የባህል ማዕከል በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ክስ መሰረተ

በብሄራዊ ባህል ማዕከል የገቡትን የፌዴራል ፖሊሶች በተመለከተ ዘሀበሳ ተከታታይ ዘገባዎችን ማቅረቧ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደደረሰ ጭምር ባለፈው ሳምንት ዘግበን ነበር፡፡ አሁን ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ሊቀረፍ ባለመቻሉ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን ለመረዳት ችለናል፡፡ የባህል ማዕከሉ የፖሊስ አባላቱ ያረፉበት መጋዘን ውስጥ የነበረ የግንባታ ንብረት ሲጠቀሙበት በመታየቱ ክስ መጀመሩን ገልጿል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ዛሬ ለታተመው መንግስታዊው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አዲስ በተገነባው የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ የነበሩ አባላቱ እንዲወጡ ሲደረግ ወደ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ግቢ በጊዜያዊነት ገብተዋል። በባህል ማዕከሉ ቅጥር ግቢ ሲገቡም ንብረቶችን ወደ አንድ ጎን አድርገው በጥንቃቄ በማስቀመጣቸው አንድም ንብረት አለመባከኑን ጠቁመዋል።
የፖሊስ ህዝብ ግንኙነቱ የሰውን ህይወት የሚጠብቁ ፖሊሶች ላይ ንብረት እያባከኑ መነገሩ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ አባላቱ የግድ ማረፊያ ያስፈልጋቸው ስለነበር ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት ወደነበረው የማዕከሉ ግቢ እንደገቡ አስረድተዋል፡፡ በንግግራቸውም ‹‹ነገርግን ፍቃድ ሳይገኙ ወደ ማዕከሉ መግባታቸው እንደክፍተት ይወሰዳል። በመሆኑም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በጥቂት ቀናት ውስጥ የመፍትሄ ምላሽ ይሰጥበታል›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ሲንግሉ ከበደ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ከባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር ስር ተጠቃሏል የሚል መረጃ በመስማታቸው ወደግቢው ገብተው መጋዘኑን ካምፕ አድርገውታል ብለዋል። ከገቡ በኋላም በተቋሙ ኃላፊዎች ህጋዊነት እንደሌላቸውና የመንግስት ንብረት በመኖሩ ፍቃድ መሰጠት እንደሚገባው ተገልጾላቸዋል። በወቅቱም ጉዳዩን ወደክስ መውሰድ እንደሚቻል ፖሊሶቹ በመግለጽ መጋዘኑን እንደማይለቁ እንዳሳወቋቸው አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ሲንግሉ ገለጻ፤ ፖሊሶቹ ለግንባታ የተቀመጡ የመንግስት ንብረቶችን እየተጠቀሙ መሆኑ ስለታወቀ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ደንብ ማስከበር ሪፖርት ተደርጓል። ችግሩ ሊቆም ባለመቻሉ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ አማካኝነት ሁከት ይወገድልኝ የሚል የፍትሃብሔር ክስ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጀምሯል። ንብረቱ በሌላ አካል ቁጥጥር ስር ከዋለ ከህግ አንጻር እንደወደመ እንደሚቆጠርም ጠቁመዋል።
https://www.youtube.com/watch?v=urrQCDkbbQE&t=489s

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወደ አዲስ አበባ የመግባት መብታችን ይከበር!    ሁለተኛ ቀን ደጅ ጥናት
Share