በሰሜን አሜሪካ ከምንገኝ የቅማንት ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ

ቁጥር 2

ሰላም የህይዎት ዋስትና ነዉ

ሰላምና መረጋጋት የሌለበት መንግሥት ምንጊዜም ቢሆን ለዜጎች የህይዎት ዋስትና አይሰጥም ። በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ገና አንድ አመት ያልሞላው ስለሆነ  መንግስት ለሃያ ሰባት ዓመታት ሲጎነጎን የኖረውን ሴራ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት ባይኖረንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊተገበሩ የሚገባቸውን የዜጎችን ደህንነት ማስከበር በተመለከተ እየታየ ያለው ዳተኝነትና ለውጡ ይነካናል ብለው በማሰብ እየሞተ ያለው ስርአት እንዲያንሰራራ የሚጥሩ ሀይሎችን በፍጥነት ማጽዳት ባለመቻሉ በብዙ አከባቢዎች ጎሳን ምክንያት እያደርጉ የሚነሱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎችን ህይዎት ቀጥፏዋል፤ አካል አጉድለዋል፤ ብዙ ዜጎች ሀብት ንብረት አፍርተው ከኖሩበት ቀየ አፈናቅሏል።

በጎሳ ግጭት ምክንያት ጎዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ጎንደር ነዉ ። በተለይም በስሜን ምዕራብ አካባቢ ቅማንትና አማራ በሚል ሰበብ የተለያዩ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ ከጀርባ በመሆን በቆሰቆሱት ግጭት ከሁሉም ወገን ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የብዙ ሰው ህይወት ተቀጥፏል፤ ቤቶችና የንግድ ቦታዎች ተቃጥለዋል፤ የእህል ክምሮች ሳይቀር በመቃጠላቸው አንድ አመት ሙሉ የተለፋበት ምርት እንዳለ ወድሟል። በዚህ ሰበብ ስዎች ከመተማ፤ ከቋራ፤ ከጭልጋና አካባቢው ባሉ ከተሞችና የገጥር ቦታዎች ዘርን መሰረት አድርጎ ከሁለቱም ህዝቦች በኩል  ከእኔ አከባቢ ውጣ በሚል በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሎ፤ በተለያዩ የመጠለያ ቦታዎች ታጎረው በርሃብና በተላላፊ በሽታ እየተሰቃዮ ይገኛሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ በላይ አርማጭሆ፤ በታች አርማጭሆ፤ በምዕራብ አርማጭሆና በጠገዴ እስከ 14 ሺህ የሚደርስ ሕዝብ ከመንግሥት መስሪያ ቤት፤ ከንግድ ቦታ እና ከርሻ ቦታዎች ተፈናቅለው ትክል ድንጋይ ፤ ሳንጃ፤ ጎንደርና ወለቃ በሰፈራ ጣቢያ ውስጥ በበሽታና በርሃብ በመሰቃዬት ላይ ናቸው። ትክል ድንጋይ ላይ በጊዜያዊ መጠለያ የታጎረው ሕዝብ እስከ 10 ሺህ ሲሆን፤ ወለቃ ደግሞ 4 ሺህ  እንደሚደርስ ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። እንዲሁም እንደ ትክል ደንጋዩና ወለቃው ሁሉ ፤ በአይንባ 9 ሺህ፤ በጫንድባ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ብዙ ሕዝብ በጊዜያዊ መጠሊያ በርሃብና በበሽታ እየተሰቃየ ይገኛል።  የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኪሽን ጽ/ቤት በማዕክላዊና በምዕራብ ጎንደር 100 ሺህ ሕዝብ መፈናቀሉንና 6 ሺህ ቤቶች መቃጠላቸውን ሲገልጽ፤ የሞቱትንና የአካል ጉዳተኞችን አላሳወቀም።

ጎንደር ከተማም ቢሆን በሥጋት ቀጠና ውስጥ ናት ፤ በርካታ ወጣቶች ክላሽ ጠመንጃ ታጥቀው በጠራራ ጸሐይ በከተማ ውስጥ ላይ ታች ላይ ሲሉ መሰንበታቸው ጸሐይ የሞቀው፤ መንግስትም ያወቀው ጉዳይ ነው። መሣሪያውን መቸና በምን ሆኔታ እንደሚጠቀም ስልጠና ያልወሰደ ወጣት አንድ ግርግር ቢፈጠር በሰላማዊ ስዎች ላይ ምን ያህል መጥፎ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል መገመት አያቅትም

ለደረሰው ክቡር የሰዎች ህይዎት መጥፋትና ንብረት ውድመት በእኛ እምነት ተጠያቂ ናቸው የምንላቸውን አካላት እንደሚከተለው ለመግለጽ እንፈልጋለን ፤

 

  1. 1. መንግስትን በተመለከተ
  • መንግሥት ያለውን የጸጥታና የሕግ አስከባሪ አካላትን ተጠቅሞ የዜጎችን ደህንነት ማስከበር ግዴታም ሐላፊነትም አለበት። ይህ በማንኛውም ጊዜ መደረግ ያለበት ግዴታ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ወንጀል ሰርቶ እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ ወደ ህግ ከማቅረብ ይልቅ ወንጀለኛውን መልቀቅ ከወንጀለኛው የባሰ ወንጀል ነው ብለን እናምናለን። በተግባርም እየተደረገ ያለው ይህ ነው ። ከመንግሥት እውቅናና ፈቃድ ውጭ የጦር መሳሪያ ይዘው በከተማ ውስጥ ጨለማን ተገን አድርገው ሰው እያፈኑ የሚገድሉትን፤ ቤቶችንና የንግድ ተቋዋማትን የሚዘርፉትን አካላት አለማስቆም የመንግስት ድክመት ነው ብለን እናምናለን ። ትምህርት ቤቶች ለበርካታ ወራት ተዘግተው የመማርና የማስተማሩ ሂደት ተጓጉሎ መንግሥት ወይም የክፍሉ አስተዳደር አንድም አይነት እርምጃ አለመውሰድ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝበናል። በነዚህና በሌሎች በጎንደር አካባቢ እየደረሱ ላሉት ጥፋቶት አፋጣኝ እና ተገቢ የሆነ የህግ ማስከበር ሀላፊነቱን ባለመጣቱ መንግስት ተጠያቂ ነው ብለን እናምናለን
ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያዊያን እየተመከተ ያለው የአሸባሪው ሕወሓት ወረራ

 

  • ከሌላ አገር ማለትም ከሱዳን ጋር የሚያገናኙ ዋና መንገዶች ተዘግተው ፤ የንግድ ልውውጡ ከህገወጥ የመሳሪያ ነጋዴዎች በስተቀር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል። የሀገርን ህግና  የዜጎችን መብት አለማስከበር ንግድ ከአገራችን ጋር  የሚለዋወጡ መንግሥታትን ሳይቀች ትዝብት ላይ ይጥላል ብለን እናምናለን። ታዲያ በዚህ ሁኔታ የሚጉላላውን ገብሬና ነጋዴ ግብር አምጡ እያሉ ያውም ከአቅም በላይ መጫን ምን ማለት ነው? የመንግሥት አካላት ለደረሰው ጥፋት ዋና ተጠያቄ ናቸው ብለን እናምናለን

 

  • መንግስት “የቅማንትን የማንነት” ጥያቄ ለመመለስ የሄደበት አካሄድ ትክክል ስላልነበር በተለይም ህገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው አካሄድ ውጭ የቅማንት የራስ አስተዳደር እንዲቋቋም የፈቀደው ውሳኔ አሁን ለደረሰው ትርምስ እና እልቂት ከፍተኛ አሰተዋጽዖ አድርጓል ብለን እናምናለን። የተውሰኑ አካላትን ፍላጐት ለማሟላት ሲባል የቅማንት የራስ አስተዳደር የፀደቀው የህገ-መንግስቱን መስፈርት ሳያሟላ የተወሰደ እርምጃ በመሆኑ ይኸው አሁን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ስለዚህ መንግሥት በአግባቡ ሐላፊነቱን ባለመወጣቱ ከመነሻው እስካሁን ድረሰ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ነው ብለን እናምናለን

 

  • መንግሥት ከማንኛውም አካል በበልጠ በሚያስተዳደረው ሕዝብና አገር ላይ ሐላፊነት ሊሰማው ይገባል ብለን እናምናለን። ነገር ግን በአማራው ክልል መገናኛ ብዙሃን በኩል የመንግሥት ሐላፊነት ያላቸው ስዎች የቅማንት ታጣቂዎች ከመንግሥት በስተቀር ማንም ሊይዘው የማይችለውን መሳሪያ ታጥቀዋል፤ የአየር መቃወሚያ ሁሉ አላቸው እያሉ በተደጋጋሚ ነገሮችን ጣራ እያስነኩ መግለጫ ሲሰጡ ሕዝብ ስምቷቸዋል። አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳሳና እልህ እንዲጋባ የሚያደርግ ይህ አይነቱ መግለጫ በመንግስት አካላት በተደጋጋሚ መሰጠቱ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን። ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ አንድም ነገር በመረጃ ሲያቀርቡ አለመታየቱ የአባባላቸውን ታማኒነት ዝቅ ያደርገዋል።

 

  1. 2. “የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ” ነኝ ባዩን ቡድን በተመለከተ
  • ቅማንትና አማራ በጎንደር ውስጥ አብረው የሚኖሩት ከብዙ ሺህ አመታት በፊት ጀምሮ ሲሆን በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ላይ በአንድነት ሆነው ኢትዮጵያን ከአቆሙ ሕዝቦች መካከል ዋነኞች ናቸው። በዚህ የረዥም ጊዜ አብሮነት ምክንያት በአንድ መልክአ ምድር እየኖሩ፤ ተጋብተውና ተዋልደው፤ አንድ ቋንቋ ተናግረው፤ አንድ አምልኮ አምልከው፤ በደምና በሥጋ ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች ናቸው። ሕዝብን የሚበድለው የመንግሥት ስርዓትና የሥራአቱ ተጠቃሚዎች እንጅ አንድ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ በደለው ብሎ መነሳሳት ገዥ መደቦችን ከመጥቀምና የእነሱን እድሜ ከማራዘም በስተቀር ለሕዝብ ምንም አይፈይድም። ጨቋኝ ስርዓትን በጋራ ታግሎ መለውጥ እንጅ አጥንት ቆጥሮ በመከፋፈል መናቆር ፋይዳ የለውም። በኩራት አብሮ የኖረን ሕዝብ አንዱ ሌላውን በባርነት የገዛው በማስመሰል የሥልጣን ጥመኞች በፈጠሩት ድራማ፤ ከሌሎች ወገኖቹ ጎን በመቆም የህወሐትን አገዛዝ ለማስወገድ የተስፋ ጮራ የፈነጠቀበትን ጎንደር የጦር ሜዳ አድርገውት ይገኛሉ። ታዲያ እነዚህ የቅማንት የማንነት ጥያቄ አንግበናል የሚሉ አካላት ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲመለሱ ህዝብንም ወደ እልቂት እንዳይወስዱ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢመከሩ አልሰማም ብለው ለዚህ ሁለ እልቂትና ለየአከባቤው አለመረጋጋት ምክንያት ከመሆናቸው በተጨማሪ  ለጎንደር የታሪክ ጠባሳ በመጣላቸው ለጠፋው የሰዎች ክቡር ህይዎትና አካል ጉዳት ፤ ለወደመው ንብረትና ለተፈጠረው ሁከት በህግ ተጠያቂዎች ናቸው ብለን እናምናለን።
ተጨማሪ ያንብቡ:  የፊታችን ቅዳሜ በመቐለ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ይካሄዳል

 

  • አንዳንድ አካላት ቆመንለታል ለሚሉት ሕዝብ በሀቅ የቆሙ ከሆነ በይፋ ወጥተው በአመኑበት አቋም መሟገት ይችላሉ። ሆኖም ግን አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሳይንስና ቴክኖሎጅ አለምን አንድ መንደር በአደረገበት ጊዜ፤ ከምንጊዜውም በበለጠ የዓለም ህዝብ ይህን የሳይንስና ቴክኖሎጅ ውጤት የሆነውን የብዙሃን መገናኛ ተጠቅሞ በተቀራረበበትና አብሮ መኖር በጀመረበት ዓለም ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጅውን ለጥፋት የሚጠቀሙም ብዙዎች ናቸው። በዚህ ሁኔታ በኮምፒተርና በሶሻል ሜዲያ ጀርባ ተደብቀው ህዝብ ለህዝብ ለማፋጀት “ጀግናው አማራ ጨፍልቃቸው፤ ጀግናው የቅማንት ልጅ ወድረህ ተኩሥ” እያሉ ሐላፊነት በጎደለው አካሂድ የሰው ህይዎት እንዲቀጠፍ የሚያደርጉ የፌስ ቡክ አርበኞች ከፍተኛውን የጥፋት ድርሻ መውሰድ አለባቸው ብለን እናምናለን። ዛሬ ስማቸውን ደብቀው በውሸት ስም እየተጠቀሙ የፈለጉትን ወንጀል  የሚፈፅሙ አካላት እውነተኛው ማንነታቸው ዛሬ ባይሆን ነገ መውጣቱ አይቀርምና ከዚህ አፀያፊ ድሪጊታቸው እንዲቁጠቡ እየመከርን ማህበረሰባችን እነዚህን የፌስቡክ አርበኞች ማንነት እንዲያጋልጥና ከጥፋት መርዛቸውም እንዲጠነቀቅ እንመክራለን። እውነተና ፍትህ ከተጨፈጨፉ ሕዝቦች አጸደ ነፍስ ትጮሃለች

 

  • የሕወሀት እሰራት፤ ግድያና ጭካኔ ህዝባችን እየጨረሰ በነበርበት ወቅት እነ አርበኛ ጎቤና አብረዋቸው የወደቁ ጀግኖች “እምብኝ አንገዛም” ብለው ህይዎታቸውን ሰጥተዋል፤ በጀግንነታችውም ለዘመናት ሲወሱ ይኖራሉ። እነ አርበኛ መሳፍንትም አብረዋቸው የተሰለፉ ብዙዎች ጓዶቻቸው ቢሰውም እንኳ አሁን በአካል ያሉት የዛሬን ቀን መስካሪ መሆናቸው እጅግ ያስደስተናል። እነዚህ እውነተኛ ፋኖዎች ናቸው ብለን እናምናለን፤ ትግልና መስዋእትነታቸውን ደግፈን ከጎናቸው እንቆማለን። የአማራ ህዝብ ለሀገሩ ክብርና ለወገኑ ደህንነት ቀድሞ የሚወድቅ መሆኑን የሚዘነጋው ኢትዮጵያዊ አለ ብለን አናምንም። ነገር ግን ከአርባ አመት በፊት ጀምሮ የአማራን ህዝብ ታሪክ ለማጥፋትና ባልሰራው ወንጀል ለመቅጣት አላማቸው አድርገው የተነሱት አካላት  በቀጥታም ባይሆን በስውር የጥፋት ሴራቸውን አሁንም ያቆማሉ ብለን አናምንይ። ከዚህ አኳያ ቸሩንና ደጉን የአማራ ህዝብ በማደናገር “በቅማንት ስም ወያኔ ጎንደር ገብቷል” በማለት ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ሁኔታ ያልተረዱ አርሶ አደሮችን በማሰባሰብ በቅማንት ሕዝብ ላይ የአዘመቱ አካላት  ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ትልቁን የአማራ ህዝብ ለማዋረድና በዘር ማጥፋት ለማስወንጀል የተሸረበ ሴራ መሆኑን ህዝባችን ሊገነዘበው ይገባል ብለን እናምናለን፤ መንግስትም እነዚህን በአማራ ህዝብ ስም ወንጀል ለመፈፀምና ለማስፈፀም የተደራጁ አካላትን ተከታትሎ ለህግ እንዲያቀርብ አጥብቀን እናሳስባለን።

ሕዝባችን ሰላም ወዳድ ነው። አርሶና ነግዶ መኖር እንጅ እርስ በርስ መሻኮት የሚፈልግ ህዝብ አይደለም። ሳይፈልግና ሁኔታውን በቅጡ ሳይረዳ በተንኳሽ ኃይሎች ተገፍቶ ጊዚያዊ ግጭት ውስጥ ገብቷል። ከዚህ በመነሳት በሰሜን አሜረካ የምንገኝ የቅማንት ተወላጆች የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ገብቶ እያካሄደ ያለውን የሰላም ማስከበር ሥራ እያደነቅን አሁን ለተከሰተው ችግር በእኛ በኩል ተጨማሪ መፍትሔ ይሆናል የምንላቸውን ሀሳቦች ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቅላዩ የጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሚስጥር አዲስ አበባ የገቡት ህወሃቶች፣ በወለጋ ሌላ የእርስበርስ ግጭት፣ ሲኖዶሱ 5 ቀን ብቻ ሰጠ

መንግሥት፤

  • በአካባቢው በሁለቱም ወገኖች በኩል ጠብ የሚፈለፍሉትን አካላት በህግ አግባብ ማሳረፍና ለህግ በማቅረብ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ
  • በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ለራሳቸው ወንጀል መደበቂ ለማድረግ በሕዝብ መሐል ግጭት የሚያባብሱ አካላትን የማጣራትና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የራሱን አስተዳደር በማጠናከር ለክልሉ ህዝብ ፍትሀዊ የሆነ አስተዳደር መመስረት፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በሁለቱም በኩል ያለውን ህዝብ አገናኝቶ ሰላም እንዲወርድ ማድረግ
  • የተፈናቀሉና በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ያሉ ስዎችን መንግሥት እንዲያረጋጋና እርዳታ በበቂ እንዲደርሳቸው ማድረግ
  • ከሥራ ቦታቸው ተፈናቅለው በመጠለያም ሆነ በከተሞች የተበተኑ የመንግሥት ሰራተኞች ደሞዛቸው እየተከፈለ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መንግሥት ዋስትና መስጠት
  • ቤትና የንግድ ቦታዎች የተቃጠለባቸው ወገኖች ካሳ እንዲከፈላቸውና ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መርዳት
  • ቤቶቻቸውና ማሳቸው የተቃጠለባቸውን አርሶ አደሮች መንግስት በአስቸኳይ እንዲያቋቁማቸው ማድረግ
  • “የቅማንት የራስ አስተዳደር” የሚለው መሰረተ ሀሳብ የህዝብ ፍላጎት ሳይሆን የቅማንትንና የአማራን ሕዝቦች ከሁለት ከፍሎ ጎንደርን ብሎም የአማራን ክልል የማያቋርጥና የማያባራ የግጭት ቀጠና ለማድረግ የታለመ ሴራ በመሆኑ የቅማንት የራስ አስተዳደር እንዲቋቋም የአማራ ክልላዊ ብሔራዊ መንግስት ምክር ቤት ያፀደቀው የህገ-መንግስቱን መስፈርት ሳያሟላ በመሆኑ የቅማንት የራስ አስተዳደር እንዲሰረዝ ማድረግ
  • በአካባቢው የሚሰማሩ የፀጥታ ኃይላት በቂ ስልጠናና ዕውቀት ያላቸው ከሕዝብ ጋር አብረው የሚሰሩና የሕዝብ ደህንነት የሚጠብቁ እንዲሆኑ
  • በመካክለኛውና በምዕራብ ጎንደር የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም የተቋቋመው ወታደራዊ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን አስፈላጊ ቢሆንም በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቂ እንዲደረግ፤ በሁለቱ ሕዝቦች (አማራና ቅማንት) ላይ ግጭት ለመፍጠር ያሴሩ፤ ሰዎችን የገደሉና ያስገደሉ፤ የሰዎችን አካል ያጎደሉ፤ ስዎችን በመንግድ ላይና በመኖሪያ ቤታቸው ያፍኑን አያሳፈኑ፤ ቤቶችን፤ ክምርና አዝመራ (ማሳ) ያቃጠሉና ባጠቃላይ ወንጀል የፈጸሙ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን

በመጨረሻም የጎንደር ጌጡ አንድነቱ፤ የጎንደር አንድነት የሚከበረው በእኛ በአማራና ቅማንት ልጆች አንድነት ነው። በመከፋፈላችን የሚደሰትና ጎንደር በነደደው እሳት የሚሞቅ ጠላት ብቻ ነው። በዚህ አደጋ ህይዎታቸውን ላጡ ፈጣሪ ነብሳቸውን በሰላምና በገነት ያስርፍልን፤ ሐዘን ለደረሰባችሁ ሐዘኑ የሁላችን ነውና መጽናናቱን ይስጠን።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም በአንድነቷ ጸንታ ትኑር!!

ጎንደር በሴረኞችና በዘረኞች አትፈታም!!!

ሰላም ለሕዝባችን!!!

አገራችን እግዚአብሔር ይባርክልን!!!

የካቲት ፳፫ ፪ሺ፲፩ ዓ.ም

 

ግልባጩ፤

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት

ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት

Ethiopian Broadcasting Corporation (EBC)

ለFana Boadcasting Corporate S.C (ፋና ሬድዮ)

ለWalta Media and Communication SC (ለዋልታ ቲቪ ዜና አገልግሎት)

ለEthiopian Television (ለኢቲቪ)

ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ሬድዮ (Ethiopian Satellite Television &  Radio (ESAT))

 

 

 

Share