ከኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል (CREW) የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል (CREW) ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለሴቶች የእኩልነት መብት መረጋገጥ፣ ለዲሞክራሲ ሥርዓት እውን መሆን፣ ለሰላምና ለሕግ የበላይነት ተግባራዊ መሆን የሚታገል ሕዝባዊ ድርጅት ነው።
እኛ በኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል የተሰባሰብን ሴቶች በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴና የመንግሥትንም በሕዝቡ ለተነሱት ጥያቄዎች የሚሰጠውን የጥይት ምላሽ እየተከታተልን ነው። ለመብታቸው ሲታገሉ መስዋዕት የሆኑትን ወገኖቻችን ነፍሳቸው በሰላም እረፍት እንድታገኝ፤ የተሰዉላት ሀገራቸውም ስቃይና መከራዋ በአጭር ሆኖ ትንሣኤዋን ለማየት እንዲያበቃን እየተመኘን ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ መጽናናትን ያድልልን እንላለን።
በሀገራችን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ ደረሷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መሠረታዊ መብቱ ተረግጦ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች ሆኖ፣ ወጣቶች የተሻለ ኑሮና ሕይወት ፍለጋ ወደ ማያውቋቸው ሀገሮች በበረሃ፣ በባህር፣ በዱር በገደሉ እየተጓዙ የአውሬና የአሣ ነባሪ ቀለብ ሆነዋል። ላለፉት 25 ዓመታት ያለማቋረጥ ሀገራቸው የምድር ሲኦል ሆናባቸው በድህነት፣ በሥራ አጥነት፣በማንነት ጥያቄ፣ መተንፈሻ በማጣታቸው ትዕግሥታቸው ገንፍሎ በቃን ተበደልን፣ በደል አንገፈገፈን ብለው በሰላማዊ መንገድ ለመብታቸው ባደረጉት ትግል ከመንግሥታቸው ጥይት እየዘነበባቸው ከፍተኛ የሆነ ቁጥር በመላው ሃገሪቷ ሕዝብ እየረገፈ ነው። ላለፈው አንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በኦሮሞ ወገኖቻችን የተነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ዛሬም እንዳለ ነው፤ የወልቃይት የማንነት ጥያቄን መሠረት አድርጎ በጎንደር በጎጃም የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቷን ጎልማሳ ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ፣ ህፃንና ወጣት ሳይለይ በሞት እየቀጠፈ ነው። በኮንሶ፣ በቤንሻንጉል፣ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምስራቅና በምዕራብ መላው ሀገሪቷ በሕዝብ ደም ማዕበል እየተጥለቀለቀችና በመንግሥት ታጣቂዎች ጥይት እየታመሰች ትገኛለች።
ይህ ሁኔታ በአግባቡ ከአልተያዘና በአስቸኳይ ካልቆመ ሀገሪቷንና የአካባቢውን ሀገራት ጨምሮ ወደ አልተገመተ አስከፊ የፖለቲካ የማህበራዊና የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። ምንም እንኳን መንግሥት በጎሳና በሃይማኖት እየከፋፈለ ላለፉት 25 ዓመታት በእጥፍ እያደገነው የሚለው የምጣኔ ሀብት እድገት ለጥቂቶች መከበሪያ ከመሆነ አልፎ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ሊቀይረው አለመቻሉ ግራ የሚያጋባ ስሌት ቢሆንም የሀገሪቱ የኤኮኖሚ ግሽበት ከ90% በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት በታች እንዲኖር አድርጎታል። በ2009 መንግሥት አትራፊ ያልሆኑ ሕዝባዊ ድርጅቶችን የሚገድብ ህግ ደንግጓል። ይህ ህግ ሕዝባዊ ድርጅቶችን፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የቆሙትንና ተቆርቋሪ ድርጅቶችን ለሕዝቡ እንዳይደርሱ አምክኗቸዋል።
በዚሁ ሥርዓት ተወልደው የጎለመሱት የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ ትውልድ ቀደም ሲል በመካከለኛ ምሥራቅ በስደት ፍዳቸውን ያዩና ያለቁት ቁጥር ስፍር የላቸውም። አሁን ደግሞ ተስፋ በማጣት መረረኝ ብለው በሀገራቸው በስላማዊ ትግል ብሶታቸውን በማሰማታቸው መንግሥት ምላሹ ጥይት ሆኖ በየቀኑ እንደ ጉድ እየረገፉ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ይባስ ብሎ መንግሥት በሀገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጅ በገዛ ሕዝቡ ላይ አመጹን የሚያባብስ እርማጃ ወስዷል።
ይህ አዋጅ የሀገሪቷን መጻኢ ዕድል ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል፣ ሕዝቡን ለከፋ ቀውስ የሚዳርግ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወማለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እየደረሰበህ ያለው አስከፊ የመብት እረገጣ፣ ግድያና እሥራቱን ለመቋቋም አንድነት ኃይል ነው፣ የሕዝብን የአንድነት ትግል የሚያሸንፈው ኃይል የለምና ትግላችሁን ከዋናውና ከጋራ ጠላታችሁ ጋር ብቻ በማድረግ ይችን ክፉ ዘመን በጋራ በአንድነት በመቆም እንድትወጡት ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታችሁን አጥብባችሁ በየቀኑ በሚያለቀው፣ እንታገልልሃለን በምትሉትና ልትሰዉለት በተዘጋጃችሁት ሕዝብ ስም ከምንግዜውም በላይ ዛሬ በሚያግባቧችሁ መሠረታዊ ጥያቄ ላይ በማተኮር በጋራ ቆማችሁ ኢትዮጵያን ለማዳን ለሕዝባችሁ እንድትደርሱለት በአንክሮ እንጠይቃለን።
የተለያያችሁ ሕዝባዊ ማህበራት፣ የእምነት የሃይማኖት ተቋማት፣ የዕድር የእቁብ፣ አትራፊ ያልሆናችሁ ወገናችሁን በመርዳት ላይ ያላችሁ ተቋማት ሁላችሁም የወገናችን ዕልቂት በአስቸኳይ እንዲቆምና ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሁሉም ኢትዮጵያውያንና የህብረተሰቡ አካሎች የተሳተፉበት ሕዝብ የመረጠው ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሰረት የበኩላችሁን ተሳትፎ እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ በተለይ የአሜሪካንና ኃያላን አገሮች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላቸውን ፖሊሲ እንድትመረምሩና የገዛ ሕዝቡን በጥይት ከሚጨርስ ከወያኔ ኢህአድግ መንግሥት ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያና ሕዝቧ ጎን እንድትቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ለዘላለም ትኑር።
የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል (CREW)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፓርላማው በሙስና/ሌብነት የተጠረጠሩ አባላቱን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው
Share