ኢትዮጵያን ማዳንና ማሳደግ ቀላል ነዉ፤ የሰላም ራዕይ ከፈጠርን – በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)

በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር) መጋቢት ፳፻፻፲፩ ዓ/ም

 

መንደርደሪያ፤

ዋና ዋና ችግሮቻችንን ጠንቅቀን እናቃለን ወይ? አይመስለኝም።
የዛሬዉ ጥያቄ ቅድሚያ የቅንጦት ነዉ ወይስ የመኖር? እኔ የመኖር ይመስለኛል።
የሚያዋጣንን ትግል እያካሄድን ነዉ ያለነዉ ወይ? አይመስለኝም።
ችግር ፈጣሪዎች ከሆን የሕዝቦቻችን ጉዳት አይባባስም ወይ? ካለጥርጥር።
የዉድ አገራችንን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እንችላለን ወይ? ካለጥርጥር።
የሕዝባችንን ደህንነት ማስጠበቅ እንችላለን ወይ? ካለጥርጥር።
በአገራችን ዘላቂ ዕድገት ማምጣት እንችላለን ወይ? ካለጥርጥር።

 

ስለዚህ እንስማማ ጎበዝ፤ ካለፉት አላስፈላጊ ጥፋቶች እንማር። በህብረት ቆርጠን እንነሳ፤ ሰላም ካለ በፈጣሪያችን ቸርነት የማንደርስበት መልካም ደረጃ አይኖርም። ስለዚህ የሚከተሉትን ቅን ሀሳቦች ዐይታችሁ የየድርሻችሁን ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ በሕዝባችንና በፈጣሪያችን ስም አደራ እላችኋለሁ።

 

፩ኛ/        ያለን ፀጋና የተፈጥሮ በረከት

 

ቸሩ አምላካችን ሁሉን ነገር አሟልቶ ነዉ የሰጠን። በዓለም ሁሉ ዞሬ እንዳየሁት እንደኛ አገር የታደለ አላየሁም።  የምድራችን ስፋት ዬትየሌለ ነዉ። ከቆላ እስከደጋ ለግብርናና ለከብት እርባታ ተስማሚ አየርና መሬት አጎናጸፎናል። በወንዞቻችንና በሃይቆቻችን ብዛት ሀብታም አድርጎናል። በተሟላ የተፈጥሮ ሀብት ያሸበረቀች እጅግ የላቀች ቅድስት አገር ሰጥቶናል። ለዚህ ነበር ዉድ አገራችን ከራስዋ አልፋ ለሌሎችም የምትተርፍ የዳቦ ቅርጫት ናት እያልን በትምህርት ቤት ያደግነዉ። ሕዝባችን በደግነት፤ በሰዉ አክባሪነት፤ በእንግዳ ተቀባይነትና በታታሪነቱ የታወቀ ነዉ። ይሄ ሁሉ እያለን ነዉ የምንቸገረዉ፤ ‘የዐባይን ልጅ ዉሃ ጠማዉ’ እንደሚባለዉ።

 

፪ኛ/        በፊት ከገጠሙን ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች መማር እንችላለን?

 

ያ ሁሉ ሀብትና ፀጋ እያለን ግን ዉድ አገራችን መድረስ ከሚገባት የእድገት ደረጃ ልትደርስ አልቻለችም፡፡ ደጋግሜ ለማስታወስ እንደሞከርኩት፤ ርሃብና ችጋር ቶሎ ቶሎ ይጎበኟታል፤ በቶሎም አይለቋትም፤ ሚሊዮኖች በየዓመቱ ይጠቃሉ፤ ሺህዎች ይሰደዳሉ፤ ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ሰላምና እርጋታ በማዉረድ የተፈጥሮ ኃብቶቻችንን  ተንከባክበን ለመጠቀም ብንችል ኖሮ ምንኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በደረስን ነበር፡፡ ከባድ እንቅፋቶች የሆኑን ብዙ የዉስጥና የዉጪ ኃይሎች ናቸዉ፤ በአጭሩ እንመልከት፡፤

 

ሀ)           ዉስጣዊ ችግሮች

 

ዋናዉን ዉስጣዊ ችግር በአንድ ሀረግ ማሳጠር ይቻላል፤ የዲሞክራሲ ማጣት። በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ወቅት ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ወጣ፤ ብዙ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች (ከነጥራታቸዉ)፤ ክልኒኮች፤ ሆስፒታሎች፤ ወዘተ ተገነቡ። የ5፤ 5 ዓመት በመባል የሚታወቁት ብዙ የዕድገት ዕቅዶች/ፕላኖች ተዘርግተዉ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል፤ የጎደለዉ አንድ ትልቅ ነገር ነበር፤ የዲሞክራሲና የመሬት ላራሹ ጥያቄ። በዘመኑ ንጉሠ ነገሥቱ ሁኔታዎችን አገናዝበዉ የሕዝቡን እሮሮ ሰምተዉ ፓርላማዉን በማጠናከር፤ የመሬት ይዞታን ቢያስተካክሉና ትንሽ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ለማድረግ ቢሞክሩ ኖሮ ያ ሁሉ ዉድቀት ባልደረሰ ነበር። በ1950ዎቹ በእነ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ የተጀመረዉ ትግል ከባድ ምሣሌ ጥሎ አለፈ። ቀስ በቀስ የወጣቶች፤ የምሁራን፤ የገበሬዎችና የሠራተኞች ብሶቶችና ትግሎች እያደጉ በመምጣታቸዉ ምክንያት ረዥም የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋናዊ አገዛዝ ሊያከትም በቃ።

 

የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን በወደቀበት ወቅት የተጠናከረ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ የሕዝቡ ትግልና ድል በወታደሮች ተቀማ። ነገር ግን ምንም እንኳን በእጁ ባለዉ ጠብ መንጃ አማካኝነት ሥልጣን ላይ ቢቆናጠጥም በጦር ኢኮኖሚ ዉስጥ እንኳን ሆኖ አንዳንድ መልካም ለዉጦች አሳይቶ ነበር። ነገር ግን ዲሞክራሲ እንደገና ታፈነ። ሕዝብ ለሚያሰማዉ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሹ ርሸና ሆነ። በሂደቱም ደርግ በገዛ ኃጢአቱና በሕዝባችን የረጅም ጊዜ ቆራጥ ትግል ኃይሉ ተደመሰሰ።  ወጣቱና ሕዝቡ በተደጋጋሚ በጠየቀዉ መሠረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተወከለበት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ቢመሰረት ኖሮ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ግንባታ ሊያመራ በቻለ ነበር። አሁንም በድጋሜ ዕድሉ አመለጠን። ያንን በታሪካችን ተሰምቶ የማይታወቅ የሕዝብ (በተለይ የንፁሐን ወጣቶች) እልቂት አስከተለ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በ19 ዓመቴ ወልጄው ሞቷል ያልኩት ልጄን አገኘሁት (ከዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ ጅግሳ0

 

ወያኔም ሲገባ ከደርግ የባሰ መንግሥት አይመጣም በማለት ብዙ ዜጋ በቀና ፊት ተቀብሏቸዉ ነበር። ‘የሚያጠግብ እንጄራ ከምጣዱ ያስታዉቃል’ እንደሚባለዉ ብዙዉ ነገር የተበላሸዉ ገና ከጅምሩ ነበር። በመጀመሪያዉ የለንደን ‘የሰላም’ ጉባኤ/ኮንፈረንስ ላይ ሆነ ቀጥሎ በተቋቋመዉ የሽግግር መንግሥት ዉስጥ ኅብረብሄር የነበሩ የፖሊቲካ ድርጅቶች እንዲሳተፉ አልተፈቀደም። ሕገ መንግሥቱም ሲረቀቅ ሕዝብን አላሳተፈም። በተለይ የአማራዉ ሕዝብ እንደጠላት ተፈረጀ። ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ በርግጥ ብዙ ግንባታዎች ተዘርግተዋል፤ ትልልቅ ፎቆችና ሰፋፊ መንገዶች ተሠርተዋል፤ በየክልሉ ብዙ ዩኒቬርሲቲዎች ተገንብተዋል። ሕዝቡ ግን ተረሳ፤ ተራበ፤ ተሰደደ፤ ተፈናቀለ። የአገር እድገት በፎቆች ብዛትና በመንገድ ስፋት ብቻ አይለካም። በተለይ የ1997ን የማያወላግድ የምርጫ ዉጤት ተቀብሉ ወያኔ/ኢሕአደግ ሥልጣኑን ቢያስረክብ ኖሮ ታሪክ በመሥራት ተመስግኖ፤ ለጥፋቶቹም ይቅርታ ተደርጎለት ተሸልሞ አገርም ሰላም ባገኘች ነበር። በኢትዮጵያ ምድር ታሪክ ራሱን ይደጋግማልና ይሄ ሊሆን አልቻለም። በዚህም ምክንያት እስከዛሬ ድረስ አገሪቷ ከባድ ጣጣ ዉስጥ ትገኛለች። ጎሣን ከጎሣ እያናከሱ ይገኛሉ። ሕዝብ በጉልበት ይፈናቀላል፤ ክፉኛ ይሰቃያል። የአገሪቷ ኅልዉና ራሱ ጥያቄ ዉስጥ እየገባ መጥቷል።

 

ለ)           የዉጪ ወራሪዎችና ከፋፋዮች ጣልቃ ገብነት

 

የዉጪ መንግሥታት የየራሳቸዉን ጥቅም ብቻ ነዉ የሚያስቀድሙት። በመጀመሪያ በ16ኛዉ ክፍለዘመን ወደ አፍሪቃ የመጡት ሕዝቡን ለባርነት ለመዳረግ ነበር። ወስደዉ አስቆፈሩ፤ አሳረሱ፤ አሽከርና ገረድ አደረጓቸዉ። ቀጥለዉ ከኢትዮጵያ በስተቀር ሁሉንም የአፍሪቃ አገሮች የቅኝ ግዛቶች አደረጓቸዉ፤ ሀብቱን ሙጥጥ አድርገዉ ዘረፉት። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ኃይላቸዉ ሲዳከም ነፃነት ተገኘ፤ ሆኖም ግን አምባ ገነኖችን ሥልጣን ላይ በማስቀመጥ የእጅ አዙር ግዛትና ብዝበዛ ቀጠሉበት። ጣሊያን በአድዋና በማይጨዉ ሞከረችን።  ፖርቱጋሎች፤ እንግሊዞች፤ ፈረንሳዮች፤ ተርኮችና ግብጾችም አንጃብበዉብን ነበር። እንግሊዝ በተለይ በኤርትራ በኩል ብዙ የክፍፍል ሴራዎች ሠርታብናለች። ዛሬ አሜሪካኖች፤ ፈረንሳዮች፤ ቻይናዎችና ዐረቦች ቀይ ባሕርንና ህንድ ዉቅያኖስን የመቆጣጠር ሽኩቻዎች ዉስጥ ናቸዉ፤ እየተቆጣጠሩም ይገኛሉ። ስለዚህ ካለሕዝባችንና ከፈጣሪያችን በስተቀር ከዉጪ ንፁሕ ወዳጆች ይኖሩናል ብሎ መገመት ሞኝነትና ግብዝነት ነዉ።

 

ኛ/        ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 

ሕዝባችንን ከመከራ፤ አገራችንን ከዉድቀት መታደግ ይኖርብናል። አገር ግን ለእኛ ብቻ ሳትሆን ለልጆቻችንና ለሚቀጥሉትም ትዉልዶች መትረፍ ይኖርባታል። ወንድሞቻችን፤ እህቶቻችን፤ አባቶቻችንና አያቶቻችን ደማቸዉን አፍስሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩዋት ቅድስት አገር በሁላችንም ትብብር ህልዉናዋ ተረጋግጦ አብባ ለዘለዓለም እንድትኖር ለማድረግ  ኃላፊነቱ የሁላችንም መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ስለዚህ የሚከተሉትን እርምጃዎች ብንወስድ ሁላችንም አቸናፊዎች እንሆናለን፤ ካለዚያ ሁላችንም ተጎጂዎች እንሆናለን። ይሄ ደግሞ የሚበጀዉ ለሴይጣንና ለዉጪ ወራሪዎችና ከፋፋይ ገዢዎች ብቻ ነዉ። ለሕዝባችን በተገባዉ ቃል ኪዳን መሠረት የሚከተሉትን ሀሳቦች ተግባር ላይ ለማዋል ግልፅ የሆነ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትና ሥራዉን ቶሎ መጀመር ይገባል ብዬ አምናለሁ።

 

(ሀ)       መጀመሪያ የዉድ አገራችንን ሕልዉና ማስጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት እናድርግ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድርድር አይሠራም! አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

 

በኢትዮጵያ አገራችን አንድ ጎሣ የሌላ ጎሣ ጠላት የሆነበት ታሪክ ጨርሶ አልነበረም። ጭቁኑ ሕዝባችን በዘር፤ በጎሣና በሃይማኖት ሳይጋጭ ተቻችሎ ተደጋግፎ የኖረ ነዉ። ዛሬ ግን የዉሸት ታሪክ እየነዙ ሕዝቡን በማሳሳት  ጎሣን ከጎሣ፤ ወገንን ከወገን ሲያጋጩና ሲያፈናቅሉ ይታያሉ። በተለይ በአማራ፤ በኦሮሞ፤ በቤኒሻንጉል፤ በሶማሌና ደቡብ ህዝቦች አካባቢ ብዙ ግጭቶች  ሲፈፀሙ ይታያሉ፤ ይሰማሉ። ወገን ተወገን ጋር ተታርቆ፤ ተፈቃቅሮና ተባብሮ እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል። ማንም ዜጋ በገዛ አገሩ በነፃ ተንቀሳቅሶ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ መብቱ እንዲጠበቅለት ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል።

 

(ለ)          የሽግግሩን መንግሥት ማስፋትና ማጠናከር

 

ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በአምባገነንነት ሲያስተዳድር የቆየዉ ኢሕአዴግ ነዉ። አሁንም የለማ ቡድን በመባል የሚታወቀዉና በዶ/ር አቢይ የሚመራዉ መንግሥት ኢሕአዴግ መሆኑን ራሳቸዉ የሚናገሩት ሃቅ ነዉ። የዚህ ቡድን ወደ መንግሥት ሥልጣን መምጣት መላዉ ሕዝብ የአካሄደዉ ትግል ፍሬ እንደመሆኑ መጠን በወሰዳቸዉ እርምጃዎች ብዙ የተስፋ ምልክቶች ፈንጥቋል። ብዙ የፖሊቲካ እስረኞች የተፈቱ ቢሆንም አሁንም ለዓመታት የታሰሩና የገቡበት የማይታወቅ ብዙ ወገኖቻችን እንዳሉ ግን መርሳት አይኖርብንም። በተቃራኒዉ ግን ግፍ ያደረሱ ግለሰቦች የተቀማጠለ ኑሯቸዉን ቀጥለዋል። እነዚህ ግለሰቦች ለአደረሱት ግፍ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ስላደረሱትም እጅግ አሰቃቂ ግፍ ይቅርታ መጠየቅ ይጠበቅባቸዋል። ደብዛቸዉ የጠፋዉንም ዜጎች ዬት እንዳደረሷቸዉ ቢነግሩን ለቤተሰብና ለወገን ትንሽ የመንፈስ እርጋታን ሊፈጥር ይችላል። ዛሬም ብዙ አስፈሪ እንቅፋቶች እየገጠሙ ናቸዉ። ከሁሉ በላይ የጎሣ ግጭቶች መባባስና የሚሊዮኖች ወገኖቻችን በግፍ መፈናቀልና ለእንግልት መዳረግ ከፍተኛ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዉ ተስፋና እምነት እያጣ መጥቷል። ስለዚህ ለሕዝባችን ሰላም ዋስትና ለመስጠትም ሆነ ጤናማ ፍትሐዊ ምርጫ ከማካሄድ በፊት አብዛኛዉ የኅብረተሰባችን ወኪሎች የሚሳተፉበት ጊዜያዊ/የሽግግር መንግሥት ማቋቋምና ማጠናከር እጅግ ጠቃሚ ይመስለኛል።  አንድነትን የሚደግፉ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶችም እየተቀራረቡ ኅብረት ቢፈጥሩ መልካም ነዉ። መቶ ቦታ እየተበጣጠሱ ማዉራት ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም።

 

(ሐ)         ነፃ አገራዊ ምርጫ ቶሎ ማካሄድ

 

የኢትዮጵያ ከባድ ነቀርሳ ሆኖ እስካሁን ድረስ የቀጠለዉ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ነዉ። አንድ ግለሰብ ጥሩ ሰዉ ሊሆን ይችላል። ግን ይሄ ብቻዉን በቂ ሊሆን ከቶ አይችልም። የሚያስፈልገዉ የሥርዓት ለዉጥ ነዉ። ፍትሃዊና ርትአዊ በሆነ ነፃ ሕዝባዊ  ምርጫ የተሰየመ ፓርላማ ሳይኖር አስተማማኝ መንግሥት ማቋቋም አይቻልም። ያዉ የተለመደዉ አምባገነናዊ ሆኖ ይቀጥላል። ከዚህ አባዜ ቶሎ መዉጣት ይኖርብናል። ሕዝቡ እንደሆነ ከዝግጁ በላይ ነዉ፤ የሚበጀዉን የመምረጥ፤ የማይፈልገዉን የማዉረድ በቂ ችሎታ አለዉ። ስለዚህ ሕዝቡ አልተዘጋጀም እያሉ ከንቱ መመፃደቅ ቦታ የለዉም። ያልተዘጋጁት አምባገነኖች እንጂ ጭቁኑ ሕዝባችን አይደለም። አሁን በአፋጣኝ የሚያስፈልገዉ ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም፤ የምርጫ ጊዜ ማሳወቅ፤ በየምርጫ ኬላዉ ላይ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ታዛቢዎች እንዲቀመጡ ማመቻቸትና ሥልጣኑን ላቸነፈዉ ፓርቲ ማስረከብ የተቀደሰ ተግባር ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ የራሴ መንግሥት የሚለዉን አስተዳደር አገኘ ይባላል። ሰላምና እርጋታም ይፈጠራል።

 

(መ)        የትላልቅ ከተሞች ምክር ቤቶችና ከንቲባዎች ምርጫ

 

ይሄም እላይ በተመለከተዉ መልክ ቢካሄድ ለሕዝቡ አመኔታና ዋስትና ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። ደግሞም የግድ ይላል። በነፃ ምርጫ ካልተሰየሙ አምባገነንነት ብቻ ነዉና። ከሆነም የሕዝቡን ፍላጎት ሊያሟላ አይችልምና። ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ነፃ ምርጫ አካሂዶ ለከተማዋ ሰላም ሊያወርድ እንደሚችል የሚያጠራጥር አይመስለኝም። በተመሳሳይ መልኩ ሌሎችም የአገሪቷ ከተሞች በዉስጣቸዉ የሚኖሩትን ዜጎች ሙሉና እኩል መብት እንደሚያስጠብቁ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Ethiopia: Muslim Protesters Face Unfair Trial

 

(ሰ)          ሕገ መንግሥት ማሻሻል

 

እላይ የተጠቀሰዉ አገራዊ ምርጫ እንደተገባደደ ሕገ መንግሥቱም አስፈላጊዉ መሻሻል እንዲደረግበት ያስፈልጋል። ያሁኑ ሕገ መንግሥት በችኮላ የተዘጋጀ ይመስላል። ብዙ ሰዎች ብሶት እያሰሙ ይገኛሉ። ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ እስከላይ ድረስ የሁሉንም ህዝብ ተወካዮች ያካተተ ሰፊ ዉይይት በማድረግ ሕገ መንግሥቱ ቢገመገምና አስፈላጊዉ መሻሻል ቢደረግበት የሕዝቡን ፍላጎት አሟልቷል ብሉ በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል። ይሄ ደግሞ የሕዝብ መሰረታዊ መብት ጥያቄ ነዉ።

 

(ረ)          ነፃ ተቋማትን ማቋቋም

 

ነፃ ፍርድ ቤቶች፤ የመከላከያ ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊቶች ማቋቋም የግድ ይላል። ይሄ ካልሆነ ሀቀኛ ፍትሕ ስለመደረጉ ዋስትና አይኖርም። የዋስትናም ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና ጉዳይ ነዉ። መተማመንን የበለጠ ነገር የለም። በነዚህም ሂደቶች ዉስጥ ካለ አድልዎ ሁሉንም ዜጎች እኩል ማሳተፍ ይጠበቅበታል።

 

፬ኛ/ ልማትና እድገት ላይ በመረባረብ ችጋር መቀነስ/ማጥፋት

 

እላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንቅፋቶች በመፈጠራቸዉ ምክንያት እንጂ ሕዝባችንን ከድህነት ለማላቀቅ አቅቶን አይደለም። ሰፊ መሬት አለን። ታታሪ ሕዝብ አለን። በአገርም ሆነ በዐለም ያካበትነዉ ከፍተኛ ትምህርትና የሥራ ልምድ አለን። ዛሬ ስንት ሺህ የላቁ የኢትዮጵያ ሣይንቲስቶችና ምሁራን ሌሎች አገሮችን ሲያቀኑ ይገኛሉ። ለሁሉም ወገኖች ሁኔታዎች ቢመቻቹ አገሪቷን ማልማት ይችላሉ። አገሪቷን ከጠፍነትና አየሩን ከብክለት መከላከል ይኖርብናል። ወንዞቻችንና ሃይቆቻችን እንዳይበከሉና እንዳይደርቁ መከላከል ይኖርብናል። እስከመቼ ነዉ በብድር፤ በልመናና በስደት ላይ ብቻ ጥገኞች ሆነን የምንቀጥለዉ? ለወጣቱ፤ ለሴቱና ለወንዱ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎች መክፈት ይኖርብናል። እድገትና ልማት ምን እንደሆኑ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ልማት የሌለዉ እድገት ብቻዉን ዋጋ የለዉም። እድገት ልማትን አስከትሎ የሕዝብን ሕይወት መቀየር አለበት።

 

፭ኛ/      የትግልን ታሪክ ጥሩና መጥፎ ጎኖች ጠንቅቆ መለየት ያስፈልጋል

 

ልጆች ሆነን ስንማርም ሆነ ለአገር ስንታገል (ከተገንጣይ ቡድኖች በስተቀር) አንዳችም የጎሣ አስተሳሰብ አልነበረብንም። ስለዚህ ሁሉንም እየጨፈለቁ ታሪክ እያዛቡ መናገር ትልቅ ኃጢአት ነው። ደም ባፈሰሰዉና አጥንት በከሰከሰዉ መራራ ትግል ዉስጥ የሁሉም ዜጋ አስተዋጽኦ ነበረ። ወያኔ/ኢሕአደግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ግን በፈረደበት አማራ ላይ የማይወረወር የዉሸት ታሪክ የለም።  የማከብራቸዉና የምወዳቸዉ ዶ/ር መረራ ጉዲና እንኳን ጥናታቸዉ ላይ ተመርኩዘዉ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ የጠቀሱት አንጀት የሚበላ ክፍል ይሄን ይመስላል፤ ቃል በቃል ባላስታዉሰዉም፤ ‘አንዳንድ ተገንጣዮች የሚስቱት ሃቅ ቢኖር በኢትዮጵያ ለመሬት ላራሹና ለእኩልነት ትግል የአማራን ልጅ ያህል ሕይወቱን የገበረ የለም’ ነበር ያሉት። የትግልን ዉጤት መንግሥት በመጨበጥና ባለመጨበጥ መታየበት የለበትም። አገር ወዳድ የሚታገለዉ ለሥልጣንና ለግል ጥቅም አይደለም። ሕይወት አጭር ናት። መተሳሰብና፤ መተባበርን የመሰለ ነገር አይኖርም።

 

ደጋግሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አሁን የቅንጦት ዘመን አይደለም፤ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነዉ። ሕዝብ እየተፈናቀለ እረፍት አይኖረንም። ወገን ከወገን እየተጋጨ ሰላም አናገኝም። ሰላም ሳይኖር እድገት አይኖርም። ለልጆቻችንና ለሚቀጥለዉም ትዉልድ እናስብ። ሕይወት አጭር ናት። ካለፉት ጠንካራና ደካማ ጎኖች እየተማርን መልካም ሥራ ሠርተን በሰላም እንለፍ እያልኩ በጥሞና እማፀናችኋለሁ። ፈጣሪ ይጨመርበት።

Share