አየር ኃይል ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ተበየነባቸው

(በጌታቸው ሺፈራው)

የቢፍቱ አየር ኃይል የጥበቃ ሁኔታ፣ የመኮንኖች ብዛት፣ የጦር ብዛት፣ የጦር መሳሪያ አይነት እና ሌሎች ጥናቶች በማድረግ አየር ኃይል ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር የተባሉ ተከሰሾች በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን በህዝብ መገልገያና ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ መዘጋጀት፣ ማቀድና ማሴር የሽብር ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Photo File

በእነ ድሪብሳ ዳምጤ የክስ መዝገብ የተከሰሱት 3ኛ ተከሳሽ አንበሳ ጎንፋ፣ 4ኛ ተከሳሽ አለሙ አንበሳ፣ 6ኛ ተከሳሽ ካፒቴን ዋቆ መርጋ እንዲሁም 11ኛ ተከሳሽ ሞሲሳ ዳግም ቢሾፍቱ የሚገኘው አየር ኃይል ላይ ጥናት በማድረግ ቢሾፍቱ በሚገኘው ራዳር፣ በዚሁ ከተማ በሚገኘው የሄሊኮፍተር ነዳጅ ማደያ እንዲሁም ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በሚመላለሱ አውሮፕላኖች ላይ ጥቃት ለማድረስ ጥናት አድርገው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በአራቱ ተከሳሾች ላይ ተመስርቶባቸው የነበረውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

በእነ ድሪብሳ ዳምጤ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 17 ግለሰቦች ላይ የፀረ ሽብር አዋጁን አንቀፅ 4 በመተላለፍ ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የነበር ሲሆን የአየር ኃይል ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር ከተባሉት አራት ተከሳሾች ውጭ ያሉት አንቀፁ ተቀይሮላቸው በአዋጁ አንቀፅ 7/1 ስር የተደነገገውን በአባልነት መሳተፍ የሽብር ወንጀል እንዲከላከሉ ተበይኗል፡፡

አንቀፁ የተቀየረላቸው ተከሳሾች መንግስትን በመሳሪያ ከስልጣን ለማውረድ ኦሮሚያ ውስጥ ምዕራብ ሸዋ ጀልዱና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ጫካዎች ውስጥ የኦነግ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመክፈት፣ አባላትን በመመልመል፣ በማሰልጠንና በማስታጠቅ ተሳትፈዋል የሚል ክስን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚገኙበት ሲሆን ካፒቴን ዋቆ መርጋ እና ሌሊሴ መርጋ የአየር ኃይል ባልደረቦች እንደሆኑ ተገልፆአል፡፡ ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ ለህዳር 28/2010 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል (CREW) የተሰጠ መግለጫ
Share