አዲስ አበባ በነዳጅ እጦት እየታመሰች ነው

አዲስ አበባ በነዳጅ እጦት የተነሳ እየታመሰች መሆኑን የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ገልጸዋል:: የዘ-ሐበሻ ሪፖርተር ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ያለውን መንገድ የቃኘ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየነዳጅ ማደያው ከፍተኛ ሰልፍ ይታያል:: በተጨማሪም አንዳንድ መኪኖች ወረፋ ለመጠበቅ በየጋዝ ማደያው አቆመው ቢያድሩም መኪኖቻቻቸው በጎታች መኪና (ቶ ትራክ) እንደተወሰደባቸው ዘጋቢዎቻቸን ገልጸዋል::
https://youtu.be/epx_GOJUaUQ

በከተማዋ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ከቦሌ እስከ አራት ኪሎ ነዳጅ ለመቅዳት. በየማደያው ወረፋ ይዘው የነበሩ መኪኖችን በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ስላለ መንገድ አትዝጉ በሚል አካባቢውን እንዲለቁ ቢያስገድዷቸውም ነዳጅ የጨረሱ መኪኖችና ባጃጆች በየመንገዱ ቆመዋል::

በዚህም የተነሳ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት ተከስቷል::

ባለፉት ቀናት በፀጥታ ችግር ምክንያት በመዲናዋ አዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተስተጓጎለው የነዳጅ አቅርቦት በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚፈታ ተገለጸ፡፡

በአፋር ክልል በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ከእሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የጂቡቲ መስመር ለሁለት ቀናት ያህል በመዘጋቱ፣ 1,000 የሚሆኑ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ መሀል አገር የሚያደርጉት ጉዞ ተስተጓጉሏል፡፡ ከጂቡቲ የሚመጡ ብቻ ሳይሆን ወደ ጂቡቲም የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ለመቆም ተገደው ነበር፡፡ በአጠቃላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች የአፋር ክልልን ለማቋረጥ ተቸግረው ቆይተዋል፡፡

በድሬዳዋ በኩል የገቡትም የተወሰኑ ነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አዋሽ ላይ መንገድ ስተለዘጋባቸው መሻገር አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት ቤንዚን፣ ናፍጣና የአውሮፕላን ነዳጅ የጫኑ 1,000 ያህል ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ቆመው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአፋር ክልል የተዘጉት ዋና ዋና መንገዶች ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በመከፈታቸው የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹የቆሙት የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ጭምር በመሆናቸው፣ መንገድ ላይ የትራፊክ መጨናነቅ ስለሚኖር አዲስ አበባ ለመድረስ አንድ ሁለት ቀን ይፈጅባቸዋል፡፡ ከማክሰኞ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ መግባት ስለሚጀምሩ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ይቀረፋል፡፡ ወደ ክልል ከተሞች እስኪደርሱ ሁለትና ሦስት ቀናት ሊፈጅ ይችላል፡፡ በክልል ከተሞች የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በሳምንቱ መጨረሻ ይፈታል፡፡ በአዲስ አበባ ግን ከረቡዕ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይረጋጋል፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከሰሞኑ ስለ ነዳጅ እጥረት እየተነገረ ባለበት በዚህ ሰዓት ዛሬ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ነዳጅ ለመቅዳት ተሽከርካሪዎች እንዲህ ተሰልፈው ታይተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ ከነዳጅ ማደያ ባለቤቶች እና አቅራቢ ተቋማት ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን በጽሕፈት ቤታቸው ፌስቡክ ገጽ ላይ ጽፈዋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ክልል ፕሬዚዳንት - ፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው ከሚድ ዌስት አሜሪካ
Share