማሪ፣ ወዘተ፣ እየሱስ ክርስቶስ ነው።

የመላ ኅዋ፣ ከዋክብት፣ ፕላኔቶች፣ ጸሃይ፣ ጨረቃና መላው ፍጥረታት ባለቤትና ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሄር ተወዳዳሪ የሌለውና በሰው ዓዕምሮ የማይመረመር በእውቀት ንድፈሃሳብ (theory of knowledge) ወይንም አመክንዖ (logic) የማይዳሰስ ኃይል ነው። ይሁንና ግን ፈላስፎች ስለ መናፍስትና አማልክት ጠቃሚ ትምህርቶችን ከማበርከታቸውም ሌላ የብርሃንን፣ የመላ ጠፈርን እጹብ ድንቅነት እንዲሁም የቃሉን (logos) መለኮታዊ ኃያልነት በማስመልከት ጠቃሚ አስተዋጾ አበርክተዋል። ፈላስፎች ዓለማችንን እስከዛሬ ድረስ ባልነጠፉ፣ የእድገትና መሻሻል መገኛ በሆኑት የተፈጥሮ፣ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ እውቀት ሞሏት። በእርግጥ እውቀት ጥበብ አልባ ሆኖ ነው ዛሬ ምድርን ከመቅሰፍት ሊያጠፋ የሚችሉት አውዳሚ መሳርያዎችና ብዙዎቻችንን ምርኮኛ ያደረጉት የመጨረሻው ዘመን የቴክኖሎጂ ውጤቶች (666) የተፈበረኩት። የዓለምን ፖለቲካ የሚያሽከረከሩት የእግዚአብሄርን ኃይል የረሱት መንግስታት ምድርን ብዙ ዋጋ እያስከፈሏት ነው።

በጥንት ዘመን አንዱ ያንዱን ሃሳብ በምክንያት (reason) እየደገፈ ወይም እየተቃወመ ሌላኛው ደግሞ አመክንዖ (logic) ተጠቅሞ ሃሳብን በማዳበር በግንዛቤ ላይ ግንዛቤን ይጨምራል። ጥበብ እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ የሰው ልጆችን ወደ ኋላ የመለሰው አሳፋሪው አዚም ከየት መጣ?

እውቀት በእግዚአብሄር ጥበብ ሲሞላ ከአንድ ቋጥን የተፈለፈለ ላሊበላን የመሰለ ከሰማይ የወረደ ትንግርት በውሃ ላይ ያቆማል። ወገኖቼ ወደ ማስተዋሉ እንመለስ።

ከጸሃይ በላይ እጅግ እጅግ ከፍ ብሎ የሚገኘው እግዚአብሄር ይመስገን። እግዚአብሄር አምላካችን ኢትዮጵያ ሃገራችንን ይጠብቃት፣ አሜን

(B.K)

Share