August 27, 2013
10 mins read

በሐውዜን ከተማ የህዝብ ተወካዩ ህዝብ እያስፈራራ ነው

Abrham Desta

-ከአብርሃ ደስታ (መቀሌ)

በሐውዜን ከተማ እየተፈፀመ ያለው ያስተዳደር ብልሹነትና የልማት አድልዎ የህዝብ ቁጣ ከቀሰቀሰ ሰንብቷል። ሐውዜን የከተማነት ደረጃ ተነፍጓታል። ህዝቡም ከወረዳ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ዞን፣ ክልልና ፌደራል መንግስት ድረስ የልማት ጥያቄውን ያስተጋባ ቢሆንም አግባብ ያለው መልስ የሚሰጥ የመንግስት አካል ግን ፍፁም አልተገኘም።

ጥያቄውና መነሳሳቱ ቀጥሏል። በጉዳዩ የሐውዜን ወረዳ ባለስልጣናት በሁለት ተከፍሏል፤ (1) የወረዳው ስራ አስፈፃሚ አባላትና (2) የወረዳው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት። የስራ አስፈፃሚዎቹ ቡድን አቶ አሕፈሮም ወ/ገብርኤል በሚባል የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ የሚመራ ሲሆን የህዝቡ ጥያቄ ‘የጠላቶች ፖለቲካዊ መነሳሳት ነው’ በሚል ሰበብ የወረዳው ህዝብ በማስፈራራት፣ በማሰርና በጥቅማጥቅም ለመደለል በመሞከር የልማት ጥያቄው ለማዳፈን የሚጥር ነው።

የወረዳው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ግን የሐውዜን ህዝብ እያነሳው ያለው የልማት ጥያቄ አግባብነት ያለውና አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑ አስረግጠው የሚናገሩ ናቸው። በዚህ አቋማቸው ምክንያት የወረዳው የህዝብ ተወካዮቹ ‘ዓረና የላካቸው ጠላቶች’ ተብለው ተፈርጀዋል። (‘ዓረና’ እየተባሉ ያሉ ሰዎች ህወሓትን ወክለው የተመረጡ የህወሓት አባላት ናቸው)።

ስራ አስፈፃሚዎቹ ለምክርቤት አባላቱ ያስፈሯሯቸዋል፤ ከሓላፊነታቸው ሊያባርሯቸውና ሊያስሯቸው እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል። በሐውዜን ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው። በመርህ ደረጃ ከፍተኛ ስልጣን ያለው አካል ስራ አስፈፃሚ ሳይሆን ምክርቤት ነው፤ ምክንያቱም የምክርቤት አባላቱ ህዝብ ይወክላሉ፣ የህዝብ ተወካዮች ናቸው። ታድያ ስራ አስፈፃሚዎች ካስፈራሯቸው ምን ዋጋ አለው?

የህዝብ ተወካዮቹ (ቢያንስ በመርህ ደረጃ) የመንግስት አካላት ናቸው። ስራ አስፈፃሚዎቹ ግን በገዢው ፓርቲ የተመለመሉ የፖለቲካ ሹማምንት ናቸው። ተወካዮቹ ጥያቄው ሲደግፉ የፖለቲካ ሹመኞቹ ግን ‘ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ’ በመሆኑ ህዝቡ ጥያቄውን እንዲያቆም ጥረት ያደርጋሉ።

የወረዳው ህዝብ ተወካዮች ለጥያቂያቸው መልስ ባለማግኘታቸው የወረዳው የፌደራል ምክርቤት (ፓርላማ) ተወካይ ጠርተው ለማነጋገር ወሰኑ። የወረዳው ህዝብ ወክሎ በፓርላማ የተቀመጠው ሰው የወከለውን ህዝብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ማንፀባረቅ እንዲሁም መፍትሔ ማፈላለግ ሕገ መንግስታዊ ግዴታው ነው። ህዝብ ሲቸገር ከህዝብ ጎን መሰለፍ አለበት፤ ምክንያቱም የህዝቡ ድምፅ ለማሰማትና ለመወከል ነው ፓርላማ የገባው።

አቶ አረጋዊ አፅብሃ ይባላል። የድምፂ ወያነ ሰራተኛ ነበር። ህወሓትን ወክሎ የሐውዜንን ህዝብ በፓርላማ ለመወከል በወረዳው ተወዳደረ። አሁን የሐውዜን ህዝብ የልማት አድልዎ ሲደርስበት የፓርላማ ተወካዩ ተጠራ። (ሳይጠራም በራሱ መምጣት ነበረበት፤ ምክንያቱም ህዝቡ ከመወክል ሌላ ህገመንግስታዊ ስራ የለውምና።)

አቶ አረጋዊ ወደ ሐውዜን ቢመጣም ጥያቄው ካነሱ የወረዳው ተወላጆችና የምክርቤት አባላት ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የፌደራል የምክርቤት አባል ሁኖ ከስራ አስፈፃሚዎቹ የፖለቲካ ሰዎች ወግኖ ጥያቄው ላነሳ ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ በከጠር ጣብያዎች (ንኡስ ወረዳዎች) እየተዘዋወረ የጣብያና ቁሸት አስተዳዳሪዎች ህዝቡን ጥያቄውን እንዲያቆም እንዲያስፈራሩት እያስፈራራቸው ይገኛል።

የህዝብ ተወካይ ተብሎ የህዝብን ችግር ከመፍታት ይልቅ ህዝብ የልማት ጥያቄ እንዳያነሳ ማስፈራራት ምን ይሉታል? ደግሞስ ህዝብ የመወከል እንጂ ህዝብ የማስፈራራት ስልጣን ማን ሰጠው? የህዝብ ጥያቄ ማንፀባረቅ ሲገባው የህዝብ ጥያቄ ለማዳፈን ጥረት ያድርግ!? ለመሆኑ ስልጣኑ ምንድነው? ለምንድነው የመረጥነው? ሁላችን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ነው።

አንድ የፓርላማ ተወካይ ስራው በደንብ ካልተወጣ የሚወሰደው እርምጃ ምንድነው? መልሶ መጥራት (Recalling) ከሐላፊነቱ ማባረር። የፓርላማ ተወካዩ ስራ ምንድነው? ህዝብን ወክሎ የህዝብን ጥያቄ በሚመለከተው አካል በኩል መልስ እንዲያገኝ ማድረግ። አሁን ስራው በአግባቡ እየተወጣ ነው? አይደለም። የተሰጠው ሕገመንግስታዊ ሐላፊነት ወደጎን በመተው ተገልብጦ ህዝብ እያስፈራራ ይገኛል። ስለዚህ በሕገመንግስቱ መሰረት ‘የማስመለሻ ትእዛዝ’ (Recalling Claim) ሊሰጠው ይገባል። ካሁን በኋላ የሓውዜንን ህዝብ ወክሎ ፓርላማ ሊቀመጥ አይገባውም። ሌላ የህዝብን ጉዳይ ወክሎ የሚናገር ሰው መመረጥ አለበት።

የሓውዜን ጉዳይ ህወሓትን (የነአባይ ወልዱ ቡድን) በሁለት ሳይከፍል አልቀረም። ጉዳይ በተደጋጋሚ እየተወያዩበት ነው። በህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ አቶ ኢያሱ ተስፋይ የተባለ (የማእከላዊ ኮሚቴ አባል) ‘የሐውዜን ጉዳይ መፍታት ያቃተን ለምንድነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሳ ሲሆን የሚያረካ መልስ የሰጠ ባለስልጣን ግን አልነበረም።

በአሁኑ ሰዓት (ከሳምንት በፊት ጀምሮ) የሐውዜን ወረዳና የምስራቃዊ ዞን አስተዳዳሪዎች ከክልል ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ በመቐለ ከተማ እየተወያዩና እየተገማገሙ ናቸው። በግምገማው መሰረት (እስካሁን) የሐውዜን ህዝብ ጥያቄ ለማዳፈን የቤት ስራ ተሰጥቶት የነበረ የምስራቃዊ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገብረ ከስልጣኑ እንዲባረር ተወስኗል።

አቶ ገብረ የሐውዜንን ጉዳይ እንደምንም ብሎ ማስቆም እንዲችል ታዞ የነበረ ቢሆንም ህዝብ ማሳመን አቅቶት ከሐውዜን ኗሪዎች ጋር ተጣልቶ፣ ህዝቡን ሰድቦ፣ ስብሰባ ረግጦ የወጣ ሰው ነው።

ደግሞስ ህዝብ ልማት አያስፈልገውም ብሎ ለህዝብ ማሳመን ይቻላል እንዴ? ከንቱ ልፋት ነው። ህዝብ ማሳመን የሚቻለው ልማት እንደሚያስፈልገው በመንገር እንጂ ልማት እንደማያስፈልገው በመንገርና በማስፈራራት አይደለም። ብቻ ይገርማል።

የሐውዜን ህዝብ የልማት ጥያቄውን የሚጋራ የራሱ ተወካይ ያስፈልገዋል።

አሜን!

3 Comments

  1. When is Abrha Desta coming to USA and play the second part of Dawit Kbede’s drama ? he is feeding to much to frequent …. only God knows the authenticity of he is feed .. but sure he is creating a good nest in the opposition camp…till it sniffs out.

  2. bravo Abraha Desta! Barvo Yehawzien Hizeb!

    Diaspora yalen yetigray tewelajoch Kegonachihu nen, Bertu!!!

  3. That is the TPLF way. TPLF has been forcing people to obey with what they order. It has NEVER givien a chance to the people to excersis their right. It has been always intimidation, arresting, killing whoever asks a question. Leave alone now when they are controling the country’s resource, even during their 17 year bush days they have been consistence brutally forcing people to abid.

Comments are closed.

Addis GudayVol 7. No. 178. Addis Ababa. 1
Previous Story

ማን ይናገር የነበረ….. የታኅሣሡ ግርግር እና መዘዙ!

Next Story

መንግሥት ለተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንጠይቃለን!!!!

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop