የፋሲካ ዕርቅን ከሰሜን አየርላንድ ብንማርስ?

በ-ዳጉ ኢትዮጵያ
(dagu4ethiopia@gmail.com)

 

ከ16 አመታት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዚያ 10 ቀን 1998፡፡ በሰሜን አየርላንድ የሰላም ሒደት ውስጥ ቁልፍ ቦታ የሚሰጠው የዕለተ ስቅለት ስምምነት (The Good Friday Agreement) ተፈረመ፡፡ ከረጅም ጊዜ የእርስ በዕርስ ጦርነት፣ ካልተቋረጠ ውጥረትና የእርስ በእርስ ጥላቻ በኋላ የተፈረመው ይህ ውል በውስጡ ሁለት ተዛማጅ ስምምነቶችን የያዘ ነበር፡፡ ቀዳሚው በአብዛኛዎቹ የሰሜን አየርላንድ ፓርቲዎች መካከል የተደረገ ስምምነት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በእንግሊዝና በአየርላንድ መንግስታት መካከል የተደረገው አለም ዓቀፍ ስምምነት ነበር፡፡

በተለምዶ The Troubles እየተባለ የሚጠራው የሰሜን አየርላንድ ግጭት ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሰሜን አየርላንድ ውስጥ ሲካሔድ የቆየ የብሔር ግጭት ሲሆን አድማሱንም በማስፋት አየርላንድ ሪፑብሊክን፣ ኢንግላንድን ብሎም መላውን አውሮፓ ያዳረሰ የዘመናዊቷ አውሮፓ የከፋ ግጭት ነበር፡፡ ግጭቱ በዋነኝነት ፖለቲካዊ መልክ ሲኖረው ብሔረሰባዊ ገጽታም ነበረው፡፡

የግጭቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሰሜን አየርላንድ ህገመንግስታዊ ቦታ (constitutional status) እና በሁለቱ ዋና ዋና የሰሜን አየርላንድ ማኅበረሰቦች፣ ማለትም ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በአንድነት መኖር በሚፈልጉት በአብዛኛው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና የተዋሐደችውን አየርላንድ መመስረት በሚፈልጉት በአብዛኛው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆኑት የአይሪሽ ብሔረተኞች መካከል የሚኖረው ግንኙነት ነበር፡፡

ልክ የዛሬ 16 ዓመት በእለተ ስቅለት ከ3,500 በላይ ለሆኑ ሰዎች መሞትና ከ50 ሺ በላይ ለሆኑት መቁሰል ምክንያት የሆነው ግጭት በስምምነት እልባት ተበጀለት፡፡ ክርስቶስ አለሙን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ቤዛነትን በከፈለበት ቀን በወንድማማቾች መካከል ያለን ፀብ በዕርቅ መፍታት ምንኛ የተወደደ ተግባር ነው!

በቅዱስ መጽሐፍ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ቁ. 14 ላይ “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ … በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ…” ሲል የክርስቶስን ቤዛነት ምስጢር ይነግረናል፡፡ እያከበርነው የምንገኘው የክርስቶስ ስቅለትና ትንሳዔ በአል በዋነኝነት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ስላለው የጥል ግርግዳ መፍረስ ቢሆንም የሰሜን አየርላንድን አርአያ ተከትለን በመካከላችን ያለውን ፀብና አለመስማማት ለመፍቻ ብንጠቀምበት የበለጠ ግሩም ይሆናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥብቅ ሚስጥር! ኦነግ ሸኔ የብልጽግና አንዱ ክንፍ ነው! // በጋራ የሚሰሩት ኦፕሬሽን ሲጋለጥ!

በወንድማማቾች መካከል ያለው የፀብ ግርግዳ ይፈርስ ዘንድ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ከዶክተር ብርሐኑ፣ አቦይ ስብሀት ከፕሮፌሰር መስፍን፣ ጄ/ል ሳሞራ ለጄ/ል ከማል መተቃቀፍ ባይችሉ እንኳን በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ስለችግሮቻቸው መፍትሔ ሲወያዩ ብናይ የክርስቶስ ትንሳዔ በዓልን ከሐገራችን ትንሳኤ ጋር አያይዘን ባከበርነው ነበር!

በአንድ ሐገር ልጆች መካከል ያለው የጥል ግርግዳ ይፈርስ ዘንድ ገዢው ፓርቲ በማጎሪዎቹ ያያዛቸውን መብታቸውን ከመጠየቅ ባለፈ አንዳች ወንጀል ያልሰሩ የህሊና እስረኛ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በዓሉን በማስመልከት ቢፈታልን የበአሉን መልዕክት ምንኛ በላቀ መልኩ መረዳት በሆነ ነበር! አንዱአለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣ እስክንድር ነጋ፣ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት… ወዘተ እና ሌሎች የማናውቃቸው በየሰቆቃ ጣቢያው ፍትህ ተነፍገው የሚሰቃዩ ሺህ በሺ ወገኖቻችን ከዕርቅና ስምምነት በመነጨ የነጻነትን አየርን ሲተነፍሱ ብናይ የክርስቶስን የዕርቅ መልዕክት በላቀ ጥልቀት በመረዳት በታሪክ ድርሳናት ላይ መስፈር በቻልን ነበር!

የእምነት አባቶቻችን ቀኑን አስመልክተው ለምዕመናኖቻቸው በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶቻቸው ለዚህ ዓመት እንኳን መንግስትን ለማስደሰት ከሚደረጉ የካድሬ መሠል መልዕክቶች ተላቀው በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ወገን ላሉ ሁሉ ይህን የእርቅ መልዕክት ቢስተላልፉ ምንኛ በኮራንባቸው ነበር!

በተቃዋሚው ጎራ ያሉትም መሪዎች አንድ መሆን ባይችሉ እንኳን በመከባበርና በመተባበር በጋራ ይሰሩ ዘንድ በስምምነት ሲጨባበጡ በጋዜጦች የፊት ሽፋን ላይ ብንመለከት፣ የሰማያዊው ኢ/ር ይልቃል ከአንድነቱ ኢ/ር ግዛቸው፣ የኦፌኮው ዶ/ር መረራ ከመኢአዱ አቶ አበባው ጋር በወንድማማችነት መንፈስ አብረው ለመስራት ሲስማሙ ብናይ የወንድማማቾች የፀብ ግድግዳ ስለመፍረሱ ምንና ህያው ምስክርነታችንን በሰጠን ነበር!

መልካም ፋሲካ!

 

Share