የቁጫ ሕዝብ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ጥሪ እናቀርባለን!!! አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ 

 

ፓርቲያችን አንድነት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚታገልላቸውና ገዥው ፓርቲ ከወረቀት በዘለለ ያልተገበራቸው ሀገራዊ ቁምነገሮች ውስጥ ዜጎች ሳይሸማቀቁ በነፃነት ሃሳባቸውን የመግለፅ፣ በነጻነት የመደራጀት፣ በገዛ ሀገራቸው በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ በፈለጉበት አከባቢ የመኖር፣ ሀሳባቸውንና አመለካከታቸውን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደገፍ፣ የመቃወም፣ ስለመብታቸው ሳይሸማቀቁ የመጠየቅ ወ.ዘ.ተ እና በአጠቃላይ የሕግ በላይነት እንዲሰፍን፣ የሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በኢትዮጵያ እንዲከበሩ፤ ከዚህም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዜጎች ዋስትና እንዲረጋገጥ ማድረግ ናቸው፡፡

የቁጫ ሕዝብም ያነሷቸውን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የአስተዳደር ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለመንግሥት ቢያቀርቡም የተሰጣቸው ምላሽ እስርና ማስፈራሪያ መሆኑ ፓርቲያችንን አሳዝኖታል፡፡ ግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ የሆነውም የዜጎችን ህጋዊ ጥያቄ በሕገ-ወጥነት መቀልበስ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ መገለጫውም በጅምላ የታሰሩትና እስር ላይ የሚገኙት ዜጎች ናቸው፡፡ ፓርቲያችን ጉዳዩን በቅርበት ተከታትሎ እንዳጣራው በርካቶች በጅምላ የታሰሩበት ምክንያት ልጆቻችን አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ ይማሩ፣ በስማችን ልንጠራ ይገባናል፣ የማንነት ጥያቄያችን ምላሽ ያግኝ፣ ፍህና መልካም አስተዳደር ይረጋገጥ፣ የልማት ጥያቄያችን ምላሽ ያግኝ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስርዓቱ አረጋግጫቸዋለሁ ከሚላቸውና በቁጥጥር ስር ባደረጋቸው ሚዲያዎቹ የሚለፍፋቸው ቢሆኑም ለቁጫዎች የተሰጣቸው ምላሽ ሰብዓዊ ክብራቸውን መጣስና ማሰር ነው፡፡ ፓርቲያችን ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር አጥብቆ ይቃወማል፡፡

መንግስትም የመብትና ማንነት ጥያቄ ስላነሱ ያሰራቸውን በአስቸኳይ እንዲፈታ፤ ያነሷቸውን ጥያቄዎች አግባብ ባለው መንገድ በፍጥነት እንዲመልስ እንጠይቃለን፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አባባUDJ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትምህርት ሚኒስቴር ከ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ውጤት እና ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል
Share