አሥር ሴቶች የተካተቱበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ በፓርላማ ፀደቀ | በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት መከላከያ ሚ/ር መረጠች

100% ኢህ አዴግ የሚቆጣጠረው ፓርላማ ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ፣ እስካሁን የነበሩትን 28 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወደ 20 በማጠፍ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቢኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አሥር የሴት ሚኒስትሮች ሲኖሩት፣ አዳዲስ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተዋቅረዋል፡፡ በተጨማሪም የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሃያኛው የካቢኔ አባል እንዲሆን ተወስናል፡፡

ከአፈ ጉባዔነታቸው መልቀቂያ አቅርበው በተነሱት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የሚመራው አዲሱ የሰላም ሚኒስቴር ሰላምና የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያና በአካባቢው አገሮች ለማስፈን እንዲሠራ የተመሠረተ መሆኑ ሲገለጽ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፣ የፌዴራል ፖሊስና የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከልን በበላይነት ይመራል፡፡ ከዚህ ቀደም የቀድሞው የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር የነበረውን ሥልጣንና ተግባር ይረከባል፡፡ የሰላም ሚኒስተር የተሰጠው ስልጣን በጣም በዛ በሚል አንድ ሰው በፓርላማው ተቃውሞ ሲያሰሙ የፓርላማ አባላቱ የግለሰብን የመናገር መብት በመጣስ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አጉረምርመዋል::

እንደ አዲስ ለተዋቀረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ብቃት አላቸው ተብለው የተመደቡት ሚኒስትሮች ሹመት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው ሙሉ ድምፅ ይሁንታ አግኝቶ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ የካቢኔ አባላቱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የሰላም ሚኒስቴር – ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

2. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር – ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)

3. የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር – አቶ አህመድ ሺዴ

4. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ – አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ

5. የግብርና ሚኒስቴር – አቶ ኡመር ሁሴን

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፀጥታ ሃይሎች በጭፍን ታዛዥነት የሚጥሷቸው መሰረታዊ መርሆች

6. የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር – ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር

7. የገቢዎች ሚኒስቴር – ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

8.የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር – ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)

9.የትራንስፖርት ሚኒስቴር – ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

10.የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር – አቶ ዣንጥራር ዓባይ

11. የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር – ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር)

12. የትምህርት ሚኒስቴር – ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር)

13. የማዕድና ነዳጅ ሚኒስቴር – አቶ ሳሙኤል ሆርቆ

14. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር – ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

15. የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር – አሚን አማን (ዶ/ር)

16. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር – ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር)

17.የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር – ወ/ት የዓለም ፀጋይ አሰፋ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወ/ት ዓለም ጸጋዬን ስም አሳስተው በመጥራት ሌላ ስም ሰጥተው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ስም አሳስተው በመጥራታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል::

18. የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

19. የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር – ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)

20. የፕላንና የልማት ኮሚሽን – ወ/ት ፍፁም አሰፋ ናቸው::

በዛሬው ፓርላማ ውሎ የካቢኔ አባላቱ ምርጫ በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ለዲሞክራሲ ጠቃሚ አይደለም እየተባለ እየተተቸ ይገኛል:: ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ “ፓርላማው ልክ እንደ መለስ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሁሉን ነገር አሜን ብሎ የሚቀበል መሆኑን አሁንም እያሳየ ነው:: የሰው ልጅ አንድ አይነት አመለካከት እንደማይኖረው ሁሉ ፓርላማው ቢያንስ 70% ወይም 60% አጸደቀው ቢባል የተሻለ ዲሞክራሲ እንዳለ ያሳይ ነበር:: ሃሳብ የማያፈልቅ; የማይሞግት; መቶ በመቶ ሁሉን የሚያጸድቅ ፓርላማው መቀየር አለበት” ሲል ተችቷል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዛሬም ይድረስ ለአማራ ምሁራንና የአማራ ሕዝብ!

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በበኩሉ “ዶክተር አብይ አህመድን ማወቅ የፈለገ በዛሬው ካቢኔ ማየት ነው!
~በርካታ ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ ዜጎችን የሚያሰቃየውን የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ጋር የሚሰረራውን እና ጠላፊውንና የዜጎችን የስልክ ግንኙነት ሲያዳምጥ የሚለውለውን ኢመድኤ (ኢንሳ)፣ ዜጎችን በጅምላ የሚያስረውንና ዘግናኝ ድብደባ የሚፈፅመውን እንዲሁም ገዳዩን ፌደራል ፖሊስን፣ በኢኮኖሚ ደሕንነት ስም ከሀብታም ጋር በዜጎችና በሀገር ሀብት ላይ ሲደራደር የሚውለውን የኢኮኖሚ ኢንተለጀንስ አጠራቅሞ የሰላም ሚኒስትር ብሎታል።
~የመረጃ ደሕንነት አገልግሎት፣ የኢመድኤ (ኢንሳ) ኃላፊዎች ደካማዎች ቢሆኑም ብአዴን በፌደራል ደረጃ ያገኛቸው ቁልፍ መስርያ ቤቶች ናቸው። የፌደራል ፖሊስ ደግሞ በደኢህዴኑ ዘይኑ ስም ተይዧል። እነዚህን በጥባጭ መስርያ ቤቶች ጥሩ ስም ባለው “ሰላም” አሽጓቸዋል። ሶስቱንም በጥባጭ ተቋማት ለዶክተር አብይ አህመድ እጅግ ቅርብ በሆነች ሴት በኩል ይዟቸዋል። ብአዴንና ደኢህዴን እንደተአምር ያገኙት የሚመስላቸውን ሶስቱን መስርያ ቤት ደኢህዴንም ሆና አብይን ልታስቀድም በምትችል ሴት በኩል ይዞታል!
~በዛሬው ዕለት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሴት የመከላከያ ሚንስትር ተሹማለች። የመከላከያ ሚኒስትሯም፣ የሰላም ሚኒስትሯም ለአብይ የሚቀርቡ አማካሪዎች ይከቧቸዋል። በቀጥታ አብይ የተቋማቱ መሪ እንደሆነ ይቆጠራል።” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል::
በኢህአዴግ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ኮከብ እየተባሉ የሚጠሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ተነስተው በሕወሓቷ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ሞንጆሪኖን መተካታቸውን በተመለከተ መምህርት መስከረም አበራ በሰጠችው አስተያየት “ሞንጆሪኖ ካልተሾመች ሃገር የማይቆም ከሆነ እንኳን ተጋዳሊት ስለነበረች መከላከያ ሚኒስትር ብትሆን ይሻል ነበር፡፡ እንጅ የህወሃትን ሰው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ማድረጉ ኢፈርት የለመደውን እንዳያጣ ከመርዳት በቀር ለእኛ ምን ሊረባን? ፡፡ከሃያ ሚኒስትር ግማሹ ሴት እንዲሆን ይሁን ሞንጆሪኖ ከዶ/ር አምባቸው የተሻለ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነት እውቀት ኖሯት ይሁን እዛ ቦታ ላይ የተቀመጠችው የኢህዴግ አምላክ ያውቃል! ” ብላለች::
https://www.youtube.com/watch?v=d1wWzuTMu2s

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፋሲካ ዕርቅን ከሰሜን አየርላንድ ብንማርስ?
Share