Sport: ጌታነህ የዓለም ዋንጫውን እየናፈቀ ነው

ከአሰግድ ተስፋዬ

ጌታነህ ለሱፐር ስፖርት እንደገለፀው ፤ዋሊያዎቹ ከናይጄሪያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ለመሳተፍ በጥሩ ጤንነትና ብቃት ላይ ይገኛል፤
የዋሊያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊውና ለደቡብ አፍሪካው ቢድቨስት ዊትስ በመጫወት ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ላይ መካፈል እንደሚሻ አጽኖኦት ሰጥቶ ተናግሯል።
ተጫዋቹ ተቀማጭነቱን ደቡብ አፍሪካ ካደረገውና ሰሞኑን በዓለም ዋንጫው የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ዋሊያዎቹ ከናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር መደልደላቸውን ተከትሎ በተለይ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን አስተያየት በተከታታይ እያቀረበ ካለው ሱፐር ስፖርት ድረ ገጽ ጋር ባደረገው ቆይታ ብራዚል በምታዘጋጀው የአውሮፓውያኑ 2014 የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆን ከምንም በላይ የሚፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል።
ጌታነህ ከበደ ዋሊያዎቹን ለመጨረሻው ዙር ባሳለፈውና በኮንጎ ብራዛቪል ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በተካሄደው ወሳኝ ጨዋታ ላይ በጉዳት ምክንያት ባለመሰለፉ ቅር መሰኘቱን ገልጾ፣ ከናይጄሪያ ጋር በሚደረገው የሞት ሽረት ጨዋታ ለመሳተፍ በሚያስችለው ጥሩ ጤንነትና ብቃት ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።
« በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጨዋታ ላይ ባለመሰለፌ ጥሩ ሰሜት አልተሰማኝም። ጨዋታውን ለማሸነፍ ያላቸውን ሁሉ በሰጡት የቡድን አጋሮቼ ኮርቻለሁ። እኛ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ረጅም ርቀት ተጉዘናል» ብሏል።
« አሁን ከጉዳቴ ሙሉ ለሙሉ በማገገሜ ሙሉ ትኩረቴ ከናይጄሪያ ጋር በምናደርገው ጨዋታ ላይ ነው። እነርሱ (ናይጄሪያዎች) የአፍሪካ ሻምፒዮና መሆናቸውን ሁላችንም እናውቃለን። በአፍሪካ ዋንጫው ላይም ተጫውተን አሸንፈውናል። አሁን የእኔና የቡድን አጋሮቼ ፍላጎት ያንን ሽንፈት በድል መካስ ነው» ብሏል የቀድሞው የደደቢት እግር ኳስ አምበል ጌታነህ።
« በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞች የአሸናፊነቱን ቅድሚያ ግምት ለናይጄሪያ ሰጥተዋል።ይህንን ተከትሎም ናይጄሪያዎች ለእኛ ዝቅተኛ ግምት ሰጥተው ከመጡ ተጸጽተው ይመለሳሉ። በእርግጥ ጨዋታው ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የእኛ ፍላጎት ማንም ያልጠበቀውን ታሪክ ለመሥራት ነው፤ ለእዚህም ቁርጠኞች ነን። በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ የቀሩን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ ያለንን ሁሉ ለመስጠትና የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ህልማችንን እውን ለማድረግ እንጥራለን» ብሏል።
በዋሊያዎቹ አባላት ላይ ያለው መነሳሳትና የቡድን አንድነት አስገራሚ መሆኑን ጠቅሶ፣ እያንዳንዱ የቡድን አባል ያለውን ሁሉ ከሰጠ የማይቻል ነገር እንደሌለ በሚገባ አስረድቷል። «ሁላችንም ለአገራችን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን» ሲልም አረጋግጧል።
አሠልጣኝ ጋቪን ሃንትን በችሎታው አሳምኖ ለደቡብ አፍሪካው ቢድቨስት ዊትስ እግር ኳስ ክለብ መፈረም የቻለው ጌታነህ በክለቡ የእስካሁን ቆይታው ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ላይ ይገኛል። ተጫዋቹ ለአዲሱ ክለቡ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል፤ ስሙ በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።
ጌታነህ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ተቀማጭነቱን ኢንተርኮንቲኔንታል አድርጎ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።
ጌታነህ ከበደ ከ200ና 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በኮከብ ግብ አግቢነት ከማጠናቀቁም በላይ በ2005ዓ.ም የኮከብ ተጫዋችነት ክብርንም ደርቦ መጎናጸፉ ይታወሳል።
ጌታነህ ከበደ ደደቢት እግር ኳስ ክለብን ከመቀላቀሉ በፊት የደቡብ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እግር ኳስ ቆሸሸ! የፖሊሶች ምርመራ ውጤት መላው አውሮፓን አስደንግጧል
Share