በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ (የኦፌኮ አመራሮች የነአቶ በቀለ ገርባ) የቪዲዮ ማስረጃዎች መታየት ቀጥለዋል (የካቲት 13 2009)

በየካቲት 13ት በዋለው ችሎት ሊቀርብ የነበረው 4ኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ ቪዲዮ የያዘ ሲዲ ነበር። ሆኖም ሲዲው ሊከፈት ባለመቻሉ ቀጣይ የሲዲ ማስረጃ እንዲታይ ዳኞች አዘዋል። አቃቤ ህግም በቀጣይ 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነጋሳ ላይ የሚቀርበው የሲዲ ማስረጃ እንዲታይ በማለት ” ተከሳሹ (አብደታ ነጋሳ) ከላፕቶፑ ተገኝተው በሲዲ የተገለበጡ የሽብር ቡድኑም አርማ ያለበት ሙዚቃዎች፤ ለቅስቀሳ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቀስቃሽ ዘፈኖች” መሆናቸውን ጠቅሷል።
በ5ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ማስረጃ በችሎት በስክሪን እንዲታይ ተደርጓል። በማስረጃነት የቀረበው ሲዲ 13 የኦሮምኛ ዘፈን ክሊፖች እና አንድ የኦሮምኛ ግጥም ናቸው። የቀረቡት የቪዲዮ ሙዚቃ ማስረጃዎች በችሎት ሲታዩ ከአንድ ሰአት በላይ ቆይቷል። የአሳንቲ ሃጂ ቱፋ፣ የጫላ ቡልቱሞ፣ የሴና ሰለሞን፣ የኤቢሳ፣ አንተነህ ለማ ጎበና፣ ጃፋር የሱፍ፣ እና ሌሎች የኦሮምኛ ዘፈኖች ክሊፕ በአራተኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ አርፍዷል።
በአብደታ ነጋሳ ላይ የቀረበው የሲዲ ማስረጃ ታይቶ ካበቃ በኋላ የእለቱ ችሎት ተጠናቋል፤ በባለፈው ችሎት በማስረጃነት የቀረበው በእንግሊዘኛ ቋንቋ አቶ በቀለ በኦሮሞ ጥናት ማህበር ( OSA) ላይ ያደረጉት ንግግር እና በዛሬው ቸሎት ቀርበው የታዩ ከአብደታ ነጋሳ ላፕቶፕ የተገኙ የኦሮምኛ ሙዚቃዎች እና ግጥም ህጋዊ የመተርጎም ፈቃድ ካለው ተቋም ተተርጉሞ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ ታዟል።
በአቶ በቀለ ላይ የቀረበውን ቀሪ ሲዲ እና በ11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዶ ላይ የቀረበውን የሲዲ ማስረጃ ለመስማት ቀጠሮ ለየካቲት 20/2009 ተይዟል።
ከቀረቡት ክሊፓች ውስጥ አራቱ ከዚህ በታች ባሉ ሊንኮች ይገኛሉ።
https://www.youtube.com/watch?v=FPqXrNzrUsY&app=desktop

ተጨማሪ ያንብቡ:  የክርስቲያኖ ሮናልዶ 28 ልዩ ቀናት (Updated)

https://www.youtube.com/watch?v=iZjyYvM00js&app=desktop

ዜናው የተገኘው ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ነው::

Share